February 10, 2011

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አፅራረ ቤተ ክርስቲያንን ለመከላከል በሚያደረገው ጥረት ማንኛውንም ድጋፍ እንደሚሰጥ የአ/አበባ ሀ/ስብከት አስታወቀ

  • የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ ጥመት - አሰግድ ሣህሉ እንደ ማሳያ (ከደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤት ዘገባ የተገኘ)
 ቀንደኛ የተሐድሶ ኑፋቄ አቀንቃኝ የተባለው አሰግድ ሣህለ

(ደጀ ሰላም፤ ፌብሩዋሪ 10/2011፤  የካቲት 3/2003 ዓ.ም)፦ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ ተልእኮ ለማፋጠን እና ለማስፋፋት፣ የተቋቋመበትን ዓላማ ለማሳካት፣ ኮሌጁንም ከማንኛውም አጽራረ ቤተ ክርስቲያን አካላት ለመጠበቅ በሚያደርገው ጥረት ሁሉ ድጋፍ የሚሰጥ መሆኑን አስታወቀ፡፡ የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ይህን ያስታወቀው፣ የኮሌጁ አስተዳደር ጉባኤ  የኮሌጁን የቅበላ መስፈርት ባለማሟላቱ ኅዳር 23 ቀን 2003 ዓ.ም ከትምህርት ገበታ ያገደው አሰግድ ሣህለ የተባለ ቀንደኛ የተሐድሶ ኑፋቄ አቀንቃኝ፣ ‹‹በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ውስጥ የቤተ ክርስቲያን አባል እንደሆነ የሚያቀርበው የመብት ጥያቄ ተቀባይነት የሌለውና በሀገረ ስብከታችን ውስጥ የቤተ ክርስቲያናችን አባል አለመሆኑን›› በመግለጽ ለኮሌጁ በጻፈው ደብዳቤ ነው፡፡

በቁጥር 1530/37/03 በቀን 26/05/03 ዓ.ም በሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ንቡረ ዕድ አባ ገብረ ማርያም ገብረ ሥላሴ ተፈርሞ በአድራሻ ለቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ በግልባጭ ለሀገረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌል እና ትምህርት መምሪያ እና ለደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት የደረሰው ይኸው ደብዳቤ፣ አሰግድ ‹‹በቤተ ክርስቲያን ሕግ እና ደንብ መሠረት በሕጋዊ መንገድ በአባልነት ያልተደራጀ፣ በደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን ሾልኮ በመግባት በአፍራሽ ተልእኮ ተሰማርቶ በመገኘቱ ከደብሩ የተገለለ›› መሆኑን አስታውሶ በሀገረ ስብከቱ ውስጥ በማንኛውም የአገልግሎት ዘርፍ እንዳልተመደበ ማረጋገጡን ግልጽ አድርጓል፡፡

ጥር ሦስት ቀን 2003 ዓ.ም በደብዳቤ ቁጥር 501/05/04/03 የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ዲያቆን አሰግድ ሣህሉን በተመለከተ በቢሮው የሚገኙትን መረጃዎች መላኩን ያመለክታል፤ ከዚያ በኋላም ከሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት እና ከደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን የተገኙትን ዝርዝር ጉዳዮች ሲፈትሽ እንደ ቆየ ገልጧል፡፡

ጽ/ቤቱ በዚህ ምርመራው የደረሰባቸውን መረጃዎች በስድስት ነጥቦች ለያይቶ አስረድቷል፤ እነርሱም፡- 1) ግለሰቡ የመኖሪያ ቦታው በደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን አጥቢያ አለመሆኑ፤ 2) በተለያዩ ጊዜያት ያለአጥቢያው በሰንበት ት/ቤት በአባልነት ሲንቀሳቀስ መቆየቱን፤ 3) በነበረው ቆይታ ሁሉ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እና ከሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ውጭ በሚያደርገው አፍራሽ እንቅስቃሴ የደብሩን ሰላም እና አገልግሎት ሲያውክ የቆየ መሆኑን፤ 4) በዚህ ጥፋቱ በደብሩ አስተዳደር ርምጃ የተወሰደበት ቢሆንም የተለያዩ ክፍተቶችን በመጠቀም ያልተቋረጠ ሙከራ ሲያደርግ መቆየቱንና አሁንም በማድረግ ላይ መሆኑን፤ 5) ‹‹በሰበካ ጉባኤ አባልነት ተመዝግቤ የአባልነት ክፍያዬን ያለማቋረጥ በመክፈል አባል ለመሆኔ መረጃ ይሰጠኝ›› ብሎ ማመልከቻ አቅርቦ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ መረጃ መውሰዱንና ይህም ስሕተት በመሆኑ ደብሩ ቀደም ሲል የተሰጠውን መረጃ በቁጥር 471/666/03 በተጻፈ ደብዳቤ መሻሩን፤ 6) በደብሩ ይሁን በሰንበት ት/ቤቱ ስም ስውር ተልእኮውን ለማስፈጸም እንዳይችል ሰንበት ት/ቤቱ በቁጥር ው/ያ/11/17/03 በተጻፈ ደብዳቤ የማያዳግም ውሳኔ ማስተላለፉንና ይህም ውሳኔ በሁሉም አካል ታውቆ ተግባራዊ እንዲደረግ መጠየቁን ያስረዳል፡፡

አሰግድ ሣህሉ ከኮሌጁ የቅበላ መስፈርቶች አንዱ የሆነውን በሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ወይም በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ የተፈረመበት የድጋፍ ደብዳቤ በተሰጠው የጊዜ ገደብ ባለማቅረቡ እና በድጋፍ ደብዳቤ ስም ያቀረበውም ማስረጃ በሕገ ወጥ መንገድ ያገኘው በመሆኑ ኅዳር 23 ቀን 2003 ዓ.ም በኮሌጁ የአስተዳደር ጉባኤ መታገዱን መዘገባችንይታወሳል (የዲሴምበር 4/2010፤ ኅዳር 25/2003 ዓ.ም ይመልከቱ)፡፡

ከእገዳው በኋላ አሰግድ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት መናገሻ ምድብ ችሎት ‹‹አላግባብ ከትምህርት ገበታው እንደታገደ›› አድርጎ በኮሌጁ ላይ ክስ መመሥረቱ ታውቋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ‹‹ጉዳዩ ውሳኔ እስኪሰጥበት ድረስ ግለሰቡ ትምህርቱን እየተከታተለ እንዲቆይ ትእዛዝ አስተላልፏል›› ቢባልም ኮሌጁ የወከላቸው ጠበቃ አቶ ደስታ በርሄ ጥር 27 ቀን 2003 ዓ.ም ለችሎቱ ባሰሙት ምላሽ የአሰግድ ችግር በዋናነት ሃይማኖታዊ መሆኑንና ሃይማኖታዊ ሕጸጽ እንዳለበት ኮሌጁ ከደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤት እና ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ባገኘው ማስረጃ ያረጋገጠ መሆኑን፣ በኮሌጁ በማታው ክፍለ ጊዜ ተመዝግቦ ትምህርቱን በዲግሪው መርሐ ግብር ለመቀጠል ሲጠይቅ በቅበላ መስፈርቱ መሠረት በቂ ማስረጃ አለማቅረቡን፣ ባለበት የሃይማኖት ሕጸጽ ሳቢያ በዲፕሎማው መርሐ ግብር ትምህርቱን በ1995 ዓ.ም ባጠናቀቀበት ወቅት ዲፕሎማው ሳይሰጠው መቆየቱን ማስረዳታቸው ተዘግቧል፡፡

አሰግድ በተጠቀሱት ምክንያቶች ከኮሌጁ እንዲባረር መወሰኑን ያስረዱት ጠበቃው፣ የግለሰቡ ችግር በዋናነት ሃይማኖታዊ ከሆነ ዘንድ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 11 ንኡስ አንቀጽ 1 እና 3 መንግሥት እና ሃይማኖት የተለያዩ መሆናቸውን፣ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ መደንገጉን፤ ኮሌጁ በቅዱስ ሲኖዶስ ተፈቅዶ በተሰጠው ሕግ መሠረት የሚያስተምራቸውን ደቀ መዛሙርት የሚመርጥበት መስፈርት ያለውና ከዚህም ጋራ በተያያዘ የተማሪዎች መተዳደሪያ ደንብ ያወጣ መሆኑን ጠቅሰው ጉዳዩ በዚሁ የተቋሙ አሠራር ብቻ ሊታይ የሚችል በመሆኑ ምስክር፣ ድርድር ሳያስፈልግ ፍርድ ቤቱ እንዲያሰናብታቸው መጠየቃቸው ተመልክቷል፡፡ ይሁንና ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለመጋቢት 27 ቀን 2003 ዓ.ም መቅጠሩ ታውቋል፡፡

የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ ጥውየት - አሰግድ ሣህሉ እንደ ማሳያ
አሰግድ ሣህሉ በደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን የዉሉደ ያሬድ ሰንበት ት/ቤት የተሐድሶ ኑፋቄን ለማስፋፋት፣ አንዳንድ የሰንበት ት/ቤቱን ወጣቶች ከእናት ቤተ ክርስቲያን ወደ ‹‹ሙሉ ወንጌል›› አዳራሽ ለመውሰድ ሲያደርግ የቆየውን እንቅስቃሴ አስመልክቶ በጥብቅ ሲከታተል በቆየው የሰንበት ት/ቤቱ ሥራ አመራር ኮሚቴ የተዘጋጀው ባለ 40 ገጽ ሰነድ ያስረዳል፡፡ እንደ ዘገባው ማብራሪያ አሰግድ ሣህሉ ከሚኖርበት ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 11/12 የቤት ቁጥር 417 በተለምዶ ቡልጋሪያ ተብሎ ከሚጠራው የደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል - የከርቸሌው ሚካኤል አካባቢ ያለሰበካው ወደ ደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን መጥቶ በዉሉደ ያሬድ ሰንበት ት/ቤት በ1985 ዓ.ም የተመዘገበው ሰንበት ት/ቤቱ በወቅቱ ያጋጠመውን የአገልግሎት መዳከም ተመልክቶ ስውር የተሐድሶ ኑፋቄ ተልእኮውን ለማራመድ እንዲያመቸው ነው፡፡

በሂደት የሰንበት ት/ቤቱ ‹‹የትምህርተ ሃይማኖት አስተማሪ››፣ የሥራ አመራር አባል እና የትምህርት ክፍል ሰብሳቢ እስከመሆን የደረሰው አሰግድ ወጣቶችን ከቤተ ክርስቲያን ጉያ በማውጣት የሚታወቁትን ግርማ በቀለ(ይህ ግለሰብ ከሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ መንፈሳዊ ት/ቤት በኑፋቄው በአባቶች ተወግዞ ከተባረረ በኋላ ‹‹የእውነት ቃል አገልግሎት›› የተባለ የተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ ድርጅት የመሠረተ ነው)፣ ‹‹አባ›› ዮናስ(በ1990 ዓ.ም. ሚያዝያ 28 ቀን ራሳቸውን ገልጠው የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄያቸውን በአደባባይ በማስመስከራቸው ከቤተ ክህነት አዳራሽ ተወግዘው ከተለዩት አንዱ)፣ እነ ስዩም ያሚን ወደ ሰንበት ት/ቤቱ እየጋበዘ እንዲያስተምሩ አድርጓል፡፡

በ1986 ዓ.ም ነሐሴ ወር በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ አዘጋጅነት በጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እና በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በተሰጠው የአንድ ወር ኮርስ ላይ ሰንበት ት/ቤቱን ወክሎ የተሳተፈው አሰግድ፣ ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ አሁንም በአብ ቀኝ ቆሞ ያማልዳል፤›› በማለት በይፋ ይከራከር እንደነበርና በኮርሰኞቹ ምላሽ ይሰጠው እንደነበር ሰነዱ ያስታውሳል፡፡ ከዚህ በኋላ አሰግድን ጨምሮ በ1984 ዓ.ም ‹‹የተዳከመውን የቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤትን እናጠናክራለን›› በሚል ሽፋን የአጥቢያ ሰንበት ት/ቤታቸውን ትተው ከመጡ ሌሎች ሁለት ግለሰቦች(በሚያስደንቅ አኳኋን አሁን የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ሆነዋል) ጋራ እንዲታገዱ የሰንበት ት/ቤቱ ወጣቶች የደብሩን ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደር ይጠይቃሉ፡፡

በየጊዜው ይደረግ የነበረው የደብሩ አስተዳዳሪዎች መለዋወጥ ጥያቄው በወቅቱ ሰሚ አግኝቶ ርምጃ እንዳይወሰድ ዕንቅፋት ፈጥሮ እንደነበር የሚያመለክተው ሰነዱ፣ ጥቆማው ከቀረበላቸው የወቅቱ የደብሩ አስተዳዳሪዎች አንዱ የትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት ዋና አስኪያጅ ሊቀ ካህናት ብርሃኑ ገብረ ዐማኑኤል ሁኔታውን በመረዳት አሰግድን ጠርተው፣ ‹‹መማር ከፈለግህ እኔ ጋራ ቢሮዬ እየመጣህ አስተምርሃለሁ፤ ለጊዜው ግን ወደ ሰንበት ት/ቤት አትሂድ›› ብለው እንደመከሩት ገልጧል፡፡ በቢሯቸው ጠርተው ባነጋገሩበት ጊዜም ግለሰቡ የኑፋቄ ችግር እንዳለበት ቢረዱም ለሦስት ወራት ደብሩን አስተዳድረው በመቀየራቸው ርምጃ ሳይወሰድ መቅረቱን ዘግቧል፡፡

በዚህ ሁሉ መካከል ግን አሰግድ የተሐድሶ ኑፋቄ እንቅስቃሴ ይራመድባቸው በነበሩ የቤት ለቤት ጽዋ ማኅበራት እና በየአዳራሹ በሚካሄዱ ጉባኤያት እንደሚሳተፍ፣ ሰንበት ተማሪዎችንም እያግባባ እንደሚወስድ፣ ‹‹የክርስቶስ ሥጋ እና ደም ተቀበልንም አልተቀበልንም ለውጥ የለውም›› እያለ እንደሚቀስጥ፣ የካህናት አባቶችን ክብር እና ማዕርግ ንቆ ሲያበቃ ሌሎችም እንዲንቁት እንደሚቀሰቅስ መረጃው በመድረሱ የሰንበት ት/ቤቱ አመራር ይኸው በዐይን ምስክሮች ተገልጦ በጉባኤ እንዲመሰከርበት በማድረግ ያጋልጠዋል፡፡ ይህም በደብሩ አስተዳዳሪ አማካይነት ለሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ቀርቦ ከታየ በኋላ ጥቅምት 10 ቀን 1988 ዓ.ም ከሰበካ ጉባኤው ጽ/ቤት በተጻፈ ደብዳቤ አሰግድ ከሰንበት ት/ቤቱ ሊታገድ ችሏል፡፡

አሰግድ ግን ‹‹ያለአግባብ ከሰንበት ት/ቤቱ ታግጃለሁ፤ ዳኝነት ይታይልኝ›› ብሎ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ያመለክታል፡፡ ሀገረ ስብከቱ ጉዳዩን እንዲያጣሩ የላካቸው ሁለት ልኡካንም መጋቢት 23 ቀን 1988 ዓ.ም የደብሩ የስብከተ ወንጌል ኮሚቴ የወከላቸው አራት አባላት ባሉበት በአሰግድ ላይ ማስረጃ ባቀረቡት የሰንበት ት/ቤቱ ተወካዮች ጠያቂነት አሰግድ እየመለሰ በሰንበት ት/ቤቱ አዳራሽ በጥያቄ እና መልስ የታገዘ ውይይት ይደረጋል፡፡ በውይይቱ ላይ የሀገረ ስብከቱ ተወካዮች አሰግድን፣ ‹‹በአንደበትህ ከተናገርከው ቃል በቂ ማስረጃ ይዘንብሃል፤ ስለምን ጥፋትህን አታምንም?›› ይሉታል፡፡ በወቅቱ የደብሩ አስተዳዳሪ የነበሩት ቆሞስ አባ ሀብተ ሚካኤል ታደሰም፣ ‹‹አሰግድ ጥፋትህን እመንና ቀኖና እንሰጥሃለን፤ እባክህ ብትመለስ ይሻልሃል፤›› በማለት ይማፀኑታል፡፡ ልቡን እንደ እብነ አድማስ ያደነደነው አሰግድም የስብሰባው ቃለ ጉባኤ እና የደብሩ አስተዳደር የውሳኔ መነሻ ወደ ሀገረ ስብከቱ ሳይላክ፣ ‹‹እኔ ተሐድሶ አይደለሁም፤ እኔ ራሴን የማውቀው የቤተ ክርስቲያን ዶግማ እና ቀኖና ጠንቅቄ መኖሬን ነው፤ ነገር ግን እናንተ የለም ተሐድሶ ነህ ካላችሁኝ ክፉ እና ደጉን ከለየሁበትና ከአደግሁበት ሰንበት ት/ቤት መለየት አልፈልግምና ቀኖና ተሰጥቶኝ እንድመለስ በልዑል እግዚአብሔር ስም አመለክታለሁ፤›› ብሎ ለደብሩ ደብዳቤ ይጽፋል፡፡

የደብሩ አስተዳደር በዕለቱ የተደረገውን ውይይት እና የደብሩን አስተያየት በማካተት ለሀገረ ስብከቱ ይልካል፡፡ ሀገረ ስብከቱም ልኡካኑ ያቀረቡትን ሪፖርት፣ የደብሩን አስተያየት እና አሰግድ ለደብሩ የጻፈውን ደብዳቤ በማገናዘብ፣ ‹‹ከቀኖና አንዱ አመክሮ ስለሆነ ወደ ሰንበት ት/ቤቱ ከመመለሱ በፊት እንደማንኛውም አማኝ ለተወሰነ ጊዜ በስብከተ ወንጌል ትምህርት እየተማረ እንዲቆይ›› የሚል ውሳኔ በቁጥር 2/58/37/88 ቀን 11/11/88 ዓ.ም በወቅቱ ሥራ አስኪያጅ በነበሩት መልአከ ሰላም ቆሞስ አባ ገብረ ሚካኤል በየነ(አሁን ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ) ፊርማ ያስተላልፋል፡፡ ይህን ውሳኔ የደብሩ አስተዳደር በቁጥር 63/534/88 በቀን 29/11/88 ዓ.ም በጻፈው ደብዳቤ ለአሰግድ ያሳውቀዋል፡፡ የውሳኔውን ተገቢነት አስመልክቶ በዘገባው ላይ የሚከተለው አስተያየት ሰፍሯል፡- ‹‹እዚህ ላይ በጣም የሚያሳዝነው በቤተ ክርስቲያን ላይ ኑፋቄ ለሚዘራ፣ ወጣቶችን ከእናት ቤተ ክርስቲያን ለሚያስኮበልል፣ ቅዱሳንን እና የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ለሚንቅ፣ ቅዱስ ቁርባን አያድንም ብሎ ለሚያስተምር ሰው የንስሐ አባቱ ቀኖና እንዲሰጡት እና የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት እግር ሥር ተቀምጦ እንዲማር አባቶች እንዲመደቡለት አለመደረጉ ነው፤ የተሰጠው ቀኖና እና አመክሮ ለአንድ ወር ብቻ በማታው የስብከተ ወንጌል መርሐ ግብር እየተገኘ እንዲማር ነው፡፡››

ሆኖም አሰግድ ይህ ደብዳቤ ከደረሰው ቀን ጀምሮ በማታው የስብከተ ወንጌል መርሐ ግብር ይሁን በዕለተ ሰንበት ቅዳሴ ለአንድም ጊዜ ስንኳ ተምሮም አስቀድሶም እንደማያውቅ በሰንበት ት/ቤቱ የተመደቡት የክትትል ቡድን አባላት ማረጋገጣቸውን ዘገባው ያስረዳል፡፡ የተባለው አንድ ወር ሲደርስ ግን ከቀኗ አንዲት ሳያሳልፍ(በ29/12/88 ዓ.ም) ለደብሩ ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት ‹‹በሥራ ምክንያት አልፎ አልፎ በስብከተ ወንጌል መርሐ ግብር ላይ ባልገኝም በአብዛኛው ጊዜ ግን ተገኝቼ ተምሬያለሁና የተሰጠኝ የጊዜ ገደብ ስለተጠናቀቀ ወደ ሰንበት ት/ቤት ለመግባት ሙሉ ፈቃዳችሁን እንድትገልጹልኝ እጠይቃለሁ›› የሚል ደብዳቤ ያስገባል፤ ይህንኑም ለሰንበት ት/ቤቱ አባላት ያስወራል፡፡

እውነቱ ግን አሰግድ ቀኖናውን ተቀብዬ እንደታዘዝሁት ፈጽሜያለሁ ባለ ማግሥት ከጳጉሜ 1 - 5 ቀን 1988 ዓ.ም ለአምስት ተከታታይ ቀናት አሁን በፈረሰው የጎተራ ማሳለጫ ፊት ለፊት በሚገኘው የጎተራ ‹‹ሙሉ ወንጌል›› አማኞች የጸሎት ቤት በተካሄደው ጉባኤ ላይ ከመሰሎቹ ጋራ ተካፍሎ ሲወጣ መረጋገጡ ነው፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ 55 የሰንበት ት/ቤቱ አባላት አሰግድ የለየለት መናፍቅ በመሆኑ ከሰንበት ት/ቤቱ እንዲታገድ እንጂ ወደ ሰንበት ት/ቤቱ እንዳይመለስ የሚጠይቀውን አቤቱታቸውን በፊርማቸው በማረጋገጥ ለሰንበት ት/ቤቱ ሥራ አመራር ኮሚቴ ያቀርባሉ፡፡ ኮሚቴውም ይህንኑ ካጣራ በኋላ ሐሳቡን በማጽናት ለደብሩ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ያስታውቃል፡፡

በዚህ ውሳኔ ኀይል ከአንድ ዓመት በላይ ወደ ደብሩ ሳይገባ ዙሪያውን ሲያንዣብብ የቆየው አሰግድ የደብሩ አስተዳዳሪ፣ የሰበካ ጉባኤ አባላት እና የደብሩ ዋና ጸሐፊ መቀየራቸውን ሲያረጋግጥ በተለይ አዲስ የተመደበው የሰበካ ጉባኤ ጸሐፊ እንደሚረዳው ሲተማመን ለአዲሱ የደብሩ አስተዳዳሪ ‹‹ወደ ሰንበት ት/ቤቱ ልመለስ›› ሲል ጥያቄውን አቀረበ፤ የደብሩ ዋና ጸሐፊም የደብሩን አስተዳዳሪ ስላሳመነለት ‹‹አሰግድ ቀኖናውን ስለጨረሰ ወደ ሰንበት ት/ቤት ይመለስ›› የሚል ደብዳቤ ተጻፈለት፡፡ ይህን ውሳኔ የሰማው የሰንበት ት/ቤቱ አመራርም ‹‹በእውነት ከልቡ አምኖበት፣ እስከ ዛሬ የመናፍቃንን ስውር ዓላማ ማራመዱ ጸጽቶት ቀኖናውን ከፈጸመ ወደ ሰንበት ት/ቤቱ ከመመለሱ በፊት በስብከተ ወንጌል መርሐ ግብር እና ከዕለተ ሰንበት ቅዳሴ በኋላ እስከ ዛሬ ሲያካሂድ የነበረውን የመናፍቃን ድብቅ ሤራ በይፋ እንዲገልጥ›› የሚጠይቅ ደብዳቤ ለደብሩ ጽ/ቤት ይልካል፡፡

በወቅቱ የደብሩ አስተዳዳሪ የነበሩት መልአከ ይባቤ ተስፋ ሚካኤል መርሻ በአንድ የሰንበት ቅዳሴ ቀን አሰግድን አጠገባቸው አቁመው፣ ‹‹ምእመናን፣ ይህ የምትመለከቱት ልጅ አስቀድሞ የተሐድሶ አራማጅ ነበር፤ አሁን ግን ጥፋቱን አምኖ ቀኖናውን ተቀብሏል፤ ምእመናን እልል በሉ፤›› ሲሉ ተናገሩ፡፡ አሰግድም ጥፋቱን አምኖ ቀኖናውን ፈጽሞ መመለሱን እንዲናገር ዕድል ሲሰጠው፣ ‹‹ምእመናን፡- እኔ ተሐድሶ አይደለሁም፤ እኔ የቤተ ክርስቲያን ዶግማ እና ቀኖና ጠንቅቄ የምኖር ነኝ፤ ነገር ግን አንዳንዶች ስሜን ሲያጠፉ ነው፤›› ብሎ የአዞ እምባውን ለቀቀው፤ ምእመናንም የደብሩ አስተዳዳሪ በተናገሩት እና አሰግድ በሰጠው የአባይ ምስክርነት ግራ ቢጋቡም በማልቀሱ ግን አዘኑለት፡፡ የሰንበት ት/ቤቱ ሥራ አመራር አባላት ግን ‹‹የፈለገው ነገር ቢመጣ እኛን ያስወጡን እንጂ እርሱ ወደ ሰንበት ት/ቤት አይገባም›› ብለው በአቋማቸው ጸኑ፡፡

ሁኔታውን አስመልክቶ የዘገባው አጠናቃሪ፣ ‹‹የአሰግድ ዋና ዓላማ ለምእመናን የተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ አለመሆኑን ተናግሮ ስሙን ለማደስ እንዲሁም ለእርሱ እጅግ በጣም ጠቃሚ የሆነውን በደብሩ አስተዳዳሪ የተጻፈለትን ቀኖናውን ስለጨረሰ ወደ ሰንበት ት/ቤት ይመለስ የሚለውን ደብዳቤ መያዝ እንጂ ወደ ሰንበት ት/ቤቱ መመለስ አልነበረም፤›› ብለዋል፡፡ ዘጋቢው እንዳሉትም ውስጠ ተኩላው አሰግድ የልቡን ከፈጸመ በኋላ እስከ 1996 ዓ.ም ድረስ ለአምስት ዓመታት ወደ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን ደርሶ እንደማያውቅ ተገልጧል፡፡ ይሁንና ከዚያ በኋላ በተመሳሳይ የኑፋቄ ተግባሩ ከጃቴ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያንም እንደተባረረ የደብሩ አስተዳዳሪ የነበሩት ቆሞስ አባ ክፍለ ዮሐንስ ለመልአከ ይባቤ ተስፋ ሚካኤል መርሻ የነገሯቸውን ምስክርነት ዘገባው አስፍሯል፡፡ በዚህም መልአከ ይባቤ ተስፋ ሚካኤል ቀደም ሲል አሰግድ ቀኖናውን ፈጽሞ ወደ ሰንበት ት/ቤቱ እንደተመለሰ በቀናነት ለሰንበት ት/ቤቱ የጻፉትን ደብዳቤ ለመሻር ወስነው የሰንበት ት/ቤቱን ጥያቄ ሲጠባበቁ ከአስተዳዳሪነታቸው መነሣታቸውን ዘገባው በቁጭት ያስታውሳል፡፡

ከዚህ በኋላ ወደ ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በማታው ክፍለ ጊዜ ገብቶ በዲፕሎማ መርሐ ግብር መማር የጀመረው አሰግድ በክፍል ውስጥ በጥራዝ ነጠቅ የኑፋቄ ሐሳቦች መምህራኑን እና ደቀ መዛሙርቱን መነትረክ በመጀመሩ የግለሰቡን ዓላማ እና ተልእኮ የሚያጠና ሦስት ደቀ መዛሙርት የሚገኙበት ኮሚቴ ይቋቋማል፡፡ ይህን ተከትሎ አሰግድ ትምህርቱን ‹‹ሲያጠናቅቅ›› በኮሌጁ ዲፕሎማው ሳይሰጠው ተይዞበት ይቆያል፡፡ ዘገባው እንደሚለው፣ እንዴት እንደተፈጸመ በማይታወቅ አኳኋን አሰግድ የተያዘበትን ዲፕሎማ ከኮሌጁ ቆይቶ ተቀብሏል፡፡

በ2003 ዓ.ም በዲግሪው መርሐ ግብር ትምህርቱን በማታው ክፍለ ጊዜ ለመቀጠል ለኮሌጁ ያመለከተው አሰግድ፣ ከነበረበት ደብር የአስተዳዳሪው ወይም የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ፊርማ እና ማኅተም ያረፈበት፣ በአገልግሎት ላይ ስለመሆኑና ተመርቆ ሲወጣ ቤተ ክርስቲያኒቱን ተመልሶ እንደሚያገልግል ዋስትና የሚሰጥ ደብዳቤ እንዲያቀርብ ይጠየቃል፡፡ ይሁንና የደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ማንነቱን በውል የሚያውቅ በመሆኑ የትብብር ደብዳቤውን ስለማይጽፍለት፣ ቀሲስ አስቻለው መሐሪ የተባሉ ግብር አበሩን በመላክ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ አባል መሆኑን የሚገልጽ ደብዳቤ ለቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ እንዲጻፍለት ኅዳር አንድ ቀን 2003 ዓ.ም በጻፈው ደብዳቤ ይጠይቃል፡፡

ደብዳቤውን የተመለከተው የወቅቱ የደብሩ ዋና ጸሐፊ ዲያቆን ክብረ በዓል ዐሥራትም ከደብሩ አስተዳዳሪ እና ከሰንበት ት/ቤቱ አመራር ጋራ አሰግድን በተመለከተ በቂ መረጃ ጠይቆ ለማግኘት ቢችልም ይህን ጥረት ሳያደርግ ራሱን ከተጠያቂነት ነጻ ለማድረግ ብቻ፣ አሰግድ የአራት ዓመት(ከ2000 - 2003 ዓ.ም) የሰበካ ጉባኤ ውዝፍ(ብር 96) እንዲከፍል በማድረግ በ01/03/2003 ዓ.ም ያስገባውን የትብብር መጠየቂያ ደብዳቤ ዕለቱኑ ‹‹የንስሐ አባቱ ነኝ›› ላሉት ቀሲስ ተጠምቀ አስፍሓ አስተያየት እንዲሰጡበት ይመራላቸዋል፡፡ የንስሐ አባቱም ‹‹በእኔ ንስሐ አባትነት የተመዘገበ እና የሰበካ ጉባኤ ክፍያውንም ወቅቱን ጠብቆ እየከፈለ መሆኑን አረጋግጣለሁ›› በማለት በውክልና በተላከላቸው ደብዳቤ ላይ ይፈርማሉ፡፡ ዘገባው አሰግድ በርቀት(በውክልና በመላላክ) የንስሐ አባቱን እና የደብሩን ዋና ጸሐፊ በማግባባት ዓላማውን ለማሳካት የሞከረበትን መንገድ ሲያስረዳ፣ ‹‹ከአፅራረ ቤተ ክርስቲያን በሚጎርፍለት የገንዘብ ድጋፍ በመደለል›› ሊሆን እንደሚችል የደጀ ሰላምን ዜና በመጥቀስ ያስረዳል፡፡

በመጨረሻም በደብሩ ዋና ጸሐፊ በዲያቆን ክብረ በዓል ዐሥራት ፊርማ አሰግድ በደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን ‹‹የንስሐ አባት ይዞ፣ ተገቢውን የአባልነት ክፍያ አሟልቶ የሚገኝ መሆኑን›› በመግለጽ ለቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በቁጥር 200/88/03 በቀን 06/03/03 የትብብር ደብዳቤ ተጽፎ በቀሲስ አስቻለው መሐሪ በኩል ተላከለት፡፡ ይህ በቅሰጣ የተገኘ የተልእኮ ደብዳቤ ግን በኮሌጁ የበላይ ሐላፊ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም፡፡

ስለሆነም አሰግድ ዐይኑን በጨው አጥቦ ራሱ ደብሩ ድረስ በመሄድ አስተዳዳሪውን መልአከ ገነት በቀለ ዘውዴን የትብብር ደብዳቤ እንዲጽፉለት ይጠይቃቸዋል፡፡ እርሳቸውም ዋና ጸሐፊው ያለእርሳቸው ዕውቅና በራሱ ፊርማ የጻፈለትን ደብዳቤ ሲመልስ የጠየቀውን ደብዳቤ እንደሚጽፉለት በብልኀት ይነግሩታል፡፡ ብልጡ አሰግድም የደብዳቤውን ኦሪጅናሌ ሳይሆን ቅጅውን ያቀርባል፡፡ ብልጥ አላንድ ቀን አይበልጥምና አስተዳዳሪው መልአከ ገነት በቀለ ዘውዴም ‹‹ዋናውን የማታመጣ ከሆነ ከዛሬ ጀምሮ እንዳትመጣ›› ብለው አሳፍረው ሸኝተውታል፡፡ በቁጥር 417/666/03 በቀን 17/05/03 ዓ.ም ለቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በጻፉት ደብዳቤም ‹‹የአሰግድ ንስሐ አባት ነኝ›› ያሉት ካህን አስተያየታቸውን በመግለጽ በአድራሻ ቁጥር 200/88/03 በቀን 06/03/2003 ዓ.ም ለኮሌጁ ያስተላለፉት መልእክት መሻሩን አሳውቀዋል፡፡

አሰግድ ቀደም ሲል ወደ ምሥራቀ ፀሐይ ቀበና መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ሄዶ የነበረ ቢሆንም የአጥቢያው አባልም አገልጋይም ባለመሆኑ የትብብር ደብዳቤ ሊጻፍለት እንደማይችል በአስተዳዳሪው ተነግሮት መመለሱን መዘገባችን ይታወሳል - የኦርቶዶክሳውያኑ አባቶች እና ወጣቶች ቀናዒነት እና መተባበር ምሳሌነት ያለው ሲሆን የተሐድሶ ኑፋቄ አቀንቃኙ አሰግድ ሣህሉ ጥውየት(ክፋት እና ጥመት) እንዲሁም ኀፍረተ ቢስነት ደግሞ እግዚኦ የሚያሰኝ ነው!!

ማስታወሻ፡- አሰግድ በኮሌጁ ላይ ላቀረበው ክስ እና የኮሌጁ ጠበቃ በሰጡት ምላሽ ላይ በፍርድ ቤት የሚሰጠው ውሳኔ እስከ መጋቢት 27 ቀን 2003 ዓ.ም ቢዘገይም የአሰግድን ሃይማኖታዊ ሕጸጽ ተመልክቶ የመወሰን ክህነታዊ ሥልጣኑ እና አስተዳደራዊ ችሎታው ያላት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መሆኗን እናምናለን፡፡ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደግሞ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በደብዳቤው ላይ እንዳመለከተው የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ ተልእኮ ለማፋጠን እና ለማስፋፋት የተቋቋመ እንጂ የተሐድሶ ኑፋቄ አዝማቾች የቤተ ክርስቲያኒቱን ሀብት እየተጣቡ የሚደራጁበት መደብር አይደለም፡፡ ከዚህ አኳያ ሀገረ ስብከቱ እና መንፈሳዊ ኮሌጁ በአሠራር ቅንጅት እና በመረጃ ልውውጥ ያሳዩት ተቋማዊ መገናዘብ በቤተ ክርስቲያን ህልውና ላይ ግልጽ እና ቅርብ አደጋ የጋረጠውን የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መዋቅራዊ እንቅስቃሴ ከመሠረቱ ለማፍለስ እየተደረገ ላለው ጥረት መንፈሳዊ ብርታት የሚሰጥ ነው፡፡

የደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ እና የዉሉደ ያሬድ ሰንብት ት/ቤት አመራርም ከመላው አባሎቻችሁ ጋራ፣ አመቺ ጊዜ እየጠበቀ ስውር ተልእኮውን ለማስፈጸም ያልተቋረጠ ሙከራ ያደረገውን የኑፋቄ አቀንቃኝ በጥብዐተ ኅሊና በቀጣይነት በማጋለጥ በፈጸማችሁት አብነታዊ ተጋድሎ ኦርቶዶክሳዊ ግዴታችሁን በመወጣታችሁ ያለንን የላቀ አክብሮት እንገልጽላችኋለን፡፡ ዘገባችሁ ለታሪክ የሚቀመጥ ብቻ ሳይሆን በአንድ በኩል የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ አቀንቃኞች የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደራዊ መዋቅር የዓላማቸው ጥገኛ ለማድረግ ምን ያህል እንደሚማስኑ በሌላ በኩል ኦርቶዶክሳውያን ሳይተኙ ተግተው ሳያንቀላፉ ነቅተው ሊያተኩሩበት ስለሚገባው ቁምነገር(ክፍተት) ጥቁምታ የመስጠት ፋይዳ እንዳለው ተስፋ አለን፡፡ ሰልፋቸውን እንደ እናንተ፣ ከእናንተ ጋራ ለሚያደርጉት ሁሉ ተጋድሏቸው እንዲሰምር በዚህ አጋጣሚ ያለንን አጋርነት ልንገልጽላቸው እንወዳለን፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)