November 2, 2010

ለድል ወንበሩ እና ለመሰሎቹ

(አብርሃም ሰሎሞን እንደጻፈው):- መጠነ ሰፊ የሆነ ማብራሪያ ለመስጠት የሞከረው ድል ወንበሩ ስለ ሐውልቱ በተቀኘው የእንግሊዝኛ ቅኔ ኃይለሥላሴን እና ሌሎች ነገሥታትን፣ አቡነ ቴዎፍሎስን እና መንግሥቱ ኃይለማርያምን፣ ከዚያም ወጣ ብሎ የግብፁን ፓትርያርክ አቡነ ሺኖዳን በመጥቀስ በተለያየ ጊዜ የተሠራላቸውን ስዕላትና ሐውልት ካየውም ከሰማውም እንዲሁም ከጉግል ውስጥ ገብቶ ከጎለጎለው ማስረጃ በመነሣት እስኪ መልሱልኝ የሚል ጥያቄ አቅርቧል። እንዲያውም የሚያሳምነኝ ካለ እኔም የይፍረስ ስምምነቱን አስተሳሰብ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ ይለናል። አንዳንዶችም በሰጡት አስተያየት የሰማዕቱን የቅዱስ አቡነ ጴጥሮስን ሐውልት ስንቀበል እንዴት የአቡነ ጳውሎስን ሐውልት ለመቀበል ልባችንን እናከብዳለን? በማለት ቅዱስ ሲኖዶሳችን መክሮ እና ዘክሮ ያስተላለፈውን ውሳኔ ለመቀልበስ የተደረገውን ሙከራ ይበል የሚያሰኝ ነው፤ እሰይ ድል ወንበሩ፤ አበጀህ፤ ደግ አድርገኻል በማለት አሞካሽተውታል። አሁን ጥያቄው እኛ ማንን እንስማ፤ ድልወንበሩን ወይስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቅዱስ ሲኖዶስን? መልሱን ለአንባብያን እተውና እኔ ጥቂት ከድል ወንበሩ ነጋ አስተያየት ጋር እሞግታለሁ።
በመጽሐፈ ምሳሌ አንበጣዎች ንጉሥ የላቸውም፤ ሁላቸውም ግን በመልካም ሥርዓት ይሄዳሉ የሚል ቃል ተጽፎ እናገኛለን። ንጉሥ የሌላቸው በመልካም ሥርዓት ሲሄዱ ንጉሥና መሪ ያላቸው በሥርዓት ለመሄድ እንዴት አልቻሉም? በእናንተ ዘንድ ሁሉ በሥርዓቱና በአግባቡ ይሁን ማለትስ ምን ማለት ነው? የነገን አላውቀውም እንጂ እስከ አሁን ባለው የቤተ ክርስቲያኒቱ አካሄድ ቀኖና ቤተክርስቲያንን ማጽደቅና መሻር የሚችሉት በሲኖዶስ ወንበር የተቀመጡት ጳጳሳት እንጂ በፓርላማ ወንበር የተቀመጡት አመራሮች እንዳልሆኑ የአደባባይ ምሥጢር ነው።
ሐውልቱን ማን አሠራው?
የፕትርክናውን ወንበር ከያዙ ጀምሮ አንዳች ነገር አልሠሩም ለማለት ሳይሆን የፓትርያርኩ ገድል እና ትሩፋት ሞልቶ በመትረፉ፣ መልካም ሥራቸው በዓለም በመዳረሱ፣ ዕርቀ ሰላም የማምጣት ሙከራቸው ስኬታማ በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶሱ ሐውልት ይገባቸዋልና እናቁምላቸው በማለት በቃለ-ጉባኤ አጽድቆ እና ሥራቸውን በየአብያተ ክርስቲያኑ አስመስክሮ በዚህ ስፍራ ለስማቸው መጠሪያ እና መታሰቢያ እንዲሆን ቦታ መርጦላቸው የተተከለ ሐውልት አይደለም። ፓትርያርኩን ፓትርያርክ ብሎ የሾመ ቅዱስ ሲኖዶስ በመሆኑ በሃይማኖት መሪነታቸው እንዲህ ይደረግላቸው ማለት የሚችለው ቅዱስ ሲኖዶሱ ነው እንጂ ጥቂት ጥቅመኞች መሆን አይገባቸውም። እንወደድ ብለውና የቤተ ክርስቲያኒቱን ሀብት ለመመዝበር እንዲያመቻቸው መንገድ ለማበጀት ሲሉ ዛሬን እንጂ ነገን ሳይመለከቱ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል በሚል ዘዬ የተከሉትን እውቅና የሌለውን ሥራ ቅዱስ ሲኖዶስ በፓትርያርኩ ሐውልት ቀንቶ ሳይሆን በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እይታ ፈቃጅ እና ከልካይ ማን እንደሆነ ለማሳየት እና ይኼን ቅጥ ያጣ አካሄድ መልክ ለማስያዝ ነው። በሚሊኒየሙ ጊዜ በየአብያተ ክርስቲያኑ ለተሰቀለው ምስል ቅዱስ ሲኖዶሱ ያላጸደቀው እና መሆን አለበት ያላለው ጉዳይ መሆኑን ቢያምንበትም ለፓትርያርኩ ካስደሰተና ውዳሴ ከንቱ ካላሰኘባቸው ይሁን ብለው አልፈውት እንጂ ይኼም ቢሆን በቅዱስ ሲኖዶስ ያልጸደቀ ጉዳይ ነው። አማካሪዎቻቸው አብረዋቸው ያሉት ጳጳሳት ሳይሆኑ በምንም የማይመስሏቸው ግለሰቦች ናቸውና ለምን ለጸሎት ተንበርክከው ፎቶግራፍ አንሥተንዎት የሰማይ ስባሪ የሚያህል ምስልዎት በየአብያተ ክርስቲያኑ አይሰቀልም ያሉ እንወደድ ባዮች እንጂ ሲኖዶስ መክሮበት አይደለም። የትናንቱ ምስል ዛሬ ወደ ሐውልትነት መልኩን ለውጦ ብቅ ሲልና በቤቱ ሰው የለም እንዴ እስከሚያስብል በማነጋገሩ ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔውን መክሮበት እና አምኖበት ተፈጻሚ የሚሆንበትን መንገድ አሳይቷል። በእርግጥ ምነው በእንቁላሉ ጊዜ በቀጣሽኝ እንዳለው ሌባ በመጀመርያ በእንቁላሉ ጊዜ ስለተሰቀለው ምስል ሲኖዶሱ በስብሰባው ጊዜ ጠቅሶ ቢሆን ኖሮ የዛሬው ድንጋይ ያለቦታው ተተክሎ አያነጋግረንም ነበር። ምሳላቸውስ ቢሆን በቅዳሴ ሰዓት መሥዋዕት ሲያሳርጉ እና ሕዝቡን ሲባርኩ ቢሆን ምን ነበረበት? ግለሰቦቹ ሊወደዱ የሚገባቸው እንደእነርሱ ፍላጎት ሲሄዱላቸው በመሆኑ እዚችጋ ተንበርከኩና አንድ ፎቶግራፍ፣ እዛችጋ ደገፍ በሉና ሌላ አንድ ፎቶግራፍ፣ እጅዎትን ከፍ አድርገው ዘርጉ እና ተጨማሪ ፎቶግራፍ ተነሡ በማለት በጸሎት ተመስጦ ውስጥ የሌለ ምስል መነሣትም ባላስፈለገ ነበር። በሌላ መልኩ ደግሞ ደም ለሚፈስበት ጦርነት እንኳን ምክር እና ክተት አዋጅ ያስፈልገዋል። እንዲህ ይሁን ተብሎ ውጊያ የሚጀመረው ፓርላማው ወይም ደግሞ የሚመለከተው ክፍል አጽድቆት እንጂ እንዲሁ አንድ መሪ ከጥቂት ሰዎች ጋር ተነጋግሮ ተዋግቼ መጣሁ የሚለው ጉዳይ አይደለም። ለመጥፎም ይሁን ለጥሩ ነገር የሚመለከታቸው ክፍሎች ይነጋገሩበታል። መንፈስ ቅዱስ የሚመራውን የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ውድቅ ለማድረግ ሌሎች ነገሥታትን መጥቀስ አስፈላጊነቱ ጠቀሜታ ያለው አይመስለኝም። 
የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት፡-
ለአንዲት ቅድስት ለሆነች ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እና ለቅድስት አገራችን ለኢትዮጵያ ብለው ግምባራቸውን ባለማጠፋቸው ኦርቶዶክሱ ብቻ ሳይሆን እስላሙም ጀግንነታቸውን መስክሮላቸው፣ የዓለም ሕዝብ ታሪካቸውን አውርቶላቸው እና ዝናቸውን (ገድላቸውን) ጽፎላቸው፤ የይገባል ስምምነት ተደርሶ በመሐል አዲስ አበባ ሐውልታቸው ቆሟል። በእርግጥም በዚህ የሚያንጎራጉር ኢትዮጵያዊ የለም፤ አቡነ ጳውሎስም አንዳች ቃል አይተነፍሱም።  አሁንም በቅርቡ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ዓለም መስክሮላቸው ሐውልታቸው በስማቸው በተሰየመው ቤተ ክርስቲያን ቆሞላቸዋል። ይኽ ግን በገድላቸው እና በትሩፋታቸው ተመስክሮላቸው ያገኙት እንጂ በድብቅብቅ የተሠራ ጉዳይ አለመሆኑን ልብ ይሏል። 
የግብፅ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያን፡-
ፓትርያርክ አቡነ ሺኑዳ በሚኖሩበት አገር ሐውልት ቆሞላቸው ከሆነ በእርግጠኝነት ያ ሐውልት የቆመው ቅዱስ ሲኖዳሳቸው ስለሥራቸው መታሰቢያ ይሆን ዘንድ አምኖበት በገሐድ እንጂ በእኛ ዘንድ እንደተተከለው ሐውልት ጥቅመኞች ያደረጉት አይመስለኝም። ደግሞስ አቡነ ሺኑዳ ሐውልት ስላቆሙ እኔስ ከማን አንሼ ነው ሐውልት የማይቆምልኝ ይባላል እንዴ? እንደዛ ከሆነስ ሰው የሚስማማውን ነገር ብቻ ነው እንዴ ከአንድ ሰው መማር የሚገባው? ለምን አቡነ ሺኑዳ ከመቶ በላይ መጻሕፍት ጽፈዋል እኔስ እንዴት አልጽፍም በማለት መጻሕፍትን አልጻፉም? ለምን አቡነ ሺኑዳ በየሳምንቱ ረቡዕ ቀን ጉባኤ በመዘርጋት የኦርቶዶክሳውያኑን ሃይማኖታዊም ሆነ ማኅበራዊ ጥያቄዎቻቸውን እንደሚመልሱት አቡነ ጳውሎስ ለመመለስ አልተዘጋጁም? ለምን አቡነ ሺኑዳ ሕዝቤ ተገደለ በማለት መንግሥት ፊት ቀርበው እምባቸውን እንዳነቡት አቡነ ጳውሎስ ወገኔ አለቀ በማለት መንግሥት ፊት ቀርበው አላለቀሱም? ለምን አቡነ ሺኑዳ ተቀማጭነታቸውን ገዳም እንዳደረጉት አቡነ ጳውሎስ ለጸሎት ተስማሚ የሆነውን ቦታ መርጠው ተቀማጭነታቸውን ገዳም አላደረጉም? ለምን አቡነ ሺኑዳ የግብፅን ገዳማት ብዙ ሚሊዮን ብር በማፍሰስ ሲሠሩ እና ቤተ ክርስቲያኒቱን አሥራት ከሕዝቡ በማስወጣት ሲያሳድጉ አቡነ ጳውሎስ ይኼን ግብራቸውን ወስደውላቸው ቤተ ክርስቲያንን አላሰደጉም? ወ.ዘ.ተ. ስለዚህም ድልወንበሩ ለዚህ ጥያቄም እራስህን አዘጋጅተህ ጽሑፍን ጻፍ እንጂ ግብፅ ስትስማማ እኛ እንዴት አንስማማም ብለህ አትንገረን። ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ጣልያን የመጣው ሃይማኖት ሊያጠፋ ነው በማለት አልገዛም ሲሉ ያንጊዜ እኮ የግብፁ አቡነ ቄርሎስ ተስማምተው እና ፈቅደው አቡነ ጴጥሮስም እንዲስማሙ መክረዋቸዋል። ታዲያ ግብፅ ተስማምታለች ብለው አቡነ ጴጥሮስ ቢስማሙ ኖሮ የዛሬው ኦርቶዶክስነት እና ኢትዮጵያዊነት ከነሙሉ ክብሩ ከየት ይገኝ ነበር? አሁንም ግብፅ ለአቡነ ሺኑዳ ሐውልት ስላቆመችላቸው የእኛ ሲኖዶስም ማቆም የለበትም። ደግሞም ማቆም ቢገባውም ተስማምቶበት እና ፈቅዶ ያደርገዋል እንጂ ከላይ እንደገለጽኩት ጥቂት ጥቅመኞች በር ዘግተው ተማክረው ያደረጉትን አበጃችሁ በማለት መቀበል አይገባውም። በመሆኑም አካሄዱ ሥርዓት የሌለው መሆኑን ተረዳ። 
የመንግሥቱ ኃይለማርያም ሐውልት፡-
ቅዱስ ሲኖዶስ ስለ መንግሥቱ ኃይለማርያም ሐውልት አያገባውም። ለዚህ ብሎም ስብሰባ መያዝ ያለበት አይመስለኝም። ስለዚህ የሚመለከተው ፓርላማ ጉዳዩን ሊነጋገርበት ይችላል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ደም የፈሰሳቸው ሰማዕት ናቸው። እንደሌሎቹ ጳጳሳት እና ፓትርያርክ አገር ለቅቀው ወደ አሜሪካ መምጣት ከብዶአቸው አይመስለኝም። ሐውልት የቆመላቸውም ከሞቱ በኋላ ስም አጠራራቸው እንዳይጠፋ አንተ በጽሑፍህ እንዳሰፈርከው ለመታሰቢያ የተሠራላቸው ሐውልት ነው እንጂ እርሳቸው በሕይወት እያሉ ለመታሰቢያ የተደረገላቸው አይመስለኝም። አሁንም ከጽሑፍህ አባዛኛውን ያልተቀበልኩልህ የግለሰቦችን ሕጋዊ ያልሆነ አካሄድ ሕጋዊ አስመስለህ ስላቀረብከው ነው። ልጓም የሌለው እና ያልተገራ ፈረስ እንደሚያስቸግረው ሁሉ ይኼን የጥቅመኞች አካሄድ ልጓም ካልገባበት ምድሪቱ ሁሉ ሐውልት በሐውልት መሆኗ ነው። ሁሉ በሥርዓት ይሁን ከሚሉት ወገን ሆነን ቤተ ክርስቲያንን እንመልከታት እንጂ በፖለቲካ እይታ፣ በጥቅመኞች አካሄድ፣ በምንአለበት እና በማን አለብኝነት አይነት መሆን አይኖርበትም። ቅድም አገር እና ሃይማኖት ሊያጠፋ መጥቶ ስለነበረው ስለጣልያን ስጠቅስልህ በነበረው ዓይነት ኃይለሥላሴን እና ምኒልክን ቃኛቸው። ይኸ ምስላቸው በቤተ ክርስቲያን እንዲሳል ያስደረገው ምን እንደሆነ እና ቤተክርስቲያኒቱ እና ቅዱስ ሲኖዶሱ ለዚህ ነበራቸው አቋም እንዴት እንደነበር ሌሎች ይዘግቡታል ብዬ አስባለሁ። ይቆየን።
    

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)