December 3, 2010

ፍርድ ቤቱ በጋሻው ደሳለኝን በነጻ አሰናበተ

(ደጀ ሰላም፤ ዲሴምበር 2/2010፤ ኅዳር 23/2003 ዓ.ም)፦ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የድሬዳዋ ማእከል የስም ማጥፋት ወንጀል ክስ የቀረበበት በጋሻው ደሳለኝ ከቀረበበት ክስ በነጻ ተሰናበተ፡፡ የድሬዳዋ አስተዳደር ካውንስል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዛሬ ጠዋት ኅዳር 23 ቀን 2003 ዓ.ም ውሳኔ የሰጠው ተከሳሹ በጋሻው ደሳለኝ ሚያዝያ 19 ቀን 2002 ዓ.ም በሳባ ደብረ ኀይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን፣ “አንድ ማኅበር አለ - ማኅበረ ቅዱሳን የሚባል፡፡ ደም አፍሳሽ ማኅበር፣ የወንድሞችን ደም በጣሳ እየተቀበሉ ለመጠጣት የተዘጋጁ. . .” በማለት ያሰማው ንግግር “አያስከስስም” በሚል ነው፡፡ ውሳኔው ጉዳዩን በሚከታተሉ ሌሎች የፍትሕ አካላት እና የሕግ ባለሙያዎች ዘንድ ከፈጠረው መደናገር የተነሣ በጥንቃቄ እየተጤነ እንደሆነ ተገልጧል፡፡


ተከሳሹ በዚህ መልክ የገለጻቸው “አንዳንድ የዋሃን የማኅበሩን አባላት” እንደማያካትት ማስረዳቱ ለፍርድ ቤቱ ውሳኔ መሠረት እንደ ሆነ ተገልጧል፡፡ ሆኖም ለፍርድ ቤቱ በማስረጃነት በቀረበው የድምፅ ማስረጃ በጋሻው የወነጀለው በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የመተዳደሪያ ደንቡ ከአንድም ሦስቴ እየተሻሻለ የጸደቀለትን፣ በሀገር ውስጥ እና በባሕር ማዶ በዘረጋቸው መዋቅሮቹ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊ እና ልማታዊ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘውን ማኅበረ ቅዱሳንን እንደ ተቋም መሆኑ በግልጽ ይደመጣል፡፡ ግለሰቡ ለፍርድ ቤቱ በሰጠው የእምነት ክሕደት ቃል “ንግግሬ አንዳንድ የዋሃንን አይመለከትም” ማለቱ “አንዳንዶቹ የዋሃን” እንደምን ከደሙ ንጹሕ እንደ ሆኑ አልያም ብዙኀኑ እንደምን “የደም ሰዎች” እንደሆኑ የተጠየቀውም ያቀረበውም መረጃም ማስረጃም የለም፡፡ በውሳኔው ላይ ዐቃቤ ሕግ ይግባኝ ለመጠየቅ እየመከረበት መሆኑ ተመልክቷል፡፡


በሌላ በኩል በጋሻው “በተስፋ ኪዳነ ምሕረት” ማኅበር እንደተዘጋጀ በተገለጸውና ተከሳሹ “እልፍ እልፍ በሉ” የሚለውን ቪሲዲውን ለማስተዋወቅ ያሳተመውን ቲ - ሸርት ወጣቶች በብዛት ለብሰው እንዲያጅቡት ያደረገው ጥረት እንዳልያዘለት ተገልጧል፡፡ በጋሻው “ውዴ ልበልህ ሽልማቴ” በሚል በጻፈው ግጥም እንደሚቀነቀንለት የሚናገሩት ታዛቢዎች በደጋፊዎቹ በኩል ከቀርሳ ቅዱስ ጊዮርጊስ እስከ ድሬዳዋ የጠየቃቸው የትምህርት ቤት ወጣቶች እና የባጃጅ ታክሲ ሹፌሮች “በወንጀል የተከሰሰን ግለሰብ አናጅብም” በማለታቸው ሳይሳካላት ቀርቷል፡፡


ከፍርድ ቤቱ ውሳኔ በኋላ ደጋፊዎቹ ወደ ሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ጽ/ቤት በማምራት “በጋሻው ከክሱ በነጻ ስለተሰናበተልን እንዲያስተምር ይፈቀድለት” የሚል ጥያቄ ቢያቀርቡም ሥራ አስኪያጁ መጋቤ ጥበብ ናሁ ሠናይ ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገሪማ በተቀበሉት መመሪያ መሠረት በምንም መልኩ እንደማይፈቀድ መልስ ሲሰጧቸው የስድብ ቃል እየተናገሩ ከቢሮው ወጥተው ሄደዋል፡፡


በጋሻው ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ውሳኔ አስቀድሞ እንደሚያውቅ በሚያሳብቅ አኳኋን “ነጻ መውጣቱን ምክንያት በማድረግ” በሚል በተዘጋጀው ምሳ ግብዣ ላይ አብረውት የዋሉትና የሀገረ ስብከቱ መመሪያ ያልገዛቸው ጥቂት ግብረ በላዎቹ በሳባ ደብረ ኀይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን እና በሌሎችም አካባቢዎች የግለሰቡ እና መሰሎቹ ፎቶ ግራፍ ያለበት “ወደ በጉ ሠርግ የተጠሩ ብፁዓን ናቸው” የሚል ፖስተር በመለጠፍ ዐውደ ምሕረቱን በኀይል ለመቆጣጠር መሞከራቸው ተጠቁሟል፡፡ ፖሊስ በጋሻው ከዚህ ድርጊቱ እንዲታቀብ አልያም ከተማውን በአስቸኳይ ለቆ እንዲወጣ ትእዛዝ መስጠቱ የተዘገበ ሲሆን የደብሩ አስተዳደርም የስብከተ ወንጌል ኮሚቴው ከሀገረ ስብከቱ የተሰጠውን መምሪያ እንዲያስከብር አሳስቧል፡፡ ይሁንና ዘግይቶ በደረሰን መረጃ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ በተዘጋበት እና የድምፅ ማጉያ መሣሪያው በተከለከለበት ሁኔታ በጋሻው አስጭኖ የመጣውን ሞንታርቦ በመያዝ ዛሬ ማምሻውን ወደ ቅጽረ ቤተ ክርስቲያኑ ከቲፎዞዎቹ ጋራ በመግባት፣ “ብዙዎች በመንግሥትም ይሁን በቤተ ክህነት እኛን ለማሳገድ ደብዳቤ በመጻፍ እና በመክሰስ ጥረት ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም፤ ከክሱ ነጻ ወጥተናል፤ ዛሬም ሆነ ለወደፊት ማንም ከመድረክ ሊያግደን አይችልም. . .” የሚል ንግግር ሲያሰማ መቆየቱ ተገልጧል፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)