January 13, 2011

ፍርድ ቤቱ ተማሪዎቹ የይቅርታ ጥያቄቸውን አስተካክለው እንዲያቀርቡ ወይም ‹ጥፋታቸውን› አምነው እንዲከራከሩ ምርጫ ሰጠ

(ደጀ ሰላም፤ ጃኑዋሪ 13/2011፤ ጥር 5/2003 ዓ.ም)፦ በልደተ ክርስቶስ የበዓል ዋዜማ አከባበር ጋራ በተያያዘ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አራት ኪሎ ካምፓስ ‹‹ሁከት ቀስቅሳችኋል›› በሚል ለእስር የተዳረጉ 18 ተማሪዎች ዛሬ ጠዋት በአዲስ አበባ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ቀረቡ፡፡

ተማሪዎቹ ታኅሣሥ 30 ቀን 2003 ዓ.ም የይቅርታ ጥያቄ ማቅረባቸውን ለፍርድ ቤቱ ቢያመለክቱም ‹‹ያልተሟላ›› በሚል ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ ‹‹የተሰጣችሁን ምክር አልተቀበላችሁም፤ ጥያቄያችሁም ጥፋታችሁን አምናችሁ በግልጽ ይቅርታ የጠየቃችሁበት አይደለም›› ያለው ፍርድ ቤቱ ‹‹ወይ ጥፋታችሁን አምናችሁ የዩኒቨርሲቲውን አስተዳደር ይቅርታ ጠይቁና ጉዳያችሁ በዚሁ ይለቅ አልያም ጥፋተኛ አይደለንም ብላችሁ ተከራከሩ›› በሚሉ ሁለት ምርጫዎች ላይ ተማሪዎቹ ወስነው ለመጪው ዓርብ ጥር ስድስት ቀን 2003 ዓ.ም እንዲቀርቡ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡

በሁለት ምድብ (ዘጠኝ፣ ዘጠኝ) ተከፍለው ከችሎቱ የቀረቡት ተማሪዎቹ በዩኒቨርሲቲው የሕንፃ መስተዋቶች ላይ በደረሰው ጥፋት አለመሳተፋቸውን፣ በምትኩ ከጥበቃ አባላት እና ከካፊቴሪያው ሠራተኞች ጋራ የማረጋጋት ጥረት ማድረጋቸውን፣ ተፈታኝ እና ተመራቂ በመሆናቸው ከትምህርታቸው ተስተጓጉለው ለሀገር እና ለቤተሰቦቻቸው ሸክም እንዳይሆኑ ጥፋት ቢገኝባቸው እንኳን ዩኒቨርሲቲው በአባታዊ ተግሣጽ (ማስጠንቀቂያ) እንዲያልፋቸውና በፈተናው ለመቀመጥ እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡

ይሁንና ይህ ‹‹ፖሊስን ሐሰተኛ፣ ዩኒቨርሲቲውን ተጠያቂ የሚያደርግ እና ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ አስመስሎ የሚክድ›› በመሆኑ ተማሪዎች በተሰጧቸው ሁለት ምርጫዎች ላይ ውሳኔያቸውን ይዘው ከነገ በስቲያ እንዲቀርቡ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡

ፖሊስ ተጨማሪ ማስረጃዎችን ለመሰብሰብ እና ከሁከቱ ጋራ በተያያዘ እፈልጋቸዋለሁ ያላቸውን ቀሪ ተጠርጣሪዎች ይዞ ለማቅረብ ተጨማሪ ሰባት ቀናትን የጠየቀ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ሁለት ቀናትን ብቻ ሰጥቶታል፡፡ ለፈተና መቀመጥን በተመለከተ ባሉበት ሁኔታ ለተማሪዎቹ እንደሚያስቸግራቸው ፍርድ ቤቱ ገልጾ ይሁንና ከፖሊስ ጋራ በመነጋገር በጠባቂ ሄደው ፈተናውን ለመውሰድ እንደሚችሉ መፈቀዱ ተገልጧል፡፡

በሌላ በኩል ታኅሣሥ 30 ቀን 2003 ዓ.ም በዚያው በአራት ኪሎ ካምፓስ በድብደባ ጉዳት ካደረሱት አንዱ እና በሁከቱ ስፍራ ስለት ይዞ የተገኘው ሌላው ተማሪ በድብደባ ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው በዛሬው ችሎት የቀረቡ ሲሆን ጉዳያቸው በተመሳሳይ አኳኋን (በይቅርታው ጥያቄ) እንደሚታይ ከችሎቱ እንደተገለጸላቸው ተዘግቧል፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)