January 13, 2011

ዩኒቨርሲቲው ለመንበረ ፓትርያርኩ ማሳሰቢያ ምላሽ ሰጠ

  • ማሳሰቢያው ‹‹የጣልቃ ገብነት እና የዛቻ ቃል ከመሆን አልፎ ዐመፅን የሚያበረታታ እና የሚያባብስ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡››  (የአ.አ.ዩ ፕሬዚደንት ጽ/ቤት)
(ደጀ ሰላም፤ ጃኑዋሪ 13/2011 ጥር 5/2003 .)የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚደንት ጽ/ቤት የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ከልደተ ክርስቶስ የበዓል ዋዜማ አከባበር ጋራ በተያያዘ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ለዩኒቨርሲቲው አመራር ያቀረቡትን አቤቱታ የመስማት፣ ክትትል እና ማጣራት የማድረግ ሥልጣንም ሆነ ሐላፊነት እንዳለው ‹‹የሚያውቀው ነገር እንደሌለ››፣ ከዚህም አኳያ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ታኅሣሥ 28 ቀን 2003 ዓ.ም በቁጥር 1780/8513/2003 ‹‹የቤተ ክርስቲያን ልጆች ለመሥሪያ ቤታችን ስላቀረቡት አቤቱታ›› በሚል ለዩኒቨርሲቲው የጻፈው ደብዳቤ ‹‹በተቋሙ አሠራር ውስጥ ጣልቃ የመግባት ሙከራ ሆኖ እንዳገኘው›› በሰጠው ምላሽ አሳወቀ፡፡

ዩኒቨርሲቲው ‹‹ከቤተ ክህነት የሚጠብቀው በተለይ ምእመናንን በተመለከተ ሰብአዊነትን እና ዕርቅን የሚያግዝ እና የሚያበረታታ አካሄድ›› መሆኑን ገልጾ ‹‹ከዚህ ተፃራሪ በሆነ መንገድ የመሄዱ ሁኔታ እንዳይደገም በአጽንዖት›› እናሳስባለን ብሏል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት በፕሮፌሰር እንድርያስ እሸቴ ስም እና ፊርማ ወጥቶ ለትምህርት ሚኒስቴር፣ ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር እና ሌሎች አካላት በግልባጭ የተሰራጨው ይኸው ደብዳቤ፣ ተማሪዎቹ ለቤተ ክህነት ያቀረቡት ለዩኒቨርሲቲው አመራር ያቀረቡትን አቤቱታ ቅጅ ሆኖ ሳለ የመንበረ ፓትርያርኩ ጠቅላይ ጽ/ቤት ‹‹ተማሪዎች አቤቱታ አቀረቡልኝ ማለቱ ትክክል አይደለም›› ሲል ነቅፏል፡፡ አቤቱታ ቀርቦም ቢሆን እንኳን የመንበረ ፓትርያርክ ጽ/ቤት የተማሪዎችን አቤቱታ የመስማትና ከዚያም ተነሥቶ ክትትል እና ማጣራት የማድረግ ሥልጣንም ሆነ ሐላፊነት እንዳለው ‹‹በኛ በኩል የምናውቀው ነገር የለም›› ብሏል፡፡

የመንበረ ፓትርያርኩ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዩኒቨርስቲው ‹‹ባለው አስተዋይነት ተመልክቶ፣ ነገሩን ብሩህ በሆነ አስተሳሰብ አይቶ ተማሪዎች የልደት በዓልን እስከ አሁን ድረስ ሲያከብሩ በነበረበት ሁኔታ እንዲፈቅድላቸው፣ በዓላቸውን አክብረው ሲፈጽሙ ለሚቀጥለው ግን የቤተ ክህነቱ እና የዩኒቨርስቲው ወኪሎች በአንድነት በመሆን የመጨረሻ መፍትሔ እንዲሰጠው እንዲደረግ›› መግለጹ ‹‹ምንም ዐይነት የሕግ መሠረት የሌለው እና በተቋሙ አሠራር ውስጥ ጣልቃ የመግባት ሙከራ ሆኖ እንዳገኘው›› አመልክቷል፡፡

በተመሳሳይ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ‹‹ተማሪዎቹ የለመዱትን በዓል ከማክበር ቢከለከሉ በሚመጣው ችግር ዩኒቨርስቲው እንዳይጠየቅበት ቢያስብበት መልካም መሆኑን እንገልጻለን›› በማለት የሰጠውን ማሳሰቢያ፣ ‹‹የጣልቃ ገብነት እና የዛቻ ቃል ከመሆን አልፎ ዐመፅን የሚያበረታታ እና የሚያባብስ ሆኖ አግኝተነዋል›› በማለት ቤተ ክህነቱ ‹‹ሰብአዊነትን እና ዕርቅን የሚያግዝ እና የሚያበረታታ አካሄድ እንዲከተል›› እንጂ ‹‹ከዚህ ተፃራሪ በሆነ መንገድ የመሄዱ ሁኔታ እንዳይደገም በአጽንዖት እናሳስባለን›› በማለት አስጠንቅቋል፡፡

ተማሪዎቹ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሐላፊዎች ጋራ በችግሩ ዙሪያ በተነጋገሩበት ወቅት አባቶች ስለ እነርሱ ሆነው ዩኒቨርሲቲውን እንዲያነጋግሩላቸው በውይይታቸው ላይ መጠየቃቸውን፣ የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ደብዳቤ መግቢያም ተማሪዎቹ ለዩኒቨርስቲው ያቀረቡት አቤቱታ ግልባጭ ደርሶት ጉዳዩ በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ በኩል ተጣርቶ ሪፖርት እንደቀረበለት መገለጹ ይታወሳል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ጽ/ቤት ደብዳቤ ቤተ ክህነቱ በተለይ በምእመናን መካከል ‹‹ሰብአዊነትን እና ዕርቅን ስለ ማገዝ እና ማበረታታት›› እንዲሠራ ይመክር እንጂ ለሰብአዊነቱም ለዕርቁም የማይናቅ አስተዋፅኦ ባላቸው የመንፈሳዊነት እና ግብረ ገባዊነት በጎ ልምዶች እየታነፀ ያለው ተተኪው ወጣት ትውልድ ከቤተሰቦቹ ርቆም ቢሆን የሚከታተላቸውን አዎንታዊነታቸው የጎሉ ሃይማኖታዊ እና ማኅበራዊ መድረኮች መንፈጉ ግብዝነቱን እንደሚያሳይ ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡ በሌላ በኩል የመንበረ ፓትርያርኩ ጠቅላይ ጽ/ቤት በተማሪዎቹ ስለ ተነሣው አቤቱታ ብቻ ሳይሆን የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የውጭ ግንኙነት አጠቃላይ ይዞታ ቤተ ክርስቲያኒቱ ባላት ታሪካዊ ሚና አገራዊ ተሰሚነቷን በሚያስጠብቅ አኳኋን ከመምራት አኳያ ተቋማዊ ቀውስ እየገጠመው ለመሆኑ እንደ እንድ ማሳያ እየተጠቀሰ ይገኛል፡፡

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)