November 17, 2010

የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ቤተ ክህነቱ ላለበት የአሠራር ብልሹነት ማሳያ ሆነ

  • የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር የሀገረ ስብከቱን ሊቀ ጳጳስ አስጠነቀቀ
(ደጀ ሰላም፤ ኖቬምበር 16/2010፤ ኅዳር 7/2003 ዓ.ም) የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር ጽ/ቤት የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ለቤተ ክርስቲያኒቱ ልማት መሰናከል እና ለገጽታዋ መበላሸት ዕንቅፋት ሆኖ የሚገኘውን የቤተ ዘመድ አስተዳደር፣ ሙስና እና የሥነ ምግባር ብልሽት በአስቸኳይ እንዲያስተካክል አስጠነቀቀ፡፡ ‹‹ኅብረተሰቡ በሀገረ ስብከቱ ላይ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ምክር ቤቱን እስከ መጠየቅ ደርሷል›› ያለው ጽ/ቤቱ “ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ” እስከ መባል የደረሰው የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት አስተዳደር በአፋጣኝ ይሻሻል ዘንድ የሀገረ ስብከቱ ሠራተኞች የሚፈጥሩት ጫና እና የኅብረተሰቡ ቁጣ እየተጠናከረ መምጣቱን ለሊቀ ጳጳሱ አስረድቷቸዋል፡፡ ችግሮቹ በምክክር የማይፈቱ ከሆነ ለሕዝቡ ምሬት ምላሽ ለመስጠት ጉዳዩ በሕግ አግባብ የሚታይ ይሆናል ብሏል አስተዳደሩ፡፡

ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ
የዞኑ አስተዳደር ይህን ማስጠንቀቂያ የሰጠው በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ከሊቀ ጳጳሱ ጋራ በመነጋገር ጉዳይ አስፈጽማለሁ በሚል ባለጉዳዮችን ሲያጉላላ እና ሲያማርር የቆየው የሀገረ ስብከቱ ሰንበት ት/ቤት ክፍል ሐላፊ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውሎ በተካሄደበት ምርመራ በአራት የሒሳብ ቋቶች ያከማቸው ከብር 280‚000 በላይ ከተያዘ እና ሐላፊውም ጥፋት ሲፈጽም መቆየቱን ካመነ በኋላ ነው፡፡ በተጭበረበረ የትምህርት ማስረጃ ወደ ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ገብቶ ትምህርቱን ከተከታተለ በኋላ በቃለ ዓዋዲው አንቀጽ 44 ንኡስ አንቀጽ ስድስት ከተደነገገው ውጭ በሀገረ ስብከቱ የአስተዳደር ጉባኤ ሳይወሰንበት በሀገረ ስብከቱ ተቀጥሮ ለሊቀ ጳጳሱ እየሰበቀ እና የግለሰቦችን ስም እያጠቆረ ‹‹በጉዳይ አስፈጻሚነት›› ከባለጉዳዮች ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ሲያደልብ ቆይቷል ተብሏል፡፡ በቃለ ዓዋዲው እንደተደነገገው ሕፃናትን እና ወጣቶችን በልዩ ልዩ የማስተማሪያ ዘዴዎች እየተጠቀመ ትምህርተ ሃይማኖትን፣ ሥርዐተ እምነትን እና ግብረ ገብን እንዲማሩ የማድረግ ግዴታ የተጣለበት የሰንበት ት/ቤት ክፍል ሐላፊው በምርመራው ወቅት ሰውነቱ በአሸንክታብ እና በንቅሳት ተዥጎርጉሮ ተገኝቷል - ጉዳዩ በሀገረ ስብከቱ የተስፋፋው የጠንቋይ እና ጥንቆላን የማዘውተር አንድ ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ በተለይ በደብረ ብርሃን ከተማ በሚገኙት ዘጠኝ ቀበሌዎች “ገበያ ሰብስብ” የሚባለው ጥንቁልና ከመበራከቱ የተነሣ ብዙዎች ለሰበካ ጉባኤ የሚሰጡት አስተዋፅኦ ከጠንቋይ የተረፈ ነው እስከ መሰኘት ደርሷል፡፡

በተለያዩ የሀገሩ ስብከቱ ክፍሎች የእኅት እና አክስት ልጆች፣ በጋብቻ የተዛመዱ አማቾች እና አክስቶች እንዲሁም በውለታ የተሳሰሩ ሹሞች በርክት ብለው የሚገኙ ሲሆን በዋናነት በሀገረ ስብከቱ ሒሳብ እና በጀት ክፍል እንዲሁም በዕቃ ግዥ ላይ የተመደቡት ሐላፊዎች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ሐላፊዎቹ በዘመድ አዝማድ ከሚሠሯቸው ተገቢ ያልሆነን ጥቅም የማካበት ተግባር ውጭ ለመናገር የሚከብዱ የሥነ ምግባር ብልሽቶች ያሉባቸው እንደ ሆኑ ይነገራል፡፡

ዕድሜያቸው ከ85 ዓመት በላይ እንደ ሆኑ የሚነገረው የሀገረ ስብከቱ ጸሐፊ ቀደም ሲል በነበረው አስተዳደር የአውራጃ ቤተ ክህነት አሁን ደግሞ የሀገረ ስብከት ጸሐፊ በመሆን በቦታው ላይ ከ40 ዓመታት ላላነሰ ጊዜ የቆዩ ናቸው፡፡ ሀገረ ስብከቱ በየጊዜው ለመንበረ ፓትርያርኩ የሚያደርጋቸውን ስጦታዎች በምስጢር በማከናወን የሚታወቁት የንብረት ክፍሉ ሐላፊ ከሀገረ ስብከቱ ከሚከፈላቸው መደበኛ ደመወዝ ባሻገር ከደብረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴም ተጨማሪ ክፍያ በመደበኛነት ያገኛሉ፡፡

በደሉ በሀገረ ስብከቱ መዋቅር ውስጥ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በታላላቅ አድባራት እና ገዳማት አስተዳደር ላይ ጭምር በከፋ መልኩ የሚታይ ነው፡፡ ለአብነት ያህል በዋጃ እና ወደራ (ሰላ ድንጋይ) ወረዳ የሚገኘው የዝነኛው ደብረ ሣህል ጻድቃኔ ማርያም ገዳም የቀድሞው አስተዳዳሪ ገባሬ ሠናይ ምእመናን በስእለት እና በጎ አድራጎት የሚሰጡትን ገንዘብ በመመዝበር በደል ሲፈጽሙ የቆዩ ነበሩ ተብሏል፡፡ ስለ ጉዳዩ በገዳሙ ባሕታውያን እና ተቆርቋሪ ምእመናን ለብፁዕነታቸው አቤቱታ ቢቀርብላቸውም አስተዳዳሪው ፈጽመውልኛል ስለሚሉት ውለታ ምላሽ ሳይሰጡ ከቆዩ በኋላ ሁኔታው ሥር እየሰደደ ሲመጣ ባሕታውያኑ እና ተቆርቋሪ ምእመናኑ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አመልክተው አጣሪ ልኡክ እንዲላክ ይደረጋል፡፡

በዚህ ወቅት የገዳሙ ተጠሪነት ለሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት መሆኑ ቀርቶ እንደ ቁሉቢ ቅዱስ ገብርኤል ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ እንዲሆን አስተዳዳሪው ያቀረቡት ሐሳብ ከሊቀ ጳጳሱ ጋራ የቅያሜ ምክንያት ፈጠረና በስንት የአቤቱታ ዶሴ ያልተነኩት መነኩሴ በዚህ ‹ተንኮላቸው› ሳቢያ ከቦታቸው ተነሥተው ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ጸባቴ ሆነው እንዲዛወሩ ተደርጓል፡፡ በሸንኮራ/ምንጃር ወረዳ የከሰም በረሓ/ጅረት አቅራቢያ በሚገኘው ዶፋ ቅዱስ ሚካኤል፣ የሳማ ሰንበት እንዲሁም በደብረ መንክራት ቅዱስ ዮሐንስ ገዳም በስእለት እና በጎ አድራጎት የሚገኘው ገቢ ቀደም ሲል የተጠቀሱት የሀገረ ስብከቱ ሐላፊዎች በየሰበቡ እየመጡ በየወሩ ያለጠያቂ እየተመዘበሩት መሆኑ ተዘግቧል፡፡

የበደሉ አስከፊ ገጽታ የሚታየው ግን በእንሣሮ እና ዋዩ ወረዳ (ለሚ) የጀማ ወንዝ ዳርቻን ተከትሎ የቀናው የበልበሊት ኢየሱስ ገዳም መነኮሳት መበተን፣ የገዳሙም መፈታት ሲታይ ነው፡፡ የገዳሙ ማኅበረ መነኮሳት በግንቦት ወር 2002 ዓ.ም፣ ንጽሕ አጉድለዋል፤ ከገዳሙ በመዘበሩት ገንዘብ በአዲስ አበባ ሁለት የተለያዩ ቦታዎች ቤት ሠርተዋል፤ በጎርፍ እና በመሬት መንሸራተት ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑን ለመናድ እያሰጋ ለሚገኘው ተፈጥሯዊ ጉዳት መፍትሔ ከመሻት ይልቅ አዲስ አበባ መቀመጥ ያበዛሉ ያሏቸው አበ ምኔት ከሐላፊነታቸው ተነሥተው በምትኩ ማኅበሩ መርጦ ይሾም ዘንድ እንዲፈቀድላቸው ደብረ ብርሃን ከተማ ድረስ እየተመላለሱ ዐጽፋቸውን በጭቃ መረማመጃ ላይ ሳይቀር እያነጠፉ ሊቀ ጳጳሱን ተማፅነዋቸው ነበር። የብፁዕነታቸው ምላሽ ግን ለወሬ የማይመች ነበር፡፡ አንዳንድ ቀራቢዎቻቸው ብፁዕነታቸው እንዲህ ላሉ የብዙኀን ጥያቄዎች አስደንጋጭ ምላሽ መስጠት የለመደባቸው መሆኑን ቀድሞ የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሳሉ በደርግ-አኢወማ የክሒዶተ እግዚአብሔር ዲስኩር ለተቸገሩ ወጣቶች ሰጥተውት በነበረው ምላሽ፣ እንዲሁም በ1990ዎቹ መጀመሪያ በደብረ ብርሃን ከተማ ለሚገኘው የታሪካዊው ዘርዐ ያዕቆብ አደባባይ ቅርስ መጠበቅ የታየባቸው የአቋም መላላት(በኋላ በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ይቅርታ ቢጠይቁበትም) እንደ ምሳሌ ያወሳሉ፡፡

በገዳሙ ላይ እየደረሰ የሚገኘው የተፈጥሮ ጉዳት በመካከላችን እየተፈጸመ ባለው በደል ምክንያት በመሆኑ አበምኔቱ ይነሡልን ለሚለው የማኅበረ መነኮሳቱ ጥያቄ “ተስማሙ፤ ታረቁ” ከሚል የደፈና ምላሽ በቀር የሊቀ ጳጳሱ ዳኝነት የተነፈጉት ቁጥራቸው ከ80 - 90 የሚደርሱ መነኮሳት ከበልበሊት ኢየሱስ ገዳም በመውጣት ወደ ተለያዩ ሌሎች ገዳማት ተበትነዋል፡፡ አቤቱታ የቀረበባቸው አበምኔት ዛሬም በወረዳው ከተማ (ለሚ) ላይ ተቀምጠው በገዳሙ የቀሩትን ከዐሥር የማይበልጡ መነኮሳት በወኪል ያስተዳድሩ ዘንድ ተፈቅዶላቸው በሐላፊነታቸው ቀጥለው ይገኛሉ፡፡ የሀገረ ስብከቱ ቁጥጥር አገልግሎት ያረጋገጠው የእኒህ የአበምኔቱ ጥፋቶች ተጨባጭ ርምጃ ሳይወሰድባቸው በወረቀት ላይ ብቻ ሰፍሮ እንደሚገኝ ተገልጧል፡፡

የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት በሥሩ በሚገኙት 30 ወረዳዎች 1860 ያህል አብያተ ክርስቲያን የያዘ ቢሆንም የሰበካ ጉባኤ አስተዋፅኦ በአግባቡ ባለመሰብሰቡ ሀገረ ስብከቱ በተነጻጻሪ መመዘኛ አነስተኛ የአብያተ ክርስቲያን እና የምእመናን ቁጥር ካላቸው አህጉረ ስብከት አኳያ አጠያያቂ የገቢ መጠን ነው ለመንበረ ፓትርያርኩ ፈሰስ ያደረገው፡፡ በሀገረ ስብከቱ ጥሩ የሥራ መንፈስ ባለመኖሩ ብዙዎቹ ሠራተኞች በቤታቸው ተቀምጠው ደመወዝ ያለሥራ የሚከፈላቸው ሆነዋል፡፡ ይህም ሆኖ በ29ው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ስብሰባ ላይ የአህጉረ ስብከት የሥራ አፈጻጸም ባቀረቡት ሪፖርት ተገምግሞ በሽልማት ኮሚቴው በሚሰጣቸው ደረጃ መሠረት የምድብ ተሸላሚ እና የአሸናፊዎች አሸናፊ በተለዩበት መድረክ ላይ የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስን በሚመለከት አስገራሚ ነገር መታየቱ አልቀረም፡፡

የምድብ ተሸላሚዎችን እንዲለይ የተመረጠው የሽልማት ኮሚቴ አህጉረ ስብከት ካቀረቡት ሪፖርት ጋራ በአመዛኙ የማይጣጣም ነገር በእጅጉ አስፈላጊ የሆኑ ነጥቦችን ያካተቱ መለኪያ መስፈርቶችን ነበር የተጠቀመው፡፡ እነርሱም፣ መልካም አስተዳደርን በማስፈን፣ ማእከላዊ አስተዳደርን ጠብቆ በመሥራት፣ በምእመናን ምዝገባ እና አዲስ አማንያንን በማብዛት፣ ሕገ ወጥ ሰባክያንን በመከላከል፣ የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ እና ማጠናከሪያ የሆነውን የአንድ ከመቶ አስተዋጽኦ በቀጣይነት በመሰብሰብ፣ የሰበካ ጉባኤን አስተዋጽኦ በአግባቡ በመሰብሰብ፣ መንፈሳዊ እና ዘመናዊ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት፣ የካህናት ማሠልጠኛን በመክፈት፣ በገዳማት እና ቅርስ አጠባበቅ እንዲሁም በንብረት አመዘጋገብ እና ቁጥጥር፣ ለገዳማት እና አድባራት የተሰጠን ርዳታ በአግባቡ በማከፋፈል፣ ሰንበት ት/ቤቶችን በሁሉም አጥቢያዎች በማደራጀት እና በማጠናከር፣ በራስ አገዝ የልማት ተቋማት ሥራ እና ባስገኙት የገቢ መጠን፣ በገቢ እና ወጪ አመዘጋገብ፣ በበጀት አጠቃቀም እና በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከል እና ቁጥጥር ሥራዎች ከየምድብ ተመጣጣኞቻቸው ጋራ ተጨባጭ የሥራ ውጤት ላሳዩ የምድብ አሸናፊዎች እና የአሸናፊዎች አሸናፊ ሽልማት መስጠት ነበር፡፡

በዚህ የሥራ ፍሬ ምዘና በምድብ ሦስት ከምዕራብ ሸዋ እና ከደቡብ ምዕራብ ሸዋ-ወሊሶ አህጉረ ስብከት ጋራ የተመደበው የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት የምድቡ አንደኛ ከሆነው የምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ቀጥሎ ሁለተኛ ደረጃ አግኝቶ ነበር፡፡

የሰበካ ጉባኤ መምሪያ ለ25ው የአጠቃላይ ጉባኤ የብር ኢዮቤልዩ በዓል በ1997 ዓ.ም ባወጣው መጽሔት ላይ ባቀረበው ስታቲስቲክስ የምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት 393 አብያተ ክርስቲያን፣ 4993 ካህናት፣ 77 መምህራን፣ 41 ሰባክያነ ወንጌል እና 945‚240 የምእመናን ብዛት ያሉት ሲሆን የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ደግሞ 1763 አብያተ ክርስቲያን፣ 27‚867 ካህናት፣ 244 መምህራን፣ 278 ሰባክያነ ወንጌል እና 1‚816‚220 የምእመናን ብዛት አሉት፡፡ ስታቲስቲካዊ መረጃው ከወጣበት ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የሚኖሩት ለውጦች እንደተጠበቁ ሆነው በዘንድሮው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የገቢ ዝርዝር የምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት የዘመኑ ገቢ ብር 4‚810‚212.24 ሲሆን የሰሜን ሸዋ ደግሞ ብር 18‚113‚361.75 ነው፡፡

ከላይ በተጠቀሱት መስፈርቶች ዐይን ሁለቱ አህጉረ ስብከት ካላቸው ዘርፈ ብዙ አቅም አንጻር አጠቃላይ አፈጻጸማቸው ሲገመገም፣ በአሁኑ ወቅት ከ1860 በላይ የአብያተ ክርስቲያን ብዛት ያሉት የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ከዘመኑ ገቢው ለጠቅላይ ቤተ ክህነት 35% ብር 1‚273‚092.82 ሚልዮን ፈሰስ እንዳደረገ እና ሀገረ ስብከቱ በልማት ያስመዘገበው ገቢ ብር 17‚250 ብቻ እንደሆነ መገለጹ ገቢው የራስ አገዝ ልማት ሥራዎችን እንደ ዋና ተግባር ሳያካትት በአመዛኙ በሰበካ ጉባኤ አስተዋፅኦ፣ በስእለት እና በሙዳየ መባዕ ላይ የተመሠረተ እንደ ሆነ በብዙዎች ዘንድ የሚታመነውን እውነት ያደርገዋል፡፡ ይህም ሆኖ ከሰበካ ጉባኤ አስተዋፅኦ የሚገኘውና በአግባቡ ከማይሰበሰበው ገቢ ጀምሮ በስእለት እና በሙዳየ መባዕ በልዩ ልዩ መልክ የሚገባው ገቢ ለግለሰቦች መጠቀሚያ እየሆነ እንዳለ ተዘግቧል፡፡

በአጠቃላይ ጉባኤው ላይ የሽልማት ኮሚቴው የተሰጠውን መምሪያ ይዞ መሥራቱን የተናገሩት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ከ47 አህጉረ ስብከት መካከል በሰሜን ሸዋ  የሁለተኛነት ደረጃ መያዝ ቅር እንደተሰኙ አልሸሸጉም፡፡ ብፁዕነታቸው ለብዙ ጊዜ ተቀዳሚነትን ይዘው የቆዩ፣ በእግር ፈረስ ታዝለውም ጭምር እየተጓዙ እና ዐጽፋቸውን አንጥፈው እየተኙ ያስተማሩ የሰሜን ሸዋ የዕድሜ ባለጸጋ አባት መሆናቸውን የተናገሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ፣ በባህላችን ሽማግሌዎችን ልናስቀይም አንችልም፤ እኔ ብሆን ሕጉን ተላልፌ ለብቻቸው በአንደኛ ደረጃ እሸልማቸዋለሁ፤ እናንተም ሸልሟቸው ማለታቸው ጉባኤተኛውን አስገርሟል። እንደ ቃላቸውም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን የወርቅ አይከን ሸልመዋቸዋል፤ በፓትርያርኩ ማሳሰቢያ መሠረትም በዋና ሥራ አስኪያጁ አቅራቢነት የ21 ኢንች ቴሌቪዥን ሽልማት እንዲበረከትላቸው ተደርጓል፡፡

የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤውን አጠቃላይ ስብሰባ ተከትሎ ከተካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መጠናቀቅ በኋላ ወደ ሀገረ ስብከታቸው ያመሩት ሊቀ ጳጳሱ ‹በቤታቸው› የጠበቃቸው ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በልዩ ሁኔታ እንደሰጧቸው ያለ የአረጋዊነት ክብር አይደለም፡፡ ቀደም ሲል ብፁዕነታቸው ያለችሎታው ያስቀጠሩት በጉዳይ አስፈጻሚነት የሚያገለግላቸው የሀገረ ስብከቱ ሰንበት ት/ቤት ክፍል ሐላፊ ዲያቆን አስቻለው ፍቅር ባለጉዳዮችን በማጉላላቱ እና እጅ መንሻ በመቀበል በሀገረ ስብከቱ ሠራተኞች እና በምእመኑ ላይ በፈጠረው ምሬት በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውሎ ነበር፡፡ ሐላፊው በተደረገበት ምርመራ ጥፋቱን አምኖ ከ280‚000 ብር በላይ ያከማቸባቸው ሰነዶች በብፁዕነታቸው መኪና ውስጥ እንደሚገኝ በጠቆመው መሠረት የፍርድ ቤት ትእዛዝ የያዘው የዞኑ ፖሊስ ብፁዕነታቸው በመልስ ጉዟቸው ከጠባሴ ወዲያ ኤልካ (የደብረ ብርሃን ከተማ መግቢያ) ላይ ሲደርሱ በድንገት ላንድክሩዘር መኪናቸውን በማስቆም እና ጉዳዩን በማስረዳት እንዲፈተሽ አድርጓል፡፡

የምርመራው ሂደት አሁንም በቀጠለበት ሁኔታ ውስጥ ጥቅምት 27 ቀን 2003 ዓ.ም የዞኑ አስተዳደር ብፁዕነታቸው የቤተ ክርስቲያኒቱን ልማት እያጓተተ እና ገጽታዋን እያበላሸ የሚገኘውን ቤተ ዘመዳዊ አሠራር እና ሙስና ከአስተዳደራቸው እንዲያጸዱ ማሳሰቢያ ሰጥቷቸዋል፡፡ በአስተዳደራቸው የተማረረው ኅብረተሰብ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ እየጠየቀኝ ነው ያለው ዞኑ ማሳሰቢያውን ለመስጠት የተገደደው ችግሩን በምክክር ለመፍታት በማሰብ መሆኑን ለብፁዕነታቸው ማስረዳቱ ተዘግቧል፡፡ ችግሩ በምክክር የማይስተካከል ከሆነ ግን በአስተዳደራዊ ብልሽቱ እየጠፋ ያለው የሀገር እና የሕዝብ ሀብት ጭምር እንደ መሆኑ መጠን ጉዳዩን ወደ ፍትሕ አካል አቅርቦ በሕግ አግባብ እንዲታይ ለማድረግ ግድ እንደሚለው ለብፁዕነታቸው እንደተነገራቸው ተገልጧል፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)