December 4, 2010

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አንድ ተማሪውን ከትምህርት አገደ

(ደጀ ሰላም፤ ዲሴምበር 4/2010 ኅዳር 25/2003 .) የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አስተዳደር ጉባኤ ለአዲስ ተመዝጋቢ ደቀ መዛሙርት ባስቀመጠው መስፈርት መሠረት ‹‹ከተቋሙ የቅበላ መስፈርቶች አንዱ የሆነውን በሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ወይም በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ የተፈረመበት የድጋፍ ደብዳቤ በተሰጠው ጊዜ ገደብ ውስጥ አላቀረበም፤ በድጋፍ ደብዳቤ ስም ያቀረበውም ማስረጃ ተቀባይነት የሌለው ነው፤ ከአንድ ወር በላይ በትምህርት ገበታው ላይ አልተገኘም››፣  ከሬጅስትራሩ፣ ከአካዳሚክ ዲኑ እና ከበላይ ሐላፊው ዕውቅና ውጭ ወደ ኮሌጁ በሕገ ወጥ መንገድ በመግባት ትምህርት ጀምሯል ያለውን አሰግድ ሣህለ የተባለ ተማሪ አገደ፡፡

የኮሌጁ ደቀ መዛሙርት እና የመምህራን ጉባኤ ቀድሞም የአሰግድ ሃይማኖታዊ አቅዋም እና ኦርቶዶክሳዊነት ይጎድለዋል በሚል ሲያቀርቡ በቆዩት ቅሬታ መነሻነት የግለሰቡን አገባብ የመረመረው የአስተዳደር ጉባኤው፣ በማታው መርሐ ግብር ተመዝግቦ በቀኑ መደበኛ የትምህርት ክፍለ ጊዜ ትምህርቱን በተመላላሽነት እንዲቀጥል በኮሌጁ የቀን እና የማታ መርሐ ግብር ሐላፊ የተሰጠው ፈቃድ አግባብነት እንደሌለው በሙሉ ድምፅ ባስተላለፈው ውሳኔው አመልክቷል፡፡

ቀደም ሲል በኮሌጁ የዲፕሎማ ፕሮግራም ተመዝግቦ ትምህርቱን የተከታተለው አሰግድ የኑፋቄ እንቅስቃሴ አራማጅ ነው በሚል ዲፕሎማው ሳይሰጠው ተይዞበት የቆየ ሲሆን ዘግይቶ የወሰደውን ዲፕሎማ መነሻ በማድረግ በዲግሪው መርሐ ግብር ለመቀጠል በበርካታ አጋጣሚዎች አመልክቶ የነበረ ቢሆንም በየጊዜው በሐላፊነት ላይ በነበሩት አካዳሚክ ዲኖች እና የቀኑ እና የማታው መርሐ ግብር ሐላፊዎች ማመልከቻው ውድቅ ሲደረግበት ቆይቷል ተብሏል፡፡

በዚህ የተነሣ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን አሰግድ በይፋ ከሚታወቀው የኮሌጁ የቅበላ መስፈርት እና በየደረጃው ከሚገኙት የአስተዳደር ጉባኤው አባላት ዕውቅና ውጭ ወደ ኮሌጁ ለመግባት ሙከራ ማድረጉ ተመልክቷል፡፡ የማታው መርሐ ግብር ሐላፊ በሆኑ አንድ ሰ ርዳታ የአሰግድ ማመልከቻ በሬጅስትራሩ እንዲፈረምበት በማድረግ ግለሰቡ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን በስመ ተማሪ ለመጠራት እንደበቃ ተገልጧል፡፡

ኮሌጁ ትምህርታቸውን በዲፕሎማ ያጠናቀቁ ደቀ መዛሙርት ከምረቃ በኋላ የነበራቸውን የአገልግሎት ቆይታ፣ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ቢፈቀድላቸው ቤተ ክርስቲያኒቱን ተመልሰው ለማገልገል ያላቸውን ዝግጁነት የሚገልጥ ለዚህም ሐላፊነት ወስዶ የሚያረጋግጥ የሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ወይም የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ፊርማ እና ማኅተም ያረፈበት ሕጋዊ ሆኖ የወጣ ደብዳቤ ሲያገልግሉ ከቆዩባቸው ስፍራዎች እንዲያመጡ ይጠይቃል፤ አሰግድም ሃይማኖታዊ አቋሙ የተነሣ ወደ ኮሌጁ እንዲገባ በመፈቀዱ ስጋት የገባቸው የኮሌጁ ማኅበረሰብ አባላት ያቀረቡትን ቅሬታ መነሻ በማድረግ ይህንኑ ሕጋዊ የድጋፍ ደብዳቤ ሲያገለግል ከቆየበት ስፍራ በተሰጠው ጊዜ ገደብ እንዲያመጣ በኮሌጁ የበላይ ሐላፊ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ተጠይቋል፡፡

ሲያገለግል የቆየበት አጥቢያ ምሥራቀ ፀሐይ ቀበና መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን መሆኑን ለበላይ ሐላፊው የተናገረው አሰግድ የድጋፍ ደብዳቤውን ቢጠይቅም በአሁኑ ወቅት አባልም አገልጋይም ባለመሆኑ ሊጻፍለት እንደማይችል ይነገረዋል፡፡ በመቀጠል ወደ የበግ ለምድ ለብሶ ከአጽራረ ቤተ ክርስቲያን በሚጎርፍለት የገንዘብ ድጋፍ የተሐድሶ ኑፋቄውን ሲያራምድ ተጋልጦ ወደተባረረበት የደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን ቢያመራም የጠየቀው ሕጋዊ ደብዳቤ ሊሰጠው እንደማይችል በደብሩ አስተዳዳሪ ይገለጽለታል፡፡ ይሁንና በዚህ ካፈርኩ አይመልሰኝ በማለት የደብሩን ጸሐፊ በማግባባት በዲያቆኑ የተፈረመበትን ደብዳቤ ለኮሌጁ በማስረጃነት ያቀርባል፡፡

ኅዳር 23 ቀን 2003 ዓ.ም ጠዋት ደብዳቤውን መነሻ በማድረግ በጉዳዩ ላይ የተወያየው የኮሌጁ አስተዳደር ጉባኤ፣ አሰግድ አገለገልሁበት ብሎ ከገለጸው አጥቢያ ‹‹የድጋፍ ደብዳቤ›› ማቅረብ ባለመቻሉ፣ ‹‹የድጋፍ ደብዳቤ›› ብሎ ያቀረበውም በደብሩ አስተዳደር ታምኖበት በአለቃው የተፈረመበት ባለመሆኑ ሕጋዊነት እንደሌለው አረጋግጧል፡፡ በተጨማሪም በሕገ ወጥ መንገድ በማታው መርሐ ግብር ተመዝግቦ በቀኑ መርሐ ግብር በመመላለስ ከጀመረው የትምህርት ገበታ ከአንድ ወር በላይ ባለመገኘቱ ኮሌጁ ከእንግዲህ በተማሪነት ሊቀበለው እንደማይችል በሙሉ ድምፅ ስምምነት ላይ በመድረስ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

በደቡብ ኢትዮጵያ እና በተለያዩ አህጉረ ስብከት በዚህ ተግባሩ ሲንቀሳቀስ የቆየው አሰግድ ሣህለ ከኅዳር ወር የመጀመሪያ ሳምንት አንሥቶ በተባበሩት ዐረብ ኤምሬትስ እና በሊባኖስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሆኑት ብፁዕ አቡነ ዲሜጥሮስ ባልተባረከው፣ በአህጉረ ስብከቱ ምእመናን መካከል ሁከት በመፍጠራቸው ውግዘት በተላለፈባቸው የጥቅም እና የኑፋቄ ቡድን አባላት በተቋቋመው ‹‹ዱባይ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን›› ሲንቀሳቀስ ሰንብቶ ወደጠፋበት የትምህርት ገበታው ቢመለስም ውሳኔው በሚመለከተው የአስተዳደር ሐላፊ በአስቸኳይ ተገልጾ እንደሚሰናበት ለመረዳት ተችሏል፡፡ ይህን የኮሌጁን ውሳኔ ተከትሎ በነገረ መለኮት ምሩቃን ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ ውስጥ ገንዘብ ያዥ ሆኖ የተመረጠበት ሐላፊነቱ በማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ጥያቄ ውስጥ እንደሚወድቅ ተጠቁሟል፡፡

ውሳኔውን አስመልክቶ አስተያየታቸው የሰጡ ታዛቢዎች እንደገለጹት፣ የኮሌጁ አስተዳደር ዘግይቶም ቢሆን ይህን ጥንቃቄ የተመላበት ርምጃ መውሰዱ በተቋሙ እና በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ መዋቅራዊ በሆነ መልኩ የሚገኙትን የተሐድሶ መናፍቃን ለመቋቋም በቀናዒ ኦርቶዶክሳውያን ለሚደረገው እንቅስቃሴ ብርታት የሚሰጥ ነው፡፡

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)