January 5, 2011

“ከሰማይ የሚወርዱ ጥቃቅን የእሳት ፍንጣሪ መሰል ነገሮች” የሣር ክዳን ቤቶችን እና የተለያዩ ስፍራዎችን አቃጠሉ

እሳት ወይስ እሳተ እሳት

(ደጀ ሰላም፤ ጃኑዋሪ 5/2010 ታኅሣሥ 27/2003.)በፊቱ የቀረበለትን ሁሉ የሚያቃጥል - ከሰል፣ ዐመድ፣ ዕመት የሚያደርግ - የሚፋጅ፣ የሚልጥ፣ የሚለመጥጥ ነው ባሕርይው - የዚህ ዓለም እሳት፡፡ እሳቱን የሚያስቆጡት እና የሚያገኑት ነዳድያት እሳታውያንን ሲያገኝ ደግሞ ላንቃው፣ ልሳኑ፣ ወላፈኑ በዝቶ ነበልባለ እሳት(ነደ እሳት) ይሆናል፤‹‹እሳት በላዒ ለዐማፅያን›› እንዲሉ፡፡ በምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ግራዋ ወረዳ ልዩ ስሙ ታቱ ጀነታ እየተባለ በሚታወቀው ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ለተከታታይ ዘጠኝ ቀናት የታየው ግን ከዚህ የእሳት ባሕርይ በመጠኑ የተለየ ነበር፡፡

ከኅዳር 27 ቀን 2003 ዓ.ም እስከ ታኅሣሥ አምስት ቀን 2003 ዓ.ም ድረስ ልዩ ተልእኮ ያለው የሚመስል ‹‹ከሰማይ የሚወርዱ ጥቃቅን የእሳት ፍንጣሪ መሰል ነገሮች›› የተመረጡ የሣር ክዳን መኖርያ ቤቶችን እና ሰባት የተለያዩ ስፍራዎችን እያቃጠለ ዐመድ ሲያደርግ ሰንብቷል፡፡ በስፍራው ለእሳቱ መስፋፋት ምቹ የሆኑ ደረቅ ቁጥቋጦዎች እና የአየር ሁኔታ ያለ ቢሆንም በአንዱ ጎጆ/ስፍራ ላይ የሚከሠተው እሳት በሰው ኀይል ከመጥፋት ይልቅ የሚበላውን ከበላ በኋላ በራሱ ጊዜ እንደሚከስም ለደጀ ሰላም የደረሰው የዐይን እማኞች ቃል ያስረዳል፡፡ ለተከታታይ ዘጠኝ ቀናት በዚህ መልኩ በቀጠለው እንግዳ ክሥተት 25 የሣር ክዳን መኖርያ ቤቶች እና አንድ መስጊድ ሙሉ በሙሉ 14ቱ ደግሞ ግማሽ በግማሽ በመቃጠላቸው የተፈናቀሉት 125 ነዋሪዎቹ በጊዜያዊ መጠለያ እንደሚገኙ ተዘግቧል፡፡ ስምንት ኩንታል በቆሎ፣ ማሽላ፣ ሰሊጥ እና በርበሬ፣ የተለያዩ የቤት ቁሳቁሶች እንዲሁም ስድስት ሺሕ ጥሬ ብር በእሳቱ ተቃጥለው ከጥቅም ውጭ መሆናቸውን የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ፖሊስ ገልጧል፡፡ ይኸው የእሳት ፍንጣሪ በአንድ የዐሥር ዓመት ልጅ ራስ ላይ አርፎ ፀጉሩ ሳይቃጠል መታየቱንም የአካባቢው ነዋሪዎች አስረድተዋል፡፡  


ከወረዳ ከተማዋ 27 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው የገጠር ቀበሌ የታየውን እንግዳ ነገር አስመልክቶ ሞያዊ ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጠየቁ የሐረምያ ዩኒቨርስቲ ምሁራን በምንነቱ ላይ ሳይንሳዊ ገለጻ ለመስጠት አዳጋች በመሆኑ ‹‹ወደፊት ቀጣይነት ያለው ጥናት እና ምርምር ተደርጎ መንሥኤው እንደሚገለጽ›› መናገራቸው ተገልጧል፡፡ ሌሊቱን ከቤታቸው ይልቅ በውጭ በማደር እንደሚያሳልፉ የተናገሩት የአካባቢው ነዋሪዎች ግን ‹‹ይህ የአላህ ቁጣ ነው፤ መዐቱን እንዲያርቅልን ልመና እያደረግን ነው፤ በእኛ ዘመን ያጠፋነው ነገር ባይኖርም ቀደም ሲል ግን በአካባቢያችን የተፈጸመ ስሕተት አለ፤›› በማለት ከወረዳ ከተማዋ 18 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በሚገኘው ዶጉ መድኃኔዓለም አጥቢያ እንዲሁም በበደኖ ቀበሌዎች በ1983/84 ዓ.ም በታጣቂዎች በግፍ ተጨፍጭፈው በጅምላ የተቀበሩትን ክርስቲያኖች እና የተቃጠሉትን አብያተ ክርስቲያን ያስታውሳሉ፡፡ በስፍራው በሚገኝ አንድ ዋሻ ውስጥ 14 ታቦታት ተሰውረው የሚገኙ ሲሆን በዋሻው ላይ የሚያልፉ ከብቶችም እንደሚሞቱ የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡

በሌላ በኩል መስከረም 10 ቀን 2003 ዓ.ም በምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሂርና ወረዳ የጋራ ንጉሥ መድኃኔዓለም አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ንዋያተ ቅድሳት በአክራሪዎች ሙሉ በሙሉ መዘረፉን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ዘራፊዎቹ በቁጥጥር ሥር ውለው ሲጠየቁ ንዋያተ ቅድሳቱን እንዳቃጠሉት ተናግረዋል፡፡ ጉዳዩን በፈጣን ችሎት የተመለከተው ፍርድ ቤት በዘራፊዎቹ ላይ የ14 ዓመት እስራት የፈረደባቸው ቢሆንም በቅጣት ውሳኔው ላይ ይግባኝ ባልተጠየቀበት ሁኔታ ወደ የቀደመው የፈጣን ችሎቱ ውሳኔ በሰባት ዓመት ጽኑ እስራት እንደተቀነሰላቸው ተገልጧል፡፡ እሳተ እሳት የሰማይ እሳት መሆኑን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይናገራሉ፡፡ የግራዋው(ታቱ ጀነታ) የእሳት ዝናም መውረድ እና መቀጣጠል የጀመረው ኅዳር 27 ቀን አንስቶ እንደነበር ልብ ይሏል!!
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)