December 19, 2010

የቀድሞው መንግሥት ባለሥልጣናት ከገና በፊት ሊፈቱ ይችላሉ

(በታምሩ ጽጌና በዘካሪያስ ስንታየሁ ሪፖርተር ጋዜጣ፤ Sunday, 19 December 2010 12:31 ):-
በዘር ማጥፋት ወንጀል ተከሰው በሞት፣ በእድሜ ልክና በዓመታት እስር እንዲቀጡ የተወሰነባቸው የደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ለገና ሊፈቱ እንደሚችሉ ምንጮች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ በወቅቱ የፈጸሙትን የተለያዩ ወንጀሎችን በማመን እግዚአብሔርን፣ ሕዝብንና መንግሥትን ይቅርታ እንዲጠይቁ ከሁለት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ላሉት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን፣ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን፣ በወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነየሱስና በእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሃይማኖት መሪዎች እንዲለምኑላቸው ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት፤ የሃይማኖት መሪዎቹ መንግሥትን፣ ተጎጂዎችንና የተጎጂ ቤተሰቦችን በማነጋገር ይሁንታ በማግኘታቸው ሳይፈቱ እንደማይቀሩ ምንጮቹ ያላቸውን ግምት ተናግረዋል፡፡


አራቱ የሃይማኖት መሪዎች በትናንትናው ዕለት በኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በደርግ ዘመን የተፈጸመውን በደልና ጥፋት፤ በአገራዊ ይቅርታና እርቅ ለመጨረስ ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ የእርቁና የይቅርታው ተካፋይ እንዲሆን ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

የእርቅና የሰላም ሥራ የአገሪቱ ተሀድሶ አንዱ አካል በመሆኑ ከፍተኛ የመንግሥት አካላት እንዲያውቁት መደረጉን የገለጹት የሃይማኖት መሪዎቹ፤ በዘመኑ የተፈጸመው በደል ፈጣሪንም፣ ሰውንም ያሳዘነ እንደነበር በመግለጽ ምሕረትንና ይቅርታን መጠየቅ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ከአራቱም የሃይማኖት ተቋማት የተውጣጣ አብይ ኮሚቴ አቋቁመው ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲሠሩ መቆየታቸውን የገለጹት መሪዎቹ፤ በዘመኑ ጥፋት ሰለባ ከነበሩ ማኅበራት ጋር በመመካከር መግባባት ላይ መደረሱንና በተለይ ከስቃይ ሰለባ ማኅበር መሪዎች ጋር ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው ተግባራትን ማከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡ ከሰማዕታት ሐውልት ግንባታ ማኅበር መሪዎች ጋርም ሲሠሩ መቆየታቸውን አልደበቁም፡፡

በወቅቱ የደረሰው በደልና ጥፋት ሰፊና መላ አገሪቱን ያዳረሰ በመሆኑ በሁሉም ክልሎች የሰላም ልዑካንን መላካቸውን፤ በሁሉም ከተማ የሚገኙትን ተጎጂዎች የሚወከሉ ሁለት ሁለት ሰዎች ተመርጠው በጠቅላላው 500 የሚሆኑ የስቃዩ ሰለባ አባላት በተወከሉበት አዲስ አበባ ውስጥ ታህሳስ 21 ቀን 2003 ዓ.ም. የይሁንታ ቀን እንደሚሆን መሪዎቹ አስታውቀዋል፡፡

ታህሳስ 21 ቀን 2003 ዓ.ም. የሚቀርበውን የይሁንታ ቀን ለመንግሥት እንደሚያቀርቡና መንግሥት እንደተቀበለውም በታህሳስ ወር መጨረሻ የደርግ ዘመን በደልና ጥፋት በብሔራዊ ደረጃ በይቅርታና በእርቅ ተካቶ የዕርቅ በዓል እንደሚደረግና የኢትዮጵያ ዳግም ሕዳሴ እንደሚበሰር መሪዎቹ አረጋግጠዋል፡፡

የሃይማኖት መሪዎቹ ጨምረው እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ የሃይማኖት መሪዎች የጋራ ሥራ ለአፍሪካና ለዓለም ምሳሌ የሆነ ታላቅ የሰላምና ‹‹የእርቀ ሰላም ማዕከል›› ለመመስረት እንቅስቃሴ እንደሚደረግም ገልጸዋል፡፡

በደርግ ዘመን በደረሰው በደልና ጥፋት በርካታ ወገኖች ሕይወታቸውን ማጣታቸውን፣ አካላቸው መጎዳቱን፣ የአእምሮ ሕመምተኛ መሆናቸውን፣ ያለጧሪና ቀባሪ መቅረታቸውን፣ የተበተኑና የተሰደዱ መኖራቸውን በመግለጽ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያስባቸው መሪዎቹ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በተቻለው አቅም እጁን እንዲዘረጋላቸው ጠይቀዋል፡፡

‹‹ይቅርታና እርቁ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን ጨምሮ በውጭ የተሰደዱ የወቅቱ ባለሥልጣናትንና በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት የተፈጸመውንም ጭምር ያጠቃልላል?›› በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹እንደ ሃይማኖት መሪነታችን ማንም ይቅርታ ሲፈልግ መጥቶ ጠይቁልን ካለ እንጠይቃለን፤ ለአሁኑ ግን በሕግ ማለቅ ያለበት ሒደት ተጠናቆና በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ሆነው ይቅርታው እንዲቀርብላቸው የጠየቁትን ብቻ የሚመለከት ነው፤›› ብለዋል፡፡

በተያያዘ ዜና፣ የስቃዩ ሰለባዎች ማኅበር ኃላፊዎችና አባላት የሃይማኖት መሪዎች ያቀረቡት የይቅርታ ጥያቄ እንደማይመለከታቸው እየገለጹ ነው፡፡ የማኅበሩ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ተረፈ ኃይሌ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አራቱም የሃይማኖት መሪዎች በጋራ ሆነው ታሳሪዎችን ለመጠየቅ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ተገኝተው ነበር፡፡

የደርግ ባለሥልጣናትን ሲያነጋግሯቸው፣ ‹‹ሕዝብንና አገርን በድለናል፡፡ የበደልነውን ሕዝብ፣ በተለይ ለሕዝባዊ ሥርዓት ሲታገሉ የነበሩትን ያለ ሕግ እንዲገደሉ አድርገናል፡፡ ከማንም በላይ የተጎጂ ቤተሰቦችን በአደባባይ ይቅርታ መጠየቅ እንፈልጋለን፤›› ማለታቸውን እንደነገሯቸው ነው፡፡

‹‹እኛ በታሰርን ጊዜ ጀርባችን በኤሌክትሪክና በዘይት ሲጠበስ፣ ያለ ሕግና ያለ ፍርድ ወገኖቻችን በአደባባይ ሲገደሉ፣ ክተት ዘመቻ እየተባለ በጄት ሕፃናት ሳይቀሩ ሲደበደቡ፣ አንዳችሁም ምንም ያላችሁን ነገር የለም፤ በታሰርንበትም ጊዜም ቢሆን በብርጭቆ ውኃ አላቀበላችሁንም፤ ላለፉት 19 ዓመታትም ቢሆን የእነዚያ ተጎጂዎችና የስቃይ ሰለባ ቤተሰቦች የት እንዳሉ አልጠየቃችሁም፡፡ ዛሬ ግን ለእነዚህ የደርግ ባለሥልጣናት ይቅርታ ለመጠየቅ መምጣታችሁ ትክክል አይደለም፤›› የሚል ምላሽ ለሃይማኖት መሪዎቹ መስጠታቸውን ምክትል ሊቀመንበሩ ተናግረዋል፡፡

በባለሥልጣናቱ ላይ ክስ ሲመሰረት የተጎጂ ቤተሰቦችን የሚመለከት የካሳ ጥያቄ ጎን ለጎን መሄድ እንደሚገባው ጥያቄ አንስተው እንደነበር የሚናገሩት አቶ ተረፈ፤ እስካሁን ምንም አለማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ በሌሎች አገሮች በዘር ማጥፋት ወንጀል የሚከሰሱ ሰዎች ሲኖሩ፣ ለተጎጂ ወገኖች የካሳ ክፍያ እንደሚከፈልና ተገቢ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የተጎጂ ቤተሰቦች መኖርያ ቤታቸውን ተነጥቀውና በየሜዳው ወድቀው፣ ጉዳት አድራሾች የሚከፍሉት ወይም ንብረታቸው ተሸጦ የሚከፈል የካሣ ክፍያ ባይኖርም፤ የሃይማኖት መሪዎች ሕዝቡንም ሆነ መንግሥትን አነጋግረው የሚረዱበትን መንገድ ሳያመቻቹና ምንም ሳያደርጉ፤ ይቅርታ እንዲደረግላቸው ለመጠየቅ ወደ እነሱ መሄዳቸው አሳፋሪ መሆኑን ምክትል ሊቀመንበሩ ተናግረዋል፡፡

የሃይማኖት መሪዎች የስቃይ ሰለባ ማኅበር ኃላፊዎችን ለማነጋገር በመጡበት ወቅት የማኅበሩ ኃላፊዎች ምንም መወሰን እንደማይችሉና ጠቅላላ ጉባዔ በመጥራት ውሳኔውን እንደሚያሳውቋቸው በመግለጽ እንደሸኟቸው የገለጹት ምክትል ሊቀመንበሩ፣ ‹‹ጉዳታችን ከአእምሯችን ሳይወጣ፤ ለጉዳታችንና ለጠፋው ንብረት ተመጣጣኝ ካሳ ባላገኘነበት ሁኔታ፣ ይኼ ጥያቄ መቅረቡ አሳዛኝ ነው፤›› የሚል መልስ ከጠቅላላ ጉባኤው መተላለፉን እንደነገሯቸው አሳውቀዋል፡፡

‹‹የሃይማኖት አባቶች በመሆናቸው ልናከብራቸው ስለሚገባ ውይይቱ መጀመሩ ይቅርታ ማለት አይደለም፤›› በማለት የሃይማኖት መሪዎቹ ከወከሏቸው አብይ ኮሚቴዎች ጋር ሲነጋገሩ መቆየታቸውን አቶ ተረፈ ገልጸዋል፡፡

ጉዳዩ የሕዝብ ጉዳይ በመሆኑ በኢትዮጵያ ክልል ያሉና ከአገር ውጭ ያሉ ተጎጂዎች መካተት እንዳለባቸው ምክትል ሊቀመንበሩ ተናግረው፤ እንቅስቃሴውም ሆነ ይቅርታ አጠያየቁ በአዲስ አበባ ብቻ መሆኑ የታሪክ ተጠያቂ ስለሚያደርግ፤ ስለ ይቅርታ መነጋገር ያለባቸው የአገር ሽማግሌዎች ወይም የሃይማኖት መሪዎች ሳይሆኑ፣ የግፉና የስቃዩ ገፈት ቀማሽ ወገኖች ብቻ መሆን እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡ ማኅበራቸውም ተጎጂውን ከየክልሉ ለማምጣት እንደሚተባበር እንጂ ስለይቅርታው እንደማያገባው ከመሪዎቹ ጋር መተማመናቸውን አሳውቀዋል፡፡

የስቃይ ሰለባዎች ማኅበር ተወቃሽ መሆን ስለማይፈልግ፤ በየክልሉ ያሉ ተጎጂዎች ተወካዮችን አዲስ አበባ መጥተው ከሃይማኖት መሪዎቹ ጋር እንዲነጋገሩ የማድረግ ሥራ መሥራቱን የገለጹት አቶ ተረፈ፤ ልጆቻቸው፣ አባቶቻቸውና እናቶቻቸው የሞቱባቸው፣ አካላቸው የጎደለ፣ ንብረታቸው የተዘረፈባቸውና አስታዋሽ አጥተው በየጎዳናው የሚኖሩ ወገኖች ባልተካሱበት ሁኔታ ስለእርቅ ማውራት ተጎጂውን የበለጠ መጉዳትና የታሪክ ተጠያቂም እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

መስቀል አደባባይ ላይ የሰማዕታት መታሰቢያ ሃውልት ያስገነቡትን የቀይ ሽብር ቤተሰቦችና ወዳጆች ማኅበር ኃላፊዎች በይቅርታ ልመናው ላይ ያላቸውን አስተያየት ጠይቀን ማኅበሩን ወክሎ መናገር የሚፈልግ አልተገኘም፡፡

‹‹ይኼ የግሌ አቋም ነው›› በሚል አስተያየታቸውን የሰጡን የማኅበሩ የቦርድ አባል አቶ ሰይፈ እሸቴ ሲሆኑ፤ የሃይማኖት መሪዎች ባነሱት ሐሳብ ላይ በግል መነጋገራቸውን እንጂ ማኅበሩን የሚወክል አቋም አለመውሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡

በመሠረተ ሐሳቡ ማኅበሩ ቂም በቀልን የማይደግፍ መሆኑን፣ የተረጋጋ ኢኮኖሚና ማኅበረሰብ እንዲኖር የሚፈልጉ መሆኑንና እርቅና ሰላም ጥሩ ነገር በመሆኑ ሐሳቡን በግላቸው እንደሚደግፉ አቶ ሰይፈ ገልጸዋል፡፡

ከ500 ሺሕ በላይ ሕዝብ የሞተበት ጉዳይ መሆኑንና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ወላጅ፣ ልጅና የልጅ ልጅ በሚሊዮን የሚቆጠሩ በመሆናቸው፣ ሁሉንም በአካል ማነጋገር እንደሚያስፈልግ የገለጹት አቶ ሰይፈ፤ ዋናው ነገር ‹‹ይጠቅማል ወይስ አይጠቅምም?›› የሚለውን ማየት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የቀይ ሽብር ቤተሰቦችና ወዳጆች ማኅበር የቦርድ አባል የሆኑና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ግለሰብ እንደገለጹልን፤ ባለሥልጣናቱ በመጀመሪያ ጊዜ ክስ ሲመሰረትባቸው ‹‹ነፃ ነን›› በማለት ተከራክረዋል፡፡ አሁን ደግሞ ሁሉም ነገር ካለቀ በኋላ ይቅርታ መጠየቅ ማሾፍ ነው፡፡

‹‹የማናውቃቸው ሴራዎችና ወንጀሎች አሉ፡፡ እሱን በግል ይናገሩ፤›› በሚል የሃይማኖት መሪዎቹን ሲጠይቋቸው፣ ‹‹በግል ሳይሆን በጅምላ ጥፋታቸውን ይመኑ›› የሚል ምላሽ መስጠታቸውን የገለጹት የቦርድ አባሉ፤ ‹‹ከቅንጅት በኋላ ጅምላ አይሠራም አልናቸው፤›› ብለዋል፡፡ ክሱ ሲጀመር ነፃ መሆናቸውን በመግለጽ ወደ ክርክር ሳይገቡ ጥፋታቸውን አምነው ይቅርታ ቢጠይቁ ኖሮ ምንም ማለት እንዳልነበር ተናግረው፤ ‹‹አንዳንዶቹ የሃይማኖት መሪዎች የግፉ ተካፋይ ስለነበሩ ከፈለጉ እነሱ ይቅር ይበሏቸው፤›› ብለዋል፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)