March 4, 2011

ብፁዕ አቡነ ይሥሓቅ (1927 - 2003 ዓ.ም) ሲታወሱ

  • ‹‹የምናሠለጥናቸው በሌላ ቋንቋ ተናግረው የሌለ ሃይማኖት እንዲያመጡ አይደለም፡፡›› (ብፁዕ አቡነ ይሥሓቅ በ1991 ዓ.ም ከተናገሩት)
  •  ሥርዓተ ቀብራቸው ነገ ይፈጸማል፤
(ደጀ ሰላም፤ ማርች 4/2011)፦ የባሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ይሥሓቅ ማረፋቸውን ትናንት መዘገባችን ይታወሳል። ብፁዕነታቸው በድንገተኛ ሕመም ማረፋቸው የተሰማው ሐሙስ የካቲት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ዘጠኝ ሰዓት ገደማ በመንበረ ፓትርያርኩ ከሚገኘው ማረፊያ ቤታቸው ነው፡፡

ከአንድ ወር በኋላ ሥልጣኑን የሚረከበው የቀጣዩ ቋሚ ሲኖዶስ አባል የነበሩት ብፁዕ አቡነ ይሥሓቅ የካቲት 21 ቀን 2003 ዓ.ም በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ፈትኖ ላቀረባቸው በርካታ ዲያቆናት ከሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ጋራ የቅስና ማዕርግ ሰጥተዋል፡፡ ከአንድ ቀን ቀደም ብሎ የካቲት 20 ቀን 2003 ዓ.ም 25 ዓመቱን ባከበረው ደብረ ምጥማቅ ቅዱስ ፊልጶስ ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ቅዳሴውን መርተው ትምህርት ሰጥተዋል፡፡ በዚሁ ሰሞንም የሀገረ ስብከታቸውን መንበረ ጵጵስና ለማሠራት ድጋፍ የሚጠይቅ ደብዳቤ ለመንበረ ፓትርያርኩ ጠቅላይ ጽ/ቤት ሠራተኞች በማሰራጨት ላይ የነበሩት ብፁዕነታቸው፣ ከትናንት ጀምሮ በንግግራቸው የመቸገር እና ሰውን የመለየት እክል ገጥሟቸው እንደነበር ተገልጧል፡፡ ይህን ተከትሎ ወደ ሆስፒታል ቢወሰዱም የጎላ ችግር እንዳልተገኘባቸው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ በተወለዱ በ76 ዓመታቸው ያረፉት የብፁዕነታቸው አስከሬን በአሁኑ ሰዓት በደጃዛማች ባልቻ ሆስፒታል ምርመራ እየተደረገለት እንደሆነ ተመልክቷል፡፡

ብፁዕ አቡነ ይሥሓቅ ከዕረፍታቸው ጥቂት ደቂቃዎች በፊት በቅዳሴ ከተሳተፉበት መንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ተመልሰው ፓትርያርኩን ጨምሮ በመንበረ ፓትርያርኩ የመመገቢያ አዳራሽ ወደተገኙት አባቶች ዛሬ የሚዘከረው የጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወርኃዊ በዓል መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ዝክር(ኅብስት) መላካቸው እና በጸሎታቸውም እንዲያስቧቸው መጠየቃቸው ተዘግቧል፡፡ ከውሎው ቅዳሴው መልስ የቀመሱት እህል እንዳልተስማማቸው እና ሕመም እንደሚሰማቸው የተናገሩት ብፁዕነታቸው ብዙም ሳይቆዩ ነው ሕይወታቸው ያለፈው፡፡

ልደት እና ዕድገት፤

ብፁዕ አቡነ ይሥሓቅ ከአዲስ አበባ በስተምሥራቅ በአድዓ ወረዳ የረር ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አጥቢያ በ1927 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ ፊደልን፣ ንባብ እና ዳዊትን ከመሪጌታ ገብረ ሚካኤል በተወለዱበት አጥቢያ አጠኑ፡፡ ከዚያም አዲስ አበባ ወደሚገኘው ደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን በመምጣት ከቀኝ ጌታ ገሪማ ለሦስት ዓመታት ያህል ዜማን ተምረዋል፡፡

ትምህርት እና አገልግሎት፤

በ1941 ዓ.ም ከብፁዕ አቡነ ይሥሓቅ ዲቁናን ተቀብለው በ1943 ዓ.ም ሚያዝያ ወር ላይ ከሁለት ባልንጀሮቻቸው ጋራ ወደ ጎጃም ተሻግረው ቡሬ ዳሞት ወረዳ ሐራ ቅዱስ ገብርኤል በሚባለው ደብር ጾመ ድጓ እና ምዕራፍ እንዲሁም የሑለት ዘመን ድጓ ዘልቀው ወደ ቅኔ ትምህርት ገቡ፡፡ ለሦስት ዓመታት በቅኔ ትምህርት ተሰማርተው እንደቆዩ ወደ ጎንደር ተሻግረው አፋፍ ወገራ በተባለ ቦታ ለአምስት ዓመታት ያህል አቋቋም ተምረው ወንበር ዘርግተው ሲያስተምሩ፣ ‹‹የለም፣ ወደ ሀገርህ መመለስ የምትችለው ድጓ ስታስመሰክር ነውና የአቋቋም ወንበር አትዘርጋ›› ብለው ጓደኛቸው ስለመከራቸው የድጓ ብራና አውጥተው ወደ ጎንደር ዳባት ቅዱስ ሚካኤል አመሩ፡፡

በዳባት ከየኔታ ገብረ ማርያም ድጓ እየተማሩ በትርፍ ጊዜያቸው ይጽፉ ነበር፡፡ ቤተ ልሔም ወርደው ካስመሰከሩ በኋላ ዙርዓምባ ማርያም ገብተው ዝማሬ መዋስዕት ተምረው እና ጽፈው በጎንደር ዙሪያ ወደሚገኝ ቁራ እጅግ ቅዱስ ገብርኤል በሚባል ደብር ወንበር ዘርግተው ድጓ ማስተማር ጀመሩ፡፡ ለሁለት ዓመት በማስተማር ቆይተው በ1964 ዓ.ም ሐምሌ ወር ወደ ትውልድ ቦታቸው ተመለሱ፡፡

ከ1965 - 1972 ዓ.ም ለስምንት ዓመታት ያህል በታዕካ ነገሥት በኣታ ለማርያም ገዳም የብሉያት ትርጓሜን ተማሩ፡፡ ዘመናዊውን ትምህርትም እስከ 12 ክፍል ድረስ ተምረው አጠናቀቁ፤ ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ወርደውም ሥርዐተ ምንኩስናን ፈጸሙ፡፡ ከ1973 - 1976 ዓ.ም ወደ ዝዋይ የካህናት ማሠልጠኛ በማምራት በርእሰ መምህርነት አገልግለዋል፡፡ የቅስናን ማዕርግ የተቀበሉት በ1977 ዓ.ም በወቅቱ የሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከነበሩት ከብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ነው፡፡

ብፁነታቸው ለአንድ ዓመት ያህል ወደ ጀርመን ተጉዘው ጀርመንኛ ቋንቋ አጥንተዋል፡፡ ከዚያም መልስ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የካህናት አስተዳደር መጋቤ ካህናት ሆነው አገልግለዋል፡፡ ቀጥሎም የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ምክትል ዲን ሆነው ለአራት ዓመታት እንደሠሩ ከ1986 - 1989 ዓ.ም በጋምቤላ ሀገረ ስብከት በማስተማር ላይ እንዳሉ ኅዳር አራት ቀን 1987 ዓ.ም የኤጲስ ቆጶስነትን ማዕርግ ተቀበሉ፡፡

ከ1987 - 1989 ዓ.ም አጋማሽ ድረስ የጋምቤላ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ከጠረፍ ጠረፍ በማስተማራቸው ብዙዎች ያስታውሷቸዋል፡፡ ከዚያም በኋላ ለአንድ ዓመት የምሥራቅ ሐረርጌ ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕነታቸው በኋላ የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ዲን ሆነው ሠርተዋል፡፡ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ዛሬዋ ዕለተ ዕረፍታቸው ድረስ የባሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ሲያገለገሉ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ይሥሓቅ ከ1999 - 2001 ዓ.ም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ በመሆን ሠርተዋል፡፡

ዝክረ ነገር፤

የመንበረ ፓትርያርኩ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ በነበሩበት ወቅት በ2001 ዓ.ም በተደረገው የግንቦቱ የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እና በሐምሌው የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ከቤተ ዘመዳዊ አሠራር እና ሙስና አጽድቶ አስተዳደሩን ለማሻሻል በተደረገው ብርቱ ጥረት ከፓትርያርኩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ጋራ አራምደውት በነበረው አወዛጋቢ አቋም ይታወሳሉ - ብፁዕ አቡነ ይሥሓቅ፡፡

የቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አስተምረው ስለሚያወጧቸው ደቀ መዛሙርት በአጠቃላይ እና በዲንነት ስለመሩት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም በተለይ በአንድ ወቅት የተጠየቁት ብፁዕነታቸው ተከታዩን መልስ ሰጥተው ነበር፡-

‹‹. . . ገጠር መሄድ ከሁሉም በላይ የሚመረጥ ነው፡፡ እኔ ብዙ ነገር ላውቅ የቻልኩት ገጠር ነው፡፡ አንደኛ የተማርኩት በገጠር ዞሬ ነው፡፡ ሁለተኛም ከተማ ቆይቼ ወደ ገጠር በሄድኩበት ጊዜ ብዙ ዕውቀት ነው ያገኘሁት፡፡ ከሕዝቡ ነው ችግሩ የሚታወቀው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ህልውና የሚታወቀው ገጠር ሲወጡ ነው፡፡ ህልውናዋ ተዳከመ ወይ; እንዴት ነው; ብሎ ማወቅ የሚቻለው ወደ ገጠሩ ዞረው ሲያዩት ነው፡፡ እዚህማ(አዲስ አበባ) ብዙ ሕዝብ ወደ ቤተ ክርስቲያን ስለሚጎርፍ ሊታወቅ አይችልም፡፡ የተማሪዎቹ ዕውቀት ታፍኖ እየቀረብን ነው፡፡ ተልእኳቸውን የተወጡም ያልተወጡም አሉ፡፡

. . . የተቋማቱ ተመሳሳይነታቸው ለአንዲት ቤተ ክርስቲያን መሰለፋቸው ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ በሌላ ቋንቋ ተናግረው ሌላ ሃይማኖት እንዲያስተምሩ አይደለም የምናሠለጥናቸው፤ ያለችቱን ቤተ ክርስቲያን ቀጥ አድርገው እንዲይዙ ነው፡፡ የሌላ ቋንቋ ስላወቁ የሌላውን ሃይማኖት እንዲያመጡብን አይደለም፡፡ የቤተ ክርስቲያንን ዓለም አቀፍ ተልእኮ እንዲያቃኑ ነው፡፡ የእኛ ት/ቤት ግን ብሔራዊውን(ቅኔ፣ ድጓ፣ ዝማሬ መዋስዕት፣ ቅዳሴ፣ ትርጓሜ መጻሕፍት) በሚገባ ማስያዝ ማስጠበቅ፣ በዚህ ሞያ ብቁ የሆኑትን ማፍራት ነው ዓላማው፡፡››

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)