December 24, 2010

በአባቶች ዕርቀ ሰላም ጉዳይ የተነጋገረው የቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ስብሰባ ተጠናቀቀ

  • በስደት በሚገኙት አባቶች የተሾሙትን ጳጳሳት ለመቀበል ስምምነት ላይ ተደርሷል
  • ቅዱስ ሲኖዶስን በመወከል የሚነጋገሩት የሰላም ልኡካን ተመርጠዋል
(ደጀ ሰላም፤ ዲሴምበር 23/2010 ኅሣሥ 14/2003 .) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በስደት ከሚገኙት አባቶች ጋራ የተጀመረውን የዕርቀ ሰላም ንግግር እና ድርድር ጉዳይ ለማስቀጠል በቀረበው ምክረ ሐሳብ (መርሐ ድርጊት) ላይ በመነጋገር ውሳኔዎችን አሳለፈ፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ትናንት በመንበረ ፓትርያርኩ ባካሄደው የአንድ ቀን አስቸኳይ ስብሰባ በጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በተመረጡት እና ሰባት ብፁዓን አባቶችን ባቀፈው ኮሚቴ በቀረበለት ምክረ ሐሳብ ላይ ጠንካራ ውይይት በማካሄድ አጽድቆታል፡፡ በኮሚቴው ከቀረቡት የምክረ ሐሳቡ ክፍሎች መካከል በምዕራቡ ዓለም በስደት በሚገኙት አባቶች የተሾሙትን 13 ጳጳሳት ስለመቀበል እና ቅዱስ ሲኖዶስን በመወከል በዕርቀ ሰላሙ ላይ ስለሚነጋገሩት ተደራዳሪ ልኡካን የተነሣው ሐሳብ የጋለ ክርክር እንደተካሄደበት ተዘግቧል፡፡
እንደ መንበረ ፓትርያርኩ ምንጮች ገለጻ ለአስቸኳይ ስብሰባው መጠራት ምክንያቱ ባለፈው ሳምንት ኮሚቴው ለቋሚ ሲኖዶሱ ባቀረበው የዕርቀ ሰላም ምክረ ሐሳብ ላይ በተለይም በስደት የተሾሙትን 13ቱን ጳጳሳት በመቀበል ጉዳይ ላይ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ እና ሌላው የቋሚ ሲኖዶሱ አንድ አባል ከተቀሩት የቋሚ ሲኖዶሱ አባላት ጋራ ባለመስማማታቸው ሰነዱ ሊጸድቅ ባለመቻሉ ነው ተብሏል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ‹‹ጳጳሳቱን መቀበል የለብንም›› ቢሉም የተቀሩት የቋሚ ሲኖዶስ አባላት ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት የሚበጅ እስከ ሆነ ድረስ በስደት በሚገኙት አባቶች እንደ የመደራደሪያ አጀንዳ የቀረበውን ‹‹የጳጳሳቱን ሢመት መቀበል›› ተገቢነት እንዳለው የያዘ አቋም አራምደዋል፡፡ 
በዚህ የአቋም ልዩነት የተገታው ምክረ ሐሳቡን (መርሐ ድርጊቱን) በቋሚ ሲኖዶሱ ተቀብሎ የማጽደቅ ጉዳይ ሳቢያ ቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በቋሚ ሲኖዶሱ አባላት ይጠየቃሉ፤ ፓትርያርኩም ሰነዱንም እንደማይፈርሙ፣ አስቸኳይ ስብሰባም መጥራት አስፈላጊ እንዳልሆነ በመግለጽ በአቋማቸው ይጸናሉ፡፡ በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ፓትርያርኩ አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራ በተገቢው የተሰብሳቢ ቁጥር ተጠይቆ ፈቃደኛ ካልሆነ ቋሚ ሲኖዶሱ መጥራት እንደሚችል በተደነገገው መሠረት ይኸው ተገልጦ ይነገራቸዋል፡፡ አቡነ ጳውሎስም አቋማቸውን በማለሳለስ አስቸኳይ ስብሰባ እንደሚጠሩ ነገር ግን የቀረበውን ሰነድ እንደማይፈርሙ በማሳወቅ ስብሰባው እንደተጠራ ተገልጧል፡፡ 
ታኅሣሥ 13 ቀን 2003 ዓ.ም ለአንድ ቀን በተካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ 25 ያህል ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በብዙ ካጨቃጨቁት ጉዳዮች አንዱ በሆነው የ13ቱን ጳጳሳት ሹመት የመቀበል ጉዳይ ሙሉ ስምምነት ላይ ስለመደረሱ ተነግሯል፡፡ ለዕርቀ ሰላሙ ድርድር የደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ፣ የሰሜን ምዕራብ ሸዋ-ሰላሌ እና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፣ የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገሪማ እና የጠቅላይ ቤተ ክህነት የአስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስከያጅ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ በልኡካንነት ተመርጠዋል፡፡ ባለፈው ዓመት በተካሄደው የዕርቀ ሰላም ንግግር ተካፋይ የነበሩት የብፁዕ አቡነ ገሪማ እና የንቡረ እድ ኤልያስ ዳግመኛ መመረጥ ሌላው አጨቃጫቂ ጉዳይ እንደነበር ምንጮቹ አመልክተዋል፡፡ በተለይ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ በጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ላይ በስደት የሚገኙት አባቶች ‹‹ፖሊቲከኞች፣ ዕርቁን የማይሹ ፀረ ሰላሞች›› አድርገው በማቅረባቸው የተሰነዘረባቸውን ተቃውሞ እና ተግሣጽ ያስታወሱ ብፁዓን አባቶች በአሁኑ ሂደት ውስጥ መካተታቸው ‹‹ችግሩን እንደሚያባብሰው›› በመግለጽ ነቅፈው ቢከራከሩም በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ድጋፍ በማግኘታቸው ሊያስቀሯቸው እንዳልተቻላቸው ተመልክቷል፡፡  
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)