November 5, 2010

ዋኖቻችሁን አስቡ (ዕብ ፲፫፥ ፯)

ቀሲስ መብራቱ (ከፌስቡክ የተወሰደ)
(ቀሲስ መብራቱ ኪሮስ (ቶሮንቶ : ካናዳ):- ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን በጻፈው መልእክት በ11ኛው ምዕራፍ አካሄዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረጉ የብሉይ ኪዳን ቅዱሳንን የእምነት ተጋድሎ በአጭሩ ይተርካል። ስለ ሁሉም “እንዳልተርክ ጊዜ ያጥርብኛል”  ካለ በኋላም እነዚህ ታላላቅ የእምነት ምስክሮች በእምነት መንግሥታትን ድል እንደነሱ፣ የአንበሶችን አፍ እንደዘጉ፣ የእሳትን ኃይል እንዳጠፉ፣ በእስራትና በወኅኒ እንደተፈተኑ እንዲሁም ይህች ዓለም ለእነርሱ ስላልተገባች የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው በዋሻና በምድር ጉድጓድ ውስጥ እንደኖሩ ይነግረናል። ይኸው የዕብራውያን መልእክት ፀሐፊ በ13ኛው የመልእክቱ ምዕራፍ ደግሞ በእምነትና በኑሮ ምሳሌ የሆኑንን መምህራኖቻችንን (አባቶቻችንን)[1] ማሰብ እንደሚገባ፦
“የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው” በማለት ይጽፋል። (ዕብ.13፥7)
      ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችን ከሐዲስ ኪዳን የቀኖና መጻሕፍት እንደ አንዱ አድርጋ የምትቀበለውና “ትዕዛዝ ሲኖዶስ”[2] የተሰኘው መጽሐፍ ደግሞ በ15ኛው አንቀጹ ቃለ እግዚአብሔር ያስተማሩንን አባቶች መምህራንን ማክበርና መውደድ እንደሚገባ ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “ይቤ ቶማስ ኦ ወልድየ ለዘነገረከ ቃለ እግዚአብሔር፥ ዘኮነ ለከ ምክንያተ ለሕይወት ወወሀበከ ሕልቀተ ክብር፥ አፍቅሮ ከመ ብንተ ዓይንከ (ቶማስም እንዲህ አለ፦ ልጄ ሆይ የእግዚአብሔርን ቃል የነገረህን፥ የሕይወት (የመዳን) ምክንያት የሆነህን እና የክብር ቀለበት የሰጠህን እንደ ዓይንህ ብሌን ውደደው)።[3] እውነት ነው፡ ለእግሮቻችን መብራት፥ ለመንገዳችንም ብርሃን የሆነንንና እኛነታችንን የቀየረውን የእግዚአብሔርን ቃል ትምህርት ያስተማሩንን አባቶቻችን ጳጳሳትንና ካህናትን ልናከብራቸው፥ በሞት ከተወሰዱም በኋላ መታሰቢያቸውን ልናደርግላቸው ይገባል። በሕይወት ዘመናቸው ቃሉን በማስተማር የተጉ፥ በዚህም ብዙዎችን ከጥፋት ጎዳና የመለሱ በአምላካቸው ዘንድ ስላላቸው ክብር በዳንኤል የትንቢት መጽሐፍ፦
“ብዙ ሰዎችንም ወደ ጽድቅ የሚመልሱ እንደ ከዋክብት ለዘለዓለም ይደምቃሉ” ተብሎ ተጽፏል (12፥3)። ቤተክርስቲያናችንም በቅዳሴዋ በምድራዊ ኑሮአቸው እውነተኛውን የሕይወት መንገድ ስለተከተሉ አባቶች ጳጳሳትና ካህናት እንዲሁም ዲያቆናት:- “በእውነት የቃልን መንገድ የሚያቀኑ ሊቃነ ጳጳሳቱን ቀሳውስቱንና ዲያቆናቱንም ሁሉ አስብ“[4] በማለት ትጸልያለች።
       
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ቃል ያስተማሩንን አበው መምህራንን አስቡ ያለን የመልካም ኑሮአቸውን ፍሬ እየተመለከትን እነርሱን እንድንመስላቸው ነው። ይኸው ሐዋርያ መድኃኒታችን ክርስቶስን የመሰለ ሕይወት ስለነበረው የቆሮንቶስ ምዕመናንን “እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ” ብሏቸው ነበር (1ኛ ቆሮ 11፥1)። ስለዚህ የአበውን እና የደጋግ መምህራንን መታሰቢያ የምናደርግበት፤ በቅድስና የተጓዙትን ጻድቃን ደግሞ ገድላቸውን የምናወሳበት ዋናው ምክንያት፡ ሕይወታቸው ክርስቶስን ስለሚያሳየን እና እኛንም ወደ ቅድስና ሕይወት ስለሚመራን ነው። በምድራዊው ቆይታቸው አርዑተ ምንኵስናን ተሸክመው ከጨለማ ዓለም ገዥዎች ጋር የሚደረገውን ውጊያ በአምላካቸው ኃይል ድል ያደረጉ የእምነት ምስክሮች በሥጋ እንኳ ከእኛ ቢለዩ በሰማያት ከቅዱሳን ማኅበር ውስጥ ሆነው እኛን እንደ ደመና በዙሪያችን እየከበቡ የእምነታችን ራስና ፈጻሚ የሆነውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንድንመለከት ይረዱናል (ዕብ 12፥2)።

      የቅዱሳን አባቶቻችን ምሳሌነት ልክ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለደቀመዝሙሩ ለጢሞቴዎስ እንደነገረው በቃል፣ በኑሮ፣ በፍቅር፣ በእምነትና በንጽሕና ተፈትኖ ያለፈ ነው (1ጢሞ. 4፥12)። አንደበታቸውም ጥበብና እውነትን የሚናገር እንዲሁም “በጨው የተቀመመ እና በጸጋ” የሆነ ነው (ቈላስ. 4፥6)። “ተሰአሎ ለአቡከ ወይነግረከ፡ ወለሊቃውንቲከ ይዜንዉከ” (አባትህን ጠይቅ ያስታውቅህማል፡ ሽማግሌዎችህን (ሊቃውንቶችህን) ጠይቅ ይነግሩህማል - ዘዳ 32፡7) ተብሎም እንደተጻፈ፡ የቅዱሳት መጻሕፍትን ምስጢር የሚያውቁ ሊቃውንቱ መምህራን አባቶቻችን ለምንጠይቃቸው ጥያቄዎች መልስ አላቸው።  መንፈስ ቅዱስ እነርሱን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመበት ለመንጋው እየተጠነቀቁም የመንፈስ ልጆቻቸውን በፍቅር ስለሚያቀርቡ በቃል ብቻ ሳይሆን በሕይወታቸው የፍቅር ጌታ እና የሰላም ንጉሥ የሆነውን ክርስቶስን ይሰብካሉ። በአገልግሎታቸውም ማንንም ላለማሰናከል ስለሚጠነቀቁ በማይነቀፈውና ተፈትኖ ባለፈው መንፈሳዊ ማንነታቸው ብዙዎችን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ይማርካሉ።

      በእውነት መንፈሳውያን የሆኑ አባቶቻችን ከአምላካቸው ጋር በጸሎት የታሠረ ግንኙነት ስላላቸው የጸሎታቸው ተጠቃሚ እንሆናለን። እንደ እኛ ሰዎች ቢሆኑም ራሳቸውን ለመንግሥተ ሰማያት ጃንደረቦች አድርገውና በንጽሕና ሆነው ዘወትር በውዳሴ እና በቅዳሴ ስለሚኖሩ “ምድራውያን መላእክት” ይባላሉ። ብዙዎቻችን በዓለሙ ኑሮና በትዳር አሳብ ስንባክን፡ ልባቸው በምንም ነገር ሳይከፈል እግዚአብሔርን እንዴት ደስ እንደሚያሰኙ የእርሱን ነገር ብቻ የሚያስቡ መነኮሳት አባቶቻችን ዘወትር በሰባቱ የጸሎት ጊዜያት ለልዑለ ባህርይ እግዚአብሔር ምስጋና ከማቅረብ ጋር ስለ ቤተክርስቲያን ሰላም፣ አሳዳጊ ስላጡ ሕፃናት፣ ስለ ባልቴቶች፣ ለእውነት ብለው ስለተሰደዱት፣ በእሥር ሆነው ስለሚሰቃዩ ሰዎች፣ እግዚአብሔርን ስለምትወድ ስለ አገራችን ኢትዮጵያ፣ በአገሪቱ ላይ ስለሚዘንሙ ዝናማት፣ ስለ ምድሪቱ ፍሬ፣ እንዲሁም ስለ ዓለሙ ሁሉ ይጸልያሉ። ለዚህም ነው በእመቤታችን ስም የተሰየመው የቤተክርስቲያናችን ቅዳሴ፦ “የሐዋርያት ተከታዮች የሆናችሁ በአንብሮ እድ (በእጅ መጫን) የተሾማችሁ አባቶች ሆይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስለ እኛ የምትለምኑ እናንተን ተቀብለናችኋል”[5] የሚለው።

      መጽሐፍ “ወኵሎ ዘተጽሕፈ ለተግሣጸ ዚአነ ተጽሕፈ፤ ከመ በትዕግሥትነ ወበተወክሎ መጻሕፍት ንርከብ ተስፋነ“ (በትዕግሥታችንና መጻሕፍትም የተናገሩትን ነገር በማመናችን ተስፋችንን እናገኝ ዘንድ የተጻፈው ሁሉ ለምክራችን (ለትምህርታችን) ተጻፈ ሮሜ 15፥3) እንዲል፡ ከሕይወታቸው በተጨማሪ አበው ቅዱሳን በጽሑፎቻቸውም ያስተምሩናል። የታላቁ የእስክንድርያ 20ኛው ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ አትናቴዎስ የምሥጢረ ትሥጉት (ሥጋዌ-Incarnation) መጽሐፍ፤ ቅዱስ ቄርሎስ የንስጥሮስን ኑፋቄ በማውገዝ የቃልንና የሥጋን ተዋሕዶ ያስተማረባቸው ድርሳናት፤ የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የዕብራውያን መልእክት ትርጓሜ፣ ስለ ክህነት (Priesthood) ጋብቻ፣ ስለ ሀብትና ድህነት የደረሳቸው ድርሰቶችና የተለያዩ ስብከቶች (Homilies)ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሳርያ በቤተክርስቲያናችን እውቅና እንዳገኘው የቅዱስ ኤጲፋንዮስ ዓይነት ድርሰት (አክሲማሮስ) በስድስቱ ቀናት ፍጥረታት ላይ የጻፈው ትርጓሜ (Haexameron) ፤ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ምስጢረ ሥጋዌን በማመስጠርና የድንግል ማርያምን ልዩ ጸጋ በማሳየት የደረሰው ውዳሴ፤ የነነዌው ጳጳስ የማር (ቅዱስ) ይስሐቅ እና የፊልክስዮስ (Philoxenus of Mabbug) የምንኵስና መጻሕፍት እኛን በእምነት ለማጽናትና በሥነ ምግባር ለማነጽ የተጻፉ ናቸው።

ወደ አገራችን ሊቃውንት ስንመጣም፡ በጣዕመ ዜማ የተቃኙ የአምላካችንን መግቦትና አዳኝነት እንዲሁም የቅዱሳንን ክብር የሚያወሱ የታላቁ ሊቅ የቅዱስ ያሬድ የዜማ መጻሕፍት በዋነኝነት ተጠቃሾች ናቸው። ከ1358 –1417 ዓ.ም የነበረውና በሞት ከእነርሱ በተወሰደ ጊዜ ደቀመዛሙርቱ “ኦ መዝገበ የውሃት ወተራህርሆት አይቴኑ ኃደገነ? ኦ ቀላየ መጻሕፍት ወምንሐረ ድርሳናት አይቴኑ ኃለፍከ እምኔነ? ኦ ፈካሬ ኅቡኣት ወጸባቴ ባሕረ መለኮት አይቴኑ ፈለስከ እማእከሌነ?“[6] (የበጎነትና የርኅራኄ መዝገብ ሆይ የት ተውከን? የመጻሕፍትና የድርሳናት ምንጭ ሆይ ከእኛ ወዴት ሄድክ? የምሥጢራት ገላጭና የነገረ መለኮት ሊቅ (Theologian) ሆይ ከእኛ ወዴት ተወሰድክ?) በማለት ያለቀሱለት አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ነገረ መለኮትን እና የእመቤታችንን ክብር የሚያወሱ በርካታ መጻሕፍትን ደርሷል። ከነዚህም መካከል፦ መጽሐፈ ምስጢር፡ ፍካሬ ሃይማኖት፡ እንዚራ ስብሐት፡ አርጋኖን፡ ውዳሴ ሐዋርያት፡ መዓዛ ቅዳሴ፡ እና መጽሐፈ ሰዐታት ዘመ ዓልት ወዘሌሊት ይገኙበታል። በአባቶቻችን ሥራ የምንኮራ ኢትዮጵያውያን በሙሉ የአባ ጊዮርጊስን መጻሕፍት ልናነብ እና ስለተሰጠው የሥነ ጽሑፍ ጸጋም እግዚአብሔርን ልናመሰግን ይገባል። በአባ ጊዮርጊስ ዘመን የነበረ እና በብዕር ስሙ “ርቱዓ ሃይማኖት” ተብሎ የሚጠራው ሌላው ኢትዮጵያዊ ሊቅ ደግሞ ድርሳናት ዘበዓላት ዐቢያት በተሰኘው ሥራው ይታወቃል።[7]
      
 አባቶቻችንን ስንዘክራቸው (መታሰቢያ ስናደርግላቸው) እነርሱን እየመሰልን ሊሆን ይገባል ብለናል። የሐዋርያት አሠረ ፍኖት ተከታዮች የሆኑት ደገኞቹ (ደጋጎቹ) አባቶች ከሐዋርያትና ከደቀመዛሙርቶቻቸው በተማሩት ትምህርት ራሳቸውን ከዓለሙ የለዩና በተጠሩበት የክህነት አገልግሎት ያለምንም ነቀፌታ በቅድስና የሚያገለግሉ ናቸው። ቅዱስ ጳውሎስ ወጣቱን ደቀመዝሙሩን ጢሞቴዎስን ሲመክረው ማንም ታናሽነቱን ሳይንቀው በቃልና በኑሮ ለሚያምኑት ሁሉ ምሳሌ በመሆን፡ የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገርና የማያሳፍር የወንጌል አገልጋይ እንዲሆን አጥብቆ ይነግረው ነበር (1ኛ ጢሞ 4፥12; 2ኛ ጢሞ 2፥15)። በመጽሐፈ ቀሌምንጦስ እንደምናነበውም ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ደቀመዝሙሩን ቅዱስ ቀሌምንጦስን የተቀደሰ የክህነት አገልግሎት ይኖረው ዘንድ እንዲህ በማለት ይመክረው ነበር፦ “አእምር ርእሰከ ከመ ትዕቀብ እምዘ ኢይሠምር እግዚአብሔር፥ ከመ በንጹሕ ይኩና እደዊከ ዘእንበለ ርኵስ ከመ ትትቀደስ ወትቀድስ ሕዝበከ፡ ወእግዚአብሔር ከመ ይሥምር በክህነተ ዚአከ ከመ ክህነተ ሙሴ ወአሮን እለ አሥመርዎ ለእግዚአብሔር በሥነ ምግባሮሙ” (ራስህን እግዚአብሔር ከማይፈቅደው ነገር እንድትጠብቅ፤ እጆችህም ርኵሰት የሌለባቸው ንጹሐን እንዲሆኑ፥ ራስህ ተቀድሰህ ሕዝብህን ትቀድስ ዘንድ በዚህም እግዚአብሔር በክህነት አገልግሎታቸውና በሥነ ምግባራቸው ደስ እንዳሰኙት እንደ ሙሴና አሮን በክህነትህ ደስ ይሰኝ ዘንድ እወቅ)።[8] እንግዲህ የአባቶቻችንን አሠረ ክህነት የተከተልን አገልጋይ ካህናት የእነርሱን የአገልግሎት ፍሬ ተመልክተን በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ አገልግሎት ሊኖረን ይገባል። “የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንደሚያደርጉ እንደ ክርስቶስ ባሪያዎች እንጂ ለሰው ደስ አንደምታሰኙ ለታይታ የምትገዙ አትሁኑ” (ኤፌ 6፥6) ተብሎም እንደተጻፈ ውዳሴ ከንቱን የማይሹና በእውነት እግዚአብሔርን የሚያከብሩ አገልጋዮች እንድንሆን ተጠርተናል። አገልግሎታችንም እንዳይነቀፍ በአንዳች ነገር ማሰናከያ ሳንሰጥ ራሳችንን እየመረመርን የእግዚአብሔርን መንጋ በፍጹም ትጋትና ቅንነት ማገልገል ይኖርብናል (2ኛ ቆሮ 6፥3; 1ኛ ቆሮ 9፥27)።

      አባቶቻችን ሁሉንም በፍቅር የሚያሸንፉ የሰላም ሰዎች ናቸው። ከሐዋርያት እንደተማሩት ትምህርት: ፍቅራቸው ግብዝነት የሌለበት ሲሆን ከሁሉም ጋር በሰላም የሚኖሩበት ጥብብ አላቸው። ክፉን በክፉ እንዳይቃወሙ በምታስተምረው የወንጌል ትምህርት መሠረት ጠላት ሰይጣን በሚያስነሳባቸው ፈተና ሳይሸነፉ የክፉውን ፈተና ከጌታ በተማሩት የፍቅር ትምህርት ድል ይነሳሉ (ማቴ 5፥38-42; ሮሜ 12፥9-21)። የደጋግ አባቶቻችንን የኑሮ ፍሬ እየተመለከትን በእምነት የምንመስላቸው ልጆቻቸው እኛም እንደነርሱ በፍቅር ማሸነፍን የምናውቅ የሰላም ሰዎች ልንሆን ይገባል። ቅዱሳን ሐዋርያትም በ12ኛው የትዕዛዝ ሲኖዶስ አንቀጽ እንደተጠቀሰው ሁላችንንም፦ “ልዼ ሆይ፡ የሚጣሉትን በሰላም አስታርቅ እንጂ የክፍፍል እና የጸብ ምክንያት አትሁን” በማለት ያዝዙናል።[9] ስለዚህ በአሁኑ ሰዓት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደገሰጻቸው እንደ ቆሮንቶስ ምዕመናን (1ቆሮ. 1፡10-15) በመከፋፈል መንፈስ ሆነው የጎሪጥ የሚተያዩትን የእናት ቤተክርስቲያን ልዾችን ወደ አንድነት እናመጣቸው ዘንድ “በአንድ አሳብ ተስማሙ፥ አንድ ፍቅር፡ አንድም ልብ፡ አንድም አሳብ ይሁንላችሁ” የሚለውን የሐዋርያውን መልዕክት የአገልግሎታችን መሪ ጥቅስ እናድርገው (ፊልጵ 2፥2)። ቅዱስ ጴጥሮስም ለቀሌምንጦስ “ቅድስት ቀኖና ኢኮነት ለሁከት አላ ዛኅን ይእቲ:”[10] ({የቤተክርስቲያን} ቅድስት ቀኖና ለሁከት (ለጸብ) ሳትሆን ለዕረፍት (ለሰላም) ናት) ብሎ እንደነገረው በቀኖና መፍረስ ምክንያት የተከፋፈለው ወገናችን አንድ ይሆን ዘንድ ወደ ሰላማዊው ንጉሥ ወደ አምላካችን ከልባችን ልንጸልይና ለእናት ቤተክርስቲያናችን አንድነትና ፍጹም ሰላም መክፈል ያለብንን መሥዋዕትነት ሁሉ ልንከፍል ይገባል

ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ።


[1]የአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡየሚለውን ግዕዙ ተዘከሩ መዃንንቲክሙ ዘነገሩክሙ ቃለ እግዚአብሔርይለዋል። የግዕዙም ትርጓሜ ወንጌልን ያስተማሯችሁን መምህራኖቻችሁን አስቡ/እርዱተብሎ ተብራርቷል። የቅዱስ ጳውሎስ መጽሐፍ ንባቡ ከነትርጓሜው (አዲስ አበባ፡ ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት, 1988 ዓ.ም) ገጽ 469ን ይመልከቱ
[2]መጽሐፈ ሲኖዶስ” በመባል የሚታወቀው የሥርዓተ ቤተክርስቲያን መድበል ከሌሎች መጻሕፍት በተጨማሪ ከሐዲስ ኪዳን የቀኖና መጻሕፍት የሚቆጠሩ 4 መጻሕፍትን (ትእዛዝ፣ ግጽው፣ አብጥሊስ፣ እና ሥርዓተ ጽዮን) ይዟል። የመጽሐፈ ሲኖዶስ መቅድም እነዚህንና ሌሎች 4 መጻሕፍትን(መጽሐፈ ኪዳን {ክፍል 1 እና 2}፣ መጽሐፈ ቀሌምንጦስንና ዲድስቅልያን) ባጠቃላይ 8 መጻሕፍትን ከሐዋርያት የተማረውና የቅ. ጴጥሮስ ደቀመዝሙር የነበረው ቅ. ቀሌምንጦስ ዘሮሜ እንደጻፋቸው ይናገራል። See Il Senodos Etiopico, ed. Alessandro Bausi (Louvain: Aedibus Peeters, 1995) 3.
[3] “The Ethiopic Text,” The Statutes of the Apostles or Canones Ecclesiastici, ed. G. Horner, (London: Williams and Norgate, 1904) 4.
[4]በእንተ ብጹዕ መጽሐፈ ቅዳሴ (አዲስ አበባ: ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት, 1984) 44.
[5]በእንተ ብጽዕት መጽሐፈ ቅዳሴ (አዲስ አበባ: ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት, 1984) 82.
[6]Vie De Georges De Sagla” (ገድለ አባ ጊዮርጊስ ዘሳግላ [ጋስጫ]), Corpus Scriptorum Christianorum Orientalium, Vol. 492, Tomus 81, ed. Gerard Colin (Louvain: In Aedibus E. Peeters, 1987) 46.
[7] See Ethiopian Manuscripts Microfilm Library, (Collegeville: MN) Project number 2375.
[8] Il Qalēmentos Etiopico (መጽሐፈ ቀሌምንጦስ ), ed. Alessandro Bausi, (Napoli: Studi Africanistici, 1992) f.71r.
[9] See “The Ethiopic Text,” The Statutes of the Apostles, 5.
[10]Il Qalēmentos Etiopico (መጽሐፈ ቀሌምንጦስ), f. 66v.
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)