November 24, 2010

መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎቹ አድማቸውን ካላቆሙ ይባረራሉ አለ

 (በምዕራፍ ብርሃኔ፤ የሪፖርተር ጋዜጣ የኖቬምበር 24/2010 እትም):- የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ከህዳር 8 ቀን 2003 ዓ.ም. ጀምሮ የምግብና የትምህርት አድማ የመቱ ከመቶ በላይ የሆኑ ተማሪዎችን (ደቀመዛሙርት) ወደ ትምህርት ገበታቸው የማይመለሱና ከሆነና የኮሌጁን ምግብ የማይመገቡ ከሆነ፣ የኮሌጁን ንብረት አስረክበው ክሊራንስ በማስፈረም የትምህርት ተቋሙን በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ ከትናንት በስቲያ አስታወቀ፡፡ ተማሪዎቹ ማለትም መነኮሳት፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት፣ መሪ ጌታዎችና ሌሎችም አድማውን የመቱበትን ምክንያት ሲያስረዱ፣ ‹‹የምንመገበው ምግብ በባእድ አምልኮ የተመረዘ በመሆኑ ለተለያዩ በሽታዎች እየተጋለጥን ነው፡፡ ለዚህም ደግሞ ኃላፊነቱን የሚወስዱት የምግብ ቤቱ ኃላፊ በመሆናቸው ከሥራቸው ይባረሩልን፤›› ነው የሚሉት፡፡ የተማሪዎቹ የተቃውሞ መነሻ የሆነው የምግብ መመረዝና የባእድ አምልኮ ግንኙነት ምን እንደሆነ አልተብራራም፡፡
መምህር ፍስሃ ጽዮን ደሞዝ የኮሌጁ የአካዳሚክ ምክትል ዲን በበኩላቸው፣ ‹‹ተማሪዎቹ ከመስከረም 26 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ህዳር 8 ቀን 2003 ዓ.ም ድረስ ሲመገቡ የቆዩትን ምግብ ምንም ዓይነት ማስጠንቀቂያና ግንዛቤ ሳይሰጡን በድንገት ተነስተው ነው አድማውን የመቱት፤›› ሲሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡


እንደ መምህር ፍስሃ ጽዮን ከሆነ፣ ተማሪዎቹ በኮሌጁ መመገብ ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ የረሃብና የትምህርት አድማ እስከመቱበት ጊዜ ድረስ የሚመገቡት ምግብ ችግር እንዳለው መናገር እንደነበረባቸው አስታውሰዋል፡፡


‹‹ተማሪዎቹ የመብት ጥያቄ ማቅረባቸውን አንቃወምም፤›› ያሉት መምህር ፍስሃ ጽዮን፣ የተማሪዎቹ መብት ያሉባቸውን ችግሮች ለሚመለከተው ክፍል ማቅረብ እንጂ ሠራተኛ ይባረርልን ማለት እንዳልሆነም አያይዘው ገልጸዋል፡፡


ከሥራቸው እንዲፈናቀሉ ከተማሪዎች ተቃውሞ የቀረበባቸው የምግብ ቤት ኃላፊ፣ በ2000 ዓ.ም ተመሳሳይ ተቃውሞ ገጥሟቸው ነበር፡፡ ይሁንና የኮሌጁ ቦርድ ጉዳዩን እንዲያጣራ ከፓትሪያርኩ ቢሮ በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ጉዳያቸው ተጣርቶ ለሰባት ወራት ከሥራ ገበታቸው ታግደው የነበሩትን እኚህ ግለሰብ ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ እንደተደረገ ኮሌጁ ገልጿል፡፡


‹‹ተማሪዎቹ ጉዳያቸውን ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እንዲከታተልላቸው ማመልከቻ በትናንትናው ዕለት አስገብተው ነበር፡፡ ተማሪዎቹ መብታቸው እንዲከበር የሚፈልጉትን ያህል የምግብ ቤቱን ኃላፊ መብት ሊያከብሩ ይገባል፤›› ያሉት መምህር ፍስሃ ጽዮን፣ ኮሌጁ የምግብ ቤት ኃላፊውን ጉዳይ እየመረመረ እንደሆነና ጥፋተኛ ሆነው ቢገኙ እንደ ጥፋታቸው መጠን በኮሌጁ ሕገ ደንብ መሰረት እንደሚቀጡ ገልጸዋል፡፡


መንፈሳዊ ኮሌጁ ተማሪዎችን የሚያሠለጥነው ቤተክርስቲያንን እንዲያገለግሉ እንጂ፣ መንግሥትን ወይም ደግሞ ሌሎች መሥሪያ ቤቶችን እንዲያገለግሉ አይደለም ብሏል፡፡ በመሆኑም ተማሪዎቹ፣ ‹‹ጥያቄያችን መብታችን ይከበር ነው›› ያሉትን ሐሳብ የኮሌጁን ዓላማ ያላገናዘበና ከተማሪዎቹ ጀርባ በመሆን እያበረታታና ገንዘብ እየሰጠ አድማው እንዲቀጥል የሚያደርግ አካል ይኖራል ሲሉ መምህር ፍስሃ ጽዮን ገልጸዋል፡፡


ተማሪዎቹ የረሃብና የትምህርት አድማውን ከመቱ በኋላ የተማሪዎች ካውንስል እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡ ይሁንና ተማሪዎቹ ካውንስሉ የተቋቋመው በውዝግብ ውስጥ ከመሆኑም በላይ የማይወክሉን ሰዎች ተመርጠዋል ብለዋል፡፡ መምህር ፍስሃ ጽዮን በበኩላቸው፣ ሥርዓት ባለው ሁኔታ አዳራሽ ውስጥ ተማሪዎች ተሰብስበው በራሳቸው ድምፅ ይወክሉናል ያሉዋቸውን ተማሪዎች እንደመረጡ ተናግረዋል፡፡  


የተማሪዎቹ ሌላው ጥያቄ ደግሞ ከተመረቁ በኋላ የሚሰጣቸው ዲግሪ ከቤተክርስቲያን ውጪ የትም እንደማያሠራቸው ገልጸው፣ በትምህርት ሚኒስቴር ዕውቅና የተሰጣቸውን የትምህርት ዓይነቶች እንዲካተቱላቸው፤ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ደግሞ  መሥራት የሚችሉት በፊሎጂ ብቻ ስለሆነ ሌሎች የትምህርት ዓይነቶችም እንደ አማራጭ እንዲቀርቡላቸው ጠይቀዋል፡፡


ኮሌጁም በበኩሉ፣ ‹‹ተቋሙን የሚመራው ቅዱስ ሲኖዶሱ ነው፡፡ ሲናዶሱ ደግሞ ተማሪዎች እንዲሠለጥኑ የሚፈልገው ቤተክርስቲያንን እንዲያገለግሉ ነው፡፡ ስለዚህ ለተማሪዎች የሚሰጠው ሥልጠና አብዛኛውን የሚያጠነጥነው በዕምነትና በቤተክርስቲያን አገልግሎት ላይ ነው፤›› ብሏል፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)