February 19, 2011

የሐዋሳ ጉዳይ አጠቃላይ ሪፖርታዥ

  • የደቡብ ክልል ርእሰ መስተዳድር ከሐዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ምእመናን ጋራ ተወያዩ
  • ርእሰ መስተዳድሩ የገዳሙን አገልግሎት እና ጸጥታ የሚያውኩ  “ድንጋይ ወርዋሪዎችን” አስጠንቅቀዋል
  • “ከአሁን በኋላ የማዳምጠው የሀገረ ስብከቱን ሊቀ ጳጳስ አቡነ  ገብርኤልን ብቻ ነው፤ እሰር ካሉኝ አስራለሁ፤ ማናችሁም ከእርሳቸው ውሳኔ ውጭ መሆን አትችሉም፡፡”(አቶ ሺፈራው ሽጉጤ)
  • “ቤተ ክርስቲያን የአንድ ክልል አይደለችም፤ ዘረኝነትን  ትቃወማለች፤ በዘረኝነት ልትታወክ አይገባም፡፡”(ብፁዕ አቡነ ገብርኤል)
  • የርእሰ መስተዳድሩ አቀራርቦ የማወያየት ጥረት ፓትርያርኩን እና ጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ክፉኛ አስነቅፏቸዋል
(ደጀ ሰላም፤ ፌብሩዋሪ 19/2011፤  የካቲት 12/2003 ዓ.ም):- ተቃውሟቸውን በሰላማዊ መንገድ ከማቅረብ ይልቅ “ጠጠር መወርወር” በሚመርጡ ሁከተኞች ላይ አስተዳደራቸው ርምጃ እንደሚወስድ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ አስጠነቀቁ፡፡ “ፍላጎታችን ተስማምታችሁ አምልኮታችሁን እንድትፈጽሙ ነው፤ ማንኛውንም ተቃውሞ ተዋረዱን ጠብቆ በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ ይቻላል፤ የአድማ ስብሰባ አይፈቀድም፤ ጠጠር እወረውራለሁ የሚል ካለ ጠባችን ከእርሱ ጋራ ነው፤ ለእርሱ የተዘጋጀ ስፍራ አለ - አቦስቶ! እዚያ ወስደን እናሳርፈዋለን!!” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ ሀገረ ስብከቱን በተመለከተ በመስተዳድሩ ዘንድ ተቀባይነት የሚኖረው እና ተፈጻሚነት የሚያገኘው የሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ውሳኔ ብቻ በመሆኑ ማናቸውም ወገኖች ከብፁዕነታቸው ውሳኔ ውጭ መንቀሳቀስ እንደማይችሉ ለተሰብሳቢዎቹ በአጽንዖት ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ከሥራ አስኪያጁ ሊቀ ኅሩያን ዓለም እሸት ገብረ ጻድቅ ጋራ የተገኙት የሲዳማ ጌዲኦ አማሮ እና ቡርጂ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል በበኩላቸው፡- 24 የአገር ሽማግሌዎችን እና ካህናትን  በመያዝ በክልላዊ መንግሥቱ የፍትሕ እና ጸጥታ ቢሮ ሐላፊዎች እገዛ ማኅበረ ምእመናንን እና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችን በማነጋገር ችግሩን ፈትቶ ሰላም ለማስፈን ሲደረግ የቆየውን ጥረት አስረድተዋል፡፡ በውይይቱ መጀመሪያ ላይ፣ “በሲዳምኛ ቋንቋችን እንዳናገለግል ማኅበረ ቅዱሳን በዘረኝነት እና በፖሊቲካዊ አካሄድ እየመታ ወደ ጎን ገፍቶናል” በሚል በገዳሙ ያልተቋረጠ ሁከት እየፈጠሩ በሚገኙት አካላት ተወካዮች  ለቀረበው ክስ ብፁዕነታቸው በሰጡት ምላሽ፣ “ቤተ ክርስቲያን የአንድ ክልል አካል ብቻ አይደለችም፤ የተለያዩ ቋንቋዎችን የሚናገሩ ጳጳሳት አሉን፤ ሥልጣነ ክህነት ያላቸው በቅስና እና በዲቁና የሚያገለግሉ በርካታ አገልጋዮች አሉን፤ ዛሬም የሲዳማ ጳጳስ ለማፍራት ፈቃደኝነቱ አለ፤ በዚህም ቤተ ክርስቲያንን ለመምራት የሚያስችል ዓላማ አለን” በማለት ተናግረዋል፡፡ ይህን ጉዳይ ለመነጋገር መድረኩ ተገቢ ቦታው አለመሆኑን ያመለከቱት ብፁዕነታቸው “ቤተ ክርስቲያን ዘረኝነትን ትቃወማለች፤ በዘረኝነት ልትታወክ አይገባም” በማለት የመከሩት ብፁዕነታቸው በከሳሾቹ እንደተባለው ሳይሆን ማኅበረ ቅዱሳን ከምሥረታው ጀምሮ ለቤተ ክርስቲያን በሚሰጠው መንፈሳዊ አገልግሎቱ እና የልማት ተግባሩ በአግባቡ እንደሚያውቁት መመስከራቸው ተዘግቧል፡፡

ከትናንት  በስቲያ ሐሙስ ከቀትር በኋላ በክልሉ ርእሰ መስተዳድር ቢሮ የተካሄደው ይኸው ውይይት ከጥር ሰባት ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ የሀገረ ስብከቱን ጽ/ቤት መመሪያ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ውሳኔ በመፃረር የሀገረ ስብከቱን የስብከተ ወንጌል መድረኮች በተለይም የደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ዐውደ ምሕረትን በጉልበት ለመቆጣጠር በፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ አቀንቃኞች እና በእነርሱ በሚደገፉ ጥቅመኞች በተደረገ ሙከራ እየተወሳሰቡ የመጡ ችግሮችን ሀገረ ስብከቱ በራሱ ይፈታቸው ዘንድ ዕድል እንደሚሰጥ ብዙዎች ተስፋ አሳድረዋል፡፡ ተቃውሞን በሰላማዊ መንገድ ከማቅረብ በመለስ ሌላው ጉዳይ “ሃይማኖታዊ በመሆኑ ቤተ ክህነቱ በውስጥ አሠራሩ የሚፈታው” መሆኑን ነው ርእሰ መስተዳድሩም ያስገነዘቡት፡፡

ከጥር ሰባት ቀን ጀምሮ በቀጠለው ውዝግብ የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ አቀንቃኞች ባሰማሯቸው ምንደኞች  ቀናዒ ኦርቶዶክሳውያን በስለት ተወግተዋል፤ በሽመል ተደብድበዋል፤ በድንጋይ ተፈንክተዋል፤ በቁጥር ከ20 የማያንሡቱም ከጥር 20 - 23 ቀን 2003 ዓ.ም በነበሩት አራት ተከታታይ ቀናት ለእስር ተዳርገው “ከትክክለኞቹ ወገን ነህ ወይስ ከማኅበረ ቅዱሳን?” በሚል በክልሉ ምክትል ፖሊስ ኮሚሽነር የተመራ አድሏዊ ምርመራ እንደተካሄደባቸው ተገልጧል፡፡ ከጥር 13 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ የገዳሙ የሠርክ ጸሎት እና የስብከተ ወንጌል መርሐ ግብር እንደ ታወከ እና እንደተስተጓጎለ ይገኛል፡፡ የካቲት ዘጠኝ ቀን 2003 ዓ.ም ከቀትር በኋላ በሁኔታው ላይ መክሮ አቋም ለመውሰድ በገዳሙ ምእመናን የልማት ኮሚቴ አባላት በተጠራው ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ የመጡ ምእመናን የገዳሙ አስተዳዳሪ በደብዳቤ በጠሯቸው የከተማው ፖሊስ አባላት ቆመጥ እና ሁከተኞቹ ባወረዱት የድንጋይ ውርጅብኝ ተድብድበዋል፤ በድንጋዩ ውርጅብኝ ስድስት ምእመናን የመፈንከት አደጋ የደረሰባቸው ሲሆን ገዳሙም ከየካቲት ዘጠኝ ቀን ምሽት 12 ሰዓት አንሥቶ እስከ የካቲት 10 ቀን 2003 ዓ.ም ቀትር ድረስ የመግቢያ በሩ ዙሪያ በገመድ ታጥሮ ለሁሉም አገልግሎት ዝግ ሆኖ ምእመናንንም ከመሳለም ተከልክለው መቆየታቸው ተዘግቧል፡፡

የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ በቅርቡ በሰጡት ገለጻ የችግሩ ምንጮች፡- የደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም አስተዳዳሪ እና ሰበካ ጉባኤ መመሪያን የመፈጸም እና የማስፈጸም፣ ቃለ ዓዋዲውን የመጠበቅ እና የማስጠበቅ በአጠቃላይ ግቢውን ከሁከት እና ከአላስፈላጊ ነገሮች የመጠበቅ እና የማስጠበቅ ሐላፊነትን አለመወጣት፤ ‹የሰንበት ት/ቤቱ አባላት ነን› የሚሉ ነገር ግን የዕድሜ ገደብ (ከ4 - 30) ያለፈባቸው (ከ40 - 50 ዓመት ዕድሜ ያላቸው)፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ እና የሊቀ ጳጳሱ ፈቃድ ሳይሰጣቸው ድርሻቸውንም ሳያውቁ ‹እኛ ብቻ ነን መስበክ እና ማስተማር የሚገባን፤ እገሌ ካልሰበከ አይሆንም› በሚል የተናጠል እና የቡድን አስተሳሰብ ሌሎችን ወደ ስሜት የሚገፋፉ፣ የቤተ ክርስቲያንን ደንብ እና መመሪያ የማይቀበሉ፣ እንደራሳቸው ሐሳብ የሚሄዱ አካላት ናቸው፡፡ አስተዳዳሪው ችግሩን እንዲፈቱ ከአንዴም ሦስቴ በብፁዕ አቡነ ገብርኤል መመሪያ እንደተሰጣቸው ያመለከቱት ሥራ አስኪያጁ፣ ለሰበካ ጉባኤ አባላቱም ቃለ ዓዋዲው ተጠብቆ ይሠራበት ዘንድ የአቅማቸውን ያህል ጥረት እንዲያደርጉ፣ ከአቅማቸው በላይ የሆነ ነገር ሲገኝ ደግሞ ለሀገረ ስብከቱ እና ለመንግሥት አካላት አቅርበው እንዲያስከብሩ ተደጋጋሚ ውይይቶች፣ የቃል እና የጽሑፍ መመሪያዎች ሲተላለፉ ቢቆዩም ተፈጻሚነት ባለማግኘታቸው በሀገረ ስብከቱ 13 ወረዳዎች ከሚገኙት 125 አብያተ ክርስቲያን በተለየ አኳኋን የደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳምን የጭቅጭቅ መድረክ እንዳደረገው አስረድተዋል፡፡

ሥራ አስኪያጁ እንዲህ ይበሉ እንጂ እንደ ቅርብ ታዛቢዎች እይታ ዘረኝነትን (የተወላጅነት መብትን) የእውነተኛ ማንነት መከለያ (ጭምብል)፣ ማኅበረ ቅዱሳንን የሤራ ማክረሪያ ስልት (መረገጫ) በማድረግ እየተከሠተ የሚገኘው ችግር ዋነኛ መንሥኤ፡- የሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳምን የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ ፕሮጀክት ‹ቤተ ሙከራ› አድርጎ ቤተ ክርስቲያኒቱን ከውስጥ በማመስ እና ከውጭ ከብቦ በማንኛውም መንገድ በማስጨነቅ ባለችበት በመውረስ አልያም ከፍሎ በመረከብ የቀናዒ ኦርቶዶክሳውያንን ቅስም የመስበር (የማሸማቀቅ) እና ሌሎች አህጉረ ስብከትን ተስፋ የማስቆረጥ ኤክስፐርመንት ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች የኤክስፐርመንታቸው ሠርቶ ማሳያ ለማድረግ ርብርብ ለሚያደርጉባቸው የሐዋሳ ከተማ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን በአጠቃላይ እና የደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም በተለይ በቀጥታ ይሁን በተዘዋዋሪ እገዛ እያደረገ ያለው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አስተዳደራዊ ይዞታ በተለይም የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጽ/ቤት የችግር አፈታት ነው፡፡

በቋሚ ሲኖዶስ አባላት ላይ ጫና በመፍጠር እና ሕገ ቤተ ክርስቲያንን በመጣስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ለሲዳማ ጌዲኦ አማሮ እና ቡርጂ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በቀጥታ ያስተላለፉት አድሏዊ ውሳኔ፣ የሀገረ ስብከቱን ችግር አጥንቶ ለቅዱስ ሲኖዶስ የመፍትሔ ሐሳብ እንዲያቀርብ በቋሚ ሲኖዶስ ተሠይሞ ጥቅምት 12 ቀን 2003 ዓ.ም ወደ ሐዋሳ አምርቶ የነበረው አጣሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የኮሚቴውን ሪፖርት በወቅቱ ለሚመለከተው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ አለማቅረባቸው፤ ይልቁንም በማጣራቱ ሂደት የታመነባቸውን 73 ገጽ የጽሑፍ እና ስምንት የኦዲዮ ቪዥዋል ማስረጃዎች መሸሸጋቸው፤ ከዚህ በከፋ መልኩ ደግሞ ሰሞኑን “ማኅበረ ካህናትን፣ ማኅበረ ምእመናንን እና ምእመናትን በማነጋገር”፣ “ሰነዶችን እና በግንባር የቀረቡ የቃል አቤቱታዎችን በመመርመር” ለቋሚ ሲኖዶሱ እንዳቀረቡት በተነገረው “ጥናታዊ ሪፖርታቸው” በአንድ በኩል - ለአቡነ ጳውሎስ የማጥቂያ መንገድ ሲያመቻቹ በሌላ በኩል - እንደ “ተስፋ ኪዳነ ምሕረት የልማት እና ፀረ-ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ማኅበር” እና “የቅድስት ማርያም የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ማኅበር” ላሉት የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ መሣሪያ የሆኑ ድርጅቶች የልብ ልብ የሚሰጥ ውሳኔ እንዲተላለፍ መንገድ መክፈታቸው ሌሎቹ መንሥኤዎች ናቸው፡፡ በጥቅምት ወር የተካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ወደ መንበረ ፓትርያርኩ ጠቅላይ ጽ/ቤት እንዳይገቡ ውሳኔ ያሳለፋባቸው ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ እግዱን እየተላለፉ ወደ መንበረ ፓትርያርኩ በመግባት የሁከት ፈጣሪዎቹ ጉዳይ አስፈጻሚ ከመሆናቸው በላይ በገንዘብ መደገፋቸውም ከዋነኞቹ መንሥኤዎች ተለይቶ የሚታይ አይደለም፡፡

ጥር 27 ቀን 2003 ዓ.ም ከተካሄደው የቋሚ ሲኖዶሱ ቃለ ጉባኤ ለመረዳት እንደተቻለው ፓትርያርኩ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ፣ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ሐላፊ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የበላይ ሐላፊ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ፣ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ፤ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ፣ የምሥራቅ ሐረርጌ እና የሶማሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ያሬድ በተገኙበት የቋሚ ሲኖዶስ ስብሰባ ተደርጓል፡፡ በዚሁ ስብሰባ ላይ በሊቀ ጳጳሱ የተመራው ልዑክ በጥቅምት ወር “ባጠናው እና ባጣራው ሪፖርት” የሀገረ ስብከቱ ውዝግብ ዋነኛ መንሥኤ “የተስፋ ኪዳነ ምሕረት የልማት እና የፀረ-ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ማኅበር እና የማኅበረ ቅዱሳን አባላት እና ደጋፊዎቻቸው የሀገረ ስብከቱን ባለሥልጣናት እንደመሣሪያ በመጠቀም የቤተ ክርስቲያኗን መድረክ እጅ ለማድረግ፣ አንዱ ሌላውን ለመቅደም እና ብሎም ለማጥቃት በሚያደርጉት የሞት ሽረት ፍልሚያ ምእመናኑን፣ ካህናቱን እና ወጣቱን ወደ ሁለት መክፈላቸው” ነው ሲል ደምድሟል፡፡

በሊቀ ጳጳሱ ሪፖርት መሠረት ከዕለት ወደ ዕለት እየሰፋ በሄደው ብጥብጥ እና ሁለቱ ማኅበራት በሚያደርጉት ትንቅንቅ “የተስፋ ኪዳነ ምሕረት የልማት እና የፀረ-ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ማኅበር” ደጋፊዎች በሀገረ ስብከቱ ከሞላ ጎደል የተሻለ ቦታ አግኝተዋል፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት እና ደጋፊዎች ግን ብዙ ነገር እያጡ በመሄዳቸው በሀገረ ስብከቱ ባለሥልጣናት [የቀድሞው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፋኑኤል፣ ሥራ አስኪያጁ መልአከ ሕይወት ፀሐይ መልአኩ. . . ] ላይ በማቄም የፈጸሟቸውን የአስተዳደር በደል፣ የገንዘብ ምዝበራ እና የሥነ ምግባር ጉድለት ጠቅሰው ከሐላፊነታቸው እንዲነሡ ምክንያት እንደሆነ ይገልጣል፡፡ ይሁንና “የተስፋ ኪዳነ ምሕረት የልማት እና የፀረ-ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ማኅበር” አባላት የቀድሞው የሀገረ ስብከቱ ባለሥልጣናት “የልማት እና የስብከተ ወንጌል መሪዎች” በመሆናቸው እንዳይነሡብን ማለታቸውን ሲያብራራ በአንጻሩ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት የአስተዳደር በደልን፣ የገንዘብ ምዝበራን እና የሥነ ምግባር ጉድለትን አስመልክቶ ያቀረቧቸው ማስረጃዎች፣ “ከችግሩ መነሣት ቀደም ብለው የተፈጸሙ” እንደሆኑ፣ “ከሳሾች [ማኅበረ ቅዱሳን?] ራሳቸው በፈቃደኝነት ያሉባቸው እና የሚያውቋቸው ከመሆኑ አንጻር ለነገር መነሻ ሊጠቀሙባቸው እንደፈለጉ የሚያስረዱ እንጂ መሠረታዊ ችግሮች አለመሆናቸውን” ሪፖርቱ መመዘኑን በቃለ ጉባኤው ላይ ተገልጧል፤ “ተፈጠሩ የተባሉት ችግሮችም እንዲታረሙ ጥቆማ ከመስጠት ያለፈ ሀገርን የሚንጥ፣ ሁከት እና ብጥብጥ የሚያስከትል እንዳልነበረ” ሪፖርቱ እንደሚያጣጥለው ቃለ ጉባኤው ያስረዳል፡፡

የሁለቱ ማኅበራት ደጋፊዎች “በማይመለከታቸው እና በማያገባቸው በቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር ጣልቃ እየገቡ” የራሳቸውን ፍላጎት ለማሳካት ሲሉ ውዥንብር መፍጠራቸውን የሚገልጸው ሪፖርቱ በብፁዕ አቡነ ገብርኤል ሊቀ ጳጳስነት እና በሥራ አስኪያጁ ሊቀ ኅሩያን ዓለም እሸት ገብረ ጻድቅ የተመራው የሀገረ ስብከቱ አስተዳደርም “የአንድ ወገን ደጋፊ ሆኖ ከመታየቱ በቀር” የሁለቱን ቡድኖች ፉክክር በመፍታት ረገድ “ጥበብ የተመላበት አመራር እንዳልተከተለ” ሪፖርቱ መንቀፉን በቃለ ጉባኤው ላይ ተመልክቷል፡፡

በቅድሚያ የቋሚ ሲኖዶሱ አብዛኛው አባላት ችግሩ በሀገረ ስብከቱ ደረጃ እንዲፈታ ሐሳብ ቢሰጥበትም ከአንድም ሁለት ጊዜ በፓትርያርኩ ተደጋግሞ በመቅረቡ የተነሣ በአጀንዳው ላይ በዚህ መልኩ ለመወያየት መገደዱን ነው የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ምንጮች የሚናገሩት፡፡ በስብሰባው ላይ በአስረጅነት የተገኙት ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ማኅበረ ቅዱሳን በዋናነት በገጠሩ ክፍል የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ከመስጠት እና የልማት ተግባራትን ከማከናወን ውጭ በአጣሪ ኮሚቴው በተዘረዘሩት ድርጊቶች ውስጥ እንደሌለበት ለማስረዳት ሞክረው እንደነበረ ተዘግቧል፡፡ ይሁንና እንደምንጮቹ መረጃ ብፁዕነታቸው “በፓትርያርኩ በደረሰባቸው ሸንቋጭ አስተያየት ይኸኛውም ያኛውም ይፈቀድለት ወደሚል አቋም እንደያዙ” ተሰምቷል፡፡ ይህኛውም ሐሳብ ያልተዋጠላቸው ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ግን ከአንድ ዓመት በፊት (በ23/02/2002 ዓ.ም) በራሳቸው ውሳኔ “የቅድስት ማርያም የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ማኅበር” የሚል ፈቃድ የሰጧቸውን እነ ያሬድ አደመን፣ በጋሻው ደሳለኝን እና መሰሎቻቸውን ከእይታ ውጭ አድርጎ በማትረፍ በማኅበረ ቅዱሳን የሐዋሳ ማእከል ላይ የሚያሳርፉትን ምት ያከረርሁ መስሏቸው በቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ውስጥ ምንም ድርሻ የሌለው እና መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት ስም የተቋቋመው “ተስፋ ኪዳነ ምሕረት የልማት እና ፀረ-ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ማኅበር” የተባለውን አካል የጦስ ዶሮ እና አቋም ማሳቻ ለማድረግ መምረጣቸውን የጉዳዩ ተከታታዮች ያብራራሉ፡፡

ይሁንና በዚህ አመለካከታቸው እና ድርጊታቸው ቅዱስ ሲኖዶስ ከ1984 ዓ.ም አንሥቶ ለሦስት ጊዜያት ያህል እያሻሻለ ባጸደቀለት መተዳደሪያ ደንብ የሚመራውን ማኅበረ ቅዱሳንን በመግፋት ከቤተ ክርስቲያኒቱ ውጭ በደ/ብ/ብ/ሕ ክልላዊ መንግሥት ፍትሕ እና ጸጥታ ቢሮ በመዝገብ ተራ ቁጥር 131/10/97 ዓ.ም ተመዝግቦ ፈቃድ እንደተሰጠው ከሚታወቀው ባዕድ ማኅበር (“ተስፋ ኪዳነ ምሕረት የልማት እና ፀረ-ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ማኅበር”) አሳንሰዋል፡፡ ለአቡነ ጳውሎስ ለይቶ ማጥቃት (surgical attack) መሣሪያ የሆነው፣ ወቅቱን ጠብቆ በአግባቡ ያልቀረበው የአጣሪ ኮሚቴው ሪፖርትም ማኅበረ ቅዱሳን “በተስፋ ኪዳነ ምሕረት” ለተወነጀለበት ጉዳይ አንድ ጊዜ ስንኳ ጠርቶ የመጠየቅ ዕድል ሳይሰጥ ማኅበሩ ከሳሽም ተከሳሽም ባልሆነበት ጉዳይ በሪፖርቱ ክፉኛ መኮነኑ ብዙዎችን አሳዝኗል፡፡

ለሦስተኛ ጊዜ በተሻሻለው የማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ ማኅበሩ ቀደም ሲል “በቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ” የተቀመጠው አንቀጽ ወጥቶ አባላቱ እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነታቸው በአስተዳደር ጉዳይም ሚና እንዲኖራቸው መፈቀዱ ተዘንግቶ፣ በቋሚ ሲኖዶሱ ቃለ ጉባኤ ገጽ አራት ላይ ማኅበሩ “የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የማያገባው እና የማይመለከተው” እንደሆነ፣ ጣልቃ የሚገባውም “የራሱን ፍላጎት ለማሳካት እንደሆነ በግልጽ ታይቷል” መባሉ፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 12 ንኡስ አንቀጽ አንድ ቋሚ ሲኖዶሱ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ እየተወሰኑ የሚተላለፉ መመሪያዎችን እና ልዩ ልዩ ጉዳዮች ተግባራዊ መሆናቸውን የመከታተል ሐላፊነቱን ያልተወጣ ያሰኘዋል፡፡

በአቡነ ጎርጎርዮስ የተመራው ልኡክ ሪፖርት ከመታየቱ ቀደም ሲል፣ ጥር 25 ቀን 2003 ዓ.ም በሐዋሳ ከተማ ምእመናን እና ሰንበት ት/ቤቶች ተማሪዎች ስም የሰንበት ት/ቤት ይሁን የሰበካ ጉባኤ አባላት ስለመሆናቸው የሚያጠራጥሩ እና ጉዳዩ በቀጥታ የማይመለከታቸውን አልፎ ሂያጆች በጥቅም በመደለል እንዲሁም በፕሮቴስታንት እምነት ተከታይነታቸው ተለይተው የሚታወቁ መናፍቃንን በመሰብሰብ ከ8-12 በሚደርሱ መኪኖች ተጭነው ወደ መንበረ ፓትርያርኩ በመምጣት በግንባር ቀርበው “የሀገረ ስብከቱ ሐላፊዎች” (ሥራ አስኪያጁ) አደረሱብን ያሉትን ችግር ቋሚ ሲኖዶሱ መመልከቱን ቃለ ጉባኤው ይገልጻል፡፡

በዘጠኝ ነጥቦች ተለይተው በሥራ አስኪያጁ ላይ ከቀረቡት አቤቱታዎች መካከል፣ ከጥቅምት 20 - 22 ቀን 2003 ዓ.ም ለቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ማስፈጸሚያ ገቢ ለማሰባሰብ በመስቀል አደባባይ ለማካሄድ ታቅዶ ስለነበረው ጉባኤ የሚገልጸው ይገኝበታል፡፡

ያሬድ አደመ እና በጋሻው ደሳለኝ ከመሰሎቻቸው ጋራ የሀገረ ስብከቱን ሊቀ ጳጳስ ፈቃድ ሳያገኙ የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ያስተላለፋባቸውን እገዳ በመጣስ ሊፈነጩበት ያቀዱትን ጉባኤ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ በቁጥር 366/51/101/2003 በቀን 19/05/2003 ለሕንጻ አሠሪው ኮሚቴ በጻፉት ደብዳቤ ወደ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም እንዲዘዋወር አድርገዋል፤ በጉባኤው ላይ ተገኝተው ትምህርተ ወንጌል የሚሰጡትም ከጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ የተመደቡት እና የተፈቀደላቸው ሰባክያነ ወንጌል፣ 1) መምህረ ሃይማኖት ባሕታዊ ኃይለ ጊዮርጊስ፣ 2) መምህር ናዖድ ኢያሱ፣ 3) በኲረ ትጉሃን ቀሲስ ደመላሽ ቶጋ ብቻ የማስተባበሩን እና የማስተማሩን ሥራ እንዲያከናውኑ አሳውቀዋል፡፡ የማኅበረ ምእመናኑን ሰላም ለመጠበቅ ሲባል ያልተፈቀደላቸው ሰዎች መድረክ ላይ እንዳይወጡ እና አላስፈላጊ የሆነ ችግር እንዳይፈጠር የገዳሙ አስተዳዳሪ እና ሰበካ ጉባኤ አስፈላጊውን ቁጥጥር ያደርጉ ዘንድም አሳስበዋል፡፡

ይሁንና የገዳሙ አስተዳዳሪ ይህን የሀገረ ስብከቱን ማሳሰቢያ ወደ ጎን በማለት ከቤተ ክርስቲያን በዘረፉት 700‚000 ብር የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ገዝተው የግል መጠቀሚያ ካደረጉት የደብረ ሰላም ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ አባ ናትናኤል እና በመሠራት ላይ የሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ አባ ሲሳይ ጋራ በመሆን መድረኩን ላልተፈቀደላቸው ለእነ ትዝታው ሳሙኤል በማስረከባቸው በተነሣው ተቃውሞ በምእመናን ላይ ጉዳት ደርሷል፤ በጉባኤው እንዲያስተምሩ የተፈቀደላቸው መምህራንም ተዋክበው እንዲባረሩ ተደርጓል፡፡ በዕለቱ(ጥር 20 ቀን 2003 ዓ.ም) በዐውደ ምሕረቱ ላይ ቆመው ሁከቱን ሲያበረታቱ የነበሩት እነ ትዝታው ከነጫማቸው መቅደስ ውስጥ ሸሽተው በመግባት ለጊዜው ተሰውረው ቢቆዩም ከሌሎች አራት መሰሎቻቸው ጋራ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለው በማግሥቱ ሲለቀቁ የቤተ ክህነቱ ሕግ እና ደንብ እንዲከበር ጥረት ያደረጉት ምእመናን ግን እስከ ጥር 22 ቀን 2003 ዓ.ም ምሽት ድረስ ከያሉበት እየታደኑ አድሏዊ እና አሸማቃቂ ምርመራ ተካሂዶባቸዋል፤ እየፈረሙ እና የመታወቂያ ዋስ እየጠሩም እንዲለቀቁ ተደርጓል፡፡

የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ያሬድ አደመን ጨምሮ ሌሎች 19 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው በሕግ እንዲጠየቁ ለክልሉ የፍትሕ እና ጸጥታ ቢሮ ያቀረበው ጥያቄም ሰሚ ጆሮ አላገኘም፡፡ በአንጻሩ የሊቀ ጳጳሱን እና የሥራ አስኪያጁን ስም የሚያጠፋ ወረቀት የበተነው፣ የአካል ጥቃት ለማድረስ እስከ መንበረ ጵጵስናው የመግባት ድፍረት ያገኘው፣ “እኔ ሳላምንበት ምንም ነገር ማድረግ አትችሉም፤ ያለዚያ ቤተ ክርስቲያኗን አምሳታለሁ፤ መረጋጋት አይኖርም” በማለት የደነፋው ያሬድ አደመ፤ “ያለነውጥ ለውጥ አይመጣም፤ የወንጌል ብርሃን ያልበራላቸውን ናቸው የሚበጠብጡት፤ እነርሱን መፍራት አያስፈልግም፤ መግደል ነው” እያሉ ድምፅ ማጉያ ጨብጠው በዐውደ ምሕረቱ የተናገሩት እነ አባ ናትናኤል በፍትሕ እና ጸጥታ ቢሮው ተጠያቂ የተደረጉበት ይሁን በቋሚ ሲኖዶሱ ስብሰባ ላይ የምር የተገመገሙበት ሁኔታ አልታየም፡፡

በምትኩ በቋሚ ሲኖዶሱ ስብሰባ ላይ የሥራ አስኪያጁ ጥረት በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ውስጣዊ አሠራር “ጣልቃ በመግባት”፣ ለደብር አስተዳዳሪዎች ማስፈራሪያዎችን እና ማስጠንቀቂያዎችን በመጻፍ “ሁከት በመፍጠር”፣ በምእመናን እና በሊቀ ጳጳሱ መካከል የጠበቀ ግንኙነት እንዳይኖር “ዕንቅፋት በመሆን” ተፈርጀዋል፤ “በቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገባ በዕርቅ ሰነድ ስምምነት የተደረሰበትን፣ በሕዝብ ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ ካለ ማኅበረ ቅዱሳን በሚባል ማኅበር ጽ/ቤት ተገኝተው የማኅበሩን ስብሰባ እየመሩ በመገኘት”ም ተጠቁረዋል፡፡ ይኸው “አቤቱታ” በሀገረ ስብከቱ ገና ከተመደቡ ሦስት ወር የሆናቸውን ሥራ አስኪያጅ “የሥራ አፈጻጸም ጉድለት እንደሚያሳይ” ቋሚ ሲኖዶሱ እንደተነጋገረበት ቃለ ጉባኤው ያስረዳል፡፡

በመጨረሻም ቋሚ ሲኖዶሱ፡-
      . በሀገረ ስብከቱ  ለተከሠተው ችግር ምክንያት ሆኖ የተገኘው “የተስፋ ኪዳነ ምሕረት የልማት እና ፀረ-ኡች.አይ.ቪ/ኤድስ ማኅበር”፣ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት እና ደጋፊዎች እንደማንኛውም ምእመን መንፈሳዊ አገልግሎት ከሚያገኙ በቀር በቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ውስጥ ጣልቃ እንዳይገቡ፤   
      . ከተማውን ለከፍተኛ ውዝግብ የዳረገው የሁለቱ ማኅበራት እና ደጋፊዎቻቸው  ፉክክር መሆኑ ስለተረጋገጠ የቤተ ክርስቲያኒቱን እና የምእመናንን ሰላም  ለመጠበቅ ሲባል ያለው ሁኔታ በአስተማማኝ እስከሚረጋጋ ድረስ የሁለቱም        ማኅበራት አባላት በቤተ ክርስቲያኒቱ መድረክ ላይ እንዳያስተምሩ፤
      . እስከዚያው ድረስ የደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ስብከተ ወንጌል ሐላፊ መልአከ ምሕረት ጳውሎስ ቀጸላ እንዳሉ ሆነው በተጨማሪ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽቤት በሚላኩ ሰባክያነ ወንጌል ሥራው እየተሸፈነ         እንዲቆይ፤  
      . በሀገረ ስብከቱ የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት እና የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ለማስፈጸም ከክልሉ መስተዳድር ጋራ በመተባበር የማረጋጋት ሥራ የሚሠራ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እና ከጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር የተውጣጣ ኮሚቴ ወደ ቦታው እንዲላክ፤
       . ጥር 25 ቀን 2003 ዓ.ም የቀረበው አቤቱታ በሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ የሥራ አፈጻጸም ጉድለት ላይ ያተኮረ ስለሆነ ከሥራ አስኪያጅነት እንዲነሡ ሆኖ ብቃቱ የተረጋገጠ ሥራ አስኪያጅ በቋሚ ሲኖዶስ የተወሰነ በመሆኑ        በውሳኔው መሠረት እንዲፈጸም እንዳዘዘ በቃለ ጉባኤው ላይ ተገልጧል፡፡

የስብሰባው ውሳኔም በቁጥር 92/54/2003 በቀን 2/6/2003 በፓትርያርኩ ፊርማ ወጭ ሆኖ በአድራሻ ለሲዳማ ጌዲኦ አማሮ እና ቡርጂ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በግልባጭ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት፣ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት፣ ለደ/ብ/ብ/ሕ/ ክልላዊ መስተዳድር ጽ/ቤት እና ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ፖሊስ ኮሚሽን ግልባጭ በተደረገ ደብዳቤ ተልኳል፡፡

በቃለ ጉባኤው ላይ የቋሚ ሲኖዶሱ ሰብሳቢ የሆኑት የአቡነ ጳውሎስ እና የብፁዕ አቡነ ጎርጎሬዎስን ጨምሮ የአራት ሊቃነ ጳጳሳት ፊርማ ያረፈበት ሲሆን የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል እና ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ፊርማ አለመስፈሩ ይታያል፡፡ ይሁንና የቃለ ጉባኤው መዝጊያ ዐረፍተ ነገር ውሳኔው “ቋሚ ሲኖዶሱ በሙሉ ድምፅ ተስማምቶ እንደወሰነ” ቢገልጽም ሁለቱ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ፊርማቸውን ካለመኖራቸው ጋራ ተያይዞ ቃለ ጉባኤው ከዋና ጸሐፊው ፈቃድ ውጭ በሌላ አካል ተጽፎ ሊሆን እንደሚችል ግምት ተወስዷል፤ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በቀጥታ ለሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት የመላኩም ሁኔታ ግምቱን የሚያጠናክር ሆኗል፡፡ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 25 መሠረት የቋሚ ሲኖዶስን ስብሰባ ቃለ ጉባኤ የመያዝ፣ ከቅዱስ ሲኖዶስ የሚሰጠውን ውሳኔ እና ትእዛዝ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት እና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ሁሉ የማስተላለፍ ሥልጣን እና ተግባር የቅዱስ ሲኖዶስ ጸሐፊ ነው፡፡ በአንቀጽ 30 መሠረት ደግሞ ቅዱስ ሲኖዶስ ስለ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር በየጊዜው የሚወስናቸውን ጉዳዮች በሕጉ መሠረት የመፈጸም እና የማስፈጸም ሥልጣን እና ተግባር የጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ነው፡፡

የሲዳማ ጌዲኦ አማሮ እና ቡርጂ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ በመሆን ከሦስት ወራት በፊት ሥራ የጀመሩት ሊቀ ኅሩያን ዓለም እሸት ገብረ ጻድቅ፣ ታኅሣሥ 25 ቀን 2003 ዓ.ም ሁሉም ወገኖች የተቀበሉት የዕርቅ ስምምነት ላይ እንዲደረስ እና ሰላም እንዲወርድ ማስቻላቸው በቋሚ ሲኖዶሱ ስብሰባ ላይ በሚዛናዊነት አልታየም፤ ሌላው ይቅርና ቀርቦባቸዋል በተባለው አቤቱታ መሠረት በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 37 ንኡስ አንቀጽ 8 መሠረት በሥራ ልምዳቸው እና በብቃታቸው መርጠው ለጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ አቅርበው በቅዱስ ፓትርያርኩ ስምምነት ባሾሟቸው፣ በአንቀጽ 38 እንደተደነገገውም ተጠሪ በሆኑላቸው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ተጠርተው አልተጠየቁም፡፡

በቃለ ዓዋዲው አንቀጽ 44 ንኡስ አንቀጽ 8 መሠረት በሀገረ ስብከት ክልል ውስጥ በመጀመሪያ ደረጃም ሆነ በይግባኝ የሚቀርቡ የሕግ እና ሥነ ሥርዐት ጉዳዮችን በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት እንዲታይ የማድረግ፣ ይግባኝ የሚጠየቅበት ጉዳይም ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ወይም ለቅዱስ ሲኖዶስ እንዲተላለፍ የማድረግ ሥልጣን እና ተግባር ያላቸው ብፁዕ አቡነ ገብርኤልም አልተጠየቁበትም፡፡ በምትኩ በፓትርያሪኩ አበረታችነት በአድማ የተጠራውና ‹‹ለሻይ›› እስከ 5000 ብር የገንዘብ ድጋፍ ለአድመኞቹ በተደረገበት የአቤቱታ አቀራረብ፣ “በሥራ አስኪያጁ የሥራ አፈጻጸም ጉድለት ላይ ስላነጣጠረ” በሚል ብቻ እንዲነሡ መወሰኑ የሀገረ ስብከቱን ምእመናን ቅር አሰኝቷል፡፡ የደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ምእመናን ልማት ኮሚቴ አባላት ይህኑ በመጥቀስ ለፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የተቃውሞ ደብዳቤ መጻፋቸው ተሰምቷል፡፡

ትናንት  ከደ/ብ/ብ/ሕ ክልላዊ መንግሥት ርእሰ መስተዳድር ጋራ በተደረገው ውይይት፡- ለልማት ተግባር ተጠርተው መምጣታቸውን፣ ከመጡ በኋላም ስሕተት በማየታቸው ስሕተቱን ለማስተካከል ተቃውሞ ማቅረባቸውን፣ ተቃውሟቸውንም ችግሩን እንዲያጣራ ለመጣው ልኡክ በመረጃ በማስደገፍ በማቅረባቸው ቀደም የነበሩት ሐላፊዎች ተዛውረው አሁን ያለው ለውጥ መደረጉን አስረድተዋል፡፡ በብፁዕ አቡነ ገብርኤል፣ በሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ እና በመንግሥት ከፍተኛ ጥረት የዕርቅ ስምምነት ተፈርሞ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ባሉበት ሁኔታ ዳግመኛ ያገረሸውን ችግር አስመልክቶ እዚህ ቀርበን ለመነጋገር ያገኘነውን ዕድል ያህል በመንበረ ፓትርያርኩ ዘንድ አለማግኘታቸውን አመልክተዋል፡፡ ችግሩ በማንኛውም ገጽታው ከማኅበረ ቅዱሳን ጋራ ሊቆራኝ የሚችልበት አግባብ እንደሌለው የተናገሩት የምእመናኑ ተወካዮች፣ “የክልሉ ተወላጆች እንዳናገለግል በዘረኝነት እና በፖሊቲካዊ አካሄድ ተገፋን፤ በቋንቋችን እንዳንሰብክ ተከለከልን. . .” በሚል ለቀረበው ክስ ምላሽ ሰጥተዋል - “እስከ ዛሬ ያልተነሣ የቋንቋ ጉዳይ አቶ ሽፈራው ሲሰበስቡን መነቀሱ ለምን ይሆን? ይህ አካሄድ የጥገኝነት ነው!!”
++++++++++++++++++++++++

የዚህን ረፖርታዥ ዝርዝር የሚያሳየውን የምእመናን የአቤቱታ ደብዳቤ እና የቅዱስነታቸውን ማጠቃለያ እዚህ http://www.tewahedotoday.org/doc.pdf መጫን ማንበብ ይቻላል።


Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)