January 5, 2011

በቤተ ክርስቲያን የቅጅ እና ተዛማጅ መብቶች ዙሪያ ያተኮረ ውይይት ተካሄደ


  • የቅጅ እና ተዛማጅ መብቶች እና የቅርስ አጠባበቅ ዐዋጆች መሻሻል ያስፈልጋቸዋል
  • ‹‹በኢትዮጵያ የእምነት ተቋማትን መስተጋብር የሚገዛ ሕግ ያስፈልጋል፡፡››
  • ‹‹በሕጎች ማርቀቅ እና ማጽደቅ ሂደት ቤተ ክርስቲያኒቱ የምትደምጠባቸውን መድረኮች ማጠናከር ይገባል፡፡››
(ደጀ ሰላም፤ ጃኑዋሪ 5/2010 ታኅሣሥ 27/2003.)በሥራ ላይ የሚገኙት የቅርስ፣ የቅጅ እና ተዛማጅ መብቶች ዐዋጆች የቤተ ክርስቲያንን ቁሳዊ እና መንፈሳዊ ሀብቶች በአግባቡ ከማስጠበቅ አኳያ ውስንነት ያለባቸው፣ ለአስፈጻሚ አካላት በቂ ሥልጣን የማይሰጡ እና በፈጻሚ ወገኖች ላይ ግዴታዎችን የማይጥሉ በመሆናቸው መሻሻል የሚያስፈልጋቸው አልያም ከቤተ ክርስቲያኒቱ ዘርፈ ብዙ ሀብቶች ባሕርይ አኳያ ተገናዝበው በወጥነት መዘጋጀት እንደሚገባቸው ተጠቆመ፡፡

በኢትዮጵያ በእምነት ተቋማት መካከል ያሉ መስተጋብሮችን የሚገዛ ሕግ ባለመኖሩ የቤተ ክርስቲያኒቱ ፈቃድ ሳይጠየቅበት ቅርስ - ንዋያተ ቅድሳቷ‹‹የሥርዐተ እምነታቸው›› አካል አስመስለው በይፋ ከማሳየት ባሻገር በተለይም ቅዳሴዋን ቅድምና ወስዶ በባለቤትነት ለማስመዝገብ የሚተጉ አካላት መኖራቸው ተገልጧል፡፡ ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ሀብቶቿን በዝርዝር ቆጥሮ እና ሰፍሮ ገላጭ በሆነ መልኩ የሚመዘግብ፣ ቀኖናዋን እና ትውፊቷን መሠረት ባደረገ መልኩ የቁሳዊ ሀብቶቿን ይዘት በአንድ ዐይነት መልክእ የሚያስጠብቅ ደረጃ እና ደንብ(Design and Standard) ማገግ፣ መደንገግ እና መደንባት እንደሚያስፈልጋት ተመልክቷል፡፡

ይህንንም ለማስፈጸም ባለድርሻ አካላት በሥሯ ተደራጅተው ይሁንታዋን በማግኘት በሕግ እና ሥራት ላይ የቆመ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል፣ ከፈቃዷ እና ስምምነቷ ውጭ ‹‹በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ደንብ እና ሥርዐት መሠረት የተዘጋጀ›› በሚል በስሟ የሚነግዱትን የሚያግድ፣ ለዚህም ተገቢውን ቁጥጥር፣ ንቃት እና ግንዛቤ የሚሰጥ ጠንካራ ማእከላዊ የቅርስ አስተዳደር መቋቋም እንደሚገባው ተነግሯል፡፡

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዝየም አዳራሽ ‹‹የቅጅ እና ተዛማጅ መብቶች በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን›› በሚል ርእስ በተካሄደውና በማኅበረ ቅዱሳን የጥናት እና ምርምር ማእከል በተዘጋጀው የሥነ ቤተ ክርስቲያን ጥናታዊ የውይይት መድረክ ላይ እንደተገለጸው፣ በ1992 ዓ.ም ‹‹የቅርስ አጠባበቅ ዐዋጅ››፣ በ1996 ዓ.ም ‹‹የቅጅ እና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ ዐዋጅ›› ሲወጡ የቤተ ክርስቲያኒቱ ተሳትፎ አጥጋቢ እንዳልነበር ወይም በሚገባ እንዳልተደመጠች ዐዋጆቹ ካለባቸው ውስንነት እና ቤተ ክርስቲያን የሀብቶቹ ባለቤት ከሆነችባቸው መንገዶች ጋራ ካልተካከለው(ወለፌንድ) ይዘታቸው መረዳት ይቻላል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ቁሳዊ እና ግዙፍ(tangible) የሆኑ ቅርሶች እና ቅርስ - ንዋያተ ቅድሳት፣ መንፈሳዊ እና ረቂቅ(Intangible) የሆኑ የዜማ እና የቅኔ ድርሳናት እንዲሁም የክዋኔ ጥበቦች(Performing arts) ባለቤት መሆኗን ያወሱት ጥናት አቅራቢዎቹ ከዐዋጆቹ አንጻር ቤተ ክርስቲያን ያላትን መብቶች መፈተሻቸውን ገልጸዋል፡፡

ከፍትሐ ብሔሩ የንብረት ሕግ ተለይቶ በ1996 ዓ.ም የወጣው የቅጅ እና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ ዐዋጅ(Copyright and Neighbouring Rights Proclamation) ዋና ዓላማ፣ በአንድ ዐይነት የመሰነጃ መንገድ(በድምፅ፣ በምስል ወይም በጽሑፍ) ተቀርጾ ለቀረበ ጥበብ ወይም ሥራ ባለቤት እና ለወራሹ ከጥበቡ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እና ሞራላዊ መብት ለተወሰነ ጊዜ(የጥበቡ/ሥራው ባለቤት በሕይወተ ሥጋ በሚቆይበት እና በሞት ከተለይበት እስከ 50 ዓመት ድረስ) በብቸኝነት የማስጠበቅ ነው፡፡ በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ ባለቤቱ እና ሕይወቱ ካለፈ በኋላ እስከ 50 ዓመት ድረስ የስጦታ ውል ያላቸው ሕጋዊ ወራሾቹ ሥራውን በማባዛት ለገበያ የማቅረብ፣ በሌሎች ቋንቋዎች እንዲተረጎም እና በተዛማጅ መንገዶች እንዲታወቅ በመፍቀድ ለብቻው በሚያገኛቸው ጥቅሞች አእምሯዊ ሀብቱን እንዲያበልጸግ እና ተጨማሪ ሥራዎችን እንዲያበረክት ይበረታታል፡፡ ከዚህ የጊዜ ገደብ በኋላ ግን ሥራው በሕዝብ ሀብት ይዞታዎች(Public domain) ውስጥ የሚካተት በመሆኑ የሥራው አመንጪ ብቸኛ ተጠቃሚ የሚሆንበት መብት አይኖረውም፡፡ ያለፈቃድ በማሳተም እና በማባዛት ለንግድ፣ ለንባብ እና ለማስተማርያ ተግባር(የአርክቴክቸር ሥራዎች ሊባዙ አይችሉም፤ በሙዚቃ ሥራዎችም ላይ የተወሰኑ ገደቦች አሉ) በማዋል ረገድ የሚጠበቁ ግዴታዎች አይኖሩም፡፡

በቤተ ክርስቲያን ጉልሕ የሆኑት ንዋያተ ቅድሳት በጥበብ መንፈሳዊ የተሠሩ፣ ረቂቅ የሆኑት ድርሳናትም በመንፈሳዊ ተጋድሎ የተጸመዱ ቅዱሳን በአምላካዊ መገለጥ ያገኟቸው፣ ሰማያዊ(ዘላለማዊ) አገልግሎት ያላቸው እና ትውልዱ በትውፊታዊ መንገድ የተቀበላቸው ናቸው፡፡ እንደ ሕግ ባለሞያው አቶ ጌታሁን ወርቁ ገለጻ፣ ‹‹በብዙዎቹ ድርሳናት ላይ አባቶቻችን ማንነታቸውን/ስማቸውን ሊገልጹ ቀርቶ ራሳቸውንም ለቤተ ክርስቲያን የሰጡ ነበሩ፤ ከመስፈርቱም በላይ ናቸው፡፡›› ከዚህ አኳያ በዐዋጁ በተገለጸው አኳኋን ሥራቸውን ‹‹በጽሑፍ በሰፈረ የስጦታ ውል ለቤተ ክርስቲያን የሚያበረክቱበት፣ ቤተ ክርስቲያንም ከእነርሱ ዕረፍት በኋላ ለተወሰኑ ዐሥርት ዓመታት ብቻ ባለቤት እንድትሆን የሚታሰብበት ሁኔታ ለሰሚው ግራ(absurd) ነው፤›› ይላሉ፡፡ በመሆኑም የቅጅ እና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ ዐዋጁ ቤተ ክርስቲያን ሥርዐተ አምልኮቷን እየፈጸመች ለዘመናት ጠብቃ ባቆየቻቸው ሀብቶቿ ሙሉ ተጠቃሚ እና ባለቤትነቷን በማስጠበቅ ረገድም የሕግ ኀይል ያላት እንድትሆን በሚያስችል መልኩ ተስማምቶ(adaptation) እንዲዘጋጅ አልያም ከዚህ ልዩ ሁኔታ በመነሣት ራሱን የቻለ ወጥ ዐዋጅ እንዲወጣ መወትወት እንደሚገባ መክረዋል፡፡

ይሁንና ዐዋጁ በዚህ መልኩ የሚሻሻልበት ዕድል እስኪገኝ ድረስ ሕጉ የሚሰጣቸውን ውስን መብቶች አሟጦ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል፡፡ በአሁኑ ወቅት ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በማእከላዊነት ለመቆጣጠር እስኪሳነው ድረስ ‹‹የቤተ ክርስቲያንን ደንብ እና ሥርዐት ጠብቆ የወጣ›› በሚል በምስል እና ድምፅ የሚወጡ ‹መዝሙራት›ን፣ ለኅትመት የሚውሉ የጸሎት መጻሕፍትን እና ሌሎች ድርሳናትን ጥንተ ይዘት ለመጠበቅ የሚያስችል አሠራር መዘርጋት እንደሚኖርበት ተመልክቷል፡፡ በዚህ ረገድ ቤተ ክርስቲያን ያላት ዋነኛ ጥያቄ ‹‹ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማግኘት ሳይሆን ሀብቶቹ ሳይበረዙ እና ሳይከለሱ ለትውልድ እንዲተላለፍ ማድረግ ነው፤›› ያሉት ሌላው የሕግ ባለሞያ ደግሞ አቶ ቢሰጥ በየነ ናቸው፡፡ ከቅጂ እና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ ዐዋጅ አኳያ በተለይም ለጸሎት መጻሕፍቱ እና ለሌሎቹ ድርሳናት የራሷን የገጽ ሥራ እና ቅንብር(ልዩ የኅትመት መልኮች) አውጥታ እነርሱን መደበኛ የደረጃ መለኪያ(ስታንዳርድ) አድርጋ ለአገልጋዮች እና ምእመናን በማስተዋወቅ ይዘታቸውን ከቅሰጣ ስጋት የምትከላከልበት የመብት ጥበቃ(copyright protection) ማግኘት እንደሚቻላት አስረድተዋል - ለንዋያተ ቅድሳቱ እና ለካህናቱ አልባሳትም እንዲሁ፡፡ በምስል እና በድምፅ የሚወጡ የዝማሬ፣ ቅኔ እና የክዋኔ ጥበብ ውጤቶችን በተመለከተም አገልግሎት ሰጪ አካላትን በማእከላዊነት በማደራጀት ሥራዎቻቸው የቤተ ክርስቲያኒቱን ይሁንታ የሚያገኝበትን መንገድ በውል በማሰር፣ ከውሉ ውጭ የሆኑ የተበረዙ እና የተከለሱ ሥራዎችን አትመው የሚያሰራጩትን በማገድ ርምጃውን ለአገልጋዮች እና ምእመናን ማሳወቅ እንደሚቻል አብራርተዋል፡፡

የቅርሶችን መበረዝ እና መከለስ አልያም ያለአግባብ ጥቅም ላይ መዋል ለመከላከል ከቅጅ እና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ ዐዋጅ ይልቅ በ1992 ዓ.ም የወጣው የቅርስ አጠባበቅ ዐዋጅ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ የመንፈሳዊ ቅርሶች ክብካቤ ስምምነቶች የተሻለ አግባብነት እንዳላቸው ባለሞያው ገልጸዋል፡፡ በዚህ ዐዋጅ መሠረት ለቅርሶቹ ቆጠራ ተካሂዶ፣ ምንነታቸው እና መሠረታዊ ይዘታቸው በተለያዩ የመሰነጃ መንገዶች ተመዝግበው ከአገር እንዳይወጡ፣ አላግባብ ጥቅም ላይ በሚውሉበት፣ በሚበረዙበት ወይም የባለቤትነት ውዝግብ በሚነሣበት ወቅት ክስ መሥርቶ በመሞገት ትክክለኛውን ለማሳወቅ ያስችላል፡፡ ሆኖም በቆጠራው እና በምዝገባው ሂደት በአመዛኙ ትኩረት የተሰጣቸው ተዳሳሽ የሆኑት ንዋያተ ቅድሳት እና ቅርስ - ንዋያተ ቅድሳት እንጂ ረቂቁ የዜማ፣ የቅኔ እና የክዋኔ ጥበቦች ባለመሆናቸው ዐዋጁ በአፈጻጸም ሰፊ ጥበቃ ከማድረግ አኳያ ውስንነት እንዳለበት ተመልክቷል፡፡ ይህን ክፍተት በመጠቀም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴያትን ያለቤተ ክርስቲያኒቷ ዕውቅና የሥርዐተ እምነታቸው አካል አድርገው ከመጠቀም አልፈው እንደ ዩኔስኮ ባሉት ዓለም አቀፍ ተቋማት በባለቤትነት ቀድመው(የማስመዝገብ ቅድምና ለባለቤትነት መብት ወሳኝ ድርሻ አለው) ለማስመዝገብ የሚተጉ አብያተ እምነት እንዳሉ ተጋልጧል፡፡

ዐዋጁ ‹‹የቅርስ ባለቤት ሕዝብ ነው›› ስለሚል በብቸኝነት የመያዝ መብትን አይሰጥም፡፡ በሀገራችን በእምነት ተቋማት መካከል ያሉ ግንኙነቶችን የሚገዛ ሕግ የለም፡፡ በዚህ ሳቢያ አንዳንድ የፕሮቴስታንት አብያተ እምነት ሲያወግዙት የኖሩትን የቤተ ክርስቲያኒቱን ንዋያተ ማሕሌት እና የካህናት አልባሳት የመጠቀም ሁኔታ በሕግ የሚጠየቅበት ዕድል እንደሌለ ተመልክቷል፡፡ የእኒህ ተቋማት ቅጥረኞች በሆኑ የተሐድሶ መናፍቃን አራማጆች በሚታተሙ የክሕደት መጻሕፍት ላይም የሚያቃልሏቸውን ቅዱሳን ሥዕለ ገጽ በሽፋንነት የመጠቀም ልምድ(‹‹መጻሕፍተ ኑፋቄ›› እና ‹‹ገድል ወይስ ገደለን?›› ያስታውሷል) የተስፋፋ መሆኑ ተገልጧል፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች በአልባሳቷ እና በንዋያተ ቅድሳቷ ሲያጭበርብሩ ቢገኙ በማስመሰል(misrepresentation) በወንጀል ሕግ ሊጠየቁ የሚችሉበት አግባብ እንዳለ ሁሉ ከላይ የተገለጹትን የቅሰጣ ተግባራት ለመከላከልም በኢትዮጵያ በእምነት ተቋማት መካከል ያሉ መስተጋብሮችን የሚገዛ ሕግ ማውጣት አስፈላጊ እንደሆነ የሕግ ባለሞያዎቹ በአጽንዖት ጠይቀዋል፡፡ በውይይቱ ከተገኙ ተሳታፊዎች መካከል ከኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት መብት ጥበቃ ጽ/ቤት የመጡ ባለሞያ የቴክኖሎጂ(ኢንዱስትሪያዊ) ግኝቶች መብት ጥበቃ(ፓተንት) እና ከሥነ ጽሑፍ፣ ዜማ እና ክዋኔ ጥበቦች መብት ጥበቃ(ኮፒራይት) ባሻገር የቤተ ክርስቲያን ቅርሶች በማኅበረሰብ ዕውቀቶች መብት ጥበቃ(ኮሚዩኒቲ ኢንተሌክቹዋል ራይት) ሊያገኝ በሚችልባቸው መንገዶች ጥናት ማካሄድ እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡

ወቅታዊ የቅርስ ቆጠራዎችን ማካሄድ፣ መመዝገብ እና አስፈላጊውን የቁጥጥር ሥራ በየደረጃው በጥብቅ መፈጸም መንፈሳዊ እና ቁሳዊ ሀብቶችን ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ፣ ምእመኑን ለማስተማር፣ የምርምር እና ፕሮሞሽን ሥራዎችን ለመሥራት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ ለዚህም በታወቁት እና ተለምዷዊ የቱሪስት መዳረሻ በሆኑ ታላላቅ ቅዱሳት መካናት ብቻ ሳይሆን በተቀሩትም ያለንን ሀብት ለማወቅ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት፣ ጠንካራ እና ማእከላዊ የቅርስ አስተዳደር ሥርዐትን መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ተመልክቷል፡፡ ከውይይቱ ተሳታፊዎች አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት ኦርቶዶክሳዊ ያልሆኑ እንቶ ፈንቶ ግጥሞች እና ዜማዎች ዐውደ ምሕረቱ ላይ በወጡበት እና ዐይነተኛው ትምህርት ባልተስፋፋበት ሁኔታ ለቤተ ክርስቲያን የቅጂ እና ተዛማጅ መብቶች መጠበቅ የሚጋደሉ ሐቀኞች እንደ ዕንቅፋት እየተፈረጁ የሚጎዱበት ሁኔታ በመፈጠሩ የሕግ እና የአስተዳደር ጥበቃ እንዲደረግላቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በሀገሪቱ ሕጎች በሚረቀቁበት እና ለሕዝብ ውይይት በሚቀርቡበት ወቅት ከ45 ሚልዮን ያላነሰውን ምእመን የምትመራው ዋነኛዋ የቅርስ ማኅደር የሆነችው ቤተ ክርስቲያን የምትደምጥባቸውን መድረኮች ማጠናከር አጠያያቂ እንዳልሆነ የሚያሳስቡ መልእክቶች ተላልፈዋል፡፡ ከዚህ አኳያ ከቤተ ክርስቲያኒቷ አስተምህሮ ጋራ በቀጥታ የሚጋጩ ሕጎችን ይዘው የወጡት የቤተሰብ ሕግ፣ የውርጃ መብት(በተሻሻለው የወንጀል ሕግ) እና በቅርቡ የወጣው የመካነ መቃብር እና የእምነት ቦታዎች ዐዋጅ የሚያስከትሉትን ጠንቅ ማጤን እንደሚገባም ተመክሯል፡፡

2 comments:

Anonymous said...

Melkam new ! tefetsaminetun lemayet yabiqa eji.yuhun enji yihenin guday letewesenu sewoch bicha yeminitewew sayihon hulachinim ye enat betekiristiyanachinin mebit lemastebek yebekulachinin mewetat yitebekibinal!!!

Anonymous said...

wonderful idea this is the point that our church has to give an emphasis. please the synodos wake up and preserve the rights of our church in every aspect.
thank u!!

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)