March 9, 2011

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በዐድዋ ድል የነበራትን ድርሻ የዘከረ ውይይት ተካሄደ


“ኢትዮጵያዊሰ እንዘ ክቡር ውእቱ ኢያእመረ”...
Photo 1 © The British Museum - 2007
(ደጀ ሰላም፤ ማርች 9/2011)፦ ለጦርነቱ በቤተ ክርስቲያን ጸሎተ ምህላ ታውጇል፤ ዘማች ታቦታት ተመርጠው የአዝማች ኮሚቴም ተቋቁሟል፤ ታቦተ ቅዱስ ጊዮርጊስ የዘማች ታቦታቱ መሪ ነበር፤ ለመላው ዘማች ሠራዊት ሥነ ልቡናዊ ጥንካሬን (የሰማዕትነት ወኔን) የሰጠ የሰባት ቀናት የቁም ፍትሐት ተደርጓል፤ ሊቃውንቱ ከጦርነቱ በድል እንደምንመለስ በቅኔያቸው ትንቢት ተናግረዋል፤ ዐፄ ምኒልክ የክተት ዐዋጅ ካስነገሩ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሄደው “አምላከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ድሉን ቢሰጠኝ ይህን ቤተ ክርስቲያን የሣር ክዳኑን ለውጨ ባማረ ሕንጻ አሠራዋለሁ” ብለው ብፅዓት አድርገዋል፡፡ ከምርኮኛ የጣሊያን ወታደሮች አንዱ በዐውደ ውጊያው “በነጭ ፈረስ ተቀምጦ ወደ ቀኝ እና ወደ ግራ እየተመላለሰ ‹ወደ ጦርነቱ ግቡ፤ ኢጣሊያኖችን ማርኩ› እያለ ትእዛዝ ሲሰጥ እና ሲወጋን የዋለ ማነው?” ብሎ ጠይቋል፡፡ በጦር ሜዳ ለበቁት ሰዎች ተገልጦ እየታየ ከአርበኞቻችን ጋራ የዋለው ፍጡነ ረድኤት ቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ዐቃቤ መልአክ (Patron Saint) ነው፡፡ በዐድዋ ድል የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የአንበሳ ድርሻ አላት፡፡

“ኢትዮጵያ ሥጋችን ቤተ ክርስቲያን ነፍሳችን ናት፤ ነፍስ እና ሥጋ ደግሞ አንድ ነው፡፡ አገር ያለሃይማኖት፣ ሃይማኖት ያለአገር የለም፤ ኢትዮጵያን ያህል አገር ማጣት እግዚአብሔርን ከሚያህል ጌታ መለየት ሞት ነው፡፡ ሃይማኖትን እና ነጻነትን ማጣት ሽንፈት ነው፤ ስለ አገር፣ ሃይማኖት እና ነጻነት መሞት ደግሞ ክብር ነው፡፡” (የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ)

“በቀደሙት የጦርነት ታሪኮች ከፍተኛ ጥቃት የደረሰባት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ለሚፈራረቅባት መከራ አንዱ ምንጭ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ቀጥተኛ ቅኝ አገዛዝን በመቃወም ሀገራዊ ሉዓላዊነትን እና ነጻነትን ከማረጋገጥ አልፋ ኢትዮጵያዊነት የጥቁሮች ኩራት እና ክብር እንዲሆን ማድረጓ ያልተዋጠላቸው የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ኀይሎች ሤራ ነው፡፡ የሀገራዊ ነጻነቱ ተቋዳሽ የሆነ ሁሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ ውለታ አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እንደ ተቋም በዓለም ቅርስነት ደረጃ ተመዝግባ ልትጠበቅ የሚገባት ናት፡፡”

ሰብእሰ እንዘ ክቡር ውእቱ ኢያእመረ” የሚለውን የቅዱስ ዳዊት ቃል “ኢትዮጵያዊሰ እንዘ ክቡር ውእቱ ኢያእመረ” በሚል ተክቼዋለሁ፤ ዐድዋ በየትኛው የአገሪቱ ክፍል እንደሚገኝ እንኳ የማያውቁ ኢትዮጵያውያን አጋጥመውኛል፤ ‹ዛሬ ደ'ሞ የምን በዓል ነው?› የሚሉ ጋዜጠኞች ጭምር አሉ፤ ከዐድዋ ድል ይልቅ የቫለንታየን ቀን ነው በልዩ ትኩረት የተከበረው፤ ዐድዋ እኛ በሲዲ ከምናስተማረው በላይ ጥቁርነትን፣ ኢትዮጵያዊነትን፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን በአንድ ጊዜ በላቲን አሜሪካ፣ በአፍሪካ እና በአውሮፓ ያበሠረ ሰባኪ ነው፤ አሁን በግሎባላይዜሽን ስም የምንሰብከው እና የምንዘምረው ሁሉ ዐድዋ የሰበከውን እያጠፋው ነው፡፡ ማንነቱን ያጣ ትውልድ ለመገዛት የተመቸ ነው፤ ለሚሆነው እና ለሆነው ነገር ሁሉ ግድየለውምና፡፡ የታሪክ ትምህርታችን ምን ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው? ስለ ባህሉ በምልዓት የሚያውቅ አለን ወይስ ዐፄ ምኒልክ አሁንም ‹ማርያምን አልምርህም› እንዲሉን እንፈልጋለን? ራሳችንን፣ ባህላችንን እስካላወቅን ድረስ ማሸነፍ አንችልም፡፡ ከየት እንደመጣን ካላወቅን ወዴት እንደምንሄድ አናውቅም፤ ወደፊት ለመገስገስ ወደ ኋላ መመለስ (ሳንኮፋ) ይኖርብናል፤ የኋላቀርነታችን መንሥኤው ታሪካችንን በመጠበቃችን ሳይሆን ማንታችንን በማጣታችን ነው፡፡ ታሪኩን የማያውቅ ከብዙ ሴቶች መካከል እናቱን ለይቶ በማያውቅ ልጅ ይመሰላል፡፡ ታሪካችን ተኝተን የምናንቀላፋበት መከዳ (headrest) ሳይሆን እንደ ጥንቱ ሥልጣኔያችን የዕድገታችን መስፈንጠሪያ (fulcrum) ልናደርገው ይገባል፡፡” (የውይይቱ ተሳታፊ የሆኑ ምሁራን)
- - - - - - - - - - - -- - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - -
የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም - የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ሀገርነት እና ነጻነት ያረጋገጠው፤ ምዕራባውያን ቅኝ ገዥዎች በበርሊኑ ኮንፈረንስ የወጠኑትን የመስፋፋት እና አፍሪካን የመቀራመት ፖሊሲያቸውን ዳግመኛ እንዲመረምሩ ያደረገው፤ ለፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ መፋፋም ምክንያት የሆነው፤ ኢትዮጵያኒዝም እየተባለ የሚጠራው ከነጮች ተጽዕኖ ነጻ የሆነ የጥቁሮች የሃይማኖት እንቅስቃሴ በተለይም በአሜሪካ እና በደቡብ አሜሪካ ያስጀመረው የዐድዋ ድል የተመዘገበበት ነው፡፡ ዘንድሮ ድሉን ለ115 ዓመት ለማክበር ዕድል አግኝተናል፡፡ አውሮፓውያን ቅኝ ገዥዎች የበርሊኑን ጉባኤ ተከትሎ በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚይዙት ቦታ የእነርሱ መሆኑን ለማረጋገጥ ብዙ የተጭበረበሩ እና የማታለያ ስምምነቶችን አድርገዋል፡፡ በ1881 ዓ.ም በኢጣሊያዊ ተወካይ አንቶሎኒ እና በዐፄ ምኒልክ መካከል የተደረገው የውጫሌ ስምምነት ለዚህ ዋናው ማሳያ ነው፡፡

የውጫሌ ውል ሃያ አንቀጾች ያሉት እና በሁለት ቋንቋዎች የተጻፈ ሲሆን የግጭቱ መንሥኤ የሆነው በጣሊያንኛ ቋንቋ የተጻፈው 17ው አንቀጽ ነበር፡፡ የአማርኛው ውል፡-”የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የውጭ ግንኙነቱን በኢጣልያ አጋዥነት ማድረግ ይቻላቸዋል” በማለት ምርጫው የዐፄ ምኒልክ መሆኑን ያሳያል፡፡ የጣሊያንኛው ትርጉም ግን፡- “የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የውጭ ግንኙነቱን በኢጣሊያ በኩል ማድረግ ይገባዋል” በማለት ኢትዮጵያን የጣሊያን ጥገኛ ያደርጋታል፡፡ በዚህም አንቀጹን አዛብተው በመተርጎም ኢትዮጵያ በኢጣሊያ የሞግዚት አስተዳደር ሥር ሆናለች ብለው ለዓለም መንግሥታት ያሳወቁበት አጋጣሚ ነበር፡፡ ከሩስያ በስተቀር ኀያላን መንግሥታት ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ላይ የውጫሌ ውል ሰጥቶኛል የምትለውን ዕውቅና ለመስጠት ዝግጁ ነበሩ፡፡ ውሉ የተጭበረበረ መሆኑ ስለታወቀ ተቀባይነት ዐጣ፣ የዐድዋ ጦርነት ሊመጣ ግድ ሆነ፡፡

የዐድዋ ጦርነት በአንድ ዐውደ ውጊያ ያበቃ ሳይሆን ሂደት ነበር፡፡ የመጀመሪያው ውጊያ ዐምባላጄ ላይ ኅዳር 29 ቀን 1888 ዓ.ም ተደርጎ በራስ መኮንን እና በፊታውራሪ ገበየሁ የጦር መሪነት በድል ተጠናቀቀ፡፡ ሁለተኛው፣ የጠላት ጦር መቀሌ መሽጎ ነበር፡፡ በእቴጌ ጣይቱ ዘዴ ውኃ የሚያገኙበት ምንጭ ስለተዘጋ ጠላት ለቆ ወጣ፡፡ ዋናው የዐድዋ ጦርነት የካቲት 23 ቀን በዕለተ ሰንበት በስድስት ሰዓት ውስጥ በኢትዮጵያ የበላይነት እና ድል አድራጊነት ተጠናቀቀ፡፡ የተሳሳተ የንባብ ካርታ፣ የመንገድ መሳሳት፣ ጠላት በታጠቀው ዘመናዊ መሣሪያ እና በሠለጠነው ሠራዊቱ የተነሣ ለኢትዮጵያውያን የሰጠው አነስተኛ ግምት፣ ኢትዮጵያውያን በሰንበት እና በድርብ በዓል ጦርነት አይገጥሙም ብለው ማሰባቸው ለወራሪው ሽንፈት የሚጠቀሱ ምክንያቶች ናቸው፡፡

የዐድዋ ድል በአራቱም ማእዝናት የሚገኙ ድፍን ኢትዮጵያውያን የከተቱበት (የተሳተፉበት)፣ የኢትዮጵያን ነጻነት ከማረጋገጥ አልፎ ዓለምአቀፋዊ እንቅስቃሴን የፈጠረ፣ በዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቁሮች ነጮችን ያሸነፉበት ዐቢይ ወታደራዊ እና ሞራላዊ ድል ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሠራዊት ድል እንዲያደርግ የረዱት ትልቅ የአገር ፍቅር ስሜቱ፣ ጦርነቱ ለአገር እና ለሃይማኖት ጭምር መሆኑን ሠራዊቱ ማመኑን፣ የላቀ ጦር ስልት እና አመራር፣ ጠንካራ የሠራዊት ሞራል እና የሥነ ልቡና ዝግጅት፣ ሕዝብን የማንቀሳቀስ እና የመምራት ብቃት ናቸው፡፡ የዐድዋ ድል በውጤቱ ለኢትዮጵያውያን የትብብር፣ የአንድነት፣ የኩራት እና የክብር ምንጭ ሆኗል፤ ዓለም አቀፍ ዝናን አጎናጽፏታል፤ አውሮፓውያኑ ድሉን ተከትሎ/ጣሊያን በቅድሚያ/ ኤምባሲዎችን በመክፈት ለዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ረድቷታል፡፡ በቅኝ ገዥዎች የተከበበችው ኢትዮጵያ ድንበሯን እንድትካለል ምክንያት ሆኗል - ሉዓላዊ ሀገርነቷ እና ነጻነቷ ተረጋግጧል፡፡
Painting commemorating the Battle of Adwa, Catalogue No. E261845-0, Department of Anthropology, NMNH, Smithsonian Institution.
 በዐድዋ ጦርነት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከመነሻው እስከ መጨረሻው፣ ከዘመቻው እስከ ድሉ፣ ከዋዜማው እስከ ጦርነቱ በመሪነት እና በተሳታፊነት ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች፡፡ “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ማእከል ያደረጉ ሀገራዊ ጉዳዮችን ትውልዱ እንዲያውቃቸው፣ እንዲጠቀምባቸው እና እንዲጠብቃቸው” በመሥራት ላይ የሚገኘው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የጥናት እና ምርምር ማእከል “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ድርሻ በዐድዋ ድል” በሚል ርእስ የካቲት 23 ቀን 2003 ዓ.ም የግማሽ ቀን የሥነ ቤተ ክርስቲያን ጥናታዊ የውይይት መድረክ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም አዳራሽ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ የጥናት እና ምርምር ማእከሉ ዳይሬክተር እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአርኪዮሎጂ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ዲያቆን መንግሥቱ ጎበዜ ለውይይቱ ባቀረቡት የመነሻ ሓሳብ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስለ ክብሪ ሀገር ባላት አስተምህሮ ሕዝብን በመቀስቀስ፣ አመራር በመስጠት፣ አብራ በመዝመት፣ የሥነ ልቡና ዝግጅት በማድረግ፣ በጦርነቱ በመሳተፍ፣ መረጃ በመስጠት እና በማስቀመጥ የአንበሳውን ድርሻ እንደምትወስድ አብራርተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እንደቀደመው ዘመን ያላት ሁለገብ ሚና እና ተደማጭነት በአመራር እና አስተዳደራዊ መዋቅር ችግሮች፣ በሉላዊነት(ግሎባላይዜሽን) ተጽዕኖ፣ በምእመናን መንፈሳዊ ሕይወት መዳከም፣ በቤተ ክርስቲያን አባቶች እና ምእመናን ትስስር መላላት፣ ዘመኑን የዋጀ እና ስልታዊ(ስትራተጂያዊ) አካሄድ ጉድለት የተነሣ በአሁኑ ወቅት ስጋት እንደተጋረጠበት በጽሑፍ አቅራቢው ተመልክቷል፡፡

“ኢትዮጵያ ካልተበታተነች በአፍሪካ ያለው ቅኝ ግዛት አይረጋም፤ ኢትዮጵያን ለመበታተን ደግሞ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን መውረስ ወይም ማዳከም” የወራሪዎች ቁልፍ ተግባር እንደነበር ያወሱት የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ዛሬም ትውልዱን ለእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ለማስመቸት ታሪኩን እንዳያውቅ እና እንዲያናንቅ በውስጥም በውጭም የሚደረገውን ዘመቻ ሊነቁበት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡ ለዚህም የዐድዋን ድል ከወሬ እና ከመፈክር በላይ ከነሙሉ ክብሩ በማሰብ እና በማስታወስ የትውልዱ ሥነ ልቡና በአኩሪ ታሪኩ ላይ እንዲገነባ፣ ስደተኛ መንፈሱ እንዲያበቃ የሚያደርግ ተጨባጭ ሥራ መሥራት እንደሚገባ ተመክሯል፡፡ ኢትዮጵያ በታሪኳ ያጋጠሟትን ከ137 በላይ ጦርነቶች በድል ብትወጣም የወራሪዎች ቀዳሚ ዒላማ ሆነው በታረዱባት መነኮሳቷ፣ ካህናቷ እና ሊቃውንቷ፣ በተቀሰጡባት እና በተሰደዱባት ምእመናኗ፣ በተቆነጠሉባት እና በተዘረፉባት ቅርሷቿ፣ በተቃጠሉባት አድባራቷ እና ገዳማቷ ከባድ መሥዋዕትነት የከፈለችው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እንደ ዐድዋ በመሳሰሉት ታላላቅ ድሎች የነበራት ሚና ከነገሥታቱ ጋራ እያቆራኙ በሚከሷት ወገኖች እና በሚዲያው ተገቢው ትኩረት እንዳልተሰጠው በውይይቱ ላይ ተወስቷል፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለረጅም ዘመናት ሀገራዊ ሓለፊነት እና ሚና ይዛ በመቆየቷ፤ አገር ያለሃይማኖት፣ ሃይማኖት ያለሀገር የሌለ በመሆኑ፤ በቀደሙት የግራኝ ወረራ፣ የመቅደላ ጦርነት እና የድርቡሽን ጥቃት እንደመሳሰሉት አስከፊ ወቅቶች ከሁሉም በላይ ጥቃት የደረሰባት መሆኑ፤ በዐድዋ ጦርነት የወራሪው መንገድ ጠራጊዎች እንደ አባ ማስያስ እና ሳሌንቢኒ/በጦር መሐንዲስ ስም/ ያሉት ሚስዮናውያን መሆናቸው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በዐድዋ ጦርነት ለነበራት አገባብ አመክንዮ መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡ ዳንኤል ሮፕስ የተባለ ታዋቂ የፈረንሳይ ጋዜጠኛ “አክሌዚያ” በተባለው ጋዜጣ የመስከረም 1963 ዓ.ም እትም “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ታውቋታላችሁ?” ሲል ባሰፈረው ጽሑፍ “ወራሪዎች ምድሯን የያዙባት መሆኑን ታሪክ ያወሳል፤ ነገር ግን ሃይማኖት የእንቅስቃሴ መሣሪያ ሆኖ በመገኘቱ ነጻነት ተመልሳ ተገኝታለች፤” ብሏል፡፡ “ከሐን ኢንተርናሽናል” የተባለ ሌላ ጋዜጣ በመስከረም 1964 ዓ.ም እትሙ ስለ ኢትዮጵያውያን ሲጽፍ፣ “ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ሃይማኖት እና ክብር ከመጠበቅ አልፈው ለሌሎች መብት እና ነጻነት የሚታገሉ ሕዝቦች ናቸው፤” ብሏል፡፡

ጽሑፍ አቅራቢው ዲያቆን መንግሥቱ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለዐድዋ ድል የነበራትን ድርሻ በቅድመ ዝግጅት፣ በዝግጅት እና በድርጊት ደረጃ ከፋፍለው አቅርበዋል፡፡ በቅድመ ዝግጅት ደረጃ ሲደረግ በቆየው የሰላም ጥረት ሜጀር ሳልሳ የተባለው ጣሊያናዊ “ከዚህ ቀደም ባንዲራችን ተተክሎ እስከነበረበት አስከ ዐላጄ ድረስ ያለውን አገር ልቀቁልንና ባንዲራችንን እንትከል” በሚል የትዕቢት ቃል በተናገረ ጊዜ ንጉሠ ነገሥቱ ዐፄ ምኒልክ “እኔ የመጣሁት እናንተ የተከላችሁትን ባንዲራ ለመንቀል እና ለመጣል ነውና ይህን የመሰለውን ውል አልቀበለውም፡፡ በተረፈ ግፍን በማይወደው በእግዚአብሔር ተማምኜ በመጣችሁበት መንገድ እቀበላችኋለሁ፤ በአገሬ በኢትዮጵያ ላይ የሮማ ሰንደቅ ዓላማ እንዲተከልበት አልፈቅድም፤” በሚል መልሰውለታል፡፡ በዚህም ቅድመ ዝግጅቱ ቀጥሎ በአብያተ ክርስቲያን የአዝማች ኮሚቴ ተቋቁሟል፤ ዘማች አብያተ ክርስቲያንም ተለይተዋል፡፡ ለምሳሌ ያህል በአዲስ አበባ የገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ የእንጦጦ መንበረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም፣ ከሸዋ የግንባሮ ማርያም፣ የበር ግቢ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ከአክሱም ጽዮን በገዳሙ አስተባባሪነት ታቦተ መድኃኔዓለምን እና ታቦተ ማርያምን ይዘው በርካታ ካህናት ተመድበዋል፡፡ ከሊቃውንቱ እጨጌ ወልደ ጊዮርጊስ፣ የደብረ ሊባኖስ ፀባቴ፣ የእንጦጦ ማርያም ደብር አስተዳዳሪ፣ ከቀራንዮ መድኃኔዓለም እና ከሆለታ ኪዳነ ምሕረት ተመድበዋል፡፡ ከንዋያተ ቅድሳቱም ከታቦታቱ በተጨማሪ መስቀል፣ ቃጭል፣ ጥላዎች እና ድባቦች ተይዘው ከሊቃውንቱ እና ካህናቱ ጋራ ዘምተዋል፡፡

ሌላው ሁነኛ የቅድመ ዝግጅቱ አካል የዐፄ ምኒልክ የክተት ዐዋጅ ይዘት ነው፤ እርሱም እንዲህ ይላል፡-
              
              “ስማ፣ ስማ፣ ተሰማ፤
              የማይሰማ የእግዚአብሔር እና የወላዲተ አምላክ ጠላት ነው፡፡
              ስማ፣ ስማ ተሰማማ፤ የማይሰማ የእግዚአብሔር እና የቤተ ክርስቲያን ጠላት ነው፡፡
              ስማ፣ ስማ፣ ተሰማማ፤ የማይሰማ የእግዚአብሔር እና የንጉሡ ጠላት ነው፡፡
              እግዚአብሔር ወሰን እንዲሆን የሰጠንን ባሕር አልፎ ሃይማኖት የሚለውጥ እና ሀገር የሚያጠፋ ጠላት መጥቶአል፡፡
 እኔ ምኒልክ በእግዚአብሔር ርዳታ ሀገሬን ለጠላት አሳልፌ አልሰጥም፡፡
         ያገሬ ሰው! ከአሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም፡፡ አንተም እስካሁን አላስቀየምኸየኝም፡፡ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ ርዳኝ፤ ጉልበት ለልጅህ፣ ለሚስትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በኀዘን ርዳኝ፡፡ ወስልተህ ብትቀር ግን ኋላ ትጣላኛለህ፣ አልተውልህም፤ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም፡፡ ዘመቻዬም በጥቅምት ነው፡፡

ከዚህ በኋላ ንጉሠ ነገሥት ዐፄ ምኒልክ ወደ አዲስ አበባ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አምርተው ጸሎት አቀረቡ፤ ብፅዓትም አደረጉ፡፡ ብፅዓታቸውም “አምላከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ድሉን ቢሰጠኝ ይህን የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሣር ክዳኑን ለውጬ ባማረ ሕንጻ አሠራዋለሁ፤” የሚል ነበር፡፡

ወደ ዐድዋ በተደረገው ጉዞ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮዋን በመቀጠል የዘማቹን ወኔ በመገንባት፣ ስለ አገር ፍቅር በመስበክ የሕዝቡን አንድነት በመሪነት ደረጃ አስተሳስራለች፡፡ ጾም እና ጸሎቱ ቀጥሏል፡፡ በሊቀ ጳጳሱ አቡነ ማቴዎስ እና በእጨጌው ወልደ ጊዮርጊስ አስተባባሪነት መንፈሳዊ አገልግሎቱ በመዓልት እና በሌሊት በሰዓታት፣ በማሕሌት፤ በቅዳሴ፣ በነግህ እና በሰርክ ጸሎት ሳይቋረጥ ጉዞው ቀጥሏል፡፡ በጉዞው ወቅት ዘማቹ ሁሉ ሃይማኖታዊ ግዴታውን ይወጣ ነበር፡፡ ለምሳሌ፡- በሰንበት ቀን አይጓዙም፤ ዐበይት በዓላትን ያከብራሉ፤ ለድኃው ይመጸውታሉ፡፡

ልዑል ራስ መኮንን ዓምባ አላጌን ለማስለቀቅ በነበራቸው ጥረት በጦርነቱ ኀይል እና ድል እንዲሰጣቸው ለአምላከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጸሎታቸውን አቅርበዋል፤ በመጨረሻም በአንገታቸው ላይ ባለው የወርቅ መስቀል አማትበው ጦርነቱን ለመግጠም ወሰኑ፤ ድልም አድርገው ዓምባ ኣላጌን ነጻ አወጡ፡፡ እቴጌ ጣይቱ በመቀሌ የመሸገው ጠላት የውኃ ምንጩ እንዲያዝበት ዘዴውን ከፈጠሩ በኋላ ሌሊቱን ሙሉ “ጌታዬ እኔን ባርያህን አታሳፍረኝ፤ በነገሬ ሁሉ ግባበት፤ ርዳታ ትችላለህና” እያሉ ይጸልዩ ነበር፡፡ ዐፄ ምኒልክ የካቲት 14 ቀን 1888 ዓ.ም ዐድዋ ሲደርሱ ከመላው ትግራይ የተውጣጡ ካህናት እና ሊቃውንት የየደብራቸውን ታቦታት ይዘው ልብሰ ተክህኖ ለብሰው በደማቅ ሁኔታ ተቀብለዋቸዋል፡፡ 

እስከ ጦርነቱ ጅማሬ ድረስ በዐድዋ በነበረው ቆይታ በመላዋ ትግራይ ለአንድ ሱባኤ ምሕላ ተይዟል፡፡ ዐፄ ምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ ከጦርነቱ በፊት ሱባኤ ይዘው የቆዩት በሥነ ጽሑፍ እና ሥነ ሥዕል ቅርሱ በዳበረው በእንዳባ ገሪማ ገዳም ነበር፡፡ ለጦርነቱ ዝግጅት እና መሰናዶ ሲጀመር አስቀድሞ የታወጀው የጸሎት እና ምሕላ ዐዋጅ ነበር፡፡ በመጨረሻም ለመላው ዘማች ለሰባት ቀናት የቁም ፍትሐት ተካሂዷል፡፡ ጀግናው ባሻይ ኣውኣሎም ሓረጎት እና መሰል አርበኞች ለኢጣሊያ የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ለዐድዋ ድል አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ የካቲት 22 ቀን 1888 ዓ.ም እቴጌ ጣይቱ ለባሻይ ኣውኣሎም ምግብ አቅርበው፣ “እንካ ይህን እንጀራ እንደ ሥጋወደሙ ቆጥረህ ብላው፤ ብትከዳ እግዚአብሔር ይፈርድብሃል፤” ብለው ሰጥተውታል፡፡ የካቲት 22 ለ23 አጥቢያ በባሻይ ኣውኣሎም መረጃ ምክንያት ጥላት ከምሽጉ እንዲወጣ ስለተደረገ ሌሊት ሲጓዝ አድሮ ዐድዋ እንደገባ በመረጋገጡ ቅዳሴው ከሌሊቱ ዐሥር ሰዓት ላይ እንዲፈጸም ተወሰነ፡፡ 

ዐፄ ምኒልክ፣ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት፣ ራስ መኮንን፣ ራስ መንገሻ እና ፊታውራሪ ገበየሁ ዐድዋ በሚገኘው የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ያስቀድሱ ነበር፤ ቀዳሹም አቡነ ማቴዎስ ነበሩ፡፡ አቡነ ማቴዎስም “ልጆቼ ሆይ፣ ዛሬ የእግዚአብሔር ፍርድ የሚፈጸምበት ጊዜ ነው፡፡ ሂዱ! ለሃይማኖታችሁ ሙቱ፤ እግዚአብሔር ይፍታህ” ሲሉ መኳንንቱ ሁሉ እየተሽቀዳደሙ የአቡኑን መስቀል ተሳልመው ለጦርነት ወጡ፡፡ ሊቀ ጳጳሱ ወደ ጦርነት የሚገባውን ወታደር ሁሉ “እግዚአብሔር ይፍታህ” እያሉ ይናዝዙ ነበር፡፡ “ኢጣሊያ በግፍ፣ በተምክህት እና በትዕቢት ተወጥሮ ባሕር ተሻግሮ ቢመጣብህ አንተ በእግዚአብሔር ስም ቁመህ መክተው፤ ታሸንፈዋለህ፤ አለዚያ ይህ ጠላት በመጀመሪያ አገርህን ወሮ ከያዘ በኋላ አንተንም ነጻነትህን ገፎ፣ ሃይማኖትህን አስክዶ ረግጦ በሥቃይ እና በመከራ ይገዛሃል፡፡ ስለዚህ ለሀገርህ፣ ለነጻነትህ እና ለሃይማኖትህ ስትል ጠንክረህ ተዋጋ፤ በርታ ታሸንፈዋለህ፡፡” በጦርነቱ ጊዜም ዐፄ ምኒልክ ነጋሪት እያስጎሰሙ ሠራዊቱን እንዲህ እያሉ ያበረታቱ ነበር፤ “ጦርነት እና የጦርነት ድምፅ ብትሰሙም አትደንግጡ፤ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋራ ሆኖ ጠላቶቻችሁን ስለሚዋጋ አትፍሩ፤ እግዚአብሔር አምላካችሁ ከፊታችሁ እየሄደ ጠላቶቻችሁን ስለሚዋጋላችሁ እናንተንም ስለሚያድናችሁ ከፊታቸው አትሽሹ፡፡” ነጋሪቱ ዛሬ በመንበረ ፀሐይ እንጦጦ ማርያም ይገኛል፡፡ በጎራዴያቸው ላይ የተቀረጸው ጽሑፍም “የምኒልክ ተስፋው እግዚአብሔር ነው” የሚል ነው፡፡

ከምርኮኛ የጣሊያን ወታደሮች አንዱ በዐውደ ውጊያው “በነጭ ፈረስ ተቀምጦ ወደ ቀኝ እና ወደ ግራ እየተመላለሰ ‹ወደ ጦርነቱ ግቡ፤ ኢጣሊያኖችን ማርኩ› እያለ ትእዛዝ ሲሰጥ እና ሲወጋን የዋለ ማነው?” ብሎ ጠይቋል፡፡ በጦር ሜዳ ለበቁት ሰዎች ተገልጦ እየታየ ከአርበኞቻችን ጋራ የዋለው ፍጡነ ረድኤት ቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ዐቃቤ መልአክ(Patron Saint) ነው፡፡ ጋዜጠኛ እና የፎክሎር ሥልጡኑ ኄኖክ ያሬድ በልጅነቱ በአንደኛ ደረጃ ት/ቤት የዐድዋ ድል በዓል ሲታሰብ ይዘምሩበት የነበረውን ግጥም በዜማ ለውይይቱ ተሳታፊዎች አሰምቷል፤
                  
                    “የዐድዋ አርበኛ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣
                    ከምኒልክ ጋራ አብሮ ሲቀድስ፣
                    ምኒልክ በመድፉ ጊዮርጊስ በፈረሱ፣
                    ጣሊያንን ጨረሱ ደም እያፈሰሱ፤”

“የዐድዋ ድል የኢትዮጵያ ባሕረ ሐሳብ/የዘመን አቆጣጠር/ ጭምር የተከበረበት ትልቅ በዓል ነው፤” ያለው ኄኖክ የዐድዋ ድል ባይገኝ ኖሮ ቋንቋችን ብቻ ሳይሆን ባሕረ ሐሳባችን ጠፍቶ በ”ዓመተ ፋሽስት”/በአውሮፓውያኑ ካሌንደር/ ይተካ እንደነበር አስገንዝቧል፡፡

ከድሉ መገኘት አንድ ወር በኋላ ዐፄ ምኒልክ ለመስኮብ ንጉሥ ኒኮላስ መጋቢት 23 ቀን 1888 ዓ.ም በጻፉት ደብዳቤ “እንዳውሮፓ ነገሥታት ሥራት ሁሉ ጠብ መፈለጉን ሳያስታውቀኝ እንደ ወንበዴ ሥራት ሌሊት ሲገሰግስ አድሮ ሲነጋ ግንባር ካደረገው ዘበኛ ጋራ ጦርነት ጀመረ፡፡ ጥንት ከአሕዛብ እና ከአረመኔ አገራችንን ጠብቋት የሚኖር አምላክ ከእኛ ባይለይ በእግዚአብሔር ኀይል ድል አደረግሁት” ብለዋል፡፡ የዐድዋ ድል በጸሎት ተጀምሮ በጸሎት የተጠናቀቀ የጸሎት ውጤት ነው፡፡ አባቶቻችን በከፈሉት መሥዋዕትነት ታሪክ እና ቅርስ ብቻ ሳይሆን ሀገርንም አቆይተውልናል፡፡ ይህ ትውልድ እንደ አባቶቹ ታሪክ መሥራት ቢያቅተው እንኳ በመሥዋዕትነት የቆየለትን ታሪክ እና ቅርስ ማወቅ፣ መጠበቅ እና መጠቀም ይኖርበታል፤ ታሪኩን የማያውቅ ከብዙ ሴቶች መካከል እናቱን ለይቶ በማያውቅ ልጅ ይመሰላልና፡፡

በዐድዋ ጦርነት በኢትዮጵያ በኩል በአጠቃላይ ከ80000 - 100000 የሰው ኀይል እንደተሰለፈ የሚገመት ሲሆን ከእኒህም ውስጥ 12000 ያህሉ በስንቅ እና ትጥቅ አቅርቦት በደጀንነት የተሰለፉ፣ የቆሰሉትን በማግለል መድኃኒትነት ባላቸው ሥራ ሥር፣ ቅጠላቅጠል እና ፍራፍሬ ሕክምና የሰጡ ሴቶች እናቶቻችን ናቸው፡፡ በውጊያው 6000 ኢትዮጵያውያን የሕይወት መሥዋዕትነት ከፍለዋል፡፡

የውይይት መርሐ ግብሩን የመሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የታሪክ መምህር አቶ ሽመልስ ቦንሳ እንደተናሩት፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ብዙ ጊዜ ተጋግሞ እንደሚነገረው የጦርነት ሳይሆን የመሥዋዕትነት ታሪክ ነው፡፡ ከደርቡሽ ወረራ ወዲህ ኢትዮጵያዊ ሓሳቦች እና ኢትዮጵያዊ ዕውቀቶች አደጋ ላይ ነበሩ፤ የዐድዋ ድል እስኪታደገን ድረስ፡፡ ፈረንጆች በብዛት መግባት ከጀመሩ በኋላ ዛሬ ያለነው ደግሞ ታሪካችንን መማር አቁመን ኅሊናችን የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ባሪያ ሆኗል፡፡ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የኢትዮጵያ ታሪክ የጻፉት ፈረንጆች ናቸው፤ ታሪካችንን በራሳችን መነጽር እና መንገድ መጻፍ እና መማር፣ እንደ ዕውቀት የተሰጡንን ነገሮች ዳግመኛ መፈተሽ መጀመር አለብን፡፡ “ታሪካችንን ተኝተን የምናቀላፋበት መከዳ (headrest) ሳይሆን እንደ ጥንቱ ሥልጣኔያችን የዕድገታችን መስፈንጠሪያ (fulcrum) ልናደርገው ይገባል፡፡

በጋለ መንፈስ በተካሄደው በዚሁ ውይይት በርካታ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች የተነሡ ሲሆን ከመድረክ እና ከተሳታፊዎች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፤ ተመሳሳይ ጥናታዊ የውይይት መድረክ በየዓመቱ የዐድዋን ድል አከባበር ምክንያት በማድረግ መካሄዱ ቀጣይነት እንዲኖረውም ለማኅበሩ የጥናት እና ምርምር ማእከል ጥያቄ ቀርቧል፡፡         

Pictures
  1. The Battle of Adwa, painting by an unknown Ethiopian artist. The painting depicts the Battle of Adwa, fought between Italy and Abyssinia in 1896. 
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)