November 27, 2010

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን የገንዘብ እና ንብረት ቆጠራ ላይ ጥብቅ መመሪያ ሰጠ


  • ለሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ እና ለሥራ አስኪያጁ ንቡረ እድ  አባ ገብረ ማርያም አቀባበል ተደርጓል፡፡
  • አጥቢያ አብያተ ክርስቲያኑ ለሀገረ ስብከቱ ፈሰስ ማድረግ የሚጠበቅባቸው የ58 ሚሊዮን ብር ዕዳ ያለባቸው ሲሆን ሀገረ ስብከቱ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ፈሰስ ማድረግ ከሚጠበቅበት የዘመኑ ገቢ የ13 ሚሊዮን ብር ጉድለት ተገኝቶበታል፡፡    
  • ‹‹ምእመናን ተቸግረው በሚሰጡት ገንዘብ መልሰው እንዲያዝኑ ልናደርጋቸው  አይገባም፡፡›› (ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ)
  • ‹‹ለቅጥር፣ ዕድገት እና ዝውውር አማላጅ የመላክ ጉዳይ አይቻለሁ፤ በግልጽ  ማስታወቂያ በሚወጣው መሠረት ከሚፈጸመው በቀር በምልጃ የሚደረግ ነገር  አይኖርም፡፡›› (ንቡረ እድ አባ ገብረ ማርያም)
(ደጀ ሰላም፤ ኖቬምበር 27/2010፤ ኅዳር 18/2003 ዓ.ም)ትናንት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ጥሪ በተደረገላቸው የአዲስ አበባ ገዳማት እና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ የሰበካ ጉባኤ ጸሐፊዎች፣ ሒሳብ ሹሞች፣ የስብከተ ወንጌል ሐላፊዎች እና የምእመናን ተወካዮች በተገኙበት በጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ለሆኑት ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ እና ለሥራ አስኪያጁ ንቡረ እድ አባ ገብረ ማርያም የአቀባበል እና የትውውቅ መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ አዲሱ ሥራ አስኪያጅ ባቀረቡት ሪፖርት ቀደም ሲል ከነበረው የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ከ2002 ዓ.ም ጠቅላላ ገቢ ለመንበረ ፓትርያርኩ ፈሰስ መደረግ የነበረበት 65 በመቶ የ13 ሚሊዮን ብር ዕዳ እና ባዶ ካዝና መረከባቸውን ገልጸዋል፡፡ ለዚህም በመንሥኤነት ከሚጠቀሱት መካከል ሀገረ ስብከቱ በቃለ ዓዋዲው መሠረት ከ160 ያህል አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ጠቅላላ ገቢ መሰብሰብ የነበረበት የ20 በመቶ አስተዋጽዖ በወቅቱ እና አግባቡ ባለመሰብሰቡ እንደሆነ በሥራ አስኪያጁ ሪፖርት ላይ ተመልክቷል፡፡ በዚህም ሳቢያ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያኒቱ ለሀገረ ስብከቱ ፈሰስ ማድረግ የሚጠበቅባቸው የ58 ሚሊዮን ብር አጠቃላይ ዕዳ እንዳለባቸው ተገልጧል፡፡

በ29ው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ስብሰባ ላይ የቀድሞው የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ ባቀረቡት የሒሳብ ሪፖርት ሀገረ ስብከቱ “ካለፉት ዓመታት በተሻለ ካዝናውን ሙጥጥ አድርጎ ስድስት ሚሊዮን ብር ያህል ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ፈሰስ ማድረጉን” ቢገልጹም ፐርሰንት ተጠይቀው የማያውቁ፣ ከብር 300,000 እስከ አራት ሚሊዮን ብር ዕዳ ያለባቸው በትንሹ ከኻያ የማያንሱ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን መኖራቸውን፣ የአንዳንዶቹም ወደ ሀገረ ስብከቱ ካዝና ገቢ ሳይደረግ አየር ባየር እንደሚበላ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የቁጥጥር አገልግሎት የኦዲት ሪፖርት መጋለጡ ይታወቃል፡፡

በትናንቱ የአቀባበል እና የትውውቅ መርሐ ግብር የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያኑን የገንዘብ እና ንብረት ቆጠራ አሠራር በማጠናከር ቀሪ ዕዳቸውን እንዲከፍሉ ለማስቻል፣ በቀጣይም ውጤታማ ቁጥጥሩን በማጥበቅ አግባብነት ያለውና ውጤታማ የሆነ የገቢ አሰባሰብ እንዲኖር ለማድረግ ያበቃል የተባለ ጥብቅ መመሪያ መሰጠቱ ታውቋል፡፡ በመመሪያው መሠረት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን በሞዴል 30 በሚቀበሉት የዕለት ተዕለት ገቢ እና በሞዴል 64 በሚሠሩት የገቢ ማጠቃለያ የገንዘብ እና ንብረት ቆጠራ ማድረግ የሚችሉት በሰበካ ጉባኤው የምእመናን እና የአጥቢያው አገልጋይ ካህናት ተወካዮች ብቻ ናቸው። በዚህ ረገድ ቀደም ሲል ዋና አስፈጻሚ የነበሩት የአጥቢያው አስተዳዳሪ፣ ጸሐፊ፣ ሒሳብ ሹም፣ ገንዘብ ያዥ እና ቁጥጥር ተግባሩን የማስተባበር ድርሻ ብቻ ይኖራቸዋል፡፡ በሰበካ ጉባኤ አስተዳደር የምእመናን ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን የሚያትተው መመሪያው እነርሱ በሌሉበት የገንዘብ እና ንብረት ቆጠራ እንዳይካሄድ ያሳስባል፡፡

መመሪያው በምእመናን ተወካዮች እና በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ አስተዳደር መካከል ጥርጥርን በመፍጠር፣ የአስተዳደር ሠራተኞች በደምሳሳው “ሰራቂዎች” እንደሆኑ አድርጎ ስለሚያስቀመጥ በመመሪያ መልክ ከመውረዱ በፊት ውይይት ሊደረግበት ይገባ እንደነበር አንዳንድ የስብሰባው ተሳታፊዎች ሐሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡ ከቅዳሜ እና እሑድ በቀር በሥራ ቀናት የሰበካ ጉባኤ ተመራጭ የሆኑ ምእመናን አባላትን ለማግኘት አዳጋች መሆኑን የሚናገሩት እኒህ አስተያየት ሰጪዎች የመመሪያውን አፈጻጸም አዳጋች እንደሚያደርገው ይገልጣሉ፡፡ በአዲሱ ሥራ አስኪያጅ የቀረበው ሪፖርት በገቢ አሰባሰብ ችግሮች ላይ ማተኮሩ ተገቢነት ቢኖረውም በአጥቢያዎች ካዝና ላይ ግን ከተጠቀሰው ችግር በላይ አዛዥ የሆኑ የበላይ አካላትን አሠራር ያየ አለመሆኑን በመጥቀስ ተችተዋል፡፡

እንደ እነርሱ አባባል በልማት እንቅስቃሴያቸው እና በገቢ አቅማቸው ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ተለይተው በተቀመጡት አጥቢያዎች ካዝና ላይ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የራሱን ሙዳየ መባዕ በተለያዩ ርእሶች በማስቀመጥ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት ለተለያዩ ክዋኔዎች ማስፈጸሚያ፣ የካህናት አስተዳደር መምሪያው ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በየጊዜው ለሚደረገው አቀባበል ጥንግ ድርብ ለብሰው ለሚሰለፉ ካህናት አበል እንዲከፈል በማዘዝ፣ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ለመስቀል ደመራ እና ለመሳሰሉት ክብረ በዓላት ጥናት ለሚያደርጉ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች አበል እንዲከፈል በማዘዝ፣ ሀገረ ስብከቱ ለሽልማት እና ለመሳሰሉት አጥቢያዎች በተሰጣቸው ደረጃ መጠን እንዲያዋጡ በማዘዝ በየአቅጣጫው አቅምን የሚያዳክሙ የግዳጅ አስተዋጽዖ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለመፈጸም የሚገደዱበት የወጥ አሠራር ጉድለት ለፈሰሱ (ለገቢው) መዳከም በምክንያትነት መጠቀስ ይገባው እንደነበር አስረድተዋል፡፡ በቅጥርም ረገድ ከላይ በሚሰጥ ትእዛዝ ብቻ ያለአቅማቸው በርካታ አገልጋይ ካህናትን እና የአስተዳደር ሠራተኞችን የሚቀበሉ አጥቢያዎች ከገቢያቸው ጋራ በማይመጣጠን አኳኋን ደመወዝ ለመክፈል መገደዳቸው፣ በዝውውርም በኩል በገቢ አሰባሰብ እና በሌሎች የተግባር አፈጻጸማቸው መመሪያን ጠብቀው በሐቅ የሚሠሩ የአስተዳደር ሠራተኞች ከቦታቸው እንዲነሡ እየተደረገ በምትኩ ለመጠቃቀም ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ ሙሰኞች እንዲተኩ መደረጋቸውም በተጨማሪ መንሥዔነት መታየት እንደሚገባው ተሳታፊዎቹ አስገንዝበዋል፡፡

አስተያየት ሰጪዎቹ አክለው እንዳስረዱት፣ በገንዘብ አሰባሰቡ ረገድ ቁጥጥርን ስለ ማጥበቅ ብቻ ሳይሆን ቤተሰብ መሥርተው ከኑሮው ውድነት እና ከትምህርት ደረጃቸው ጋራ በማይመጣጠን አኳኋን ሁለት ዓመት ጠብቀው በዕርከን ጭማሪ የሚያገኙት ደመወዝ ስለማይበቃቸው አስተምረው በማጥመቅ፣ ቀድሰው በማቁረብ ዋናውን ተግባር ስለሚፈጽሙት አገልጋዮች አኗኗርም ሊታሰብበት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)