January 29, 2011

በሐዋሳ ገብርኤል ትናንት አለመግባባት ነበር

  • ፖሊስ ሁከተኞቹን ያሬድ አደመን እና ትዝታው ሳሙኤልን ጨምሮ 12 ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አዋለ
  • ምእመናን የክልሉ መንግሥት ሐላፊዎች ችግሩን ለመፍታት ባላቸው ሐቀኝነት ላይ የተፈጠረባቸው ጥርጣሬ እየተጠናከረ ነው
  • ‹‹ፓትርያኩ ውሸታም ናቸው፤ ጉባኤያችንን ከመስቀል አደባባይ ወደ ገብርኤል አመጡብን፤ የማንፈልጋቸውን መምህራን አስመደቡብን፤ የጳጳሱን ግቢ በር እናሽጋለን፤ መኪና ወደ ገዳሙ እንዳይገባ እናግዳለን፤ የተላኩብንን መምህራን እስክንመለስ እና የታሰሩብንን እስክናስፈታ ድረስ ጸልዩልን፡፡›› (ዛሬ ጠዋት የእነ ያሬድ አደመ መናጆዎች በደ/ም/ቅ/ገብርኤል ገዳም ያሰሙት ክስ እና ፉከራ)
(ደጀ ሰላም፤ ጃኑዋሪ 29/2011፤ ጥር 21/2003 ዓ.ም)፦ ንት ማምሻውን በሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ማሠሪያ ገቢ ለማሰባሰብ በተዘጋጀ ጉባኤ ላይ የሀገረ ስብከቱን ፈቃድ ጥሶ ዐውደ ምሕረቱን በኀይል ለመቆጣጠር በተደረገ ሙከራ ሳቢያ በተቀሰቀሰ ብጥብጥ ምእመናን በድንጋይ የተፈነከቱ ሲሆን ለብጥብጡ መንሥኤ ናቸው የተባሉት የሐዋሳ ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ አባ ናትናኤል፣ ያሬድ አደመን፣ ዲያቆን ትዝታው ሳሙኤልን ጨምሮ 12 ሁከት ፈጣሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡

በሀገረ ስብከቱ ጥያቄ ከመንበረ ፓትርያክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ለጉባኤው ተልከው በዐውደ ምሕረቱ የተቀመጡትን ሦስት መምህራን (መምህር ናዖድ ኢያሱ፣ መምህረ ሃይማኖት ኃይለ ጊዮርጊስ፣ በኵረ ትጉሃን ቀሲስ ደመላሽ) በመጋፋት ሕገ ወጦቹ ‹‹ያሬድ አደመ፣ በጋሻው ደሳለኝ ካላስተማሩ፤ ምርትነሽ ጥላሁን፣ ሀብታሙ ሽብሩ፣ ትዝታው ሳሙኤል ካልዘመሩ›› በሚል በጥቅም ያደራጇቸው ቲፎዞዎቻቸው ያደረጉትን ዐውደ ምሕረቱን በኀይል የመቆጣጠር ሙከራ ይቃወሙ ከነበሩት ምእመናን አምስቱ ሁከተኞቹ ይወረውሩት በነበረው ድንጋይ መፈንከታቸው ተገልጧል፡፡ የድንጋይ ውርጅብኙን ለማስቆም የገዳሙ ጥበቃ አባል በተኮሱት ጥይት ፖሊስ ወደ ገዳሙ ቅጽር በመግባት ሁኔታውን ካረጋጋ በኋላ 12ቱን ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር አውሏል፡፡

ችግሩ የገዳሙ አስተዳዳሪ አባ ኀይለ ጊዮርጊስ በዐውደ ምሕረቱ ከጅምሩ አንሥቶ በተቀመጡበት በዐይናቸው ፊት መከሠቱ ብዙዎችን አሳዝኗል፡፡ ሀገረ ስብከቱ ሦስቱን መምህራን የላከበትን ደብዳቤ በመያዝ ‹‹ሕግ ይከበር›› እያሉ አሰምተው በመናገር አቤቱታቸውን ለማቅረብ ወደ ዐውደ ምሕረቱ የወጡት ምእመናን በሚወርድባቸው የድንጋይ ውርጅብኝ እየተራወጡ ‹‹ስሙን እንዳልጠራው ከለከሉኝ›› ብሎ እንደሚዘምር በአጉራ ዘለሉ መርሐ ግብር መሪ የተጋበዘው ዲያቆን ትዝታው ሳሙኤል ‹‹ደስ ይበለን፤ እልል በሉ›› የሚል ቅስቀሳውን በመቀጠሉ ሞራል የለሽነቱን አሳይቷል፡፡

የሐዋሳ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ በስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ያልተፈቀደላቸውን ግለሰቦች በመጥራት በገቢ ማሰባሰቢያው ጉባኤ ላይ እንደሚገኙ በከተማው ውስጥ በሞንታርቦ የሚያደርገው ቅስቀሳ ተገቢ ያይደለና ግለሰቦቹም ያልተፈቀደላቸው መሆኑን በመግለጽ ሀገረ ስብከቱ ለአጥቢያው አስተዳደር፣ ለኮሚቴው ለራሱ እና  ለክልሉ መንግሥት በደብዳቤ አሳውቆ እንደነበር ተመልክቷል፡፡ በሀገረ ስብከቱ በቀጣይነት እያገረሸ ላለው ብጥብጥ ቀንደኛ ናቸው የተባሉ 14 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለው በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ሀገረ ስብከቱ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ በአድራሻ ለክልሉ መንግሥት በግልባጭ ደግሞ ለቅዱስ ሲኖዶስ እና ለፓትርያሪኩ ጽ/ቤት ጥያቄ ያቀረበ ቢሆንም የትኛውም አካል ለችግሩ እልባት የሚሰጥ ርምጃ መውሰድ እንዳልተቻለው እየታየ መሆኑን ነው ታዛቢዎች የሚናገሩት፡፡ ከዚህ አኳያ በተለይ ሁኔታውን በቅርበት እንደሚያውቁ እና እንደሚከታተሉ የሚታመንባቸው የክልሉ መንግሥት የፍትሕ እና ጸጥታ ቢሮ ሐላፊዎች እና ሌሎች የአስተዳደር አካላት ሐቀኝነት በተመለከተ ምእመናን ጥርጣሬ እያደረባቸው እና ይህም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መምጣቱ በሰሞኑ የግጭት አያያዝ ግልጽ እየሆነ መጥቷል፡፡

ዛሬ ከጠዋቱ ጀምሮ እንኳን ሕገ ወጦቹ በዚያው በደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ቅጽር ተሰብስበው፣ ‹‹እኛ እነ በጋሻውን የጠራነው በቅዱስነታቸው ፈቃድ ስለተሰጣቸው ነው፤ ፓትርያሪኩ ግን ውሸታም ናቸው፤ የማንፈልጋቸውን መምህራን አስመደቡብን፤ እነርሱን ወደ መጡበት እስክንመልስ ድረስ በጸሎት አስቡን፤. . .የጳጳሱን መግቢያ በር እናሽጋለን›› እያሉ በድምፅ ማጉያ ሲለፍፉ ሊያስታግሣቸው የሞከረ ወገን አለመኖሩ፣ በአንጻሩ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በወጣው መምሪያ መሠረት ለእውነት የቆመው ወገን በየጊዜው እየተሸማቀቀ የጥቃት ሰለባ መሆኑ እና በደኅንነት ስጋት ውስጥ መውደቁ ከዕለት ወደ ዕለት ችግሩ በሀገረ ስብከቱ በሐላፊነት ከተቀመጡት አባቶችም አቅም በላይ እየሆነ ለመምጣቱ ማሳያ ተደርጎ እየተወሰደ ነው፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)