March 11, 2011

ተሐድሶ - በወሊሶ

(ደጀ ሰላም፤ ማርች 11/2011)፦ የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-መናፍቃን እምነት አራማጅ ነው የሚባለው “የቅድስት ማርያም የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ማኅበር” በሚል ራሱን የሚጠራው ቡድን ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን በማናለብኝነት በመጣስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔን በመተላለፍ የሚፈጽመውን ተግባር አጠናክሮ በመቀጠል የቡድኑ መሪዎች በዐቢይ ጾም በወሊሶ መካነ ሕይወት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ከበሮ በመምታት ምእመኑን ሲያውኩ  እና ግራ ሲያጋቡ አምሽተዋል፡፡

  •  “እግዚአብሔርን በልቤ አመሰገንኩት፤ የወሊሶ ሕዝብ ከእስራት ተፈታ፤ ነጻ ወጣ፡፡” (ከበሮ ለመምታት ከጳጳሱ ጋራ ተነጋግሮ የተፈቀደለት በጋሻው ደሳለኝ)
  • በከተማው ስታድየም የተካሄደውን የፕሮቴስታንቶች ኮንፈረንስ ሰበብ በማድረግ ‹ጉባኤ ለማድመቅ› በሚል ከበሮ እንዲመታ ፈቃድ የሰጡት የሀገረ ስብከቱ ጳጳስ ናቸው፡፡ 
  •  “ወሊሶ ላይ የተደረገው ሕገ ወጥ እና በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ሊወገዝ  የሚገባው ነው፡፡” (ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን)
  • ቡድኑ በስብከተ ወንጌል ስም የሰበሰበውን በሚልዮን የሚቆጠር ብር ‹ይዞ መሰወሩን› የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሓላፊ ተናግረዋል፡፡
  • መምሪያው በማኅበሩ አባላት ላይ የጣለው እገዳ እንደ ጸና ነው፡፡
  • “የማኅበሩ አባላት በሆኑ ግለሰቦች ባለቤትነት “ታኦሎጎስ” በሚል ስያሜ በኢቢኤስ የሳተላይት ቴሌቪዝን ለሚተላለፈው ስርጭት  መምሪያው ዕውቅና አልሰጠም፤ ዝግጅቱም የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተምህሮ አይወክልም፡፡” (የመምሪያው ሓላፊ)
የመጀመሪያው ጾም፤ ዐቢይ ጾም፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ ስለ እኛ ቤዛ እና አርኣያ ለመሆን በገዳመ ቆርንቶስ አርባ መዓልት እና አርባ ሌሊት የጾመው ጾም ነው(ማቴ.4.1-11)፡፡ ጾሙ ዐቢይ የተባለበት ምክንያት ጌታችን የጾመው ጾም ስለሆነ፣ ታላላቅ የሰይጣን ፈተናዎች ወይም አርእስተ ኃጣውእ(ስስት፣ ትዕቢት፣ ፍቅረ ነዋይ) ድል የተነሱበት ስለሆነ፣ ዛሬም ክርስቲያኖች የመድኃኔዓለም ክርስቶስን አርኣያ ተከትለን ድል የምንነሳበት ጾም ስለሆነ ነው፡፡ በሕዝቡ ዘንድ ጾሙ ሁዳዴ ይባላል፤ ሁዳድ ማለት የመንግሥት መሬት፣ የመንግሥት ርስት ማለት ነው፡፡ የመንግሥት ሁዳድ በሚታረስበት እና አዝመራውም በሚሰበሰብበት ጊዜ ልጅ ዐዋቂ ሳይባል የመንግሥቱ ዜጋ ሁሉ ለሥራ ታጥቆ እንደሚነሣ ይህንንም የጌታ ጾም የጌታ-ሁዳድ-የክርስቶስ-ዜጎች የሆኑ ምእመናን ሁሉ ይጾሙታልና የሁዳዴ ጾም ተብሏል፡፡

ጌታችን የጾመው አርባ መዓልት እና አርባ ሌሊት ሲሆን እኛ ግን በስምንቱ የዐቢይ ጾም ሳምንታት የምንጾመው 56 ቀናትን ነው፡፡ በእውነቱ እንኳን 56 ቀናትን ዓመትም ብንጾም እግዚአብሔር በጸጋ ላይ ጸጋ ይጨምርልናል እንጂ አያስኮንነንም፡፡ ከ56ቱ የዐቢይ ጾም ቀናት ሰባት ቅዳሜ ስምንት እሑድ ይገኛሉ፡፡ እኒህም በድምር 15 ቀናት ሲሆኑ ከጥሉላት(ሥጋ፣ ቅቤ፣ ወተት፣ ዕንቁላል) መባልዕት እንጂ ከእህል ውኃ ስለማይጦሙ 15ቱ ተጨማሪ ቀናት ለእኒህ ሰንበታት ምትክ የሚሆኑ ናቸው፡፡ በጾም ወራት ከመባልዕት መወሰን ብቻ ሳይሆን ዐይን ክፉ ከማየት፣ አንደበት ክፉ ከመናገር፣ ጆሮ ክፉ ከመስማት የተቆጠበ እንደሆነ ጾሙን ክርስቲያናዊ ያደርገዋል፤ “ይጹም ዐይን፤ ይጹም ልሳን፤ እዝንኒ ይጹም እምሰሚዓ ሕሡም በተፋቅሮ” እንዳለ (ቅዱስ ያሬድ፣ ድጓ)::

በየዓመቱ በዐቢይ ጾም ለሚገኙ እሑዶች መደበኛ የሆነ ያሬዳዊ ዜማ እና በቅዳሴ ጊዜም ቋሚ የሆኑ ምንባቦች እና ምስባክ ተመድቦላቸዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያናችንን መዝሙር ንባቡን ከዜማው አስማምቶ፣ አጠናቅሮ ያዘጋጀው ኢትዮጵያዊው ማሕሌታይ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓው(የጾምን፣ የምጽዋትን እና የጸሎትን ጠቃሚነት የሚያስተምረው የዜማ ድርሰቱ) በሁዳዴ ለሚገኙት እሑዶች ሁሉ የተለየ መዝሙር ስለሚሠራላቸው እያንዳንዱ እሑድ በመዝሙሩ ስም ይጠራል፡፡ ከ14ቱ ቅዳሴዎች መካከል የዐቢይ ጾም ቅዳሴዎች - ቅዳሴ ባስልዮስ፣ ቅዳሴ አትናቴዎስ እና ቅዳሴ ጎርጎርዮስ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል ያሳለፍነው የመጀመሪያው የዐቢይ ጾም ሰንበት ዘወረደ ይባላል፡፡ 

ይኸውም ቅዱስ ያሬድ በመጽሐፉ መጀመሪያ አምላክ ከሰማይ መውረዱን፣ ሰው መሆኑን እና መሰቀሉን ስለሚያወሳ ነው፡፡ ሙሴኒም ይሉታል፡፡ ምናልባት ስለ ሙሴ ሕግ እና ጾመ ሙሴን ስለሚያነሣ ይሆናል፡፡ በዕለቱ የሚባለው ምስባክ “ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሃት= ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ፤ ወተሐሠዩ ሎቱ በረዓድ= እርሱን በማምለክ ደስ ይበላችሁ፤ አጽንዕዋ ለጥበብ ከመኢትመዐዕ እግዚአብሔር= እግዚአብሔር እንዳይቆጣ ጥበብን አጽንታችሁ ያዙ” የሚለው የመዝሙረ ዳዊት 2. 11 ጥቅስ ሲሆን ወንጌሉም ከዮሐንስ 3. 10-29 “. . .ወደ ሰማይ የወጣ የለም፤ ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር፤ እርሱ በሰማይ የሚኖረው ነው፡፡. . .” የሚለው ክፍል ነው፡፡ ቀጣዮቹን የዐቢይ ጾም ሰንበታት እንደ ቅደም ተከተላቸው ለማውሳት ያህል ቅድስት፣ ምኩራብ፣ መጻጉዕ፣ ደብረ ዘይት፣ ገብርሔር፣ ኒቆዲሞስ፣ ሆሳዕና በመጨረሻም ትንሣኤ ይባላሉ/መጽሐፈ ግጻዌ፤ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ ገጽ 125/፡፡

መዝሙር ስልት ባለውና ልብን በሚመስጥ ቃና ተቀነባብሮ ከጉሮሮ የሚወጣ ድምፅ ሲሆን የባሕርይ አምላክ ልዑል እግዚአብሔር በሰማይ እና በምድር የሚመሰገንበት እና የሚለመንበት ዐቢይ የጸሎት ክፍል የሆነ ጣዕመ ዜማ ነው፡፡ ለጆሮ በሚያስደስትና በስሜትም ትርጉም የሚያገኙ ተከታታይ ድምፆችን በማዛመድ በዜማ የሚቀርበው የምስጋና እና የልመና መዝሙር ለመማሪያ እና ለማስተማሪያ እንዲሁም ክፉ መንፈስን ለማራቅም ይጠቅማል፡፡ ከዚህ የተነሣ መዝሙር የምስጋና፣ የንስሐ/የልመና፣ ይቅርታ/ እና ትምህርታዊ/የዶግማ፣ ቀኖና እና ትውፊት ትምህርቶችን የሚሰጥ/ የሚሉ ሦስት ዐይነታዎች አሉት፡፡ ከመዝሙር ጥቅም አንዱ ማስተማር ነውና ትምህርተ ሃይማኖትን ወይም ሥርዐተ እምነትን ወይም ክርስቲያናዊ ትውፊትን ያላካተተ፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ እና ከአባቶች ትእዛዝ ውጭ በሆኑ መሣሪያዎች የሚጠቀም፣ ከያሬዳዊ ዜማ ውጭ የሆነ መዝሙር መሰል ዘፈን ኦርቶዶክሳዊ መዝሙር ሊባል አይችልም፡፡

መዝሙርን ጊዜ እና ወቅት ባይገድበውም ወቅቱን እና ጊዜውን የማይመስል መዝሙር ደግሞ አይዘመርም፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን የሥርዐት ቤት ስለሆነች በየወቅቱ እና በየጊዜው በየሰዓቱም ቢሆን የሚዘመር መዝሙር አላት፡፡ በሠርግ ጊዜ የአዳም እና የሔዋን ታሪክ እየተጠቀሰ፣ የአብርሃም እና የሣራ ሕይወት እየተዘከረ፣ ሕይወትን ወደ ቅድስና ሊመራ የሚችል ታሪክ እየተተረከ ይዘመራል፡፡ በክረምትም ውኆች እስከ ልካቸው እንዲሞሉ፣ ሰብሉ ፍሬውን እንዲያፈራ እየተለመነ ይዘመራል፡፡ በኀዘንም ጊዜ ኃጢአትን በማሰብ ፍጹም ይቅርታን የሚለምን መዝሙር ይዘምራል፡፡ ብሉይ ኪዳን እና ሐዲስ ኪዳንን ከሌሎች ዓለማት ቀድማ የተቀበለችው ኢትዮጵያ እጅዋን ዘርግታ ከእግዚአብሔር ካገኘቻቸው ስጦታዎች አንዱ በቅዱስ ያሬድ አማካይነት የተቀበለችው ልዩ መዝሙር ነው፡፡ ከመዝሙሩ ጋራ አብሮ የሽብሸባው፣ የጭብጨባው፣ የእልልታው ሁኔታም እንደ ወቅቱ እና እንደ መዝሙሩ ሁኔታ ይወሰናል፡፡ ስለ ኀዘን እየተዘመረ “እልል” አይባልም፡፡

ከቤተ ክርስቲያናችን የዝማሬ እና የምስጋና ሥርዐት አንዱ ማሕሌት ነው፤ የማሕሌቱ ይዘት እና አፈጻጸም ደግሞ አቋቋም ይባላል፡፡ አቋቋም የመቆም ሥርዐት፣ የዜማውን ስልት የሚገልጽ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ይህ ሥርዐት ፍጹም ሰማያዊ ነገርን የሚያመለክትና የጌታችንን መከራ በዐይነ ኅሊናችን እያየን ወደ ንስሐ እና እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ የሚያደርሰን፣ አባ ሕርያቆስ እንደነገረን “ከጣዕሙ ብዛት የተነሣ አጥንትን የሚያለመልም” ነው፡፡ በእንቅስቃሴው ሁሉ ስለ ክርስቶስ መከራ ሰፊ ትምህርት የሚሰጥበት የቤተ ክርስቲያናችን መዝሙር የሚጠቀምባቸውም የዜማ መሣሪያዎች -ንዋያተ ማሕሌት - በሰማይ መላእክት ዘንድ ያሉ፣ ሰማያዊ ምስጢርን የሚገልጡ፣ የቤተ ክርስቲያናችንን እምነት፣ ሥርዐት እና ትውፊት ከድኅነት ጋራ በማቀናጀት ሥጋዊ ስሜትን በማጥፋት በተመስጦ ወደ እግዚአብሔር የሚያደርሱ ናቸው፡፡ ከንዋያተ ማሕሌቱም ከበሮ፣ ጸናጽል፣ መቋሚያ፣ በገና እና መሰንቆ ተጠቃሽ ሲሆኑ በተናጠል እና በቅንጅት ጥቅም ላይ የሚውሉበት የየራሳቸው የአገልግሎት ጊዜ አላቸው፡፡

የሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን እና የድጓው ሊቃውንት እንደሚያስረዱት በዐቢይ ጾም ለየት የሚል የስብሐተ እግዚአብሔር አደራረስ አለ፡፡ የዚህም መሠረቱ በጾመ ድጓ እና በጾም ምዕራፍ በቅዱስ ያሬድ የተሠራው ቀኖና እና በኋላም በቅዱስ ሲኖዶስ ብያኔ የተደነገገውን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ በመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የሊቃውንት ጉባኤ አባል የሆኑት ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ እንደሚያስረዱት በቀኖናው በታዘዘው መሠረት በዐቢይ ጾም ማሕሌት አይቆምም፤ ማሕሌት ተቁሞ ክብረ በዓል እንዲደረግ ቀኖናው አይፈቅድም፤ ከበሮ አይመታም፤ ጸናጽል አይንሿሿም፤ እልልታም የለም፡፡ እንደ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል ማብራሪያ በዐቢይ ጾም ስብሓተ እግዚአብሔሩ የሚፈጸመው በዘንግ ወይም በዝማሜ ብቻ ነው፤ የሚቆመውም ጾመ ድጓ እና የጾም ምዕራፍ የሚባለው ነው፡፡ እሑድ እሑድ የመወድስ አደራረስ አለ፤ ቅኔ በየምዕራፉ ይደረጋል፡፡ በየምዕራፉ ደግሞ ጾመ ድጓው ይገባል፡፡ በዘወትር ግን ቅኔ የለም፡፡ ምሕላ የሚባል አለ፤ የዘወረደ፣ የምኩራብ የተጽዕኖ ምሕላ አለ፤ ዓርብ ዓርብ ነው የሚደረገው፡፡ በዚህ ቀን ዝማሜም የለም፤ ዝም ብሎ በዜማ ብቻ በጾመ ድጓ የሚደርስ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ ከሦስቱ የቅዱስ ያሬድ የዜማ መደቦች ቅዳሴው የሚቀደሰው በመጀመሪያው ስልት በግእዝ ነው፤ ማሕሌት ስለማይቆም ሁለተኛው ስልት በዕዝል ቅዳሴ የለም፡፡

ከዚህ መሠረታዊ የቀኖናው ትእዛዝ ቅዱስ ሲኖዶስ በብያኔ ያሻሻላቸው ነገሮች ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አብራርተዋል፡፡ ይኸውም በዐቢይ ጾም ውስጥ ያሉ የጌታችንን ዐበይት በዓላት እና የቅዱሳንን ክብረ በዓላት፣ ጥምቀተ ክርስትናን እና የክህነት ሹመትን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ ክብረ በዓላትን በሚመለከት አሁን ለምሳሌ ነገ (መጋቢት አምስት ቀን) የጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በዓል ነው፡፡ ባለፈው የካቲት 23 ቀን ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ በዐድዋ ያደረገውን ተኣምራት በማስመልከት በዓል አክብረናል፡፡ የካቲት 16 ቀን እመቤታችን ቃል ኪዳን የተቀበለችበት ቀን አንዳንድ ጊዜ ጾሙ ይገጥማታል፡፡ መጋቢት መድኃኔዓለም(27) በስቅለቱ ቤዛነቱ የተፈጸመበት፣ መጋቢት 29 በትስብእቱ(ፅንሰቱ) ደገኛ ምስጢር የተፈጸመበት ነው፡፡ ከሆሳዕና በፊት ያሉት ክብረ በዓላት እኒህ ናቸው፡፡ በቅዱስ ሲኖዶስ ብያኔ መሠረት በእኒህ በዓላት ከበሮ እየተመታ ማሕሌት ይቆምና በዕዝል ይቀደሳል፡፡ በደብረ ዘይት ዕለት በአንዳንድ ቦታ ማሕሌት ይቆማል፡፡

በቀኖናው መሠረት የ40 እና የ80 ቀን ጥምቀተ ክርስትና አይፈጸምም ነበር፡፡ ይኸውም የደስታ ጊዜ እንዳይታይ ነው፤ ክርስትና ካለ ሰዎች ድግስ ይደግሳሉ፡፡ ክህነት (ዲቁና፣ ቅስና፣ ጵጵስና) መሾም አልነበረም፤ ሹመት ካለ በወገኑ ማጨብጨብ፣ መብላት፣ መጠጣት አይቀርምና፡፡ ይሁንና አሁን ግን ይህ በቅዱስ ሲኖዶስ ብያኔ ተሻሽሎ ጥምቀተ ክርስትናውም ይፈጸማል፤ ሹመቱም ይሰጣል፡፡ በዚህ መልኩ ቅዱስ ሲኖዶስ በብያኔ ቀኖናውን በማሻሻል ከላይ የተጠቀሱት የቅዱሳን ክብረ በዓላት በተመለከተው አኳኋን በዐቢይ ጾም እንዲከበሩ ቢፈቅድም ከልክ ያለፈ ፈንጠዝያ እና ዳንኪራ ሊደረግበት ከቶም እንደማይገባ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል በአጽንዖት ያሳስባሉ፡፡

ከዚህ አኳያ ባለፈው ሳምንት እሑድ፣ የካቲት 27 ቀን 2003 ዓ.ም ምሽት በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ወሊሶ መካነ ሕይወት ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን በመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ፈቃድ ያልተሰጣቸው እና ሕገ ወጥ በሆኑ ዘማርያን ነን ባዮች የተፈጸመው ተግባር “ሕገ ወጥ እና በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ሊወገዝ የሚገባው” እንደሆነ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል ገልጸዋል፡፡ በተጠቀሰው ቀን ራሳቸውን “የቅድስት ማርያም የስብከተ ወንጌል ማኅበር” በሚል ማስመሰያ የሚጠሩት ሕገ ወጥ ሰባክያኑ አመሻሹ ላይ ከቅዳሜ ጀምሮ ቀስ በቀስ የጀመሩትን በዐውደ ምሕረቱ ላይ የመፋነን ድርጊት እሑድ ዕለት እስከ ምሽቱ አምስት ሰዓት ድረስ በመቀጠል ምእመኑን ግራ ሲያጋቡ እና ሲያውኩ መቆየታቸው ተዘግቧል፡፡ 

በዚሁ ዕለት ጠዋት ቅዳሴው እንዳበቃ በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ አቅራቢያ በሚገኘው የከተማው ስታዲየም ኮንፈረንስ ያደረጉትን ፕሮቴስታንቶች  ሰበብ በማድረግ የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-መናፍቃን ሎሌ የሆነው የዚህ ቡድን ቀንደኛ አባል በጋሻው ደሳለኝ “እነዚህ መናፍቃን እንደፈነጩ አይቀሩም፤ እኛም ዛሬ አምሽተን በዝማሬ፣ በከበሮ እና በእልልታ እናሳያቸዋለን” በማለት መናገሩ ተዘግቧል፤ አመሻሹም ላይ የሀገረ ስብከቱን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሳዊሮስን አነጋግሮ እንደተፈቀደለት በመጥቀስ መሰሎቹ ትዝታው ሳሙኤል፣ ዘርፌ ከበደ እና ሌላ አንድ መሰላቸው ሳይገባቸው እና ሳይባቸው በያዙት ንዋየ ማሕሌት/ከበሮ/ በዐውደ ምሕረቱ ላይ ሲረግጡ/ዘርፌ ከበደ በቅርቡ በድሬዳዋ ዐውደ ምሕረት ላይ “ዛሬ ይሄን መድረክ እንቀውጠዋለን” እንዳለችው/ ማምሸታቸው ተገልጧል፡፡

በመጀመሪያ ላይ በማጉረምረም ለመቃወም የሞከረው ምእመን በጋሻው “ከሊቀ ጳጳሱ ተነጋግሮ እንደተፈቀደለት” ሲናገር ከጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በኋላ ተዛውረው በመጡትና ብዙም በማያውቃቸው ብፁዕ አባት ግራ በመጋባት እያመነታ እና ገሚሱም ቀስ በቀስ እየተላመደ አብሮ ለማጨብጨብ መገደዱን ከስፍራው የተገኙ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ በላይ ግን ሕዝቡን ያስቆጣው ሊቀ ጳጳሱ በተቀመጡበት በዐውደ ምሕረቱ ላይ እንዳሻው የፈነጨው በጋሻው ደሳለኝ ፕሮቴስታንቶቹን መስሎ እና አህሎ የደረበው “የነጻ አውጪነት” ካባ ነው፡፡ ነጻ ያልወጣው “ነጻ አውጪው” በጋሻው እንዲህ ሲል ነበር ዴማጎጂውን የለፈፈው፡- “ብፁዕ አባታችን ታላቅ አባት ናቸው፤ እግዚአብሔርን በልቤ አመሰገንኩት፤ የወሊሶ ሕዝብ ከእስራት ተፈታ፤ ይሄ ሕዝብ ነጻ ወጣ፡፡”


የሊቃውንት ጉባኤ አባሉ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል በጋሻው በማናለብኝነት በተናገረው እና “ሊቀ ጳጳሱ ፈደዋል” በተባለበት መልክ አንድ ሀገረ ስብከት ወይም አንድ አጥቢያ ብቻውን ቀኖናን በማሻሻል ፈቃድ ሊሰጥ እንደማይችል ነው አብክረው የሚያሳስቡት፡፡ “ወሊሶ ላይ የተደረገው ሕገ ወጥ ነው፤ ቅዱስ ሲኖዶስ ብያኔ ያልሰጠበት ነው” ያሉት ሊቁ ድርጊቱ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ሊወገዝ እንደሚገባው አመልክተዋል፡፡ “የደስታ ስሜት የሚሰጡ ነገሮች ሁሉ መታቀብ አለባቸው፡፡ ሃገራችን ኢትዮጵያ ተጠብቃ የኖረችው በጾሟ፣ በጸሎቷ እና በትሩፋቷ ነው፡፡ ጾምን ብናከብረው ያከብረናል፤ ብንወደው በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደድን ያደርገናል፡፡ ዐቢይ ጾም ደግሞ እንደ ስሙ ዐቢይ ነው፡፡ ከሌሎች አጽዋማት ለይተን ልናከብረው ይገባናል፡፡ ጾም ከእህል ከውኃ መከልከል ብቻ አይደለም፤ ትልቁ ነገር የጾሙን ሥርዐት አክብሮ ማስከበር ነው፡፡”

“እነዚህ ሰዎች ለስንት ዘመን ከበሮ ሲመቱ ኖረዋል፤ ስንት ሰው አምጥተዋል?” በማለት የሚጠይቁት ሌሎች መምህራን በበኩላቸው ሎሌው እና ጥቅመኛው ቡድን ለንስሐ የሚያበቃ ስብከትም ይሁን የንስሐ መዝሙር እንደማይሆንላቸው ስለሚያውቁ “ከበሮ ካልተመታ አይሞቅልንም” በሚል ክሕደታቸውን ለማሰራጨት ወቅቱ ስላልፈቀደላቸው የመረጡት የማደናገሪያ ስልት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ “ወራቱ የኀዘን፣ የዝምታ እና የለሆሳስ እንጂ በከበሮ ፍሥሓ የሚደረግበት አይደለም፤ ሥርዐተ እምነት እና የቅዱስ ሲኖዶስ ብያኔ በአንድ አጥቢያ እና ሀገረ ስብከት ፈቃድ ሊሻሻል አይችልም፡፡ እኒህ ሕገ ወጥ ሰባክያን እና ዘማርያን ነን ባዮች ዛሬ ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን ጥሰው በጾም ከበሮ በመምታት ‹ሕዝቡን ከመናፍቃን እንጠብቃለን› ካሉን ነገ ‹ጾሙን ሽረን ሕዝቡን እናምጣው› ላለማለታቸው ማረጋገጫ የለም፤ ወትሮስ ቢሆን የመናፍቃኑ ጥፋት ምን ሆነና ነው? ምእመኑን ከሥርዐት ውጭ እያደረጉ ጥበቃ ብሎ ነገር የለም፡፡ ድርጊታቸው ሁሉ ምእመኑን ወደ መናፍቃኑ የመውሰድ እንጂ ምእመኑ ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን ተምሮ እና አምኖ እንዲጸና አይደለም፡፡”

ሁኔታው በስፋት ከተሰማ በኋላ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ለሕገ ወጦቹ ‹ዘማርያን› እና ‹ሰባክያን› ፈቃድ በሰጡት እና ያለአገባቡ የጾሙ ቀኖና በመጣሱ የተሰማቸውን ኀዘን ገልጸዋል፡፡ ከስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ፣ ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አስተዳደር፣ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የስብከተ ወንጌል ክፍል፣  ከማኅበረ ቅዱሳን፣ ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች እና የስብከተ ወንጌል ሓላፊዎች ጋራ የፀረ-ፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ ንቅናቄ በመፍጠር ከ12 በላይ የሀገረ ስብከቱ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ተከታታይ ጉባኤያትን እያካሄዱ የሚገኙት ሰባክያነ ወንጌልም ትላንት በቦሌ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ባካሄዱት ጉባኤ ድርጊቱን በማጋለጥ ምእመኑ ሕገ ወጦቹን እንዲቋቋማቸው አሳስበዋል፡፡

የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ቅዱስ ሲኖዶስ ሕገ ወጥ ሰባክያነ ወንጌልን እና ዘማርያንን በሚመለከት የካቲት 12 ቀን 2001 ዓ.ም ባስተላለፈው ውሳኔ፣ “የየሥራ ዘርፉ እንቅስቃሴ የሚጀመረው በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ስለሆነ የእያንዳንዱ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ የተጣለበትን ሓላፊነት ተገንዝቦ ሕገ ወጦች ፈቃድ ሳይኖራቸው እንዳያስተምሩ የቁጥጥር ተግባሩን በማጠናከር የቤተ ክርስቲያኒቱን ህልውና ከሚፈታተን ተግባር ይጠብቅ ዘንድ” ጥብቅ መመሪያ መስጠቱ ይታወሳል፡፡ የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሓላፊ አባ ኀይለ ማርያም መለሰ መምሪያው በእነ በጋሻው ደሳለኝ ላይ የጣለውን እገዳ እስከ አሁን እንዳላነሣና እግዱን የማስከበር ሓላፊነት የየአህጉረ ስብከቱ ሓላፊዎች እና የአጥቢያ አስተዳደር ተግባር መሆኑን በዚህ ወር ታትሞ ከወጣው ሐምራዊ መጽሔት ቅጽ 4 ቁጥር 44 እትም ጋራ ባካሄዱት ቃለ ምልልስ አስታውቀዋል፡፡

ሕገ ወጦቹ መቀመጫውን በአሜሪካ ባደረገው ሲ.ቢ.ኤስ የቴሌቪዥን ጣቢያ “ታኦሎጎስ” በሚል ስያሜ ለሚያስተላልፉት ፕሮግራም ከመምሪያው ምንም ዐይነት ዕውቅና ሳይሰጣቸው እና በሚዲያ ማገልገል እንደሚችሉ ፈቃድ ሳያገኙ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም የአየር ሰዓት ይዘው ፕሮግራም ማስተላለፋቸው እንዳስገረማቸው የመምሪያ ሓላፊው አልሸሸጉም፡፡ ቤተ ክርስቲያን መልእክቷን የሚያስተላልፉ ሰዎችን የዕውቀት፣ የሥነ ምግባር ደረጃ እና ተጠሪነት መኖር አለመኖሩን በቅድሚያ እንደምታጤን የተናገሩት ሓላፊው፣ በጣቢያው ኤዲቲንግ ሳይሠራባቸው እና ሳይጣሩ በሚሠራጩ ዶግማዊ እና ቀኖናዊ ያልሆኑ መልእክቶች ሳቢያ ቅሬታዎች እየተሰሙ መሆኑን ተናግረው ዝግጅቱ ቤተ ክርስቲያንን እንደማይወክል አስታውቀዋል፡፡
“ቤተ ክርስቲያን የምትጓዘው እነሱ በሚሉት እና በመረጡት መንገድ አይደለም፡፡ ምን መስፈርት ማሟላት እንዳለባቸው ተጠርተው ከተነገራቸው በኋላ ቅጽ አዘጋጅተን ሰጥተናቸዋል፡፡ የት እንደተማሩ፣ የት እንዳገለገሉ. . .ወዘተ የመሳሰሉትን የሚጠይቅ ቅጽ እና መታወቂያ አዘጋጅተናል፡፡ በመንፈሳዊ ትምህርት ዲግሪ እና ዲፕሎማ ከሌላቸው ደግሞ በካህናት ማሠልጠኛ የተማሩ እና ከስድስት ዓመት በላይ በሰንበት ት/ቤት ያገለገሉ መሆናቸውን፣ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናቸው የሚታወቅ መሆን እንዳለበትም ተዘርዝሯል፡፡ ከዚህ በኋላ ፈተና ይፈተናሉ፤ የቤተ ክርስቲያኒቱን አቋም በትክክል የሚገልጹ እና የሚያሟሉ ሆነው ሲገኙ ፈቃድ ይሰጣቸዋል፡፡”
ይህን መመዘኛ ወደ ጎን በማለት ከዕውቀት እና ሕጋዊነት ጋራ የተጣሉት እነበጋሻው የመምሪያው የበላይ ሓላፊ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ለ29ው የመንበረ ፓትርያሪክ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ እንደተናገሩት፣ “ስሙ የማይጠራ ሰባኪ አለ፤ አጥቢያህ የት ነው? አገሩን ሁሉ የምታማሰል፣ የምታሸብር አንተ ማነህ?” ሲባል “የሕዝብ ነኝ” አለ፡፡ “የሕዝብ ነኝ የሚል አንደኛ መንግሥት ሁለተኛ ቃልቻ ነው፤ ለመሆኑ ተመዝግበሃል ወይ? ሲባል ፍጥጥ አለ፤ አፈረ፡፡ ይህንኑ ሁኔታ ለብፁዕ አቡነ ፊልጶስ በደብዳቤ አሳወቅን፡፡ በኋላ ግን በየት እንደገባ፣ በየት እንደሾለከ ሳናወቅ በዚሁ አዳራሽ ሲሾም ሲሸለም [ከፓትርያሪኩ] ዐየን፡፡ እባካችሁ ሥራ አስኪያጆች የምናወጣውን መመሪያ አስከብሩልን፡፡ ይህ ማኅበር [“የቅድስት ማርያም የስብከተ ወንጌል ማኅበር”] አደገኛ ነው፤ መብረቅ ብልጭ ቢል ሰዓሊ ለነ ቅድስት የማይል፤ ፍላጎቱ እና ስሜቱ ገንዘብ ማግኘት ብቻ ነው፡፡”

ብፁዕነታቸው በአጠቃላይ ጉባኤው ላይ ስለእነ በጋሻው የተናገሩትን አባ ኀይለ ማርያም መለሰ በሐምራዊ መጽሔት ቃለ ምልልሳቸው ላይ አጠናክረውታል፡፡ “በተለያየ ምክንያት ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናትን፣ ጧሪ ቀባሪ የሌላቸውን አረጋውያንንና የመሳሰሉትን ለመርዳት” በሚል በፓትርያሪክ አቡነ ጳውሎስ ፈቃጅነት እና በልዩ ጽ/ቤታቸው ሓላፊ ብፁዕ አቡነ ገሪማ ፊርማ በቁጥር ል/ጽ/103/2002 በቀን 23/02/2002 ዓ.ም በወሰደው ፈቃድ የተቋቋመው “የቅድስት ማርያም የስብከተ ወንጌል ማኅበር” ታኅሣሥ 25 ቀን 2002 ዓ.ም “የገናን ዋዜማ በወንጌል እና በዝማሬ” በሚል በሚሌኒየም አዳራሽ በ30 ብር የመግቢያ ዋጋ ‹ጉባኤ› አዘጋጅቶ ነበር፡፡ ከዚህ ጉባኤ ቀደም ሲል ግን ጉባኤውን ለከተማው ባለጸጎች ለማስተዋወቅ፣ ለስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያው “በየክፍለ ሀገሩ ጉባኤ ለማካሄድ የሚያስችል ሞንታርቦ፣ ላንድ ክሩዘር መኪና፣ ድምፅ ማጉያ ለመግዛት” በሚል ሌላ የገቢ ማስገኛ ስብሰባ በሒልተን ሆቴል ጠርቶ ነበር፡፡ በዚህ ስብሰባ እስከ 150‚000 ብር በጥሬ እና በቃል ኪዳን ተገኝቷል፡፡ ለዋናው የሚሌኒየም አዳራሽ ጉባኤ 78‚000 የመግቢያ ትኬቶች እያንዳንዱ በብር 30 ተሸጧል፡፡ 300 የቪ.አይ.ፒ ትኬቶች እያንዳንዳቸው በ300 ብር ተሸጠዋል፡፡ በአጠቃላይ የአዳራሽ ኪራይ እና ሌሎች ወጪዎች በስፖንሰርሽፕ መሸፈናቸው ግምት ውስጥ ሲገባ ቢያንስ ከ3.5 ሚልዮን ብር በላይ እንደተሰበሰበ መገመት ይቻላል፡፡

እስኪ አባ ኀይለ ማርያም ይህን አስመልክቶ ከሐምራዊ መጽሔት ጋራ ያደረጉትን ጥያቄ እና መልስ እንከታተል፤

ሐምራዊ፡- ከአንባብያን የደረሰን ሌላ መረጃም አለ፡፡ “ቅድስት ማርያም የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ማኅበር” የተሰኘው ማኅበር ከዚህ ቀደም ከእናንተ ፈቃድ አግኝቶ በሚሌኒየም አዳራሽ ጉባኤ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ አነሣሡ መልካም የነበረውን ያህል እንቅስቃሴውን ሊቀጥል ያልቻለበት ምክንያቱ ምን ነበር?

አባ ኀይለ ማርያም፡- እንቅስቃሴው መልካም የነበረ ቢሆንም ፍጻሜው ትራጄዲ ነበር፡፡ በዚያን ወቅት እኔና የመምሪያው ሠራተኞች አዲሶች ነበርን፡፡ ፈቃዱ በቀጥታ ከላይ ሲያገኙት ፈቃድ ከማን እንደተሰጣቸው ጠየቅን፤ እኛ ሳናውቅው ጉባኤው መካሄድ የለበትም ብለን ሰፊ ውይይት አካሄድን፡፡ በመጨረሻም ስምምነት አድርገን ፈቃዱን ከጠቅላይ ቤተ ክህነት አግኝተዋል፡፡ ያ ፈቃድ እነርሱ በስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሥር እንደሆኑ ቢገልጽም ግልባጭ ግን አልተጻፈልንም፡፡ በኋላ ወደ ስምምነት ስንደርስ በሚሌኒየም አዳራሽ የሚካሄደውን ጉባኤ ስብከተ ወንጌል መምሪያ መቆጣጠር አለበት ተባባልን፡፡

በሚሌኒየሙ አዳራሽ ጉባኤ እኔም ተገኝቻለሁ፡፡ ፕሮግራሙ በመልካም ሁኔታ ተጠናቀቀ፡፡ ገንዘቡ ተሰበሰበ፡፡ “ምን ያህል ገንዘብ እንዳስገባችሁ ሪፖርት አድርጉ” አልናቸው፡፡ የተወሰነውን ከገለጹ በኋላ የተቀረው ሰዎች እጅ ላይ ነው የሚገኘው አሉን፡፡ ብዙ ጠበቅናቸውና በደብዳቤ ጠየቅናቸው፡፡ መልስ አልሰጡንም፡፡ መጨረሻ ላይ ጠፉ፤ ስልካቸውን አጠፉ፤ አድራሻቸውን ሰወሩ፡፡ የባንክ አካውንታቸውን ስላላወቅን መስዘጋት አልቻልንም፡፡ መቼም የሃይማኖት ሰው ይዋሻል ብለን አልጠበቅንም፡፡

ሐምራዊ፡- ጉባኤውን ያዘጋጀው ማኅበር 900‚000 ብር ለእናንተ ማስገባቱ ነበር በሚዲያ ጭምር የተነገረው. . .

አባ ኀይለ ማርያም፡- ለማን ነው ያስገቡት?

ሐምራዊ፡- ለስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መመሪያ ማስገባታቸውን ነበር የሰማነው. . .

አባ ኀይለ ማርያም፡- በፍጹም! እኛ ጋራ ሠባራ ሳንቲም ገቢ አልሆነም፡፡ ጠይቀን፣ ጠይቀን በመጨረሻ ጠፉብን!፤. . .ተሰወሩ፡፡ የፕሮግራሙ አዘጋጆች ወጣት ባለሃብቶች እና የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት መሆናቸውን ነበር በጽሑፍ ያገኘነው መረጃ የሚጠቁመው፡፡

ሐምራዊ፡- እና እነዚህ ባለሃብቶች ከጉባኤው የሰበሰቡትን ገንዘብ በሙሉ ይዘው ተሰወሩ ነው የሚሉን?

አባ ኀይለ ማርያም፡- ምንም ያስገቡት ገንዘብ የለም፡፡

ቤተ ክርስቲያንን በዚህ መልኩ የንግድ ማእከል በማድረግ ጥቅሙን እያሳደደ ወዲያውም ደግሞ ከተሐድሶ መናፍቃን ጋራ ተሳስሮ እና ተመጋግቦ በአሽከርነት የሚያገለግለው ይኸው ቡድን በቅርቡ በኀያል መንፈሳዊ ወኔ እየተቀጣጠለ በሚገኘው የፀረ-ፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ ንቅናቄ በወሳኝ መልኩ እየተመታ ገኛል፡፡ አንዳንድ አባላቱም በንቅናቄው ተማርከው የውግንና እና የአሰላለፍ ለውጥ እያደረጉ ናቸው፤ በወላዋይነት የሚያመነቱም አልታጡም፡፡ ከ‹80›ዎቹ አንዱ ሊሆኑ እንደሚችሉ ስጋት ከገባቸው አንዳንዶቹ ለንቅናቄው ግንባር ቀደም አባላት አማላጅ ሲልኩ አንዳንዶቹም ችግሩን በመካድ ጥረቱን ጥላት ለመቀባት በየመድረኩ እየተወራጩ ይገኛሉ፡፡ ለሁለቱም የሚበጃቸው ግን ለቡድናዊ ጥቅማቸው እና ለግል ዝናቸው ሳይሆን ለኅሊናቸው እውነት ማደር ነው፡፡ 

በዚህ ሐተታዊ ዜና የተዘረዘረው ዐውደ ምሕረት የወጣ የቀሪው ጭፍራ ድርጊት ግን የቀቢጸ ተስፋ ነውና እርሱን የማጋለጥ እንቅስቃሴ በማጠናከር ለማሟሸሽ አልያም ለይቶለት አባቱ እና እናቱ ወደሆነው የፕሮቴስታንት ጎራ እንዲቀላቀል ለማድረግ የተጀመረው የአርቲስቶቹ “ማኅበረ ላሊበላ” (የእነ ፍረ ሕይወት መለሰ፣ ሽመልስ አበራ፣ ካሌብ ዋለልኝ፣ ዋስይሁን ንጋቱ፣ ዳንኤል፣ እስጢፋኖስ እና ሌሎችም “ተዋሕዶ” የተሰኘ ልጅ ዐዋቂውን በእንባ ያራጨ መንፈሳዊ ድራማ)፣ የመዝሙር ቤቶቹ የቪሲዲ ኅትመት (የማኅበረ ቅዱሳን ኦዲዮ ቪዥዋል የዲያቆን ዓባይነህ ካሴን “ውኃ የሌላቸው ምንጮች” የመምህር ዘመድኩን በቀለ ጌልጌላ መዝሙር ቤት የዲያቆን ዳንኤል ክብረትን “የገሃነም ደጆች” እንዳሳተመው በቀጣይም “አርማጌዶን ቁጥር ሁለት” ለማሳተም እንደተዘጋጀው)፣ በመንበረ ፓትርያሪክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በመምህር ዳንኤል ግርማ ሰብሳቢነት በመምህር ሱራፌል ወንድሙ ፀሓፊነት እየተሰበሰቡ የመድረክ ውሏቸውን ያለ ምሕረት በመገምገም፣ ቀጣይ ስምሪቶችን በማቀድ የሚተጋው የሰባክያኑ (መ/ር መኮንን ደስታ፣ መ/ር ተስፋዬ ሞሲሳ፣ መ/ር በላይ ወርቁ፣ መ/ር ዳዊት ጥበቡ፣ መ/ር ታዴዎስ ግርማ፣ መ/ር ወንድወሰን መገርሳ፣ መ/ር አስቻለው ከበደ፣ መ/ር ዘመድኩን በቀለ፣ መጋቤ ብሉይ ዓምደ ወርቅ፣ መ/ር ኅብረት የሺጥላ፣ መ/ር ኀይሉ ጉተታ፣ መ/ር ቀለም ወርቅ፣ መ/ር ንጉሡ፣ መ/ር ምሕረተአብ አሰፋ፣ መ/ር ዮናስ ፍቅረመ/ር ፈቃዱ አረጋ፣ ባሕታዊ ሶፎንያስ፣ መ/ር ጳውሎስ መልክአ ሥላሴ፣ መ/ር ዘኤልያስ ወልደሚካኤል፣ መ/ር ዳንኤል ክብረት፣ መ/ር ታደሰ ወርቁ፣ መ/ር ያረጋል አበጋዝ፣ መ/ር ዘማሪ ኤርሚያስ አሰፋ) ጥምረት፣ የነገረ መለኮት ምሩቃን ማኅበር እገዛ እና የተቋማቱ ሁሉ ትብብር ቀጥሎ በአስተዳዳራዊ እና ቀኖናዊ ርምጃ ሊታገዝ ይገባል፡፡ ከአሜሪካ ዘማሪ ወንድወሰን በቀለ እና ዘማሪት ፋንቱ ወልዴ፣ ከአገር ቤት ወ/ሮ ዘውዴ ገብረ እግዚአብሔር፣ ወ/ሮ ሓዳስ እና መ/ር ዳንኤል ክብረት ጥረቱን በገንዘባቸው ጭምር ረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ምእመኑ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን አዳክሞ ለመውረስ ወይም ከፍሎ ለመረከብ የተወጠነው ሤራ በየመድረኩ በሚገለጽበት ወቅት ሌላ ነጋሪ ወይም አስታዋሽ ሳያስፈልገው የሤራውን አስፈጻሚዎች በራሱ ትንተና በስም ዝርዝር ሳይቀር ወደሚለይበት መደምደሚያ፣ የስብከተ ወንጌል ሓላፊዎች ትክክለኛውን መምህር ብቻ እንዲመድቡ ወደሚጠይቅበት ንቃት፣ ሕገ ወጥ ሰባክያንን እና ዘማርያንን ከየመድረኩ ወደሚያባርርበት ቁርጠኝነት ተሸጋግሯል፤ በቅርቡ በገርጂ ቅዱስ ጊዮርጊስ በያሬድ አደመ፣ በናዝሬት እግዚአብሔር አብ በአሰግድ ሣህሉ ላይ የወሰዳቸው የማባረር ርምጃዎች ቀናዒው ምእመን የሚሰጡትን መረጃዎች ከራሱ ጋራ አዋሕዶ የተግባር መመሪያው ማድረግ መጀመሩን አመላካች ነው፡፡ ጥንቱንም በኅሊናው ጓዳ በልቡናው ሰሌዳ የተቀረጸለትን የቀናውን የአባቶቹን ሃይማኖት ገላልጦ እንዲሞቀው የሚያደርጉትን ደገኛ መምህራን ከመድረኩ ግርጌ ጠብቆ ግንባራቸውን ይስማል፡፡ “ይህ ሁሉ እየተፈጸመ እስከዛሬ የት ነበርን?” በሚል ቁጭቱን፣ “መርሐ ግብሩ እንዲህ እንዳማረበት ይቀጥል ይሆን?” በማለት ስጋቱን ይገልጻል፤ “ቸብ ቸብ አድርጉ፤ እጃችሁኝ አውጡ እየተባልን ቢዝነስ ሲሠራብን ኖረናል፤ ቤተ ክርስቲያን እውነተኛውን ከአስመሳዩ እንድትለይልን አሳስቡልን” በማለት የአደራ መልእክቱን ያስተላልፋል፡፡ ከዚህም በላይ ጥረቱን በምን እናግዝ በማለት በገንዘቡ፣ በጉልበቱ አስተዋፅኦ ሊያደርግ ከንቅናቄው ጎን ተሰልፏል፡፡

ከአገልጋዮችም መካከል አንዱ የሐዲስ ኪዳን መምህር እንዲህ ብለዋል - “ውሻ ተነክሼ ቁራሽ ለምኜ ተምሬ መጋቤ ሐዲስ የተባልሁበትን ማንም በሜዳ ሲጠራበት አፍሬበት ነበር፡፡ እግዚአብሔር ይስጣችሁ አሁን አንገቴን ቀና እንዳደርግ፣ ቦታ እንዳገኝ አደረጋችሁኝ፡፡ ምነው ጌታ፣ ነጋዴዎቹን በጅራፍ ከመቅደስህ አስወጥተህ ከሓዲዎቹን ዝም አልሃቸው?”

የቤተ ክርስቲያናችን ከፍተኛ አስተዳደር ለዚህ ዐይነቱ መተባበር ተገቢውን የበላይ አመራር በመስጠት ለውጤት እንዲያበቃው ይጠበቃል፡፡  

ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ …. 

ቸር ወሬ ያሰማን፣ አሜን

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)