December 22, 2010

ጎንደር ጥምቀትን በካርኒቫል ደረጃ ልታከብር ነው

በሔኖክ ያሬድ
 (ሪፖርተር ጋዜጣ፤ Wednesday, 22 December 2010 11:14) ዓመታዊው የጥምቀት በዓል ለመጀመርያ ጊዜ በጎንደር በካርኒቫል ደረጃ ለአምስት ቀናት እንደሚከበር የጎንደር ባህልና ቱሪዝም መምርያ አስታወቀ፡፡ የመምሪያው ኃላፊ አቶ ጌታሁን ሥዩም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከዚህ ቀደም ከጥር 10 እስከ ጥር 12 ቀን ለሦስት ቀናት ይከበር የነበረው የከተራ ጥምቀት በዓል በሁለገብ ዝግጅቶች ለአምስት ቀናት በብሔራዊ ካርኒቫል ደረጃ ይከበራል፡፡
‹‹ኢትዮጵያን በጎንደር ብሔራዊ ካርኒቫል›› በሚል እየተዘጋጀ ያለው ብሔራዊ ካርኒቫል መሠረቱን የጥምቀት በዓል አድርጎ ከጥር 9 ቀን እስከ ጥር 13 ቀን 2003 ዓ.ም. ድረስ በሚቆይ በርካታ ትምህርት ሰጭና መስህባዊ ይዘት ባላቸው ዝግጅቶች የሚደምቅ ነው፡፡

በውጮቹ አጠራር ካርኒቫል አይባል እንጂ በጎዳና ላይ የሚታዩ በርካታ በዓላት እንደ መስቀል ደመራ፣ ከተራ መኖራቸውን ያስታወሱት አቶ ጌታሁን፣ ለቱሪስቶች መስህብነት እንዲያመች ቀኑን በመጨመር በካርኒቫል ደረጃ መከበሩ አገሪቱን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አመልክተዋል፡፡

ከሃይማኖታዊና ባህላዊ አከባበሩ በተጓዳኝ በየመንገዱ ፈንጠዝያውን ሊያስተናግድ የሚችል ባህላዊ መጠጥና ባህላዊ ምግብ የሚኖርበት፣ ጎንደርና አካባቢውን ሊገልጹ የሚችሉ የሸክላና የእንጨት የእደ ጥበብ ውጤቶች የሚታዩበትና የሚገበዩበት ትዕይንት ይኖራል፡፡

ኅብረተሰቡ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ በባህላዊ አልባሳት በሚገኙበት ክብረ በዓል በስምንት ቦታዎች ባህላዊ ባንዶች እንደሚገኙበት ኃላፊው አውስተዋል፡፡ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበርም የዘጠኙ ክልሎች ብሔረሰቦች አልባሳት የሚታዩበት ትዕይንት፣ ላሁንነታችን የዘመናዊ ትምህርት መሠረት የሆነው ያሬዳዊ ዜማና ቅኔ፣ የቆሎ ተማሪዎች ሥርዓት የሚቀርብበት ዝግጅት በየዕለቱ እንደሚኖር ያመለከቱት ኃላፊው፣ ቱሪስቶች ባህላዊውን የኢትዮጵያ ትምህርት እንዲቀስሙ በማድረግ በቁም ጽሕፈት የተጻፈ ምስክር ወረቀት ለመስጠት መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡

በአቶ ጌታሁን አገላለጽ፣ 44ቱ ታቦታት ያሉበት አድባራት መገኛ የኾነችው ጎንደር፣ ከ200 ዓመታት በላይ የኢትዮጵያ መዲና እንደነበረች ይታወቃል፡፡ በዩኔስኮ (የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና ባህል ድርጅት) በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ አብያተ መንግሥትና የስሜን ብሔራዊ ፓርክ መገኛ የኾነችው ጎንደር ያሏትን ቁሳዊና መንፈሳዊ ሀብቶችን የሚያስተዋወቅና አገሪቷን በቱሪዝምና ባህል ተጠቃሚ የሚያደርግ የፓናል (መድረክ) ውይይት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጥናት የሚቀርብበት ዝግጅት ይኖራል፡፡

የከተማዋ አፈ ጉባኤ አቶ ሞገስ መኰንን እንግዳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ካርኒቫሉን ለመታደም ከውጭና ከውስጥ ብዙ ቁጥር ያላቸው ጎብኚዎች የሚገኙ ሲሆን፣ በተለያዩ የመዝናኛ ዝግጅቶችና መንፈሳዊ ትዕይንቶች በዓሉ ድምቀት ያገኛል፡፡

ጎንደር ይህን ታላቅ ሥነ ሥርዓት ወደ ብሔራዊ ብሎም ዓለም አቀፋዊ ይዘት ወዳለው ካርኒቫል በማሸጋገር ከቱሪዝሙ ዘርፍ ተጠቃሚ ለመሆን በሚያስችል መልኩ ኅብረተሰቡን ለማሳተፍ ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አፈጉባኤው ገልጸዋል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com/index.php?option=com_content&view=article&id=4476:2010-12-22-08-16-04&catid=105:2009-11-13-13-47-17&Itemid=625
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)