November 27, 2010

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት ወደ ትምህርት ገበታቸው ተመለሱ

(ደጀ ሰላም፤ ኖቬምበር 26/2010፤ ኅዳር 17/2003 ዓ.ም)የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት ከኅዳር ስምንት ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ ትምህርት በማቆም እና ከምግብ ቤቱ አገልግሎት በመከልከል ባነሷቸው ችግሮች አፈታት ላይ ስምምነት ተደረሰ፤ ደቀ መዛሙርቱም ከትናንት ኅዳር 18 ቀን 2003 ዓ.ም ምሽት ጀምሮ በኮሌጁ የምግብ ቤት አገልግሎት መጠቀም መጀመራቸው ታውቋል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ከኮሌጁ አስተዳደር እና ቦርድ ጋራ ከስምምነት ላይ እንዲደርሱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉት የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የነገረ መለኮት ምሩቃን ማኅበር እና ደቀ መዛሙርቱ አቤቱታቸውን ካቀረቡላቸው የውጭ አካላት አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ናቸው፡፡

ለጤና ክትትል ወደ ደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል ከገቡ ሦስተኛ ቀናቸውን ያስቆጠሩት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ  ደቀ መዛሙርቱ ለብሰው በመሰለፍ ወደ ኮሚሽኑ እና ሌሎች የውጭ ተቋማት ዘንድ ማመልከታቸው እንዳሳዛናቸው ተገልጧል፡፡ ይሁንና የቤተ ክርስቲያኒቱን ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲከታተል ቅዱስ ሲኖዶስ ሐላፊነት የሰጠው በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የሥርዓተ ትምህርት እና ሥልጠና መምሪያ በችግሩ አፈታት ዙሪያ አንዳችም ጥረት አለማድረጉ አጠያያቂ ሆኗል፡፡

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ዳግመኛ ከተከፈተበት 1986 ዓ.ም ጀምሮ የተቋሙ የምግብ ቤት ሐላፊ ሆነው የቆዩት አቶ ደስታ እስጢፋኖስ ከምግብ ቤቱ ንብረት ክፍል ሐላፊዋ ጋራ ለአንድ ወር የግዳጅ ዕረፍት እንዲወጡ፣ ለጥያቄ ሲፈለጉ ካልሆነ በቀር ወደ ኮሌጁ ግቢ እንዳይገቡ ተወስኗል፡፡ በጥራቱ መጓደል የተነሣ በደቀ መዛሙርቱ ጤና ላይ እክል እንዳስከተለ የተገለጸውን የምግብ ቤቱን አሠራር አጥንቶ ችግሩን በመሠረታዊነት የሚፈታ ስድስት አባላት ያሉት ኮሚቴ ከኮሌጁ ቦርድ፣ ከኮሌጁ አስተዳደር እና ከደቀ መዛሙርቱ መማክርት ጉባኤ ተውጣጥቶ ተቋቁሟል፡፡ ቀደም ሲል የምግብ ቤቱን የግዥ እና ንብረት ክፍሎች ከሐላፊነት ጋራ አጣምረው ይዘው የቆዩት አቶ ደስታ እስጢፋኖስ በ2000 ዓ.ም በተመሳሳይ አኳኋን ከሥራቸው ተወግደው ከቆዩ በኋላ ከመንበረ ፓትርያርኩ በተሰጠው ትእዛዝ በዚያው ዓመት ደቀ መዛሙርቱ ለዕረፍት በወጡበት ክረምት ወቅት እንዲመለሱ ተደርጎ በ2001 ዓ.ም ደቀ መዛሙርቱ ሲገቡ ጥያቄውን ዳግመኛ ላያነሡ እየፈረሙ ትምህርታቸውን እንዲጀምሩ ተደርጓል፡፡ አቶ ደስታ በቀጣይ ወደ ሐላፊነታቸው የመመለሳቸው ዕድል እንዳከተመ፣ በምትኩ የኮሌጁ አስተዳደር ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጋራ በመነጋገር በሌላ የሥራ ዘርፍ ሊመደቡ እንደሚችሉ ተነግሯል፡፡

‹‹የውስጥ ደዌ›› በተለይም ከኩላሊት እና ጨጓራ ጋራ የተያያዙ የጤና እክሎች በርካታ ደቀ መዛሙርት ‹‹እንደ አንድ ኮርስ›› የሚጋሯቸው መሆናቸውን የሚናገሩት የኮሌጁ ደቀ መዛሙርት፣ ምንነታቸው የማይታወቁ “የአፍዝ አደንግዝ ቅጠላ ቅጠሎች” በምግቡ ላይ ተጨምረው እንደሚያገኙ በመጥቀስ አቶ ደስታ እስጢፋኖስን ይከሳሉ። “የአንዳችን አስከሬን አለመውጣቱም የሃይማኖት ቤት ሆኖ ነው” ይላሉ ተማሪዎቹ፡፡ ትናንት ማምሻውን አቅርቦቱ እንዲሻሻል የተደረገው ምግብ ቤቱ በካህናቱ ጸሎት እና በዲያቆናቱ ዝማሬ ተከፍቶ አገልግሎቱን ሲቀጥል አንዳንድ ደቀ መዛሙርት እንደገለጹት፣ ፍላጎታቸው ከዓመታት በፊት በተመደበው ውስን በጀትም ቢሆን ተገቢ የሕክምና እና የምግብ አገልግሎት ያገኙ ዘንድ ነው፡፡

ደቀ መዛሙርቱ ተቃውሟቸውን በሚያሰሙባቸው ቀናት መካከል የተቋቋመው እና ችግሩ መልኩን ሳይስት እንዲፈታ አስተዋጽዖ አድርጓል የተባለው የተማሪዎች መማክርት የምርጫ መሥፈርቱ፣ ዓላማው፣ ሥልጣን እና ተግባሩ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ነባራዊ ሁኔታዎች ጋራ ተጣጥሞ በጽሑፍ ከተዘጋጀለት በኋላ በመጪው ሳምንት ውስጥ ዳግመኛ ምርጫ በማካሄድ ቀደም ሲል የተመረጡትን የመማክርቱን አባላት እንደሚያጸድቅ አልያም በሌሎች እንደሚተካ ይጠበቃል፡፡ የምርጫ መሥፈርቱ በትምህርታቸው ታታሪ፣ በሥነ ምግባራቸው ምስጉን እና ከፖለቲካ አመለካከት ለጸዱ ላሏቸው ትኩረት እንደሚሰጥ ተገልጧል፡፡

በኮሌጁ በተመሳሳይ (የዲግሪ) መርሐ ግብር በሥርዓተ ትምህርቱ ተካትተው የሚሰጡት የትምህርት ዓይነቶች “በክሬዲት አወር” ብዛት እና በዝርዝራቸው በየጊዜው በመለያየታቸው ቀጣይነት እንደሚጎድላቸው፣ ተጠቃልለው ሊሰጡ የሚገባቸው የትምህርት ዓይነቶች በመነጣጠላቸው በተማሪው ላይ አላስፈላጊ ጫና ከመፍጠራቸውም በላይ ተማሪው በቅምሻ እንጂ “አድምቶ የማይማራቸው” እንደሆኑ፣ የአንዳንድ መሠረታዊ የትምህርት ዓይነቶች ህልውና በመምህራን መኖር እና አለመኖር ላይ እንደተመሠረቱ፣ መምህራኑ በየራሳቸው ከሚያወጡት በቀር ለሚሰጧቸው ኮርሶች ሞጁል እና ቢጋር እንደሌላቸው፣ በብዙዎች አገላለጽ “ያመኑትን ለማጽናት” ከሚረዳው የታሪክ፣ ዶግማ እና ቀኖና ትምህርቶች ጋራ በውል የታወቁ “በኦርቶዶክሳዊ ሐዋርያዊ ተልእኮ” (Orthodox Missionary) ላይ ያተኮሩ የልዩ ሥልጠና መስኮች እንዳልተደራጁ በሥርዓተ ትምህርቱ ላይ የተለዩት ውስንነቶች በኮሌጁ አካዳሚክ ኮሚሽን ተጠንተው ማሻሻያ እንደሚደረግባቸው ተመልክቷል፡፡

ኮሌጁ የሚሰጠው ዲግሪ እና ዲፕሎማ ከትምህርት ሚኒስቴር ዕውቅና እንዲጠየቅበት በደቀ መዛሙርቱ ቀርቧል የተባለው ጥያቄ ብዙ ወገኖችን “ቀድሞ የበቀለን ጆሮ ከኋላ የመጣን ቀንድ በለጠው” አሰኝቷል፤ “የራስዋን ሥርዓተ ትምህርት ቀርጻ የትምህርት ሚኒስቴር ሆና ለኖረችው ቤተ ክርስቲያን የማይመጥን እና አግባብነት የጎደለው” የሚልም ነቀፌታ አግኝቶታል፡፡ ኮሌጁ በሀገር ውስጥ እና በባሕር ማዶ ታላላቅ ዩኒቨርስቲዎች እና ልዩ ልዩ ተቋማት ከማንም ጋራ ተወዳድረው የማያሳፍሩ እንዲያውም በሚያኮራ ደረጃ የሚገኙ ምሩቃን የወጡበት መሆኑን እኒህ ወገኖች ያስታውሳሉ፡፡ በ1937 ዓ.ም “የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት” በሚል በኦፊሴል ተከፍቶ “የቀሳውስት ክፍል” በሚል ጠቅላላ ትምህርት፣ ‹‹የዲያቆናት ክፍል›› በሚል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ዶግማ፣ ዜና አበው እና ዜማ ይሰጥበት ነበር፡፡ በ1945 ዓ.ም ወደ ሁለተኛ ደረጃ ያደገው ተቋሙ ትምህርት እና ሥነ ጥበብ ሚኒስቴር ለአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚፈልጋቸውን “የሃይማኖት እና የሞራል መምህራን” በ“ሃይማኖት ትምህርት መምህራን ማሠልጠኛ ክፍል” ለሦስት ዓመት እያሠለጠነ ያወጣ ነበር፡፡

በ1952 ተመርቆ የተከፈተው የኮሌጁ ክፍል በ1953 ዓ.ም ሥራ በጀመረው በቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ውስጥ ከሚተዳደሩት ኮሌጆች እንደ አንዱ ተቆጥሮ ጠቅላላ አስተዳደሩ በቀ.ኃ.ሥ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ሥር ሆነ፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሐዋርያዊ ድርጅት›› ይታተም የነበረው ትንሣኤ መጽሔት እንደዘገበው በ1956 ዓ.ም በቀ.ኃ.ሥ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በተካሄደው የምረቃ ሥነ በዓል የመጀመሪያዎቹ ስድስት የመንፈሳዊ ኮሌጁ ደቀ መዛሙርት በባችለር ኦቭ ቴዎሎጂ ተመርቀው በልዩ ልዩ የሐላፊነት ቦታዎች ላይ ተመድበው ለሀገራቸው እና ለቤተ ክርስቲያናቸው ሲሠሩ ማየት ‹‹ክብር እና ደስታ የተመላበት የምሥራች ነው፡፡›› ከመጀመሪያዎቹ የመንፈሳዊ ኮሌጁ ምሩቃን መካከል በኋላ የድኅረ ምረቃ ትምህርታቸውን በአሜሪካው የሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ በሕግ ያጠናቀቁት እና ‹‹የሰበካ ጉባኤ አባት›› በመባል የሚታወቁት ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ እና አቶ አእምሮ ወንድማገኘሁ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ዛሬም በአገር ውስጥ መንግሥታዊ በሆኑ እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት እንዲሁም በባሕር ማዶ አንጋፋ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚገኙቱ ፍሬዎቹ ተመልሰው በአስተዳደርም በመምህርነትም ሊያገለግሉ የሚችሉበትን መንገድ እንዲያመቻች ተጠይቋል፡፡ ከዚህ አኳያ አሁን በደቀ መዛሙርቱ ስም ቀርቧል የተባለው የዲግሪ ዕውቅና ጥያቄ በአንዳንድ ታዛቢዎች አገላለጽ “ቤተ ክርስቲያኒቱን ተመልሶ ላለማገልገል የታሰበ የስንፍና ሀሁ ነው” ተብሏል፡፡

በሰሞኑ የደቀ መዛሙርቱ ጥያቄዎች መነሻነት ከኮሌጁ ማኅበረሰብ አባላት ለደጀ ሰላም የደረሱ አስተያየቶች፣ የኮሌጁ አስተዳደር በደቀ መዛሙርቱ መካከል እና በመምህራኑ ዘንድ በአጽንኦት ሊመለከታቸው ይገባሉ የሚሏቸውን ነጥቦች ይጠቁማሉ፡፡ በጥቆማዎቹ መሠረት ኮሌጁ በተለይ ከ2000 ዓ.ም ወዲህ ተማሪዎችን የሚቀበልባቸውን መስፈርቶች ከዕድሜ ገደብ እና ከትምህርት ደረጃ ጀምሮ በአግባቡ እንዲያጤን ተጠይቋል፤ አህጉረ ስብከትም ከኮሌጁ የሚወጣውን መስፈርት በማክበር እንጂ በተለያዩ ሽፋኖች ድብቅ የተሐድሶ ኑፋቄ ዓላማቸውን በረጅም ጊዜ ሂደት የማሳካት ተልእኮ አንግበው ወደ ኮሌጁ በመግባት ብዙኀኑን ደቀ መዛሙርት በአስተዳደሩ ላይ በማነሣሣት ተቋሙን ከዋናው ዓላማው የሚያዛቡትን እና ኦርቶዶክሳዊ ላህይ የሌላቸውን ከመላክ መቆጠብ እንደሚኖርባቸው ተመልክቷል፡፡ “በክፍል ወስጥ ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድስና እና ክብር ትምህርት ሲሰጥ ወጥተው ከሚሄዱ፣ አካዳሚያዊ ነጻነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ የመናፍቃኑን አስተሳሰብ የሚያዘልቁ ጉንጭ አልፋ ክርክሮችን ከሚያሥነሱ፣ እንደ ዋልታ እና ማገር የሚታዩትን የቤተ ክርስቲያኒቱን ሥርዐተ እምነት እና የተቀደሰ ትውፊት ከሚያቃልሉ አንዳንድ ደቀ መዛሙርት ምን ይጠበቃል?” በማለት የሚጠይቀው አንዱ አስተያየት ሰጪ ኮሌጁ እንደ ትምህርት ተቋም በጎላ እና በተረዳ መልኩ ለታወቀ ዓላማ ለሚያሠለጥናቸው ደቀ መዛሙርት ሥነ ምግባራዊ ሕይወት የሚያደርገውን ክትትል እና ክብካቤ እንዲያጠናክር ይማጠናል፡፡

በሌላ በኩል አስተያየቶቹ መምህራኑ ቀደም ሲል ከኮሌጁ ተመርቀው የወጡት ደቀ መዛሙርት ባለፉበት መንገድ ተማሪውን በስም ጥሪ ከመከታተል አንሥቶ ዕለት ተዕለት በሚያተጋ አኳኋን የመማር ማስተማር ሂደቱን እንዲያጠናክሩ ያሳስባል፡፡ “Theology is the beginning of wisdom and fear of God” በሚል መምህራኑ የነገሩትን ብሂል የሚያስታውሰው አንድ የኮሌጁ የቀድሞ ደቀ መዝሙር፣ “ካፍቴሪያው በሰው ተሞልቶ የሚታየውን ያህል ቤተ መጻሕፍቱ ሰው ተጠምቷል” በማለት አብዝቶ መጻሕፍትን ከመመርመር አኳያ የታዘበውን መዘናጋት አካፍሏል፡፡ “የኬልቄዶንን ጉባኤ መቃወም ፀጉር ስንጠቃ ነው፤ . . . በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መቁረብ ችግር የለውም” በማለት ከሚናገሩት አንዳንድ መምህራን አንሥቶ ባለፈው ዓመት በአባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ቅዱስ ፍሬምናጦስ ኮሌጅ የተጀመረው እና በፕሮቴስታንቱ “ብሪጅ ኦቭ ሆፕ” የሚደገፈው የድኅረ ምረቃ መርሐ ግብር በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅም እንዲተከል ያቀረቡት ምክረ ሐሳብ ውድቅ የተደረገባቸው ጥቂት መምህራንም እንደ ሰሞኑ የመሰሉትን የደቀ መዛሙርቱን የመብት ጥያቄዎች አቅጣጫ በማሳት አስተዳደሩን የማስጨነቅ አካሄዳቸውን በንቃት እንዲከታተለው ተጠቁሟል፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)