January 29, 2011

የጥምቀት በዓል በጎንደር፦ የደጀ ሰላም ሪፖርታዥ

  • በ17 ማኅበራት የተደራጁ ከ2000 በላይ ወጣቶች ተሳትፈውበታል
  • ካርኒቫል እና ጥምቀት ‹‹አልተገናኝቶ›› ሆኗል
  • ‹‹የጥንቷ ጎንደር ክብር ተመልሷል›› (ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ)
(ደጀ ሰላም፤ ጃኑዋሪ 29/2011፤ ጥር 21/2003 ዓ.ም)፦ የጥምቀት በዓል በደመቀ ሁኔታ በመላ ኢትዮጵያ የሚከበር ቢሆንም በዓይን ገብነታቸው እና በቱሪስት መስሕብነታቸው ከሚታወቁት መካከል ግን የአዲስ አበባውን የጃንሜዳን እና የጎንደሩን የሚስተካከል የለም። በተለይም በዘንድሮው የ2003 ዓ.ም (2011) የጎንደር ጥምቀት በዓል አከባበር ዋዜማ የከተማው አስተዳደር ከጥምቀት በዓል አከባበር ጋር “ካርኒቫል” የሚል ሐሳብ ማንሣቱ የመወያያ ነጥብ ሆኖ ሰንብቷል። ደጀ ሰላምም የአንባብያንን አስተያየት ስታስተናግድ ቆይታለች። አከባበሩ እንዴት አለፈ? ምን ተከሰተ? ምን ሆነ? ዝርዝሩ ቀጥሎ ይቀርባል።

(ደጀ ሰላም፤ ጃኑዋሪ 29/2011፤ ጥር 21/2003 ዓ.ም)፦ የጥምቀት በዓል በደመቀ ሁኔታ በመላ ኢትዮጵያ የሚከበር ቢሆንም በዓይን ገብነታቸው እና በቱሪስት መስሕብነታቸው ከሚታወቁት መካከል ግን የአዲስ አበባውን የጃንሜዳን እና የጎንደሩን የሚስተካከል የለም። በተለይም በዘንድሮው የ2003 ዓ.ም (2011) የጎንደር ጥምቀት በዓል አከባበር ዋዜማ የከተማው አስተዳደር ከጥምቀት በዓል አከባበር ጋር “ካርኒቫል” የሚል ሐሳብ ማንሣቱ የመወያያ ነጥብ ሆኖ ሰንብቷል። ደጀ ሰላምም የአንባብያንን አስተያየት ስታስተናግድ ቆይታለች። አከባበሩ እንዴት አለፈ? ምን ተከሰተ? ምን ሆነ? ዝርዝሩ ቀጥሎ ይቀርባል።

ከአውሮፓውያኑ የቤተ አሕዛብ ልማዶች ተወርሰው ከተስፋፉት ሕዝባዊ በዓላት አንዱ ካርኒቫል ነው፡፡ ካርኒቫል - ካርኔ(ሥጋ) እና ሌቫሬ(ማስወገድ፣ መራቅ) ከተሰኙ ጥምር ላቲናዊ ቃላት የተገኘ ሲሆን በቀጥተኛ ፍቺው ሥጋ ከመመገብ መከለከል ማለት ነው፡፡ ካርኒቫል በሮማውያኑ ዘመን የክረምቱ አፈና አልፎ የጸደዩ (የበልግ) ወራት ሲመጣ በዓል የሚደረግበት ወቅት የነበረ ቢሆንም በኋላ ዘመን በተለይም የሮም ካቶሊክ እምነት ተከታዮች በብዛት በሚገኙባቸው አገሮች ከጾመ ዐርባ መባቻ በፊት ባሉት ቀናት የቅበላ ዝግጅት የሚካሄድበት እንደሆነ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡

በመካከለኛው የታሪክ ዘመን በፖርቱጋል፣ ስፔይን እንዲሁም ኢጣልያዊ ሰፋሪዎች ወደ ደቡብ አሜሪካ አገሮች ከተስፋፋ በኋላ ከአፍሪካዊ እና ነባሪ አሜሪካውያን ልማዶች ጋር ተቆራኝቶ የዳበረው ካርኒቫል በመብል መጠጥ ፌሽታ፣ ቡረቃ፣ ጭፈራ የከተማ አደባባዮች የሚናጡበት፣ በሕብረ ቀለማት አብረቅራቂ ልብሶች አሸብርቀው እና በጌጣጌጥ አንቆጥቁጠው በምት እና የትንፋሽ ሙዚቃ መሣሪያዎች እየጮሁ እና እየደለቁ የሚፈነጩበት፣ በየጎዳናው የሚፏልሉበት የፈንጠዝያ ወቅት ነው፡፡ አፍሮ - ብራዚላዊ መሠረት ያለው የሳምባ ዳንስ ትርኢት በፉክክር መልክ የሚካሄድበት እና በየዓመቱ በርካታ ቱሪስቶች የሚጎርፉበት የሪዮ ዲ ጄኔሮ ቅድም ጾመ ዐርባ ካርኒቫል(pre-Lenten Carnival Celebration) እና እስከ ሦስት ሚልዮን በሚደርሱ ታዳሚዎች ከአንድ ቢልዮን ዶላር በላይ የቱሪዝም ገቢ በየዓመቱ የሚገኝበት የኒው ኦርሊየንሱ ትዕይንት(Mardi Gras) የካርኒቫል ዓለም አቀፋዊ መለዮዎች ናቸው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቃሉ ከቤት ውጪ በአደባባይ ለደስታ የሚደረጉ ሕዝባዊ ክዋኔዎችን (ስፖርታዊ ጨዋታዎች፣ የመዝናኛ ጉዞዎች፣ የክህሎት ውድድሮች. . . ) የሚያካትት ሆኗል፡፡

ከጥር 9 - 17 ቀን 2003 ዓ.ም በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚካሄድ ተገልጾ የተሟሟቀ ቅሰቀሳ የተደረገበት የ‹‹ጎንደር ካርኒቫል›› ግን እኒህን የበዓሉ መልኮች ‹አፋልጉኝ› የሚያሰኝ አልተገናኝቶ ነበር፤ በምትኩ የከተራ-ጥምቀት በዓል ከመቼውም ጊዜ በላይ በድምቀት የተከበረበት፣ ለክብረ በዓሉ ድምቀት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉት የከተማው ወጣቶች ‹‹ካርኒቫል›› የሚለውን ስያሜ በተመለከተ ለከተማው ከንቲባ ጽ/ቤት እና ለሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ተቃውሟቸውን ያቀረቡበት እንደነበር ተገልጧል፡፡ ቱሪስቶችን ጨምሮ ከመላው የአገሪቱ ክፍል እና ከዓለም ዙሪያ በጎረፉ ከ70‚000 ያላነሱ እድምተኞች በተጨናነቀችው የ17ው መቶ ክፍለ ዘመኗ የኢትዮጵያ መዲና ጎንደር የተከበረው የዘንድሮው የጥምቀት በዓል መንፈሳዊ ድባቡን እና ሃይማኖታዊ ሥርዐቱን ጠብቆ እንዲከናወን በ17 ማኅበራት የተደራጁ ከሁለት ሺሕ በላይ ወጣቶች እንዲሁም የአውራጅ እና ጫኝ ማኅበራት የድርሻቸውን ተወጥተዋል፡፡ የወጣቶቹ ተወካዮች ለከንቲባው ጽ/ቤቱ ላቀረቡት ተቃውሞ አዘል ጥያቄ ዝግጅቱ በተጠቀሰው ስያሜ ‹‹በሚዲያ እና በፖስተር ስለ ተዋወቀ›› አሁን መለወጥ እንደማይቻልና ወደፊት እንደሚታሰብበት የሚገልጽ ምላሽ እንደተሰጣቸው ተመልክቷል፡፡

ከሱስ እና ከሌሎች ጎጂ ተግባራት በመታቀብ ዝግጅት ያደረጉት የከተማው ወጣቶች የገቢ ማሰባሰቢያ ሥራዎችን በመሥራት፣ በአጥቢያ ሰንበት ት/ቤቶች እገዛ መዝሙራትን በማጥናት መሰናዷቸውን የጀመሩት ከበዓሉ አንድ ወር በፊት ነው፡፡ ጥር 12 ቀን 2001 ዓ.ም የቃና ዘገሊላ በዓል ሲከበር አጽራረ ቤተ ክርስቲያን በከተማው ቀስቅሰውት በነበረው ረብሻ በመነሣሣት የከተማይቱን መንገዶች በማጽዳት፣ ታቦታቱ በሚያልፉባቸው መንገዶች ባንዲራ በመስቀል፣ ምንጣፍ በማንጠፍ እና ቄጤማ በመጎዝጎዝ የጀመሩትን ተሳትፎ ዘንድሮም አጠናክረውት ታይተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ተውበው እንደ ጋሻ ጃግሬ ሰይፍ በያዙ ዘጠኝ ወጣቶች ግርማ ሞጎሱ ተጠብቆ የሚሽከረከረው ሠረገላ በጌታችን ሥዕለ ጥምቀት፣ በምስለ ፍቁር ወልዳ የእመቤታችን ሥዕል፣ በሥዕለ ቅዱስ ሚካኤል፣ ‹‹አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት›› የሚለው ኀይለ ቃል እንዲሁም የዐሥርቱ ሕግጋት እና ትእዛዛት ጽሑፍ በአራቱም አቅጣጫ እየተዟዟሩ የሚታዩበት ገጽታ ነበረው፡፡ በብር 20‚000 ወጪ የተሠራው ሠረገላ ከሥዕላቱ ጋራ አራት ማኅጠንት በየማእዝናቱ ታስረውበት ዕጣን በካህናቱ እየተጨመረ ከተማይቱ ታጥናበታለች፡፡ ሠረገላው ከፊቱ ቀይ ቲ-ሸርት በለበሱ የጫኝ እና አውራጅ ማኅበራት አባላት በሆኑ ወጣቶች የተመራ ሲሆን ከኋላው ደግሞ በሐመረ ኖኅ አምሳል የተሠራ ቅርጽ ያረፈበት እና ቅዱሳት ሥዕላት የተሣሉበት ተሽከርካሪ ነጭ ቲ-ሸርት እና ነጭ ሱሪ በለበሱት ወጣቶች ታጅቦ ይከተል ነበር፡፡ በወጣቶቹ ፊታውራሪነት የሰንበት ት/ቤቶች አባላት፣ ጥንግ ድርብ እና ካባ የለበሱ ካህናት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንደ ቅደም ተከተላቸው ተሰልፈው ታቦታቱን በዝማሬ በማክበር ወደ ባሕረ ጥምቀቱ በመውረድ ወደ መንበረ ክብራቸው እንዲመለሱ አድርገዋል፡፡ ታቦታቱ ወደ መንበረ ክብራቸው ሲመለሱ ዝቅ ብሎ ከሚበር አውሮፕላን ቄጠማ የተበተነ ቢሆንም ወደ ባሕረ ጥምቀቱ በሚወርዱበት የከተራ ዕለት ስለ ካርኒቫል የሚያትት ወረቀት መበተኑ ግራ አጋቢ ነበር፡፡

ጥር ዐሥር ቀን ጠዋት ከ2፡00 - 6፡30 በጎንደር ዩኒቨርስቲ የተዘጋጀ እና በጎንደር ከተማ አመሠራረት፣ በቅርሶቿ አጠባበቅ እና ወደፊት የከተማይቱን ታሪካዊ ገጽታ በጠበቀ አኳኋን የሚካሄዱ ግንባታዎች ስለሚመሩበት ፖሊሲ አስፈላጊነት የመከረ ዐውደ ጉባኤ ተካሂዷል፡፡ በዩኒቨርስቲው ሳይንስ ዐምባ አዳራሽ በተካሄደው ዐውደ ጉባኤ ላይ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ (አቶ አበባው አያሌው እና አርክቴክት ፋሲል ጊዮርጊስ)፣ ከጅማ ዩኒቨርስቲ (ኢንጂነር አስማማው) እንዲሁም ከክልሉ የቅርስ ጥገና ቢሮ በመጡ ባለሞያ የመወያያ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡ በዚሁ ዕለት ከሰዓት በኋላ ‹‹መጪው ዘመን እንዳይቀድመን እንነሣ›› በሚል መሪ ቃል በማኅበረ ቅዱሳን የጎንደር ማእከል የተዘጋጀ ባለ ዘጠኝ ትዕይንት ዐውደ ርእይ፣ በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት የተዘጋጀ የአራቱ ቤተ ጉባኤያት የመማር ማስተማር ሥርዐት የቀጥታ ክዋኔ (live performance/show) እንዲሁም ከተመሠረተች 300ኛ ዓመቷን የምታከብረው የመካነ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊ ቅርስ -ንዋያተ ቅድሳት (የብራና መጻሕፍት፣ መስቀሎች እና አልባሳት)፣ የጥንታዊ ትምህርት ሥርዐት ዐውደ ርእይ ተከፍቷል፡፡

ከሰሜን ጎንደር ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ጋራ በመሆን ዐውደ ርእዩን እና የቤተ ጉባኤያቱን የቀጥታ ክዋኔ ትዕይንት መርቀው የከፈቱት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ናቸው፡፡ ከፕሬዝዳንቱ ጋራ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር አቶ በረከት ስምዖን፣ የብሔራዊ ክልላዊ መንግሥቱ ፕሬዝዳንት አቶ አያሌው ጎበዜ፣ የሕፃናት ወጣቶች እና ሴቶች ሚኒስትር እና አቶ አዲሱ ለገሰ በመሆን ዐውደ ርእዩን ጎብኝተዋል፡፡

በሰባቱ ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን አምሳል በተሠሩ ሰባት ጎጆ ቤቶች (ቤተ ጉባኤያት) በተከናወነው የቀጥታ ክዋኔ ትዕይንት በንባብ ቤት - ከደብረ ብርሃን ሥላሴ፣ ከአደባባይ ኢየሱስ፣ ከደብረ ምጥማቅ ማርያም እና ከአቡን ቤት ቅዱስ ገብርኤል፤ በቅዳሴ እና ዝማሬ መዋስዕት - ከቀዳሜ አድባራት አበራ ጊዮርጊስ፣ ከአደባባይ ኢየሱስ፣ ከደብረ ምጥማቅ ማርያም፣ ደብረ ብርሃን ሥላሴ፣ ከደብረ ፀሐይ ቁስቋም ማርያም እና ከአቡን ቤት ቅዱስ ገብርኤል፤ በቅኔ እና ድጓ - ከደብረ ብርሃን ሥላሴ፣ ከደብረ ፀሐይ ቁስቋም ማርያም እና ከአቡን ቤት ቅዱስ ገብርኤል፣ በአቋቋም - ከደብረ ኀይል ወደብረ ጥበብ በኣታ ለማርያም፣ በመጽሐፍ ትርጓሜ በአራቱም ጉባኤያት - ከመካነ ነገሥት ግምጃ ቤት ማርያም፣ ከመንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም፣ ከዐቢየ እግዚእ ኪዳነ ምሕረት እና ከሐመረ ኖኅ ሠለስቱ ምእት አብያተ ክርስቲያን ከነደቀ መዝሙሮቻቸው የተመደቡ 28 መምህራን ጉባኤዎቻቸውን በማሔድ ተሳትፈዋል፡፡

የብራና መፋቅ፣ የብርዕ መቅረጽ፣ የቀለም መበጠብጥ፣ የቁም ጽሕፈት ሞያ እና የጭራ እና ሰሌን ሥራ ከደብረ ኀይል ወደብረ ጥበብ በኣታ ለማርያም እና ከደብረ ብርሃን ሥላሴ በመጡ የጥበበ እድ ባለሞያዎች እዚያው በተግባር እየተሠራ ታይቷል፡፡ የእንግዳን እግር ማጠብ የጉባኤ ቤት ሥርዐት መሆኑ የተገለጸላቸው ፕሬዝዳንቱ ሕጽበተ እግር ተፈጽሞላቸዋል፡፡ ከፈረስ ጭር እዚያው የተሠራ ጭራ እና ከሀ - ቀ የፊደል ተራ የተጻፈበት የብራና ቅጠል በሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ አማካይነት ተበርክቶላቸዋል፤ ቅኔም በመምህሩ ሊቀ ኅሩያን ነቅዐ ጥበብ እሸቴ ተሰጥቷል፡፡ ከመምህር እስከ ደቀ መዝሙር የተማሪው ቀለብ የሆነው ኮቸሮ ተዘጋጅቶ ፕሬዝዳንቱን ጨምሮ ለባለሥልጣናቱ በሰሌን እየቀረበ እንዲቀምሱት ተደርጓል፡፡ ‹‹ጳጳሳቱ እና ሊቃውንቱ ይህን እየተመገቡ ነው ለታላቅ ሐላፊነት የሚበቁት፤ እኛም የምንማረው ይህን እየበላን ነው፤›› ብለዋቸዋል ደቀ መዛሙርቱ፡፡

በመንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም የአራቱ ጉባኤያት መምህር ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ፣ ‹‹ጥንት ነገሥታቱ ታቦታቱን አጅብው ይወርዱ ነበር፤ እናንተም ታቦታቱን አክብራችሁ ያን ታሪክ በመድገማችሁ ደስ ብሎናል፤ እናከብራችኋለን፤›› በማለት በባሕረ ጥምቀቱ ካባ ለብሰው የተገኙትን ፕሬዝዳንቱን እና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን አመስግነዋል፡፡ ሀገረ ስብከቱ ወጣቶቹን ለማመስገን በመንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም ባዘጋጀው የምስጋና ምስክር ወረቀት አሰጣጥ መርሐ ግብር ላይም ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ፣ ‹‹የጥንቷ ጎንደር ክብር ተመልሷል፤ ከዚህ በኋላ ብሞት አይቆጨኝም›› በማለት ደስታቸውን መግለጻቸው ተዘግቧል፡፡

‹‹የ44ቱ ታቦታት መካን›› በሆነችው ጎንደር ከተማ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት ከተመዘገቡት ቅርሶች አንዱ በሆነው የፋሲል ግንብ ውስጥ ወደሚገኘው የፋሲል ባሕረ ጥምቀት (በተለምዶ የፋሲል መዋኛ - Fasiledes' Bath ከሚባለው የተለየ ነው፤) የሚወርዱት ታቦታት ስምንት ሲሆኑ እነርሱም፡- መንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም፣ ፊት ሚካኤል፣ አጣጣሚ ሚካኤል፣ እልፍኝ ጊዮርጊስ፣ አባ ጃሌ ተክለ ሃይማኖት፣ ቀሃ ኢየሱስ፣ ቅዱስ ፋሲለደስ እና መጥምቁ ዮሐንስ ናቸው፡፡

ፊት ሚካኤል እና አጣጣሚ ሚካኤል ሲቀሩ (ጥር 12 በቃና ዘገሊላ ስለሚመለሱ) ስድስቱ ታቦታት ወደ መንበረ ክብራቸው የሚመለሱት ጥር 11 ቀን ረፋድ ነው፡፡ የራሷ መውረጃ ያላት መካነ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን የበዓለ ጥምቀቱ ቅዳሴ እንደተፈጸመ ወደ ቀሃ ወንዝ ወርዳ የተከተረው ውኃ ተባርኮ ውኃው ለምእመኑ ከተረጨ በኋላ ወደ ድንኳኗ ተመልሳ ምእመኑ ማዕድ ቆርሶ ይመለሳል፤ ከሰዓት በኋላም ታቦቷ ወደ መንበረ ክብሯ ትመለሳለች፡፡ ከንጉሥ ፋሲል በፊት የአገሬው ትክል ሆነው ከተሠሩት አብያተ ክርስቲያን አንዱ የሆነው የቀዳሜ አድባራት አበራ ቅዱስ ጊዮርጊስ ታቦት ለጥምቀቱ በዓል መታሰቢያ ጥር 17 ቀን ወጥቶ ጥር 18 ቀን ይመለሳል፤ የአዘዞዋ ሎዛ ማርያም ጥር 20 ወርዳ ጥር 21 ትመለሳለች፤ እስከ 2000 ዓ.ም ጥር 11 ቀን ወርዳ ዕለቱኑ የምትመለሰው የመካነ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ከኢትዮጵያ ዕሥራ ምእት በኋላ ከቅዱስ ዑራኤል ጋራ ጥር 21 ቀን ወርዳ ጥር 22 ቀን ትገባለች፡፡ በደቡብ ጎንደር የሰማዕቱ መርቆሬዎስ ታቦት ጥር 24 ቀን ወርዶ ጥር 25 ቀን ወደ መንበረ ክብሩ ይመለሳል፡፡ በዕለቱ በተለይ ቅዱሳን ሰማዕታትን በማዘከር የፈረስ ጉግስ ጨዋታ በደማቅ ሁኔታ የማካሄድ ልምድ እንዳለ ይታወቃል፡፡ በዚህም በጎንደር የበዓለ ጥምቀት መዋዕል ፍጻሜ ይሆናል፡፡

ስለ ጥምቀት በዓል በየአብያተ ክርስቲያኑ የተለያየ ትውፊት አለ፡፡ በአንዳንድ አገሮች ምእመናኑ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ወይም በውጭ እንደ አየሩ ሁኔታ ተሰብስበው ካህኑ የጌታን ጥምቀት የሚያመለክተውን ጥቅስ ከወንጌል አንብቦ በምእመናኑ ላይ በመርጨት በዓሉ ይታሰባል፡፡ ሌሎች ደግሞ ወደ ወንዝ (ባሕር) ወርደው ሻማ አብርተው ሊሰጥም በማይችል ተንሳፋፊ ዕቃ ላይ በመትከል በባሕሩ ላይ ይለቁታል፡፡ ሻማው ቀልጦ እስከሚያልቅ ድረስ በንፋስ ኀይል እየተንሳፈፈ ይጓዛል፡፡ ይህም ብርሃነ ዓለም ክርስቶስ ወደ ጨለማው ዓለም መጥቶ በሞት ጥላ ውስጥ ለነበሩት የሰው ልጆች ብርሃነ ትምህርቱን እና የማይታየው አምላክ በሥጋ መገለጡን ያስረዳል፡፡ ፊትም በሕገ ልቡና በኋላም ሕገ ኦሪትን ተቀብላ ስለ ድኅነተ ዓለም የተነገረውን ትንቢት የተቆጠረውን ሱባኤ ስትጠባበቅ የኖረችው አገራችን ኢትዮጵያ ዜና ጥምቀትን የሰማችው በመንፈሰ እግዚአብሔር መሪነት እና አስፈጻሚነት የራስዋ ሐዋርያ በጥምቀት ከመንፈስ ቅዱስ የመወለድን ዕድል በማግኘቱ ነው (የሐዋ ሥ. 8፡ 29)፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለመታሰቢያ ያህል በጸሎት ብቻ በማሰብ ሳይሆን በሥዕላዊ መልክ ከምታከብራቸው በዓላት አንዱ የሆነው በዓለ ጥምቀት ትውፊታዊ ሥነ ሥርዐት ዓለምን ወደ አድናቆት ስቦት ይገኛል፡፡ በአሁኑ ጊዜም የሃይማኖት በዓልነቱን ሳይለቅ ጥንታዊ ታሪኩንም ሳይለውጥ የቱሪስቶችን አትኩሮት በብዛት ሲማርክ ይገኛል፡፡ በዓለ ጥምቀትን በሜዳ እና በውኃ አካላት ዳር ማክበር የተጀመረው በዐፄ ገብረ መስቀል ዘመነ መንግሥት (530 - 544 ዓ.ም) እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይኸውም ከማሕሌታዊው ቅዱስ ያሬድ ዜማ መስፋፋት ጋራ ተያይዞ ታቦታቱ በየዓመቱ ጥር 11 ቀን ጠዋት ወደ ወንዝ ወርደው ማታ ወደ መንበረ ክብራቸው እንዲመለሱ ይደረግ ነበር፡፡ ጻድቁ እና ጠቢቡ ንጉሥ ላሊበላ (1140 - 1180 ዓ.ም) ሁሉም አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ለየብቻቸው በሚቀርባቸው ቦታ በተናጠል ሲፈጽሙት የነበረውን ልምድ አስቀርቷል፡፡ በምትኩም በአንድ አካባቢ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያን በአንድነት ተሰብስበው በአንድ ባሕረ ጥምቀት እንዲያከብሩ ትእዛዝ አስተላልፏል፡፡ ይህም ተግባራዊ በመሆኑ የበዓሉ አከባበር ቅንጅት እና ድምቀት እንዲኖረው ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡

ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ (1424 - 1460 ዓ.ም) ታቦታቱ ወደ ወንዝ ወርደው ዕለቱን እንዳይመለሱ፣ በምትኩ በጥምቀት ዋዜማ ጥር 10 ቀን ከሰዓት በኋላ ወደ ባሕረ ጥምቀት ወርደው እንዲያድሩ፣ አገሩን በኪደተ እግር ይባርኩም ዘንድ በወረዱበት መንገድ እንዳይመለሱ በዐዋጅ አዝዘዋል፡፡ ይህን ታሪክ በመከተል ዐፄ ናዖድ (1485- 1500 ዓ.ም) ማንኛውም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመን ታቦተ ሕጉ ወደ ባሕረ ጥምቀት በሚወርድበት እና ወደ ቤተ መቅደሱ በሚመለስበት ጊዜ አጅቦ ወርዶ፣ አጅቦ መመለስ እንዳለበት በዐዋጅ አስወስነው ነበር፡፡ ሕዝቡም ታቦታተ ሕጉን በሆታ እና በእልልታ ከቤተ መቅደስ ከአወጣ በኋላ በባሕረ ጥምቀቱ ዙሪያ ማደር ጀመረ፤ ሊቃውንቱም ለበዓሉ የሚስማማውን ቃለ እግዚአብሔር ሲያደርሱ ያድሩ ጀመር፤ በመንፈቀ ሌሊትም ሥርዐተ ቅዳሴው ተጀምሮ ከሌሊቱ በዘጠኝ ሰዓት ሠርሆተ ሕዝብ ይሆናል፡፡

በአጠቃላይ የጥምቀት በዓል ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለጥንታዊነቷ እና ለከፍተኛ እምነቷ ትልቅ መታወቂያ ምልክት ሆኖ ኖሯል፤ ይኖራልም፡፡ የጥምቀትን በዓል ምክንያት በማድረግ ከጥር 9 - 17 በቆየው የጎንደሩ ዝግጅት በመስቀል አደባባይ፣ አውቶፓርኮ፣ ፒያሳ እና ጃን ተከል በተባሉ ቦታዎች በተተከሉ ነጫጭ ድንኳኖች እና በተሠሩ መድረኮች ይታይ ከነበረው ባህላዊ ውዝዋዜ፣ ከሰፊው የመጠጥ እና ምግብ መስተንግዶ ውጭ ውሎው በመንፈሳዊ ሥነ ሥርዐት የተመላ እንደነበር ከስፍራው የደረሰን ዘገባ ያስረዳል፡፡

የከተማ አገልግሎት ጽ/ቤት ከክብረ በዓሉ ቀደም ብሎ ከፍተኛ በጀት መድቦ (የአብነት መምህራኑን አበል ጨምሮ 3.5 ሚልዮን ብር ያህል) የከተማይቱን መንገዶች እና የኤሌክትሪክ መሥመሮች በማስተካከል እና በማስዋብ አዘጋጅቷል፡፡ የባህል እና ቱሪዝም ጽ/ቤት ታቦታቱ ከየመንበረ ክብራቸው ወጥተው የሚያርፉበትን በንጉሥ ፋሲል ባሕረ ጥምቀት የሚገኘውን የቅዱስ ፋሲለደስ ቤተ መቅደስ (ቀደም ሲል በድንኳን ነበር የሚያድሩት) እንዲሁም የባሕረ ጥምቀቱን መመላለሻ በሮች እና በዙሪያው የሚገኘውን ባለአራት ዕርከን መቀመጫ ከስድስት ሚልዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ አድሷል፡፡ በመንግሥት የአምስት ዓመቱ የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በዓለም አቀፍ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ተወዳዳሪ ሆኖ በመዝለቅ በአፍሪካ ተመራጭ መዳረሻ ሆኖ መገኘት፣ ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆኑ የኢኮኖሚ ጠቀሜታዎችን በማሳደግ የአገሪቱን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እና የአገሪቱን መልካም ገጽታ መገንባት የቱሪዝሙ ዘርፍ ፖሊሲ ሆኖ ተቀምጧል፡፡

ይሁንና ይህ የሚፈጸመው ‹‹ሐላፊነት በተሞላበት አኳኋን የሴክተሩን ልማት የሚያስቀጥል፣ የሕዝቡን ባህል እና የአኗኗር ዘይቤ እንዲሁም የተፈጥሮ አካባቢያዊ ሁነቶች ሳያናጋ ማደግ የሚችል የቱሪዝም ዘርፍ በመገንባት›› እንደ ሆነ በሰነዱ ውስጥ ተገልጧል፡፡ በዚህ መሠረት የከተማው አስተዳደር ያደረገው ቅድመ ዝግጅት የሚያስመሰግነው ቢሆንም ‹‹ካርኒቫል በጎንደር›› በሚል ስያሜ እስከ አሜሪካ ከዘለቀው የፖስተር ቅስቀሳ ጀምሮ ‹‹እንኳን ወደ 'ጎንደር ካርኒቫል' በሰላም መጣችሁ›› እስከሚለው አቀባበል ድረስ ከኢትዮጵያውያን የጥምቀት በዓል አከባበር ጋራ የታሪክም ይሁን የባህል ዝምድና በሌለው የባዕድ ስያሜ መጠቀሙ ከማስተዋወቂያ ፋይዳው ባሻገር ባለው የጎን ጠንቁ እና የኋልዮሽ ውጤቱ ሊጤነው እንደሚገባ ታዛቢዎች ይገልጻሉ - ለአካባቢ ጥበቃ ጠንቅ ነው የሚባለው ‹‹የገና ዛፍ›› ትውፊት ከልደተ ክርስቶስ በዓል አከባበር ጋራ ግንኙነት እንደሌለው ሁሉ!!

7 comments:

Ze-Christos said...

Deje Selam?
Your News is appreciative herewith yet you should have kept back from stepping to until enough comments have been handed over to the “Free Media” article by the fact of its burning and upto the pole agenda.

Anonymous said...

Thanks to God! I wish I could have been there. Betam des yilal.

Would you please tell us what is happening in Awassa St. Gebriel Church? I heard from friends living in Awassa about yesterdays' situation in the church, there was big broblem (quarel) in the compound of the church. Really I am sorry for everything what is going on in Ethiopia. It seems that there is no Government in the country. I heard that Begashaw, Mirtinesh, and other their colleagues were in the church serving as usual. If they are applogized for what they did so far and 'ewunetegna nisiha gebitew kohone', that will be nice. But I didn't hear about this people's situation. My question is are they applogized and allowed to serve the church as usual? What is their status at this time? What was the cause for yesterday's problem in the program? The Government Identified the causes of the problem in Awassa before few months.So, What kind of action took the Governmernt?

Would you please tell us about these things and the current situation in Awassa (if you have information)?

Melaku
From Berlin

Anonymous said...

የዛሬ ዓመት እንደዋዛ፣ ተለኩሶ የነደደው
ቋያ ሆኖ ለዘንድሮ፣ አዲስ አባ’ን አነደደው፡፡
ባተሌው ሠራዊት ጎረምሳ ዘስሙ
ጎንበስ ቀና እያለ ደከመ ለስሙ፡፡
ጠቅልሎ ሲሸከም፣ ተርትሮ ሲያነጥፍ
በሽር ጉድ ብዛት ላቡ ሲንጠፈጠፍ
ግራና ቀኝ ከቦ፣ ቀርቦ ላስተዋለ
ጉልበትና ትዕቢት በአንድ ተፈተለ
ተቀድሞ ፊተኛ ኋላ ተከተለ፡፡

(ለስሙ የሚለው የእግዚአብሔርን ስም በአገልግሎትና በምስጋና አከበረ ለማለት ነው)
እግዚአብሔር አገልግሎታችሁን ይባርክ፡፡ አሜን
ተስፋዬ

መብሩድ said...

ጥቀ ዘያስተፈስህ ዜና! እሴብሐኪ ደጀ ሰላም

በረተረዳ ነገር
ነአምር ጥምቀተ ባህር
ዝንቱ ውእቱ ክብራ ለሀገር
ምንትኑ ለጎንደር?
ካርኒ ቫል ብሎ ነገር

Anonymous said...

thankyou dejeselam.FIKIRE SELAM wordo TINSIE ETHIOPIAN YASAYEN.2004 TIMKET NO MORE TW0 SINODOS. wolde gebreal.

Zekios said...

The blessed youths of Gondar may God be with you.Mind you that much remains to be done.And above all you have to show your chiristianity always and be ready for holy communion.That is when saints in heaven will be delighted.
God be with us.
DINGIL ATELEYEN.

Anonymous said...

be good do good leave the rest to God

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)