January 15, 2011

ፍርድ ቤት ተማሪዎቹ በዋስ እንዲለቀቁ ወሰነ

  • "ይህ የክርስትናችን ፍሬ ነው፤ እግዚአብሔር ለበጎ አድርጎልናል፡፡"(ተማሪዎቹ) 
  • "እግዚአብሔር ባወቀ ወደ እስር ቤት ወስዶ አስተምሮኛል፤ ወደ ቀደመ ሃይማኖቴ ተመልሻለሁ፡፡"
(ደጀ ሰላም፤ ጃኑዋሪ 15/2011፤ ጥር 7/2003 ዓ.ም)፦ በልደተ ክርስቶስ የበዓል ዋዜማ አከባበር ጋራ በተያያዘ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አራት ኪሎ ካምፓስ ‹‹ሁከት ቀስቅሳችኋል፤ በንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ አድርጋችኋል›› በሚል ቀደም ሲል ለእስር የተዳረጉት 18 ተማሪዎች በብር 400፣ ትላንት ከዩኒቨርሲቲው በፖሊስ ተወስደው የተጨመሩት አራት ተማሪዎች ደግሞ የብር 500 ዋስ አቅርበው ከእስር እንዲወጡ እና ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ተወሰነ፡፡

የአዲስ አበባ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት በትናንት አርብ የጠዋቱ ውሎ ውሳኔውን የሰጠው ተማሪዎቹ ቀደም ሲል በቀረበላቸው ምርጫ መሠረት የይቅርታ ጥያቄያቸውን ለዩኒቨርሲቲው በጽሑፍ ስለማቅረባቸው ፖሊስ በሰጠው ማረጋገጫ ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡ ተማሪዎቹ የዋስትናውን ሂደት ፈጽመው ከእስር ከተለቀቁ በኋላ ማምሻውን መደበኛ መንፈሳዊ መርሐ ግብር በሚከታተሉበት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሰንበት ት/ቤት ተሰብስበው ይጠብቋቸው በነበሩ ኦርቶዶክሳውያን ባልንጀሮቻቸው እንዲሁም በሥፍራው በሚገኙ ምእመናን በመዝሙር እና በእንባ የታጀበ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡ በአቀባበሉ መርሐ ግብር ላይ ከእስር ከተለቀቁት ተማሪዎች አንዳንዶቹ ‹‹ያሳለፍነው ችግር የክርስትናችን ፍሬ ነው፤ እግዚአብሔር ለበጎ አድርጎልናል›› ሲሉ መጽናናታቸውን መግለጻቸው ተዘግቧል፡፡ ከሁከቱ ጋራ በተያያዘ በድብደባ ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው በቁጥጥር ሥር ከዋሉት እና በዋስ ከተለቀቁት ተማሪዎች አንዱም “ቀደም ሲል ቤተ ክርስቲያኔን አላውቃትም ነበር፤ እግዚአብሔር ባወቀ ወደ እስር ቤት ወስዶ አስተምሮኛል” በማለት በእስር በቆየባቸው ቀናት ከኦርቶዶክሳውያኑ ጋራ በፍቅር ተቀራርቦ በመግባባት መንፈስ ባደረገው ውይይት “ወደ ቀደመ ሃይማኖቴ ተመልሻለሁ” በማለት ምስክርነቱን በገሃድ ሰጥቷል፡፡

በትናትናው ዕለት ጠዋት እና ተሲዓት በኋላ ከፈተና ላይ ሳይቀር በፖሊስ ተይዘው ከተወሰዱትና በቀደሙት 18 እስረኞች ላይ ከተጨመሩት አራት ተማሪዎች ሁለቱ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ምእመናን ሲሆኑ የተቀሩት ሁለቱ ደግሞ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ናቸው፡፡ ዳኛው ለተማሪዎቹ ምክር፣ ዩኒቨርሲቲውን በመወከል ለቀረቡት ሐላፊም በቀጣይ ከመማር ማስተማሩ አንጻር ያሉ ጉዳዮች በበጎ መንፈስ የሚስተካከሉበትን ሁኔታ አስመልክቶ ማሳሰቢያ መስጠታቸው ተነግሯል፡፡ ተማሪዎቹ ይቅርታ ጠይቀው በዋስ የወጡበትን ሁኔታ ከዳር አድርሰው ፋይላቸውን የማዘጋት ሂደት የሚጠብቃቸው ሲሆን ፖሊስ እስከ መጪዎቹ ሦስት ወራት ተጨማሪ ነገር ካላቀረበ ለዋስትና ያስያዙት ገንዘብ ተመላሽ ተደርጎላቸው ፋይሉ ሊዘጋላቸው እንደሚችል ተመልክቷል፡፡ በሌላም በኩል ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎቹ ያመለጧቸውን የመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት ፈተና የሚወስዱበትን አሠራር በማመቻቸት ትምህርታቸውን የሚከታተሉበትን ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ይጠበቃል፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)