January 27, 2011

“ነጻው ሚዲያ” ስለ ቤተ ክርስቲያን ባለው አመለካከት “ነጻ” መሆኑን ያሳይ

  • ኦርቶዶክሳዊ ፀሐፊዎች እየመሰሉ፣ በመግቢያቸው “ወያኔ ይውደም” የሚል ማባበያ ቃል እየጨመሩ ነገር ግን “ቤተ ክርስቲያን ትውደም” የሚለውን ግብ ያነገቡ ጽሑፎች በየዕለቱ ማንበብ ይዘናል።
(ደጀ ሰላም፤ ጃኑዋሪ 26/2011፤ ጥር 18/2003 ዓ.ም)፦በተለምዶ “ነጻ ሚዲያ” እየተባለ የሚጠራው ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ የሆነውና በተለያዩ ግለሰቦች እና ቡድኖች የሚንቀሳቀሰው ሚዲያ ነው። “ሚዲያ” ያልነውን ራሱን ከለተመለከትነው ደግሞ የሕትመት ውጤቶችን ማለትም ጋዜጣና መጽሔቶችን፣ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያውን ማለትም ሬዲዮና ቴሌቪዥኑን፣ እንዲሁም ድረ ገጾችን ሁሉ ያጠቃልላል። እነዚህን ሁሉ ጠቅልሎ በማጥናት ስለ ቤተ ክርስቲያናችን የሚያስተላልፉትን ለመመልከት ብዙ ጊዜ እና የሰው ኃይል እንዲሁም ገንዘብ የሚጠይቅ ቢሆንም በመጠነኛ የወፍ በረር (Birds Eye-view) ቅኝት ያገኘነውን ሐሳብ መነሻ አድርገን ትዝብታችንን ለመጠቆም እንደማይከለክለን እንረዳለን።

ድረ ገጾችን በተመለከተ ያለውን ስብጥር ቀረብ ብሎ ለተመለከተ ሰው አብዛኞቹ ኢትዮጰያውያውን ድረ ገጾች ዋና አትኩሮታቸው ፖለቲካ ነው። ይህም እጅግ ጽንፈኝት ያለበት፣ የአንድ ወገን ደጋፊነት ብቻ የሚንጸባረቅበት ነው ማለት ይቻላል። በአንድ ወገን በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት አምርሮ የሚጠላ ሚዲያ (ከ www.ethiopianreview.com/ እስከ www.quatero.net/)፣ በሌላ በኩል ደግም መንግሥትን እንደ ነፍሱ የሚወድ (ከ www.ethiopiafirst.com/ እስከ www.aigaforum.com/) ሚዲያ ነው። ዜናዎቹና ሐተታዎቹ፣ ርዕሰ አንቀጾቹ እና ትንታኔዎቹም በዚሁ መልክ የተቀረፁ ናቸው። ወይ ደጋፊ ሆነው የሚያጸድቁ አሊያም ደግሞ ነቃፊ ሆነው የሚያሰየጥኑ (ሰይጣን የሚያደርጉ)። በሁለቱ መካከል ያለ ኢትዮጵያዊ ሚዲያ እና ድረ ገጽ ማግኘት እጅግ አስቸጋሪ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ እንዳለው “ከእኛ ወገን ነህ ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን?” የሚል ጥያቄ ያለበት ጊዜ ነው።

ዋናው ትኩረታችን ስለነዚህ ድረ ገጾች ፖለቲካዊ አቋም መገምገም ባይሆንም “በፖለቲካቸው ውስጥ” ቤተ ክርስቲያኒቱ የምትነሣበት መንገድ ከዕለት ወደ ዕለት አሳሳቢ ወደሆነ ደረጃ እያዘገመ በመሆኑ የራሳችንን ሐሳብ ማካፈል ግድ ስላለን ነው።  በነዚህ ሁለት ወገን ጽንፈኛ የአገራችን ድረ ገጾች ግምገማ ቤተ ክርስቲያን ከአንዱ ወገ ትፈረጃለች። አባቶችም ጭምር። በሀገር ቤት ያለው ቤተ ክህነት እስከ ግሳንግሱ “የወያኔ ነው”፤ በውጪ ያሉት አብያተ ክርስቲያናት እና አባቶች ደግሞ ከነግሳንግሳቸው “የተቃዋሚዎች ናቸው” የሚል ድምዳሜ ላይ የተደረሰ ይመስላል።

ይህ ስሌት ፖለቲካዊ ስሌት ስለሆነ ተቃውሞውም ፖለቲካዊ ሆኖ ቆይቷል። ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለይም “የወያኔ” የተባለውን ቤተ ክህነት “ለማጥቃት እና ወያኔን ለመጉዳት” የሚፈልገው ከአገር ውጪ ያለው ሚዲያ ከፖለቲካዊ ሐተታ በዘለለ ኦርቶዶክሳዊቱን የተዋሕዶ እምነት በይፋ ከሚቀናቀኑ ወገኖች እና ፀሐፊዎች ጋር በመቆም ላይ ይገኛል።

ሚዲያዎቹ የቤተ ክርስቲያን ተቃዋሚዎች መጠቀሚያ የሆኑት አብዛኞቹ በሥልጣን ላይ ያለውን ፓርቲ ለመቀናቀን ካላቸው ፍላጎት ነው። የሚዲያው ባለቤቶች ስለ ነገረ ሃይማኖት ያላቸው ዕውቀት ውሱንነት ለእምነታቸው በጎ ያደረጉ እየመሰላቸው ቤተ ክርስቲያናቸውን እንዲጎዱ እያደረጋቸው ነው። ኦርቶዶክሳዊ ፀሐፊዎች እየመሰሉ፣ በመግቢያቸው “ወያኔ ይውደም” የሚል ማባበያ ቃል እየጨመሩ ነገር ግን “ቤተ ክርስቲያን ትውደም” የሚለውን ግብ ያነገቡ ጽሑፎች በየዕለቱ ማንበብ ይዘናል። በፕሮቴስታንታዊ ቅኝት የሚዘፍኑ የተሐድሶ ቡድኖች ወይም ለኢትዮጵያ ድህነት ታሪካዊ ምክንያት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ናት የሚለው ታሪካዊ ማስረጃ የጎደለው ጥራዝ ነጠቅ አመለካከት አራማፀረ ተዋሕዶ ፀሐፊዎች ሚዲያዎቹን እንደፈለጉት በመጠቀም ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ መንግሥት በእምነት ውስጥ ጣልቃ ገብቷል ብለው የሚከሱ ወገኖች ያውም ቤተ ክርስቲያኒቱ ስለ ትምህርተ ሃይማኖቷ መልስ እንድትሰጥ ዕድል ባልተሰጣት ሁኔታ ለተቃዋሚዎቿ ብቻ በር በመክፈት የአጽራረ ተዋሕዶ ዒላማ ማድረግ በየትኛውም መመዘኛ ቢሆን ሚዛናዊ አይሆንም። መንግሥትን በሚከሱበት ጉዳይ እነርሱም ተጠያቂዎች ሆነዋል ማለት ነው። ልዩነቱ መንግሥት አዲስ አበባ እነርሱ በአውሮፓ፣ አሜሪካ እና አውስትራሊያ መቀመጣቸው ነው።

ከዚህ በፊት በአንድ መልእክታችን እንዳልነው ተራሮችን አንቀጠቀጥኩ የሚለው የኢሕአዴግ ቡድንም ሆነ “ያ ትውልድ” የሚባለው የኢሕአፓ፣ የመኢሶን፣ የኢሰፓ ወይም በየብሔሩ የተደራጀው ፓርቲ በሙሉ ቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ የጫነውን እጁን ማንሣት አለበት። ሚዲያዎችም ቤተ ክርስቲያኒቱን መዋጋታቸውን ማቆም አለባቸው። አቡነ ጳውሎስን ለመቃወም ቅዱስ ሲኖዶስን መቃወም የለባቸውም፣ ኢሕአዴግን ለመቃወም በጠቅላላው ቤተ ክህነቱን መቃወም የለባቸውም። አንዱን ጳጳስ ለመቃወም ጵጵስናን በሙሉ መዋጋት የለባቸውም።

ከነዚህ ድረ ገጾች መካከል በተለይ አቡጊዳንቋጠሮንኢትዮጵያን ሪቪውን ብንጠቅስ በአብዛኛው በነገረ ማርያም ላይ ለሚነሡ ኢ-ኦርቶዶክሳዊ ተቃውሞዎች ዋነኛ መጠቀሚያ በመሆናቸው ሙያዊ ሥነ ምግባራቸውን እንዲፈትሹ እንጠይቃለን። ወይም ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚያብጠለጥል ጽሑፍ የሚያወጡ ከሆነ ለዚያ መልስ የሚሆን ነገር ከሚመለከታቸው ሊቃውንት መጠየቅ ይኖርባቸዋል። የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር የሚያዘው ይህንን ነው። ወይም “በእምነት ጉዳይ ጣልቃ መግባት የለባቸውም” የሚባለውን  መተግበር አለባቸው።

ቸር ወሬ ያሰማን፣ አሜን።
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)