February 25, 2011

በዐውደ ምሕረት ላይ ስሙን በማጥፋት በተሰማሩት ጥቅመኞች እና ይህን ተግባር በሚያበረታቱ አካላት ላይ ቅ/ሲኖዶስ ርምጃ እንዲወስድ ማኅበረ ቅዱሳን ጠየቀ

  • ማኅበሩ በቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ ማዘኑን ገልጧል::
  • “የሐዋሳ ከተማ ምእመናን ጥያቄ የሃይማኖታዊ መብት ጥያቄ እንጂ የማንም አለመሆኑን ተረድተናል፡፡”
 (ደጀ ሰላም፤ ፌብሩዋሪ 25/2011፤  የካቲት 18/2003 ዓ.ም):-  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን በሲዳማ ጌዲኦ፣ አማሮ እና ቡርጂ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ሀገረ ስብከት በሐዋሳ ከተማ ከ2002 ዓ.ም ወዲህ ከተከሠተው የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ችግር ጋራ በተያያዘ እየተደረገበት ያለው የስም ማጥፋት ዘመቻ እንዲቆምለት ጠየቀ፡፡
በከተማው በተፈጠረው ውዝግብ አንዳችም የሚመለከተው ነገር እንደሌለ የገለጸው ማኅበሩ ይሁንና “የግል ጥቅማቸውን ለማሳካት የሚሯሯጡ ግለሰቦች እና የተለያዩ አካላት ከምእመናን ጥያቄ ሲነሣባቸው ጥያቄውን ያነሣው ማንም ይሁን ማን ‹ማኅበረ ቅዱሳኖች ናቸው› በማለት ጉዳዩን ሌላ መልክ ለመስጠት ሲሞክሩ ማየት እየተለመደ መጥቷል” ብሏል፡፡ የዚህም ምክንያቱ፣ “የዋሁን እና ተንኮላቸውን ያልተረዳውን ምእመን በተለያዩ ጥቅሞች በማታለል የማኅበሩ ስም በክፉ አንሥቶ በመወንጀል የጥፋት ድርጊታቸውን ለመሸፈን” እንደሆነ አመልክቷል፡፡

የማኅበሩ ሥራ አመራር ጉባኤ ጽ/ቤት በቁጥር ማቅሥአመ/09/02/ለ/03 በቀን 09/06/03 በአድራሻ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ጽ/ቤት በግልባጭ ለሁሉም ሊቃነ ጳጳሳት፣ ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ ለብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ቢሮ፣ ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል አስተዳደር ጽ/ቤት፣ ለሲዳማ እና ጌዲኦ አማሮ እና ቡርጂ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በጻፈው በዚሁ ደብዳቤ፡- በሐዋሳ ከተማ የተበላሸው የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር እንዲስተካከል ከአንድ ሺሕ በላይ የሆኑ የምእመናን ተወካዮች አቤቱታቸውን ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት እና ለመንበረ ፓትርያርኩ ጠቅላይ ጽ/ቤት ለማቅረብ ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ወደ አዲስ አበባ ሲመላለሱ መቆየታቸውን አውስቷል፡፡ በዚህም መሠረት በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የተመራ አጣሪ ልኡክ ወደ ሀገረ ስብከቱ ማምራቱን ተከትሎ በጥቅምት ወር የተካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የቀድሞውን የሀገረ ስብከቱን ሊቀ ጳጳስ እና ሥራ አስኪያጁን በማንሣት አስተዳደራዊ ለውጥ በመደረጉ ችግሩ ይቀረፋል የሚል እምነት ተይዞ መቆየቱን ጠቅሷል፡፡

ይሁንና ከቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ በኋላ ከችግሩ ጋራ በተያያዘ የግል ጥቅማቸውን ለማሳካት የሚሯሯጡ ግለሰቦች እና የተለያዩ አካላት በማኅበሩ ላይ ሲያደርጉ የቆዩትን የስም ማጥፋት ዘመቻ በስፋት በመቀጠል ወጣቶችን በስሜታዊነት በመቀስቀስ እና ገንዘብ እየከፈሉ በጥቅም በማነሣሣት ወደ መንበረ ፓትርያርኩ በማሰለፍ ብዙዎችን ለማሳሳት መሞከራቸውን አስረድቷል፡፡ ከዚህ የተነሣ የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ኅዳር ሰባት ቀን 2003 ዓ.ም በቁ/59/51/2003 ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል አስተዳደር ጽ/ቤት፣ የካቲት ሁለት ቀን 2003 ዓ.ም በቁ/92/54/2003 ለሲዳማ ጌዲኦ፣ አማሮ እና ቡርጂ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በጻፋቸው ደብዳቤዎች ማኅበረ ቅዱሳን የችግሩ አካል እንደሆነ ተደርጎ መጠቀሱ እንዳሳዘነው የማኅበሩ ሥራ አመራር ጉባኤ ጽ/ቤት ገልጧል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል ከቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ ያገኘ በመሆኑ ጥያቄ እንኳ ቢኖር የቤተ ክርስቲያኒቱን መዋቅር ጠብቆ ለሚመለከተው አካል በሕጋዊ መንገድ ጥያቄውን የሚያቀርብ መሆኑን ባለፉት 18 ዓመታት አገልግሎቱ ያስመሰከረ ከመሆኑ አኳያ በሐዋሳ በተከሠተው ችግር “አንዳችም የሚመለከተው ነገር እንደሌለ” ጥር 25 ቀን 2003 ዓ.ም ፓትርያርኩ ዘንድ በአካል ቀርቦ በቃል ለማስረዳት መሞከሩን አሳውቋል፡፡ በወቅቱም የጥፋት ድርጊታቸውን ለመሸፈን ማኅበሩን በማይመለከተው ነገር እየወነጀሉ ከሚገኙት አካላት ጋራ ፊት ለፊት መነጋገር መፍትሔ ይሆን ከሆነ ፓትርያርኩ ይህንኑ እንዲያደርጉ ጠቁሞ እንደነበር ደብዳቤው ይገልጻል፡፡

ከሃያ በላይ የሐዋሳ የአገር ሽማግሌዎች ጥር 30 ቀን 2003 ዓ.ም ወደ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት በመምጣት ለፓትርያርኩ ካቀረቧቸው ጥያቄዎች ጉዳዩ “የምእመናኑ የሃይማኖት መብት ጥያቄ እንጂ የሌላ የማንም አለመሆኑን” መረዳቱን ያመለክታል -  የማኅበሩ ደብዳቤ፡፡ ይሁን እንጂ በተለይም ከየካቲት ሦስት ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ [ቋሚ ሲኖዶሱ በፓትርያርኩ ጫና በሐዋሳ የማኅበረ ቅዱሳን ማእከልን ከ”ተስፋ ኪዳነ ምሕረት የልማት እና ፀረ ኤድስ ማኅበር” ጋራ በማዳበል በሀገረ ስብከቱ ለተከሠተው ችግር በምክንያትነት ፈርጆ በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ጣልቃ እንዳይገባ እና በቤተ ክርስቲያኒቱ መድረክ እንዳያስተምር መወሰኑን የካቲት ሁለት ቀን 2003 ዓ.ም በወሰነ ማግሥት] በማኅበሩ ላይ ያልተደረገው እንደተደረገ በማስመሰል በሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ዐውደ ምሕረት ላይ ሕገ ወጦቹ በሚፈጽሙት ተግባር ቤተ ክርስቲያንን የውንብድና ዋሻ እያደረጓት እንደሚገኙ ደብዳቤው አስታውቋል፡፡ ይህም “ማኅበረ ቅዱሳንን ብቻ ሳይሆን ቅዱስ ሲኖዶስን መዳፈር እና ማንአለበኝነት ሆኖ አግኝተነዋል” ብሏል፡፡

በመሆኑም ቅዱስ ሲኖዶስ ጉዳዩን ከመሠረቱ በማጥናት ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጥ ያሳሰበው የማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አመራር ጉባኤ ጽ/ቤት፣ የማኅበሩን ስም በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት በአደባባይ በማጥፋት ላይ የተሰማሩትን እና ይህንንም ተግባር እያበረታቱ በሚገኙት አካላት ላይ ቅዱስ ሲኖዶስ ተገቢውን ርምጃ ይወስድ ዘንድ ጠይቋል፡፡

ግንቦት ሁለት ቀን 1984 ዓ.ም በቤተ ክርስቲያን አባቶች እና በቅዱስ ሲኖዶስ ዕውቅና አግኝቶ አገልግሎቱን በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር በይፋ የወጠነው ማኅበረ ቅዱሳን፡- በ1985 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ በሥራ ላይ በዋለውና ሐምሌ 10 ቀን 1994 ዓ.ም ለሦስተኛ ጊዜ ተሻሽሎ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በጸደቀለት መተዳደሪያ ደንቡ፣ ባለንበት ዘመን በተለያየ ሽፋን የሚካሄደውን የሃይማኖት ወረራ በተቀናጀ መንገድ ለመከላከል ሃይማኖቱን የሚጠብቅ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚከባከብ እና አገሩን የሚወድ ብቁ ዜጋ ለማፍራት በመንፈሳዊው እና በዘመኑ ትምህርት የበሰለው የኅብረተሰብ ክፍል በቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ሥር ሆኖ የሚጠበቅበትን አስተዋፅኦ ሥርዐት ባለው መንገድ እንዲያበረክት የማዘጋጀት ሐላፊነት ተጥሎበታል፡፡

ማኅበሩ ላለፉት 18 ዓመታት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት፣ ሥርዐት፣ ትውፊት እና ታሪክ ተጠብቆ እንዲቆይ፣ ሐዋርያዊ ተልእኮዋ እንዲሳካ እና መንፈሳዊ አገልግሎቷ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በሀገር ውስጥ እና በውጭ ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት፣ ቅዱሳት መካናትን እና የአብነት ት/ቤቶችን በጉልበቱ፣ በሞያው እና በገንዘቡ በመርዳት አገልግሎቱን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ከዋናው ማእከሉ ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ አባላቱ የሰንበት ት/ቤት እና ወይም የሰበካ ጉባኤ አባል በመሆን የቤተ ክርስቲያኒቱን መብት እና ጥቅም ለማስጠበቅ ከሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት ጋራ የመቆም፣ ወቅቱ በሚፈቅደው ሁኔታ በቂ ዝግጅት አድርጎ ትምህርተ ወንጌልን ለሁሉም የማዳረስ እና ወጣት ሰባክያንን የማበረታታት፣ ሰንበት ት/ቤቶችን የማቋቋም እና የማጠናከር ግዴታ ሲኖርባቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በምትመራው መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎት የመሳተፍ መብት ደግሞ አላቸው /የማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ አራት፤ አንቀጽ ሰባት ንኡስ አንቀጽ አንድ እና ሁለት/፡፡ በመተዳደሪያ ደንቡ አንቀጽ አምስት መሠረት ማኅበሩ ምንም ዐይነት ጣልቃ ገብነት እንደማይኖረው የተገለጸው በፖሊቲካዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ብቻ ነው፡፡

በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ከጸደቀለት መተዳደሪያ ደንብ አኳያ የማኅበሩ የሐዋሳ ማእከል በቤተ ክርስቲያኒቱ መድረክ እንዳያስተምር እንዲሁም አባላቱ “እንደማንኛውም ምእመን መንፈሳዊ አገልግሎት ከሚያገኙ በቀር በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ጣልቃ እንዳይገባ” በሚል መወሰኑ አግባብነት ያለው መስሎ አይታይም፡፡ በሌላ በኩል መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎት የሚሰጠውን ማኅበር ከቤተ ክርስቲያኒቱ ውጭ ባገኘው ፈቃድ የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ መሣሪያ በመሆን እያወከ እና ጥቅሙን እያሳደደ ከሚገኝ ማኅበር ጋራ ማስተካከል በተወሰነ ገጽታውም ማሳነስ ፍትሐዊነት የጎደለው ነው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አካላት ጋራ የሚያደርገውን ግንኙነት የማመቻቸት፣ የሚገጥሙት ዕንቅፋቶች እንዲወገዱ አግባብነት ያለው ትብብር እና ድጋፍ የማድረግ ሐላፊነት ያለበት የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ እስከ አሁን በጉዳዩ ላይ ያለው ነገር የለም/መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ ዘጠኝ ንኡስ አንቀጽ 5 - 7/፡፡

አንዳንድ የጉዳዩ ታዛቢዎች በሀገረ ስብከቱ በተለይም በሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ዐውደ ምሕረቱን በኀይል በመቆጣጠር ሁከት እየፈጠረ ያለው “የተስፋ ኪዳነ ምሕረት የልማት እና ፀረ ኤድስ ማኅበር” ስለሆነ የቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ ቦታ እንዲያጣ ያደርገዋል፤ ማኅበረ ቅዱሳን በዐውደ ምሕረቱ መከልከሉ አሳዛኝ ቢሆንም በሌሎች መንገዶች የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴውን ማካሄድ ስለሚችል ውሳኔው ፈሊጣዊ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ይሁንና ውሳኔው ጠንካራ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ያሉትን የሀገረ ስብከቱን ሥራ አስኪያጅ መነሣት ጭምር ያስከተለ በመሆኑ ከረጅም ጊዜ እይታ አኳያ የሀገረ ስብከቱን አስተዳደር እና የስብከተ ወንጌሉን እንቅሰቃሴ በማዳከም የሐዋሳው የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ አንጃ ምእመናን በማስመረር ከቤተ ክርስቲያን ለማስወጣት ምስነቱ ምቹ ሁኔታ ሊፈጥር እንደሚችል በመስጋት ለውሳኔው አርምሞን መምረጥ እንደማይገባ ያስረዳሉ፡፡

ከሁሉ አስቀድሞ ጥያቄው የምእመናኑ የራሳቸው ሆኖ ሳለ ችግሩ በማኅበረ ቅዱሳን እና በ”ተስፋ ኪዳነ ምሕረት የልማት እና ፀረ ኤድስ ማኅበር” መካከል እንደሆነ ማስመሰል ጥቅም አሳዳጆቹን እና የተሐድሶ ኑፋቄ መሣሪያዎቹን ለመቋቋም የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ለማኮላሸት የታቀደ መሆኑን የሚገልጹት የሐዋሳ ምእመናን በበኩላቸው፣ ውሳኔው በቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ አመራር አካል - በቋሚ ሲኖዶሱ የተላለፈ በመሆኑ ተቀብለው በሂደት ስሕተቱ እንዲታረም ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉ ይናገራሉ፡፡

የሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የልማት ኮሚቴ አባላት የሆኑ ምእመናን “የመጨረሻ ጊዜ አቤቱታ” በሚል ርእስ የካቲት ስድስት ቀን 2003 ዓ.ም ለፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ በጻፉት ደብዳቤ፣ እነርሱ ለስድስት ወራት ወደ መንበረ ፓትርያርኩ ጠቅላይ ጽ/ቤት በመመላለስ ጥያቄያቸውን ለቅዱስ ሲኖዶስ እንዲያቀርቡላቸው ሲማፀኗቸው ቆይተው ሳለ የእነርሱን ጥያቄ ወደ ጎን በመግፋት እና የቋሚ ሲኖዶሱን አባላት በመጫን በሌላው ወገን የቀረበው አቤቱታ ብቻ በቃለ ጉባኤው ተይዞ ለሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት የተላለፈው ውሳኔ ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ከአባታዊ ሐላፊነታቸው እየወጡ በመሆናቸው እግዚአብሔር እንደሚወቅሳቸው እና እንደሚፋረዳቸው ያመለከተው የምእመናኑ ደብዳቤ፣ ከዚህ በኋላ ወደ እርሳቸው ከመሄድ ይልቅ አቤቱታቸውን እና የተሸሸጉባቸውን ማስረጃዎች ከእርሳቸው በላይ ላለው አካል እንደሚያቀርቡ አስጠንቅቀዋል፡፡

አስተያየታቸውን ለደጀ ሰላም የሰጡ ምእመናን የካቲት ዘጠኝ ቀን 2003 ዓ.ም በደ/ብ/ብ/ሕ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ቢሮ ከተካሄደው ውይይት ወዲህ የደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ዐውደ ምሕረት አንጻራዊ ሰላም የሰፈነበት ቢሆንም ከጎጠኝነት ጋራ የተያያዙ አካሄዶች እየጎሉ መምጣቸውን ይገልጻሉ፡፡ እውነተኛ ማንነታቸው የተጋለጠባቸው ጎጠኝነትን የመጨረሻ ምሽግ አድርገውታል፡፡ ባለፈው እሑድ የካቲት 13 ቀን 2003 ዓ.ም የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ከቅዳሴ በኋላ ለማስተማር ወደ ዐውደ ምሕረቱ ቢወጡም ጥቂት ወጣቶች ያለማቋረጥ በመጮኽ እና ጥቁር ጨርቅ በማውለብለብ አጸያፊ ንግግሮችን እየተናገሩ የትምህርተ ወንጌሉን መርሐ ግብር ማስተጓጎላቸው ተዘግቧል፡፡ ሁሉንም እዚህ ላይ ለመናገር ተገቢ ባይሆንም ሊቀ ጳጳሱን “ምን ሊሠሩ እዚህ መጡ፤ ታግደው የለም ወይ? ደ'ሞ አንተ ከየትኛው ሲኖዶስ ነህ?” የሚሉ ንግግሮች እንደሚገኙባቸው የዐይን እማኞች ገልጸዋል፡፡


ብፁዕ አቡነ ገብርኤል በበኩላቸው፣ “እናንተ ወደዚህ አላካችሁኝም፤ የላከኝ ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፣ የሚያነሣኝም ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፤ እኔ በመሄዴ ብጠቀምም ለእናንተ ግን ሰላም አይመጣም፤. . . ምእመናን ሆይ፣ እነዚህ ልጆች ናቸው፤ ጸልዩላቸው” በማለት ለብዙኀኑ ምእመን አባታዊ ምክር ሰጥተዋል፡፡ ከጥንቱም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች መሆናቸው በሚያጠራጥረው በእኒህ ጋጠ ወጦች አነጋገር በርካታ ምእመናን አዝነዋል፤ ብፁዕነታቸውን አጅበውም እስከ መንበረ ጵጵስናቸው አድርሰዋቸዋል፡፡

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)