January 18, 2011

የከተራ - ጥምቀት በዓል ዝግጅት

  • በመዲናይቱ አዲስ አበባ በ62 ማኅበራት የተደራጁ ከ25‚000 በላይ  ወጣቶች በቅድመ ግጅቱ ታቦተ እግዚአብሔር የሚያልፋባቸውን  ጎዳናዎች በማጽዳት እና በመደልደል፣ መንገዶችን እና አደባባዮችን በሰንደቅ ዓላማ በማሸብረቅ ግንባር ቀደም ተሳትፎ እያደረጉ ነው
  •  የማኅበራቱ አደረጃጀት እና ባለቤትነት በጠቅ/ቤተ ክህነቱ የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ እና የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ መካከል ውዝግብ ያስነሣ ሲሆን በቀጣይ ወጣቶቹን ‹‹የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያው በትምህርተ ወንጌል አንጾ ለአገልግሎት በማዘጋጀት በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር እንዲዋቀሩ ስምምነት ተደርሷል፤›› ተብሏል፡፡ ማኅበራቱን ከክፍለ ከተሞች የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ አመራሮች እና ከማኅበረ ቅዱሳን ጋራ ለማጋጨት የታቀደውን ተንኮል እንደደረሱበት የገለጹት የማኅበራቱ ተወካዮች በበኩላቸው ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ተሰጥቶናል በሚሉት ፈቃድ መሠረት በስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሥር መቆየትን እንደሚመርጡ በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡
  •  ማኅበራቱ ‹‹የበላይ መዋቅር ስለሌላቸው የጥፋት ኀይል መጠቀሚያ እንዳይሆኑ ስጋት ገብቶኛል›› ያለው መንግሥት ጠቅ/ቤተ ክህነቱ ለአደረጃጀታቸው ዕውቅና ሰጥቶ በማእከላዊነት እንዲቆጣጠራቸው፣ ቲ-ሸርት እንዳይለብሱ አልያም በሚለብሷቸው ቲ-ሸርቶች ላይ ከሚጽፏቸው ‹ተንኳሽ ጽሑፎች›፣ በመንገዶች ላይ
  • ቄጤማ ከመጎዝጎዝ እና ምንጣፍ ከማንጠፍ እንዲቆጠቡ፣ የሰንደቅ ዓላማን ሕግ አክብረው እንዲጠቀሙ አልያም ባንዲራ ከመስቀል እንዲከለከሉ ካህናቱ በየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያኑ እንዲመክሩ አሳስቧል፡፡
  •  ‹‹ቲ-ሸርቱ ተዘጋጅቷል፤ ቄጤማ መጎዝጎዝ እና ማንጠፍም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው፤ ባንዲራውም ሃይማኖታዊ ምሳሌ እና ትርጉም አለው፤. . .በዓሉ በደረሰበት ዋዜማ ምንም ልናደርግ አንችልም፤ በሚስተካከሉት ጉዳዮች ላይ ከበዓሉ በኋላ ተነጋግረን እንወስናለን፡፡›› (የጠቅላይ ቤተ ክህነት እና የአ.አ ሀገረ ስብከት ተወካዮች)
  •  ጉዳዩ ‹‹ወደ እኔ የመጣውን ወደ ውጭ አላወጣውም›› በሚለው ቃለ ወንጌል መሠረት እንዲጤን የሚመክሩት አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው ጠቅ/ቤተ ክህነቱ መምሪያዎቹ ከመዋቀራቸው ከዘመናት አስቀድሞ ስብከተ ወንጌልም የሰንበት ትምህርትም ነባራዊ መሆናቸውን አስቦ ከሁሉም በላይ የወጣቶቹ     ክርስትና ከአንዳንድ ጥቅመኞች እና የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አቀንቃኞች የሚጠበቅበትን የሽግግር መዋቅር እንዲያመቻች፣ መንግሥትም ዝንባሌያቸውን በበጎ እንዲመለከተው ወጣቶቹም እንደ ትላንቱ ከማሰብ ተቆጥበው እስከ አሁን በተግባር እንዳስመስከሩት በነገራቸው ሁሉ ፈሪሃ እግዚአብሔርን እና አክብሮተ ሰብእን(ግብረ ገባዊነትን) እንዲላበሱ መክረዋል፡፡
 (ደጀ ሰላም፤ ጃኑዋሪ 18/2011፤ ጥር 10/2003 ዓ.ም)፦ ከተራ - ከተረ ከሚለው ግስ ግእዛዊ የተገኘ ሲሆን ዘጋ፣ አቆመ፣ አገደ፣ ከለከለ ማለት ነው፤ ከተራ የማገድ፣ የመክበብ ሥራ ነው፡፡ በሃይማኖታዊ ፍቺው ከተራ የበዓለ ጥምቀት ዋዜማ ነው፤ ጥር 10 ቀን ወራጅ ውኃ የሚገደብበትን፣ ታቦት እና ምእመናን የውኃው አካል በተሰባሰበባቸው ባሕረ ጥምቀት በማምራት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በ30 ዓመቱ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ወርዶ በእደ ዮሐንስ ለመጠመቅ በማእከለ ዮርዳኖስ በቆመ ጊዜ ውኃው ለሁለት እንደ ግድግዳ ተከፍሎ መቆሙን ያመለክታል፡፡ 

በዚህም ጌታችን የዕዳ ደብዳቤያችንን ደምስሶ ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ልደት የምናገኝበትን የልጅነት ጥምቀት ሰጥቶናል፤ በዓለ ጥምቀትም የዚህ መታሰቢያ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ዜና ጥምቀተ ክርስቶስን ከሰማችበት ከመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን አንሥቶ በተለይም ከአጤ ገብረ መስቀል ዘመነ መንግሥት (6ኛው መ/ክ/ዘ) ወዲህ የጥምቀትን በዓል ዛሬ በሚታየው አኳኋን ስታከበር እንደ ቆየች ይታመናል፡፡ በክብረ በዓሉ ከመንበረ ክብራቸው ወጥተው ወደ ባሕረ ጥምቀት የሚወርዱት ታቦታት በካህናቱ ሃሌታ፣ በምእመናኑ እልልታ እና በየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያኑ በተቋቋሙ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች መዝሙሮች ታጅበው በተመሳሳይ አኳኋን እንደሚመለሱ ይታወቃል፡፡

በዘንድሮው የጥምቀት በዓል አከባበር በየአካባቢያቸው በልዩ ልዩ ማኅበራት የተደራጁ የከተማ ወጣቶች በተለይም ከ2001 ዓ.ም አንሥቶ በጀመሩት አኳኋን ሲያደርጉ የሰነበቱትን የተጠናከረ ቅድመ ዝግጅት በማጠናቀቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክን የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሥር ‹‹የጥምቀት በዓል ተመላሾች ወጣቶች ኅብረት›› በሚል ስያሜ በ62 ማኅበራት የተደራጁት ከ25‚000 በላይ ወጣቶች ከወራት በፊት ከምእመናን እና ከበጎ አድራጊዎች ባሰባሰቡት ገንዘብ ታቦተ እግዚአብሔር እና ምእመናን የሚያልፉባቸውን እና የሚቆሙባቸውን ጎዳናዎች በማጽዳት፤ አውራ መንገዶችን፣ አደባባዮችን እና ዐጸዶችን በተለያዩ መልኮች በሰንደቅ ዓላማ በማስዋብ ላይ ይገኛሉ፡፡ በዓሉ ተከብሮ በሚውልባቸው ዕለታት ማኅበራቱ ምእመናንን ከማስተናበር እና ነዳያንን ከመመገብ ጀምሮ የተለያዩ የበጎ አድራጎት ተግባራትን እንደሚያከናውኑ ተዘግቧል፡፡

ይሁንና የማኅበራቱ አደረጃጀት እና በተጠናከረ መልኩ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የመንግሥትን ትኩረት መሳቡን ተከትሎ ሐላፊነት ወስዶ በማእከላዊነት ከመቆጣጠር አኳያ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ እና በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ መካከል የባለቤትነት ውዝግብ ማስነሣቱ ተሰምቷል፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት የቤተ ክርስቲያንን መሠረታዊ ህልውና እና ብሔራዊ መብት በመጋፋት አድልዎ እና ግፍ በሚፈጽሙ አካላት ድርጊት ተቆጭተው የተነሣሡት ወጣቶች በየአካባቢያቸው በመሰባሰብ በጥር ወር 2001 ዓ.ም የጥምቀትን በዓል በድምቀት እንዲከበር ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ ልምዱ ባለፈው ዓመት በተከበረው የጥምቀት በዓል የአስፋልት መንገዶችን በማጠብ፣ ቄጤማ በመጎዝጎዝ፣ ሥነ ሥርዐት በማስከበር እና በሌሎች የበጎ አድራጎት ተግባራት ጭምር ተጠናክሮ ታይቷል፡፡ ለቀጣይነቱ የወጣቶቹ ተወካዮች ወደ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ቀርበው በመወያየት በስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሥር ተደራጅተው እንዲንቀሳቀሱ እንደተፈቀደላቸው ተዘግቧል፡፡ መምሪያው በተለይ ከዚህ ዓመት መጀመሪያ አንሥቶ በማኅበራቱ(መጀመሪያ ላይ ብዛታቸው እስከ 85 ይደርስ ነበር) ሥር የተደራጁትን ወጣቶች በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ በመጥራት ከውሏቸው እና ከግንዛቤያቸው ጋራ የሚመጣጠን ትምህርት እና ምክር ለመስጠት ዐቅዶ ነበር፡፡

በአንጻሩ በሰበካ ጉባኤው ቃለ ዐዋዲ አንቀጽ 21 ንኡስ አንቀጽ አንድ መሠረት ዕድሜያቸው ከአራት እስከ ሠላሳ ዓመት የሚገኙ ሕፃናት እና ወጣቶች በየአጥቢያቸው የማደራጀት ሐላፊነት ያለበት የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ፣ ‹‹በማኅበራቱ የታቀፉት ወጣቶች እንደመሆናቸው መደራጀት ያለባቸው በእኔ ሥር ነው፤›› በሚል የይገባኛል ጥያቄ አንሥቶባቸዋል፡፡ ወጣቶቹ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች ባላቸው የአባላት አቀባበል፣ ሥልጠና እና አገልግሎት መስፈርት መሠረት ታቅፈው በየሰበካቸው እንዲንቀሳቀሱ አልያም ‹‹ከጥምቀት በዓል በፊት እንዲበተኑ›› የሚሹት የማደራጃ መምሪያው ሐላፊ የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያን በመክሰስ ለፓትርያሪኩ አቤቱታ ማቅረባቸው ተመልክቷል፡፡ የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ በበኩሉ ‹‹በማኅበራቱ ውስጥ ዕድሜያቸው ከሠላሳ ዓመት በላይ የሚሆናቸው ጎልማሶችም ስለሚገኙ በስብከተ ወንጌል አሠልጥኖ ለአገልግሎት የማዘጋጀት ድርሻው የእኔ ነው፤›› በማለት አቤቱታውን ቢከላከልም ከፓትርያሪኩ ጽ/ቤት ወጣ በተባለ ደብዳቤ ማደራጃ መምሪያውን ይቅርታ እንዲጠይቅ መደረጉ ተጠቁሟል፡፡

ቀደም ሲል ወጣቶቹን በማእከላዊነት የሚቆጣጠር አካል አለመኖሩን መነሻ በማድረግ በቲ-ሸርት ላይ የሚጻፉ ‹‹ተንኳሽ›› የሚላቸው ጽሑፎች (‹‹ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት›› የሚለው ዓይነት) እና ወጣቶቹ በተጠናከረ አኳኋን የሚያካሂዷቸው ግልጽ የአደባባይ ክዋኔዎች በሌሎች ላይ ሊያሳድሩ ከሚችሉት ሥነ ልቡናዊ ጫናዎች አንጻር እንዲታገዱ ቤተ ክርስቲያኒቱ ትእዛዝ እንድታስተላልፍ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሐላፊዎች ፓትርያሪኩን ጨምሮ ከቋሚ ሲኖዶስ አባላት ጋራ መምከራቸው ተዘግቧል፡፡ በዓሉ ሃይማኖታዊ እና ይዘቱም መንፈሳዊነቱን የጠበቀ እስከሆነ ድረስ የተነሣው ስጋት ሊኖር እንደማይገባው ይልቁንም በተለያዩ ቦታዎች በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ የሚደርሰው የፍትሕ መጓደል እንዲገታ የሚያሳስብ ጥያቄ መቅረቡ ተገልጧል፡፡

ባለፈው ሳምንት ጥር ሦስት ቀን 2003 ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ በጠሩትና የሚመለከታቸው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የመምሪያ ሐላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም የወጣቶቹ ተወካዮች በተገኙበት በተደረገው ስብሰባ ማኅበራቱ፣ ”የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኀይል አሠልጥኖ የላካቸው ወንጭፎች ናቸው” የሚል ክስ እንደቀረበባቸው እና ይህም ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን ባካሄደው ጥናት በማስረጃ መረጋገጡ›› ተገልጾ እንደነበር ተነግሯል፡፡ ይሁንና ፓትርያሪኩ አለ የተባለው ማስረጃ በጥንቃቄ ተትንትኖ ለኀሙስ ጥር አምስት ቀን 2003 ዓ.ም እንዲቀርብ ትእዛዝ ቢሰጡም በዕለቱ በተደረገው ስብሰባ የተባለውን ‹‹ማስረጃ ተንትኖ ያቀረበ››ም ይሁን እንዲቀርብ ያስታወሰ አካል አለመኖሩ ታውቋል፡፡ ጉዳዩን አስመልክቶ አስተያየታቸውን የተጠየቁ ታዛቢዎች ‹‹እባብን ግደል ከነበትሩ ገደል›› ሲሉ ወጣቶቹን እና ማኅበረ ቅዱሳንን ለማጋጨት የታቀደውን ተንኮል አጣጥለውታል፡፡ በምትኩ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ፣ ‹‹ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሐላፊነት ወስዶ ወጣቶቹ እንዲማሩ እናደርጋለን እንጂ እንዴት እንበትናቸዋለን?›› በማለት የማኅበራቱ አደረጃጀት እና ባለቤትነት ጉዳይ ከበዓሉ በኋላ ባለው የሳምንቱ መጨረሻ በሚካሄደው ምክክር እልባት እንደሚሰጠው መናገራቸው ተሰምቷል፡፡ በማደራጃ መምሪያው ሥር የሚገኘው የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ አመራሮችም የማኅበራቱን አመጣጥ እና ወቅታዊ ሁኔታ በማጤን የመፍትሔ ሐሳብ ለማቅረብ እየተዘጋጀ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

በሌላ በኩል ቅዳሜ ጥር ሰባት ቀን 2003 ዓ.ም በአዲስ አበባ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ስብሰባ የተጠሩት የአዲስ አበባ ገዳማት እና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት መምሪያ ሐላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ እና ሥራ አስኪያጁ ንቡረ እድ አባ ገብረ ማርያም ገብረ ሥላሴ በተገኙበት በጥምቀት በዓል አከባበር ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ስብሰባውን የመሩት ምክትል ከንቲባው አቶ ከፍ ያለው አዘዘ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፈቃዱ ሰቦቃ በበዓሉ አከባበር በሰንደቅ ዓላማው ሕግ መሠረት ወጣቶቹ በሚያደርጉት የበዓል ቅድመ ዝግጅት የኮከቡ ዓርማ ያለበት ባንዲራ ጥቅም ላይ እንዲውል አለበለዚያ ባንዲራ መስቀሉ እንዲቀር፣ ቄጤማ ከመጎዝጎዝ፣ ‹‹ተንኳሽ ጽሑፍ›› የሰፈረባቸውን ቲ-ሸርቶች ከመልበስ፣ ምንጣፍ ከማንጠፍ እና ሞንታርቦዎችን ከመጠቀም እንዲከለከሉ ምክር እንዲሰጥ አሳስበዋል፡፡ ‹‹ጥምቀት በነጭ ልብስ እንጂ በቲ-ሸርት ይከበራልን? ቄጤማ መጎዝጎዝንስ ሥርዐቱ ይፈቅዳል?›› ሲሉም ጥያቄ ማቅረባቸው ተሰምቷል፡፡

የተባሉት ነገሮች በሙሉ ወጣቶቹ ቀደም ሲል በተዘጋጁበት አኳኋን እየተከናወነ በመሆኑ፣ የበዓሉ ዋዜማም በመድረሱ ምንም ለማድረግ አዳጋች እንደሆነ ከተሳታፊዎች ምላሽ ተሰጥቷል፤ ሂደቱን ከበኋላ በሚደረግ ውይይት ቢወሰንበት እንጂ አሁን ለማገድ መሞከርም በቅርቡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ‹‹ለአንዱ የሚደረገው ለሌላው እየተነፈገ የአንድ ወገን ዐምባገነናዊ አሠራር›› በመስፈኑ የተፈጠረውን ዐይነት ችግር እንደሚያስከትል የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ለዩኒቨርስቲው አስተዳደር የጻፉትን ደብዳቤ በመኮነን ከመድረክ ለቀረቡት ትችቶች እና ጥያቄዎች ምላሽ ተሰጥቷል፡፡ አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ መደብ ያለው የኢትዮጵያ ባንዲራም ሃይማኖታዊ ምሳሌ እና ትርጉም ጭምር ያለው በመሆኑ ባንዲራን መጠቀም የፖሊቲካ ወይም የተቃውሞ ምልክት ብቻ ተደርጎ ሊታይ እንደማይገባው፣ አገር የምትጠበቀው በጸሎትም እንደሆነ ቤተ ክርስቲያንም በክብረ በዓላቷ የስጋት ምንጭ ተደርጋ መታየት እንደማይገባት ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ መክረዋል፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)