December 8, 2010

ከፍተኛ የመንፈሳዊ ትምህርት ተቋማቱ ትኩረትና ድጋፍ ይሻሉ


(ለደጀ ሰላም፤ ከቅ/ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት አንዱ)፦ ፕሮቴስታንቲዝም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን አጥፍቶ ሀገሪቱን ለመረከብ ከአንድ ምዕት ዓመት በላይ የዘለቀ ጥረት አድርጓል፡፡ በዚህ ጥረቱ ከተከተላቸው እና እየተከተላቸው ካሉ ስልቶች አንዱ የቤተክርስቲያንን የክህነትና የስብከተ ወንጌል አገልገሎት እንዲሁም አስተደደር ለመቆጣጠር መሞከር ነው፡፡ በዚህ ስልት መሠረት የአብነት ትምህርት ቤቶቻችንን እና መንፈሳዊ ኮሌጆቻችንን ለመቆጣጠር በርካታ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆኑ ባለፉት ወራት በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የተደረጉ እንቅስቃሴዎችን እናንሣ::

በነሐሴ ወር አካባቢ ለቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አስተዳደር አንድ ግብዣ ቀረበለት፡፡ ግብዣው የቀረበው Proclamtion Trust (http://www.proctrust.org.uk/) ከሚባል ከአንድ በእንግሊዝ ሀገር ከሚገኝ የፕሮቴስታንት ኮሌጅ ሲሆን ግብዣው የቀረበው በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በሚያስተምር በአንድ እንግሊዛዊ ፕሮቴስታንት አማካኝነት ነው፡፡

በግብዣው መሠረት ከሆነ ለኮሌጁ 30,000 ብር ያህል ይሰጠዋል፡፡ ኮሌጁ በዚህ ብር ለቀድሞ ተመራቂዎቹ የአምስት ቀናት ሴሚናር ያዘጋጃል፡፡ በዚህ ሴሚናር ላይ ዳግላስ ደንስ የተባለ ፓስተር የፕሮክላሜሽን ትረስት የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ "ሥነ ፍጥረት፣ የሰው ልጅ አወዳደቅ፣ ነገረ ድኅነት እና እግዚአብሔር ለዚህ ዓለም ስላለው ዕቅድ" ያስተምራል፡፡

ከዚህ አስገራሚ ግብዣ ጋር የሚከተሉት ጉዳዮችም ልብ ሊባሉ ይገባል፡፡
  • Proclamation trust ለዚህ ለኮሌጁ ርዳታ የሰጠው ስም Mission of help /የዕርዳታ ተልዕኮ/ የሚል ነው፡፡ ይህ ስም 20ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ አንግሊካን ቤተ ክርስቲያን በቅኝ ግዛት በያዘቻቸው ቦታዎች የተሃድሶን እንቅስቃሴ ለመጀመር እንደ መግቢያ ለተጠቀመችበት ርዳታ ሲሰጥ የኖረ ስም ነው፡፡
  • Proclamation trust በኮሌጃችን የሚገኘውን አስተምህሮ ፕሮቴስታንታዊ ለማድረግ ለኮሌጁ መምህራን ነጻ የትምህርት ዕድል በመስጠት በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ መሠረት ያለ ኮሌጁ እውቅና አንዳንድ መምህራን ወደ እንግሊዝ በመሔድ እየሠለጠኑ ነው፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ይህንን proclamation trust ግብዣ ወደ ኮሌጅ ያመጡትና ሲያራግቡት የቆዩት በዚሁ የትምህርት ዕድል የተማሩና ለመማር በዝግጅት ላይ ያሉ የኮሌጅ ሠራተኞች ነበሩ፡፡ ወደፊትም ከኮሌጁ አባላት ባሻገር ተመሳሳይ የትምህርት ዕድል ለሌሎችም የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ለመስጠት መታቀዱም ታውቋል፡፡

ምን ተወሰነ?
Proclamation trust ባቀረበው ግብዣ ላይ ለመወያየት የኮሌጁ አካዳሚክ ኮሚሽን ተሰበሰበ፡፡ በዚህ ውይይት ላይ ሁሉም በተለይም Father Dr. Josie (Jose) Jacob (በኮሌጁ በማስተማር ላይ ያለ የሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ካህን) ሊመጣ ያለውን አደጋ በግልጽ በማሳየት በምንም ዓይነት ፕሮቴስታንቶች ወደ ኮሌጅ ሊገቡበት የሚችሉበት መንገድ መክፈት እንደሌለበት ተናገሩ፤ ተቃወሙ፡፡ ርዳታውን ልንቀበለው የምንችለው ትምህርቱ በኦርቶዶክሳውያን መምህራን ከተሰጠ ብቻ ነው የሚል ውሳኔም ተወሰነ፡፡

ይኸው ውሳኔ ለድርጅቱ ሲነገረውም ተቃውሞው የመጣው ከየት እንደሆነ በማወቁ Fr.Josie Jacob ከአምስቱ ቀን ለሁለት ሰዓታት ያህል እንዲያስተምሩ እንፍቀድላቸው የሚል አሳበ አቀረበ፡፡ ይህም አሳብ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ የኮሌጁ ዲን ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስይሁዳ ጌታን 30 ብር እንደሸጠው ቤተ ክርስቲያናችንን 30,000 ብር ለመሸጥ ፈቃደኛ አይደለንምበማለት ቁርጥ አቋማቸውን ጥያቄውን ሲያራግቡ ለነበሩ ግለሰቦች አቀረቡ፡፡ በዚህም መሠረት የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ግብዣውን እንደማይቀበል በአካዳሚክ ዲኑ በመ/ ፍስሐ ጽዮን ደመወዝ አማካኝነት proclamation trust  ተነገረው፡፡

ማጠቃለያ
  • ኮሌጁ እስከ አሁን እንዳደረገው ኢኮኖሚያዊ ችግሩን ችሎ ለመናፍቃን ባለመንበርከክ መቀጠል አለበት፡፡ ኦርቶዶክሳዊ አቋም ይዘው፣ ወስነው ለተገበሩት ምስጋና ይገባቸዋል፤ መጨረሻቸውን ያሳምርልን፡፡
  • መናፍቃኑ ይህን ጥያቄ ለማቅረብ ብር ያገኙት ከኮሌጁ ላይ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ችግር እንደ በር በመጠቀም ነው፡፡ ስለዚህ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ኮሌጁን ለማጠናከር በቂ በጀት መመደብ ይገባዋል፡፡ ይህ እስኪሆን ድረስም ሁላችንም የኮሌጁን አቅም ለማጠናከር የተለያዩ ጽጋፎችን ማድረግ ይገባናል፡፡ አንድን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ለማሠራት በርካታ ሚሊዮኖችን እናወጣለን፡፡ ይህ መልካም ነው፡፡ የነገይቱ ቤተክርስቲያን መሠረት ለሆነው ለዚህ ኮሌጅ ደግሞ ከዚህ የበለጠ ሊደረግለት ይገባል፡፡ ኮሌጁም ለዚህ መዘጋጀት፣ ፕሮጀክቶችን መቅረጽ፣ ምእመናንን ማሳተፍ ይገባዋል፡፡
  • ኮሌጁን ከእነዚህ ቅሰጣዎች ለመጠበቅ አርበኛ በሆኑት መምህራን ላይ የመናፍቅነት ታርጋ የመለጠፍና የማሰጠት፣ በላያቸው ላይ ተማሪ የማሳመጽ፣ የማስፈራራት እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡ በዚሁ ብሎግ ላይም ስለ Fr.Josie የተጻፈ አንድ ሁለት የፈጠራ ክሶችንና አስተያየቶችን አይተናል፡፡ በብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ላይ እየተነሱ ያሉ ክሶችም ተመሳሳይ ዓላማ አላቸው፡፡ ኮሌጁን ያለ አጥር የማስቀረት ሙከራዎች ናቸውና ልንነቃባቸው ይገባል፡፡
  • ወደ ፕሮቴስታንት ኮሌጆች እየሔዱ የሚማሩ የቤተክርስቲያናችን አገልጋዮች ጉዳይም አንድ ሊባል ይገባል፤ በኮሌጁም፣ በቤተ ክርስተያን አስተዳደርም፡፡
  • በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የተሞከረው በዚህ ጽሑፍ የቀረበው ነገር በሁሉም ተቋማቶቻችን ለሚሞከረው ነገር ማሳያ ነው፡፡ ለምሳሌ ይኸው “proclamation trust” ዕቅድ በመቀሌው የከሳቴ ብርሃን ኮሌጅ ተቀባይነት አግኝቶ መተግበሩም ተሰምቷል፡፡ ስለዚህ የዚህ ጽሑፍ መልእክት ሁሉም ከፍተኛ መንፈሳዊ የትምህርት ተቋማት ካሉ መምህራን፣ ተማሪዎች እና አስተዳደር አካላት ነው፡፡

ቸር ወሬ ያሰማን፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)