March 6, 2011

የብፁዕ አቡነ ይሥሓቅ የቀብር ሥነ ሥርዐተ ተፈጸመ

  • ብፁዕነታቸው ወደ አሜሪካ ለመሄድ ዝግጅታቸውን አጠናቅቀው ነበር
  • ‹‹ብፁዕነታቸው በመንፈሳዊው ትምህርት የተሟላ ሊቅነት ያላቸው፣ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን በኩል እግዚአብሔርን በዝማሬ መላእክት፣ ሕዝበ ምእመናንን በትምህርት፣ በስብከተ ወንጌል እና በጸሎተ ቡራኬያቸው ያገለገሉ ያሬዳዊ ቅርስ ነበሩ፡፡›› (ዜና ሕይወታቸው)
  • ‹‹ድጓው፣ ጾመ ድጓው፣ ዝማሬ መዋስዕቱ አልሞተም፤ እዚያው ከዋናው ከቅዱስ ያሬድ ጋራ በሰማይ ያመሰግኑበታል፤ የካቲት 24 ቀን የተክለ ሃይማኖት በዓል ዕለት በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም እንዲቀድሱ ተራ ደርሷቸው ነበር፤ ነገር ግን በወዲያኛው ዓለም ከእነ ቅዱስ ያሬድ እና ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጋራ እንዲቀድሱ ተጠሩ፡፡›› (ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ)
(ደጀ ሰላም፤ ማርች 5/2011)፦ ከትናንት በስቲያ በድንገተኛ ሕመም በተወለዱ በ76 ዓመታቸው ያረፉት የባሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ይሥሓቅ ሥርዐተ ቀብር ዛሬ፣ የካቲት 26 ቀን 2003 ዓ.ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡ የብፁዕነታቸው አስከሬን ትናንት ዓርብ የካቲት 25 ቀን 2003 ዓ.ም በዘጠኝ ሰዓት ወደ ካቴድራሉ ተወስዶ ጸሎተ ፍትሐት ሲደረስለት ያደረ ሲሆን በመላው አህጉረ ስብከትም ጸሎተ ፍትሐቱ ተደርጓል፡፡

ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጋራ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመመሪያ እና የድርጅት ሐላፊዎች፣ የባሌ ሀገረ ስብከት ሠራተኞች፣ የአዲስ አበባ አድባራት እና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች እና በርካታ ምእመናን በተገኙበት ዛሬ ረፋዱ ላይ በተፈጸመው የብፁዕነታቸው የቀብር ሥነ ሥርዐት የየረር ቅድስት ሥላሴ እና የየረር በኣታ አብያተ ክርስቲያን ካህናት ዕለቱን የሚመለከት አመላለስ ቀርቧል፡፡ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የአስተዳደር መምሪያ ሓላፊ መጋቤ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ዘማርያም፣ በሊቃውንት ጉባኤ አባሉ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ እና ሌሎች ሁለት ሊቃውንት ብፁዕነታቸው በሰብእናቸው የነበራቸውን መልካምነት፣ በትምህርታቸው የነበራቸውን ምሉነት የተመለከቱ ቅኔዎች ቀርበዋል፡፡

የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገሪማ በንባብ ባሰሙት የብፁዕነታቸውን ዜና ሕይወት፣ ብፁዕ አቡነ ይሥሓቅ በትምህርት ይሁን በሥራ ላይ ቁጥብ እና ርጉ አንደበትን ገንዘባቸው ያደረጉ፣ የማንንም ጥቅም እና ክብር የማይነኩ፣ ከራሳቸው ጥቅም እና ክብር ይልቅ የሌላውን የሚያስቀድሙ ኢትዮጵያዊ ብፁዕ አባት እንደነበሩ ተገልጧል፡፡ ብፁዕነታቸው በመንፈሳዊው ትምህርት የተሟላ ሊቅነት እንደነበራቸው የገለጹት ብፁዕ አቡነ ገሪማ፣ ብፁዕ አቡነ ይሥሓቅ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን በኩል እግዚአብሔርን በዝማሬ መላእክት፣ ሕዝበ ምእመናንን በትምህርት፣ በስብከተ ወንጌል እና በጸሎተ ቡራኬያቸው ያገለገሉ ‹‹ያሬዳዊ ቅርስ ነበሩ›› ብለዋቸዋል፡፡

የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ትምህርተ ወንጌል የሰጡ ሲሆን ከእርሳቸው በኋላም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ባሰሙት ቃለ ምዕዳን ብፁዕ አቡነ ይሥሓቅ ወደ ውጭው ዓለም ሄደው ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል አማክረዋቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ‹‹ያልተለመደ ስለሆነ ነው እንጂ እንደ ብፁዕነታቸው ያሉትን የምንሸኘው ኀዘንተኞች መስለን አይደለም፤ እንዲህ ላሉ ሰዎች ሞት ዕረፍት ነው፤ እንዲህ ላሉ አባቶች ሞት ክቡር ነው፤ ከሰማያውያን ማኅበረ መላእክት ጋራ የሚደመሩበት ነውና፤›› ያሉት ፓትርያርኩ የምናዝንበት ነገር ካለ ‹‹በእነርሱ መለየት ስለጎደለብን ነገር ብቻ›› መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ፓትርያርኩ ብፁዕነታቸው ከቁጣ እና ዐምባገነናዊ ንግግር የራቀ፣ ተባሕትዎ ያልተለየው ጸጋ እንደነበራቸው አስታውሰው የዜማው ሊቅ በማረፋቸው ድጓው፣ ጾመ ድጓው፣ ዝማሬ መዋስዕቱ እንዳልሞተ፣ እንዲያውም ከዋናው ከቅዱስ ያሬድ ጋራ በሰማይ እንደሚያመሰግኑበት አመለክተዋል፡፡ ‹‹ቅዱሳን ሥራቸው ምስጋና፣ ምስጋናቸው ዕረፍት ነው፤ ብፁዕነታቸው ለአገልግሎት በሄዱበት ቀድሰው፣ አቁርበው እና አስተማረው ነው የሚመጡት፤›› በማለት ያስተማሩት አቡነ ጳውሎስ ስለ ብፁዕነታቸው የመጨረሻ ተልእኮ እና ጠቅላላ ሰብእና የሚከተለውን በመናገር ቃለ ምዕዳቸውን አጠናቅቀዋል፤

‹‹የካቲት 24 ቀን የተክለ ሃይማኖት በዓል ዕለት በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም እንዲቀድሱ ተራ ደርሷቸው ነበር፤ ነገር ግን በወዲያኛው ዓለም ከእነ ቅዱስ ያሬድ እና ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጋራ ለመቀደስ ተጠሩ፡፡ ብዙ ሰው ድምፁን ለማሰማት፣ የሚፈልገውን ለማስፈጸም፣ ራሱን ለማስቀደም ሲወጣ ሲወርድ ነው የሚኖረው፤ እኚህ ብፁዕ አባት ግን በማስተዋል የሚጓዙ፣ ሰው ሲናገራቸው ፈገግ ከማለት በቀር ክፉ የማይመልሱ ርጉ ናቸው፡፡ የሚያስፈልጉን እንደርሳቸው በትሕትና የተመሉ አባቶች ናቸው፡፡                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                      

ወደ ውጭው ዓለም ሄደው ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል አማክረውኝ ነበር፤ የጻድቃን ጥሪ ቀጠሮ የለውም፤ ዕረፍት አልነበራቸውም፤ ወደ ዘላለም ዕረፍት ሄዱ፡፡ በሥራቸው ተጠቃሚ የነበረች ቤተ ክርስቲያን ግን እንዳትጎዳ፣ የሚያበረታቱ እና የሚያንጹ አባቶች እንዳይጎድሉ፣ እግዚአብሔር የበቁ አባቶችን በእግራቸው እንዲተካላት ያሉትንም እንዲያበረታቸው ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡››

ብፁዕ አቡነ ይሥሓቅ ከሰኔ አንድ ቀን 1992 ዓ.ም ጀምሮ በሊቀ ጳጳስነት ይመሩት ለነበረው የባሌ ሀገረ ስብከት መንበረ ጵጵስና ለማሠራት በነገው ዕለት በመንበረ ፓትርያርኩ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ የሚካሄድ የገቢ ማሰባሰቢያ የስብከተ ወንጌል ጉባኤ መርሐ ግብር ነበራቸው፡፡ ፓትርያርኩ ያመለከቱት የብፁዕነታቸው የውጭ ጉዞ ከሕክምና እና ከቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ጋራ የተያያዘ እንደነበር ቀራቢዎቻቸው ይናገራሉ፡፡ ከ1965 - 1972 ዓ.ም በታዕካ ነገሥት በኣታ ለማርያም ገዳም ለስምንት ዓመታት የብሉያት ርጓሜን እየተማሩ ሲያገለግሉ የሊቀ መዘምራንነት ማዕርግ የተሰጣቸው የድጓው ሊቅ፣ በ1980 ዓ.ም ወደ ጀርመን ተጉዘው ለአንድ ዓመት ቋንቋውን ባጠኑበት ወቅት በኮሎኝ ቅዱስ ሚካኤል በመቀደስ እና መንፈሳዊ አገልግሎት በመስጠት የቆዩ መሆናቸው በንባብ በተሰማው ዜና ሕይወታቸው ላይ ተገልጧል፡፡

የብፁዕነታቸው ዜና ዕረፍት እና በተለይም የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ንግግር በስፍራው በተገኙ ኀዘነተኞች ዘንድ የተደበላለቁ ስሜቶችን አጭሯል፡፡ ፓትርያርኩ ስለ ብፁዕነታቸው የሰጡት ምስክርነት በራሱ ብዙዎችን ያስደመመ እና ፍጹም አባታዊ ከመሆኑም በላይ በትውፊታዊው ጥንታዊ ትምህርት ምሉዕ እና በርጋታቸው ታዋቂ ለነበሩት ብፁዕ አቡነ ይሥሓቅ የሚገባ እንደሆነ የሚያስረግጡ አስተያየቶች ተደምጠዋል፤ ‹‹ምነዋ ፈጣሪ፣ ደግ ደጉን ብቻ. . .›› በሚል ሮሮ የብፁዕነታቸውን ድንገተኛ ሞት መንሥኤ የሚጠራጠሩ ጥቂት አልነበሩም፡፡ በአንጻሩ ብፁዕነታቸው ከግንቦት አንድ ቀን 1999 ዓ.ም ጀምሮ የመንበረ ፓትርያርኩ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው በሠሩበት በአንዱ ወቅት የተጫወቱትን ሚና የሚያስታውሱ ወገኖች ‹‹ለዚችው ዕድሜያችን ነበር'ንዴ›› በሚል ቁጭታቸውን በግላጭ ከማሰማት ወደ ኋላ አላሉም፤ በድንገት ማረፋቸውንም እንደምላሽ አይተውታል፡፡

በ2001 ዓ.ም በተደረገው የግንቦቱ የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ እና በሐምሌው የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ከቤተ ዘመዳዊ አሠራር እና ሙስና አጽድቶ አስተዳደሩን ለማሻሻል በተደረገው ብርቱ ተጋድሎ ብፁዕነታቸው በዋና ሥራ አስኪያጅነታቸው ያራመዱት አቋም በድርጅታዊ ቁመናው ዘመን የተሻገረው ተቋም ያጋጠመውን ወርቃማ ዕድል በማጨናገፍ ረገድ ወሳኝ ድርሻ እንደነበረው ተደርጎ ተወስዷል፡፡ ወቀሳውን የሚሰነዝሩት ወገኖች ግንቦት ስድስት ቀን 2001 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በቤተ ክርስቲያናችን መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን፣ ሕጓ እና ሥርዐቷ እንደተጠበቀ ሆኖ የተቀላጠፈ አመራር እና አሠራር እንዲኖር ለማድረግ በመወያያ አጀንዳነት መዝግቧቸው የነበሩ ነጥቦችን ያስታውሳሉ፡፡

ይኸውም በሥራ አፈጻጸም ያለው ችግር እና ድክመት እንዲቀረፍ፣ የበጀት አመዳደብ እና አጠቃቀም በሥርዐቱ መሠረት እንዲፈጸም፣ ደረጃውን ጠብቆ ያልመጣ አቤቱታ ተቀባይነት እንዳይኖረው፣ ሥራ እና ሠራተኛን ለማገናኘት፣ ሕገ ቤተ ክርስቲያን እና ቃለ ዓዋዲው ተጠብቆ እንዲሠራ ማድረግ፣ ከሊቃነ ጳጳሳት ጀምሮ ሌሎችም ባለጉዳዮች መጉላላት ሳይደርስባቸው በቀጠሮ እንዲስተናገዱ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ እና የቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔዎች እንዲፈጽሙ እና እንዲያስፈጽሙ፣ ሊቃነ ጳጳሳት በሀገረ ስብከታቸው ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት እና ልዩ ልዩ የልማት ዘርፎችን በመክፈት የበጀት ችግሮችን ለመቅረፍ እንዲችሉ የሚሉና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ከእኒህም ውስጥ በሥራ አፈጻጸም ያለው መጓተት፣ የቤተሰብ አስተዳደር እና ሙስና ለቤተ ክርስቲያኒቱ ዕድገት ዋና ማነቆ መሆናቸውን ይገልጣል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶሱ በወቅቱ ከላይ የተገለጹት ችግሮች ዘለቄታዊ መፍትሔ እንዲያገኙ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እና በቋሚ ሲኖዶስ እየተወሰኑ የሚተላለፉ ጉዳዮችን እየተከታተለ የሚፈጽም እና የሚያስፈጽም፣ ለወደፊቱም የሚሠሩ ሥራዎችን ሁሉ የሚገመግም እና የሚቆጣጠር ብሎም መፍትሔ የሚሰጥ ከብፁዓን አባቶች ኮሚቴ መሠየሙ ‹‹አስፈላጊ እና ጊዜው የሚጠይቀው የሥራ አፈጻጸም ስልት›› እንደሆነ በቃለ ጉባኤው ላይ ያመለክታል፡፡ ቋሚ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ሰባት ብፁዓን አባቶች በአባልነት የሚገኙበት ተጠሪነቱም ለቅዱስ ሲኖዶስ የሆነ ነበር፡፡ የአንድ ዓመት የሥራ ጊዜ የነበረው ቋሚ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ሥራውን እየሠራ የመተዳደሪያ ደንብ አርቅቆ ለሐምሌው ምልአተ ጉባኡ እንዲያቀርብ ይጠበቅ ነበር፡፡

ፓትርያርኩ በቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ዐምባገነናዊ ሥልጣን ይገድባል የሚል ተስፋ የተጣለበት ቋሚ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የሥራው መጀመሪያ ያደረገው በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 15 ንኡስ አንቀጽ 12፣ ‹‹ፓትርያርኩ በውጭ አገር በሚደረግ በማናቸውም ስብሰባ ላይ ለመገኘት እና ጉብኝት ለማካሄድ በሚያስፈልግ ጊዜ ስለተልእኮው ጉዳይ አስቀድሞ በቅዱስ ሲኖዶስ እና በቋሚ ሲኖዶስ ያስወስናል፤›› የተቀመጠውን ድንጋጌ በመፃረር ፓትርያርኩ ሰኔ ሁለት ቀን 2001 ዓ.ም ወደ ጣልያን አድርገውት ስለነበረው ጉዞ የዋና ሥራ አስኪያጁ ብፁዕ አቡነ ይሥሓቅ ጽ/ቤት ማብራሪያ እንዲሰጠው የሚጠይቅ ነበር፡፡ 


በሥራ አስፈጻሚው እይታ የፓትርያርኩ ጉዞ ‹‹ሕገ ቤተ ክርስቲያንን እና የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔን በመተላለፍ ቤተ ክርስቲያኗ በበጀት እጥረት ችግር ላይ በወደቀችበት ወቅት›› የተደረገ በመሆኑ አግባብነት አልነበረውም፡፡ በተመሳሳይም ኮሚቴው ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት በጻፋቸው ሌሎች ሁለት ደብዳቤዎች (ሰኔ አንድ እና ሦስት ቀን 2001 ዓ.ም) ያለኮሚቴው ዕውቅና እና ፈቃድ በጽ/ቤቱ በመከናወን ላይ ያለው የሠራተኛ ዝውውር እና ሹመት ‹‹ከሲኖዶሱ ውሳኔ ውጭ በሆነ መንገድ እየተከናወነ›› በመሆኑ እንዲቆም አሳስቦ ነበር፡፡ የቀድሞው የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ኮሚሽነር ከሐላፊነታቸው ከለቀቁ በኋላ በጊዜያዊ ኮሚሽነርነት በመመራት ላይ ለሚገኘው ኮሚሽን ሲኖዶሱ ሳያውቅ ኮሚሽነር ለመመደብ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን የሚገልጸው የሥራ አስፈጻሚው ደብዳቤ እንቅስቃሴው እንዲቆም አሳስቧል፡፡ ከእኒህ የማብራሪያ እና የማሳሰቢያ ደብዳቤዎች ባሻገር ኮሚቴው ሰኔ 10 - 11 ቀን 2001 ዓ.ም ‹‹ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ሠራተኞች በሙሉ›› በሚል ባሠራጨው ደብዳቤ ሠራተኞቹ ‹‹ማንኛውንም የቤተ ክርስቲያኒቱን ችግሮች ለሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ በማቅረብ እና መረጃ በመስጠት ለመልካም አስተዳደር መስፈን በሚደረገው እንቅስቃሴ ተሳታፊ በመሆን ሐላፊነታቸውን እንዲወጡ›› ጥሪ አስተላልፎ ነበር፡፡

በአጠፌታው የወቅቱ የመንበረ ፓትርያርኩ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ይሥሓቅ ከፓትርያርኩ ጋራ ከተጓዙበት እና ‹‹ለመጀመሪያ ጊዜ ከኩሽና ወደ አደባባይ ብወጣ ምቀኛ በዛበት›› ካሉት የጣሊያን ጉብኝት መልስ ‹‹የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን የአስተዳደር ጉባኤ›› እና ‹‹የአዲስ አበባ ገዳማት እና አድባራት አስተዳዳሪዎችን›› ስብሰባ በመጥራት ‹‹ኮሚቴው ቤተ ክርስቲያኒቱ ከምትተዳደርባቸው ከሕገ ቤተ ክርስቲያን፣ ከቃለ ዓዋዲው እና ከሠራተኞች አስተዳደር ሕጎች ውጭ የሆነ አሠራር በመፈጸም ያልተጠበቀ ችግር በመፍጠር አላስፈላጊ ውሳኔዎችን ያስተላልፋል ብለን አልጠበቅንም ነበር፤›› በሚል ‹‹የሥልጣን ተዋረዱን ያልጠበቀ›› ተግባር እንደፈጸመ ያሳውቃሉ፤ የውሳኔ ሐሳብም ያቀርባሉ፡፡ የሥራ አስፈጻሚው ተግባር ‹‹የተጓተቱ ጉዳዮችን እንዲያስፈጽም እንጂ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ የተሰጠውን ሓላፊነት በመጋፋት ወይም የበላይነቱን ሥልጣን በመያዝ ቤተ ክህነቱን ተክቶ እንዲሠራ አልነበረም›› በማለትም ይከሳሉ፡፡ የፓትርያርኩ የውጭ ጉዞ ‹‹ለቤተ ክርስቲያኒቱ ዕውቅና የሚጠቅም በመሆኑ ቀጣይነት እንዲኖረው የአስተዳደር ጉባኤው ያመነበት›› ስለመሆኑ በወቅቱ ተገልጧል፡፡

የዚህን ‹‹የአስተዳደር ጉባኤ›› ውሳኔ መነሻ በማድረግ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የተሠየመውን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በማገድ ስድስት ውሳኔዎችን ያስተላልፋሉ፡፡ በውሳኔው መሠረት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የከፈተው ጽ/ቤት በአስቸኳይ እንዲዘጋ፣ ኮሚቴው ያሳተማቸው ክብ ማኅተም፣ ቲተር እና ሄዲንግ ማዘዣ ወረቀቶች የቤተ ክርስቲያኒቱን ቃለ ዓዋዲ እና ሕገ ቤተ ክርስቲያን የጣሱ በመሆኑ በሥራ ላይ እንዳይውሉ ያግዳል፡፡ በተጨማሪም ሥራ አስፈጻሚው ‹‹በሚያከናውነው ሕገ ወጥ ተግባር›› ከጀርባው ‹‹የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕግ እና ደንብ መዋቅርንም ጭምር ለማፍረስ የተዘጋጀ አካል እንዳለ ስለሚያመለክት አስፈላጊ ክትትል እንዲደረግበት›› የፓትርያርኩ የእግድ ደብዳቤ ያዝዛል፡፡ 


በአራተኛ ውሳኔው ላይ በሥራ አስፈጻሚው የተላለፉት ‹‹ሕገ ወጥ እና ፀረ ሰላም ጽሑፎች›› በኢንተርኔት (ደጀ ሰላም) እና በአዲስ ነገር ጋዜጣ (አሁን ከኅትመት ውጭ የሆነ) በመውጣታቸው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አባላት እንዲጠየቁ እና የአዲስ ነገር ጋዜጣ አዘጋጅም በሕግ እንዲጠየቅ ይጠይቃል፡፡ የሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ አባላት የሆኑ ብፁዓን አባቶችም ‹‹ላሳዩት እንቅስቃሴ እና ለፈጠሩት ውዥንብር በሕግ ፊት እንዲቀርቡ እና እንዲጠየቁ›› መወሰኑን ያስታውቃል፡፡ ይህንኑም በመረዳትም የኮሚቴው አባላት የሆኑ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በአስቸኳይ በተመደቡበት ሀገረ ስብከት ተገኝተው መደበኛ ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ሲል ደብዳቤው ትእዛዝ ያስተላልፋል፡፡ ይህን ተከትሎ የለውጥ አማጭነት ተስፋ የተጣለበት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በተለይም ጸሐፊው ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስነታቸው ጭምር በግፍ በመታገዳቸው ከሥራ ውጭ እንደሆነ ይታወሳል፡፡

በሌላ በኩል ብፁዕነታቸው አስተዳደሩን ለማሻሻል የተደረገውን ጥረት ከላይ በተገለጹት ውሳኔዎች መግለጫነት እንዲደናቀፉ በምክንያትነት ይጠቀሱ እንጂ ዋነኛው ችግር በወቅቱ የሚዲያዎች አገላለጽ ‹‹የብፁዕ አቡነ ሳሙኤል አዲስ የኀይል ሚዛን›› ሆኖ መውጣት የሚጠቅሱ ወገኖች አልጠፉም፡፡ በነዚህ ወገኖች ትንታኔ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ከፍተኛ የአስፈጻሚነት ሥልጣን የነበራቸውን ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስን ባልተለመደ አኳኋን በተቀመረ የተቃውሞ ሐሳብ በመቃወም ‹ተፎካካሪ› ምናልባትም ‹ቀጣዩ አማራጭ› ሆነው እንዲታዩ ሳያደርጋቸው አልቀረም፤ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል በውጭ በመንግሥት ባለሥልጣናት በውስጥ በሚበዙት የቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት ዘንድ ሰፊ ተቀባይነት እና ድጋፍ ማግኘታቸው ይህን ያረጋገጣላቸው የመሰላቸው ‹‹ቀጣዩ ፕትርክና ለሸዋ›› ባዮች አቡነ ጳውሎስ ለለውጡ የነበራቸውን ተፃራሪ አቋም በመበዝበዝ ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ህላዌ መክሰም አሉታዊ ሚና መጫወታቸውን እኒሁ ወገኖች ለማስረዳት ይጥራሉ፡፡

በብፁዕነታቸው ሥርዐተ ቀብር አፈጻጸም አጋጣሚ ጎልተው የተስተዋሉት የወዲያ ወዲህ አስተያየቶች እኒህን ቢመስሉም ሐቁ ግን ለቀሪዎቹ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ አጥኚዎች የምርምር ጉዳይ ሆኖ ይቀራል፡፡

አምላከ ቅዱሳን የብፁዕ አባታችንን ነፍስ ከብፁዓን አበው፣ ጻድቃን ሰማዕታት መካን ይደምርልን፡፡ አሜን፡፡

7 comments:

Anonymous said...

enant yemut weqashoch! enquan beheiwet yalewin yemotewinim yiqr yematilu bebeetekrstiyan sm yerasachun drjtawi aquam yemtaramdu aremeneewoch nachu. Amlak yiqr ybelachihu.

Anonymous said...

Thanks DS betam arif zegeba new. ye abatachinin nefis kekidusan gar yidemirilin! legnam lelijochu melkamun abat yisten!

Anonymous said...

Besme Ab Weweld WemenfesKidus!Getaye hoy Yemyadergutn(Yemitsfutn) alawekum ena yikr belachew!

መርከቤ ንጉሴ/ከአዲስ አበባ/ said...

በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሕዱ አምላክ።አሜን!!

ብፁዕ አባታችን ምንም እንኳን በድንገተኛ ሕመም ብዙም ሳይቆዩ አረፉ ቢባልም እረፍታቸው ጣር ያልበዛበት የፃድቅ ሰው እረፍት መሆኑን ያሳያል። ለቅድስት ቤተ-ክርስቲያንም የሰሩት ስራ ዘወትር ከመታወሱ በላይ ሐሜት፣ክፋት፣ጥላቻ፣ምቀኝነት፣ተንኮል፣ድካም፣መከራና ሌላም ከሌለበት እውነተኛው ቦታ ሔደዋል። ሆኖም ሰው በአካል ሲለይ ያሳዝናልና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መፅናናትን እመኛለሁ።

ቸሩ ፈጣሪያችን መጨረሻችንን እንዲያሳምርልን የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን።አሜን!!
መርከቤ ንጉሴ/ከአዲስ አበባ/

Anonymous said...

ጻድቃን ጥሪ ቀጠሮ የለውም

Anonymous said...

የፃድቃን ጥሪ ቀጠሮ የለውም
እግዚሐብሔር አምላክ የተበተነውን መንጋ የሚሰበስቡ ፤ ለሀገር የሚተርፉ ፤ ባለፉት አባቶቻችን እግር የሚተኩ አባቶችን አያሳጣን ላሉትም ሰላማቸውን ይመልስልን ፤ ተስማተው የሚሰሩ ያድርግልን እስከ አሁን በተሰራው ስራ ቂምን የሚይዙ ሳይሆኑ ይቅር የሚባባሉም ያድርግልን…ቸር ወሬ ያሰማን

Anonymous said...

ጥሩ ነው በመንፈሳዊው ትምህርት የተሟላ ሊቅነት እንደነበራቸው "ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገሪማ በንባብ ባሰሙት የብፁዕነታቸውን ዜና ሕይወት፣ ብፁዕ አቡነ ይሥሓቅ በትምህርት ይሁን በሥራ ላይ ቁጥብ እና ርጉ አንደበትን ገንዘባቸው ያደረጉ፣ የማንንም ጥቅም እና ክብር የማይነኩ፣ ከራሳቸው ጥቅም እና ክብር ይልቅ የሌላውን የሚያስቀድሙ"
ተነግሮናል ስለ ቤተ ክርስቲያን ጥቅም ያደረጉትን ብንሰማም ጥሩ ነበር

ያባ ጳውሎስ የድንጋይ ሃውልት ሲሰራና - አሁንም እንደቆመ በቀረበት ቦታ ሲተከል
እኒህ ጳጳስ የት ነበሩ ስለ ሃውልቱስ ከቀኖና ውጭ ባደባባይ መቆም የመንበረ ፓትርያርኩ
ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሀላፊነታቸው ምን አደረጉ

ሌላው ይሄ "የሞተ ሰው አትውቀሱ"
የሚለው የድንቁርና ባህል ከንግዲህ ይብቃ

አንድ ሰው የሰራውን ጥሩ ተግባር አመስግኖ ያጠፋውንም ዘርዝሮ መወያየት
መውቀስም አስፈላጊ ነው

ያለዚያ እየታጠቡ ጭቃ መለውስ ነው
መሸፋፈን መደበቅ የክርስትና ባህል አይደለም

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)