December 29, 2010

የአባቶች ዕርቀ ሰላም ንግግር በጥር ሊጀመር ይችላል


  • በንግግሩ ቅድመ ሁኔታዎች ስምምነት ላይ ከተደረሰ በሁለቱም ወገኖች የተላለፈው ቃለ ውግዘት ይነሣል
  • የዕርቀ ሰላም ንግግሩን የሚያስተናብሩ ሽማግሌዎች ተመርጠዋል
(ደጀ ሰላም፤ ዲሴምበር 29/2010 ታኅሣሥ 20/2003 .)በምዕራቡ ዓለም በስደት ከሚገኙት አባቶች ጋራ የሚደረገው የዕርቀ ሰላም ንግግር በመጪው ጥር ወር 2003 ዓ.ም አንድ የመገናኛ መድረክ በማመቻቸት እንደሚጀመር የቅዱስ ሲኖዶስ ምንጮች አመለከቱ፤ ቅዱስ ሲኖዶሱ ታኅሣሥ 13 ቀን 2003 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ‹‹በባሕር ማዶ በሚገኙት አባቶችም ዘንድ ተቀባይነት ይኖራቸዋል፤ የዕርቀ ሰላም ንግግሩን በገለልተኝነት ያስተናብራሉ›› ብሎ ያመነባቸውን ሦስት ሽማግሌዎችንም መርጧል፡፡ እነርሱም ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም፣ ፊታውራሪ ዘውዱ አስፋው እና ዶ/ር ሳሙኤል አስፋው (በአሜሪካ የኢትዮጵያ የቀድሞ አምባሳደር) ናቸው፡፡ የዕርቀ ሰላም ንግግሩን ከአላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት ለመጠበቅ እና ነጻ ውይይት ለማካሄድ ይቻል ዘንድ ውይይቱ ከአሜሪካ ውጭ ከግብፅ - ካይሮ፣ ከእስራኤል - ኢየሩሳሌም ወይም ከኬንያ - ናይሮቢ ከተሞች በአንዱ ለማድረግ እንደ ታሰበ ምንጮቹ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ባካሄደው እና በቋሚ ሲኖዶሱ በተጠራው አስቸኳይ ስብሰባ በጥቅምቱ የሲኖዶሱ ምልአተ ጉባኤ በተመረጡት ብፁዓን አባቶች የቀረበውን የዕርቀ ሰላም ንግግር ምክረ ሐሳብ በመመልከት ሰነዱ በተጨማሪ አራት ሊቃነ ጳጳሳት ተመርምሮ እና ዳብሮ እንዲቀርብ አድርጓል፡፡ ምክረ ሐሳቡ በዋናነት አራተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ ሀገር በሚመለሱበት፣ ከእርሳቸው በኋላ ከሀገር የወጡት ሦስቱ ሊቃነ ጳጳሳት አገልግሎታቸውን በሚቀጥሉበት፣ በአራተኛው ፓትርያርክ እና በሦስቱ (አራተኛው ብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ በማረፋቸው) ሊቃነ ጳጳሳት በ1999 ዓ.ም የተሾሙት 13 ኤጲስ ቆጶሳት ሢመት አግባብነት ታይቶ እና ተቀባይነት አግኝቶ አገልግሎታቸውን በሚቀጥሉበት ሁኔታ ላይ ያተኮሩ ነጥቦች የሚገኙበት መሆኑ ተገልጧል፡፡

በእኒህ ነጥቦች ላይ በውጭ በሚገኙት አባቶች ዘንድ ‹‹ብዙም የማይጎረብጡ እና ለዕርቀ ሰላሙ ሂደት ምቹ›› የተባሉ መቅድማዊ ሁኔታዎች ተቀምጠዋል ተብሏል፡፡ በምክረ ሐሳቡ መሠረት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ አገር ቤት ተመልሰው ለፓትርያርክ በሚገባ አኳኋን ለመንፈሳዊ ኑሯቸው እና ለጤንነታቸው አስፈላጊ የሆነው አገልግሎት ተሟልቶላቸው በመረጡት ገዳም በጸሎት ተወስነው እንዲቀመጡ፤ ሦስቱ ሊቃነ ጳጳሳት (አቡነ መልከ ጼዴቅ፣ አቡነ ጎርጎርዮስ እና አቡነ ኤልያስ) ወደ ሀገር ተመልሰው ቅዱስ ሲኖዶሱ በሚመድባቸው ቦታ አገልግሎታቸውን እንዲቀጥሉ፤ የ13ቱን ኤጲስ ቆጶሳት ሢመት ያለቅድመ ሁኔታ በመቀበል ቅዱስ ሲኖዶስ በሀገር ውስጥም ይሁን በባሕር ማዶ በሚመድባቸው ቦታ እንዲያገለግሉ የሚሉ ናቸው፡፡ የመጨረሻውን ነጥብ አስመልክቶ ‹‹ኤጲስ ቆጶሳቱ የተሾሙበትን ከፍተኛ ማዕርግ የሚያስከለክል ነውር እና ነቀፋ የሌለባቸው፣ የታመነባቸው እና ብቃት ያላቸው መሆኑ እየታየ ነው መቀበል ያለብን›› የሚል ሐሳብ ቀርቦ የነበረ ቢሆንም ለዕርቀ ሰላሙ ሂደት እና ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ሊፈጥረው ከሚችለው መሰናክል አኳያ በጉባኤው ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ የጉዳዩ ታዛቢዎች የቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነት ከሁሉም ቅድሚያ የሚሰጠው ቢሆንም ከሥነ ምግባር በመለስ ውለው አድረው ሃይማኖታዊ እና ቀኖናዊ ችግር የሚፈጥሩ ጉዳዮች ካሉ ጨርሶ ቸል ሊባሉ እንደማይገባቸው አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡

በውይይቱ እነዚህ ነጥቦች ስምምነት ከተደረሰባቸው ጥር 25 ቀን 1999 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ‹‹በሌላቸው የፓትርያርክነት ሥልጣን ተወግዘው ከተለዩት ጋራ ኤጲስ ቆጶሳትን ሾመናል በማለት በመንፈስ ቅዱስ ላይ በመዋሸት ተዳፍረዋል፤ በአንድነቷ ጸንታ የኖረችውን ቤተ ክርስቲያን ሆን ብለው ለመገነጣጠል አቅደው እና አስበው ሕገ ወጥ ሲኖዶስ በማቋቋም የክሕደት፣ የሐሳዊ መሲሕ ወይም የመናፍቅ ተግባር ፈጽመዋል›› በማለት ያስተላለፈውን ቃለ ውግዘት ያነሣል፡፡ በሌላ በኩል በውጭ የሚገኙት አባቶች ጥር 30 ቀን 1999 ዓ.ም ባወጡት መግለጫ ‹‹የአራት ኪሎው ሕገ ወጥ ሲኖዶስ›› ያሉት አካል ያስተላለፈውን ውሳኔ ‹‹በመሻር›› ውሳኔውን ያሳለፉትን ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስን ከእርሳቸውም ጋራ ሊቃነ ጳጳሳቱን እና በእርሳቸው የተሾሙትን ኤጲስ ቆጶሳት በመቃወም ያስተላለፉትን ቃለ ውግዘት ያነሣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ለዕርቀ ሰላም ንግግሩ ቅዱስ ሲኖዶስን በመወከል ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፣ ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ፣ ብፁዕ አቡነ ገሪማ እና በመ/ፓ/ጠ/ክ ጽ/ቤት የመንፈሳውያን ጉዳዮች ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ በልኡካንነት ተመርጠዋል፡፡ ለልኡኩ በጸሐፊነት የሚያገለግሉት ንቡረ እድ ኤልያስ በጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ባቀረቡት አሉታዊ ሪፖርት ሳቢያ ተቃውሞ የተሰነዘረባቸው ቢሆንም በፓትርያርኩ ድጋፍ ሊካተቱ ችለዋል፡፡ ይሁንና በውጭ በሚገኙት አባቶች ዘንድ በእርሳቸውም ይሁን በሌሎቹ የልኡካን ቡድኑ አባላት መካተት ጉዳይ ላይ የሚቀርብ ቅሬታ ቢኖር በሲኖዶሱ በኩል እስከ መለወጥ ድረስ ፈቃደኛነቱ እንዳለ ተመልክቷል፡፡ የንግግሩን ሂደት እንዲያስተናብሩ በሲኖዶሱ በተመረጡት ሦስት ሽማግሌዎች ላይም ተመሳሳይ ጥያቄ ቢነሣ ሁሉም ወገኖች የሚስማሙባቸው ሌሎች ሽማግሌዎች እንደሚተኩ ተገልጧል፡፡ ቀደም ሲል ለተካሄዱት ውይይቶች ግንባር ቀደም ሚና ከነበራቸው ውስጥ እንደ አምባሳደር ካሳ ከበደ ያሉት በአሁኑ ዙር ባይካተቱም ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይሥሐቅ እና ሌሎች ተጨማሪ ሦስት ሽማግሌዎች በውጭ በሚገኙት አባቶች በኩል መዘጋጀታቸው ተጠቁሟል፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)