January 7, 2011

የተማሪዎቹ የልደት በዓል ዋዜማ መርሐ ግብር በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ ተካሄደ

  •  ‹‹ማንኛውንም ዓይነት ሃይማኖታዊ ሥርዐት በዩኒቨርስቲው ግቢዎች ውስጥ ማካሄድ እጅግ በጣም የተከለከለ መሆኑን በመገንዘብ ከዚህ ዐይነቱ ድርጊት እንዲቆጠቡ እናሳስባለን፡፡›› (የአ.አ.ዩ ፕሬዝዳንት)
  • ‹‹የወጣው መግለጫ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡››(ተማሪዎች)                                
  • ‹‹የቤተ ክርስቲያን ልጆች የለመዱትን በዓል ለማክበር ቢከለከሉ በሚመጣው ችግር  ዩኒቨርስቲው እንዳይጠየቅበት ቢያስብበት መልካም መሆኑን እንገልጻለን፡፡›› (ጠቅላይ ቤተ ክህነት)
(ደጀ ሰላም፤ ጃኑዋሪ 6/2010፤ ታኅሣሥ 28/2003 ዓ.ም)፦ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አስተዳደር የልደት በዓል በዩኒቨርስቲው ተማሪዎች በሚዘጋጁ ልዩ ልዩ መርሐ ግብሮች እንዳይከበር ባስተላለፈው እግድ ሳቢያ የዋዜማው መርሐ ግብር ማምሻውን በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አዳራሽ ተካሂዷል፡፡ 

ዛሬ ከቀትር በኋላ ከፕሬዝዳንቱ ጽ/ቤት በወጣው መግለጫ የዘንድሮውን የልደት በዓል ‹‹የበዓል ድባብ በሚኖረው መልኩ›› ልዩ የምግብ እና ሌሎች የካፊቴሪያ አገልግሎቶች እንደሚኖሩ ቢገልጽም ‹‹ማንኛውንም ዓይነት ሃይማኖታዊ ሥርዓት በዩኒቨርስቲው ግቢዎች ውስጥ ማካሄድ እጅግ በጣም የተከለከለ መሆኑን በማሳሰብ ተማሪዎች ከዚህ ዐይነቱ ድርጊት እንዲቆጠቡ›› አሳስቧል፡፡ አስተዳደሩ እግዱን ያስተላለፍኩት ‹‹በተቋሙ የሚታየው ያለመቻቻል አደጋ አሳስቦኝ ነው›› ማለቱ ተዘግቧል፡፡ 
የፕሬዝዳንቱ መግለጫ የወጣው ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ከትምህርት ሚኒስትሩ እና ከዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ጋራ በስልክ ከተነጋገሩ እና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የውሳኔውን አሳሳቢነት የሚገልጥ ጠንካራ የተባለ ደብዳቤ ከጻፉ በኋላ መሆኑ ታውቋል፡፡

ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ በደብዳቤያቸው የልደት እና የትንሣኤ በዓላትን ለረጅም ዓመታት ሲያከብሩ የነበሩ ወጣቶች እንደተለመደው በዚህ ዓመትም ለማክበር ቅድመ ዝግጅታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ መከልከላቸውን ገልጸው ለዩኒቨርስቲው የጻፉት ደብዳቤ በግልባጭ ደርሷቸው ጉዳዩ በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ በኩል ተጣርቶ ሪፖርቱ እንደቀረበላቸው አመልክተዋል፡፡ ለአከባበሩ ጥቂት ቀናት በቀሩበት እና የተማሪዎቹም ዝርዝር ታውቆ ዝግጅት እየተደረገ ባለበት ሁኔታ እንዲህ ያለ ውሳኔ በድንገት በመወሰን ወደ ርምጃ መገባቱ አግባብነት እንደሌለው ገልጸዋል፡፡ እግዱን ተከትሎ በአዲስ አበባ እና በሌሎች የክልል ዩኒቨርስቲዎች በሚፈጠረው ቁጣ ለሚከተለው ችግር የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሐላፊነቱን እንደሚወስድም አሳስበዋል፡፡ 

በመሆኑም ዝርዝር ጉዳዮችን ወደፊት የቤተ ክህነቱ እና የዩኒቨርስቲው ወኪሎች ተመካክረው የመጨረሻ መፍትሔ እስኪሰጡት ድረስ ተማሪዎቹ በተለመዱት መርሐ ግብሮች አማካይነት በዓሉን ለማክበር እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡
የብፁዕነታቸውን ደብዳቤ እና የፓትርያርኩን ጥያቄ መሠረት በማድረግ የትምህርት ሚኒስትሩ የተላለፈው እግድ እንዲነሣ ከዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ጋራ በመነጋገር ለሁሉም ካምፓሶች ትእዛዝ መተላለፉ ተነግሯል፡፡ 

ይሁንና በፕሬዝዳንቱ ፕሮፌሰር እድርያስ እሸቴ ፊርማ የወጣው መግለጫ ዩኒቨርስቲው ‹‹እንደወትሮው ሁሉ ከቤተሰቦቻቸው ርቀው ለሚገኙት ተማሪዎች አቅም በፈቀደ መጠን የበዓል ድባብ በሚኖረው መልኩ የምግብ እና ሌሎች የካፊቴሪያ አገልግሎቶች እንደሚኖሩ፣ በሌሊቱ ሥነ ሥርዓት ተማሪዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን በሚሄዱባቸው እና ከቤተ ክርስቲያን በሚመለሱበት ጊዜ ከመደበኛው ፕሮግራም ውጭ ሁሉም የዩኒቨርስቲው በሮች ክፍት እንደሚደረጉ፣ ከዚህ ባሻገር ግን ማንኛውንም ዓይነት ሃይማኖታዊ ሥርዓት በዩኒቨርስቲዎች ግቢዎች ውስጥ ማካሄድም ሆነ የሌሎችን የዩኒቨርስቲውን አባላት መብት ሊነኩ የሚችሉ ማንኛውንም ዓይነት ድርጊቶች መፈጸም እጅግ በጣም የተከለከለ መሆኑን በመገንዘብ ከዚህ ዐይነቱ ድርጊት እንዲቆጠቡ›› የሚገልጽ ነው፡፡ 

ይሁንና በየግቢዎቹ ውስጥ እና መግቢያ በሮች ላይ የተለጠፈው መግለጫ ጥያቄውን ለማድበስበስ ካልሆነ በቀር እግድ የተላለፈበት የሌሊቱ የማዕድ ዝግጅት እና መንፈሳዊ መርሐ ግብሩ እንደተፈቀደ የሚያሳይ ግልጽ ትእዛዝ የተሰጠበት እንዳልሆነ ተማሪዎቹ ይገልጻሉ፡፡ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ‹ብጥብጡን አስተባብራችኋል›› በሚል ትላንት እኩለ ሌሊት ላይ እንደተወሰዱ ሳይመለሱ የቀሩት 21 ወንድሞቻቸው ዕጣ ፈንታም እንደሚያሳስባቸው አልሸሸጉም፡፡

በሌላ በኩል ዘግይቶ የደረሰን ጥቆማ እንደሚያስረዳው በየዓመቱ የልደትን በዓል ምክንያት በማድረግ በአምስት ኪሎ ቴክኖ ፋርም ግቢ ጉባኤ ተማሪዎች በካምፓሱ አዳራሽ ይዘጋጅ የነበረው የዋዜማ መርሐ ግብር በክልከላው ሳቢያ በመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ መካሄዱ ታውቋል፡፡ ከምሽቱ 12፡30 ተጀምሮ እስከ መንፈቀ ሌሊት በቀጠለው በዚሁ መርሐ ግብር የዕለቱ ምስባክ ደርሷል፤ ቃለ ወንጌሉም ተነቧል፡፡ የዘንድሮ ተመራቂዎች ዝማሜ፣ የመንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤት መዘምራን መዝሙር፣ ታዋቂ አርቲስቶችም መንፈሳዊ ድራማ አቅርበዋል፡፡ በጉባኤው ላይ የታደሙ የቴክኖሎጂ ፋካልቲ መምህራን በምክር፣ ሊቀ መዘምራን ኪነ ጥበብ ወልደ ቂርቆስ እና ዘማሪ ምንዳዬ ብርሃኑ በመዝሙር ተማሪዎቹን አጽናንተዋል፡፡ በዓሉን የተመለከተ ትምህርት የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መምህር በሆኑት መጋቤ ሐዲስ እሸቱ ዓለማየሁ ተሰጥቷል፡፡ በተላከልን የምሽቱ መርሐ ግብር ዝርዝር ላይ እንደተመለከተው እንደወትሮው ሁሉ የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ቡራኬ እንደሚኖር የተገለጸ ቢሆንም እንዳልነበረ ታውቋል፡፡

መርሐ ግብሩ እኩለ ሌሊት ገደማ እንዳበቃ ከተማሪዎች ገሚሶቹ/እንደየመጡበት ግቢ/ ጸሎተ ቅዳሴውን ለመሳተፍ  ወደ መንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን፣ መንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም እና መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ልዩ ልዩ መዝሙራትን በማሰማት አምርተዋል፡፡ ከወጣው መግለጫ በተፃራሪ ከጸሎተ ቅዳሴው በኋላ ምንም ዓይነት የምግብ ዝግጅት እንደማይኖር የተረዱት የተቀሩት ተማሪዎች ደግሞ በማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማእከል ጽ/ቤት እና በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሰንበት ት/ቤት ለማዕዱ ዝግጅት ጉድ ጉድ ማለት መጀመራቸው ተዘግቧል፡፡

በዓሉ ሰማያውያን መላእክት እና ምድራውያን ሰዎች በጌታ መወለድ የምሥራች በአንድነት የዘመሩበት፣ ሰላም የተሰበከበት ሲሆን በተፈጠረው ነገር የተሰማንን  ቅሬታ እየገለጽን በያለንበት መልካም በዓል ያድርግልን ዘንድ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)