November 16, 2010

አ.አ ዩኒቨርሲቲ መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ዮሐንስን ዘከረ

  • የመጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ዮሐንስ ፋውንዴሽን›› እንዲቋቋም ተጠይቋል
  •  ዝክሩ ለቤተ ክህነቱ ነቀፌታ(ተግሣጽ) ሆኖታል
  •  መጋቤ ምስጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ በዝክሩ ላይ ስለ መጋቤ ብሉይ ሰይፈ  አሟሟት የሰጡት እና ቤተ ክህነቱን የተቹበት ቅኔ ታዳሚዎችን አነጋግሯል
  • ዩኒቨርስቲው ዕውቀታቸው ለሀገር እና ለትውልድ የሚተርፉ ሌሎች ሊቃውንትንም አሥሦ የሚዘክርበት ‹‹አጉሊ መነጽር›› እንዲያደርግ ተጠይቋል
(ደጀ ሰላም፤ ኖቬምበር 16/2010፤ ኅዳር 7/2003 ዓ.ም)የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሊቃውንት ጉባኤ መምሪያ ሐላፊ ለነበሩት እና ነሐሴ አንድ ቀን 2002 ዓ.ም መንሥኤው ባልታወቀ ድንገተኛ ዕረፍት ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩት ለሊቁ መጋቤ ሰይፈ ሥላሴ ዮሐንስ የመታሰቢያ መርሐ ግብር አካሄደ፡፡ መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ዮሐንስ በዋናነት ተሳታፊ የነበሩበትን የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ፕሮጀክት ከሊቁ ዕረፍት ጋራ በአንድነት ለመዘከር ‹‹የቀለም ቀንድ ስብራት›› በሚል ርእስ በተዘጋጀው በዚሁ መርሐ ግብር በመጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ስም - የግእዝ ቋንቋ ጥናት እና ምርምር ማእከል እንዲገነባ፣ የሊቁን ፈለግ ተከትለው ጥናት እና ምርምር ለሚያደርጉ ደቀ መዛሙርት ድጋፍ የሚሰጥበት ፋውንዴሽን እንዲቋቋም፣ በክርስትናው ስም በሚጠሩ እምነቶች መካከል ለሰላም እና ልማት ተቀራርቦ የመሥራት ውይይት የሚዳብርበት መድረክ እንዲመሠረት፣ የሊቁ ነባር እና ጅምር ሥራዎች ተደራጅተው ለብርሃነ ኅትመት እንዲበቁ፣ በተለያዩ ጊዜያት ከበርካታ አገሮች ያሰባሰቧቸው መጽሐፎቻቸው እና በግል የተጻፏፏቸው ደብዳቤዎቻቸው በጥንቃቄ እንዲጠበቁ ተጠይቋል፡፡

መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ዮሐንስ መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ በሙሉ በግእዝ ቋንቋ ተተርጉሞ በአንድ ጥራዝ እንዲታተም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በተሰጠው ትእዛዝ መሠረት ከኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ጋራ በመሥራት ላይ እንደነበሩ በማኅበሩ ጠቅላይ ጸሐፊ አቶ ይልማ ጌታሁን ተገልጧል፡፡ መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ሰባክያን፣ መምህራን እና ተመራማሪዎች በሰፊው የሚጠቀሙበትን የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ካዘጋጁት አንዱ በመሆን ታላቅ እና ዘወትር የማይረሳ ተግባር ማከናወናቸውን የተናገሩት ጠቅላይ ጸሐፊው ሊቁ በማኅበሩ የቦርድ አባል እና የትርጉም ኮሚቴ ሰብሳቢ በመሆን ጥናታዊ ሥራዎችን በመሥራት እና በማማከር የፈጸሟቸውን ጉልሕ ተግባራት አስታውሰዋል፡፡

የሰማኒያ አሐዱ መጽሐፍ ቅዱስ ከግእዝ እና ከሰባ ሊቃናት ትርጉም ጋራ ተገናዝቦ በአማርኛ ሲዘጋጅ የመተርጉማኑ ቡድን ሰብሳቢ የነበሩት መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ፣ ከሞተ ዕረፍታቸው ቀደም ብሎ ለአባቶች የዕርቀ ሰላም ውይይት እና ድርድር ከተጓዙበት አሜሪካ እንደተመለሱ ‹‹ግእዝ ለኢትዮጵያ ቋንቋዎች ዕድገት እና ለቅዱሳት መጻሕፍት ትርጉም ያበረከተው አስተዋፅኦ›› በሚል ርእስ ታላቅ ዐውደ ጉባኤ ለማካሄድ የጋራ ውጥን እንደነበራቸው ጠቅላይ ጸሐፊው በሐዘን አሳውቀዋል፡፡ “ዕውቀት በአገልግሎት ሲታጀብ አገልግሎት ደግሞ በትሕትና ሲደገፍ በእጅጉ ያማረ ይሆናል” ያሉት ጠቅላይ ጸሐፊው ዛሬ ዕውቀትን ከአገልግሎት አገልግሎትን ከትሕትና አስተባብረው የያዙ ሰዎችን ማግኘት ከባድ በሆነበት ወቅት መጋቤ ብሉይ ሰይፈን ማጣታችን ከፍተኛ ጉዳት መሆኑን አመልክተዋል። ዩኒቨርስቲው መጋቤ ብሉይን መዘክሩ ያስመሰግነዋል፤ በቀጣይ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ ሊቃውንት እምነትን ለማስፋፋት ብቻ የሚሠሩ አድርጎ ሳይቆጥር ዕውቀታቸው ለሀገርም ለትውልደ ትውልድም የሚተርፉ ብዙዎች ያሉ በመሆናቸው እነርሱን በመብራት እየፈለገ ይዘክራቸው ዘንድ ‹‹አጉሊ መነጽር ማድረግ›› እንደሚያስፈልገው አሳስበዋል፡፡

መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ሩቅ በማይባል ጊዜ ውስጥ ቤተሰባቸውን መልክ አስይዘው በገዳም ተወስነው ለቤተ ክርስቲያን የሚበጅ አንድ ታላቅ ተግባር ማከናወን የዘወትር ተምኔታቸው እንደ ነበር የማኅበረ ቅዱሳን ኦዲዮ ቪዥዋል እና ሥነ ጥበባት ሥራዎች ማእከል ‹‹ቤተ መጻሕፍቱ›› በሚል ርእስ አዘጋጅቶ በመርሐ ግብሩ መካከል ባቀረበው አጭር ዶክሜንታሪ ፊልም ላይ ስለ ሊቁ የተናገሩ ቀራቢዎቻቸው ተናግረዋል፡፡ በነባሩ የቤተ ክርስቲያን ሞያ ይሁን በዘመናዊው ትምህርት ሁለ ገብነት ያላቸው ውጤታማ፣ ተኣዛዚ እና ትሑት ስለነበሩት መጋቤ ብሉይ ሰይፈ - “በመንፈሳዊ ትምህርት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል፤ በዘመናዊ ትምህርት ግን ራሱን በራሱ ያስተማረ ነበር” ብለዋል አንድ ተጠያቂ ወዳጃቸው፡፡ እኒሁ ወዳጃቸው ጨምረው እንደተናገሩት መጋቤ ብሉይ ሰይፈ በዕሥራ ምእቱ በዓል አከባበር ወቅት ‹‹የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከልደተ ክርስቶስ እስከ 2000›› በሚል ርእስ በታተመው መጽሐፍ ላይ የአንድምታ ትርጓሜን ምንነት እና አመጣጥ በተመለከተ ያበረከቱትን ጽሑፍ በመጽሐፍ መልክ አስፋፍተው የማዘጋጀት ዕቅድ ነበራቸው፡፡

የመታሰቢያ መርሐ ግብሩን የመሩት እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፊሎሎጂ መምህር የሆኑት አምሳሉ ተፈራም፣ መጋቤ ብሉይ ሰይፈ በትርጓሜ መጻሕፍት ውስጥ ባለቤታቸው ተወስኖ ሳይገለጽ ‹‹እንዲል›› እና ‹‹እንዳለ›› በሚል ብቻ የተቀመጡትን የሊቃውንቱን ጥቅሶች ሰብስቦ ምንጫቸውን ከማብራሪያ ጋራ የሚያመለክት ሥራ ለመሥራት የነበራቸውን ውጥን እንዳጫወቷቸው መስክረዋል፡፡

ሊቁ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ በመምህርነት እና በቦርድ አባልነት፣ በርእሰ መምህርነት እና በሥርዐተ ትምህርት አዘጋጅ ኮሚቴ አባልነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳበረከቱ ለመታሰቢያ የተዘጋጀው መግለጫ ያትታል፡፡ ሊቁ ለዚሁ ት/ቤት ‹‹የብሉይ ኪዳን ማስተማሪያ›› መጽሐፍ አዘጋጅተው በማቅረባቸው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት “መጋቤ ብሉይ” የሚለውን የማዕርግ ስም የካቲት 14 ቀን 1977 ዓ.ም ሰጥተዋቸዋል፡፡ በመርሐ ግብሩ ላይ ይህን ያስታወሰው የመጋቤ ብሉይ ልጅ ተዋነይ ሰይፈ ሥላሴ የማስተማሪያ ማቴሪያሉ እና ሌሎችም የሊቁ ጅምር እና ነባር ሥራዎች ለኅትመት የሚበቁበት ሁኔታ እንዲመቻች፣ በመጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ስም ፈለጋቸውን ለመከተል ለሚሹ ደቀ መዛሙርት ድጋፍ የሚሰጥበት ፋውንዴሽን እንዲቋቋም ጠይቋል፡፡ ዶ/ር አባ ቴዎድሮስ አብርሃም የተባሉ የመጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ተማሪም ሊቁ ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ለረጅም ጊዜ ያሰባሰቧቸው መጻሕፍት እና ጽሑፎቻቸው በጥንቃቄ እንዲጠበቁ፣ በስማቸውም በግእዝ ቋንቋ ዙሪያ ጥናት የሚደረግበት ማእከል እንዲቋቋም ከጣሊያን በላኩት እና በንባብ በተሰማው ደብዳቤያቸው ጠይቀዋል፡፡

ከትናንቱ የመታሰቢያ ምሽት ተናጋሪዎች መካከል ቀዳሚ የሆኑት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ባህሎች እና ቋንቋዎች አካዳሚ አጥኝ እና ተመራማሪ ዶ/ር ሥርግው ገላው መጋቤ ብሉይ ሰይፈ በግእዝ ቋንቋ እና ቅኔያት ስብስብ መድበል (ቅጽ ሁለት እና ሦስት) ዝግጅት ሂደት በአሰናጅነት፣ ተማሪዎችን በማማከር እና ጥናቶችን በማቅረብ የነበራቸውን የረጅም ጊዜ አስተዋፅኦ በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ “የሰይፈ ሞት ቅጅ እና ምትክ የሌለው መጽሐፍ እንደ መቃጠል ይቆጠራል” ብለዋል ተመራማሪው፡፡ ባለፉት ሠላሳ ዓመታት ካለፉት ዓይናማ ሊቃውንት መካከል ዩኒቨርሲቲው የክብር ዶክትሬት ዲግሪ የሰጣቸውን ዶ/ር አለቃ አየለ ዓለሙን፣ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬን፣ ሊቀ ሊቃውንት መሐሪ ትርፌን (በኋላ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ)፣ ሊቀ ሊቃውንት መንክር መኰንንን፣ ሊቀ መዘምራን ሞጎስ ዕtበ ጊዮርጊስን፣ ብፁዕ አቡነ እንድርያስን፣ ብፁዕ አቡነ ማርቆስን እና ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስን በስም እየጠቃቀሱ አነሣስተዋቸዋል፡፡ ባለፉት ዐሥር ዓመታት በሚለው የዘመን መለኪያቸውም ብፁዕ አቡነ አብርሃምን፣ ብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስንን፣ አለቃ አያሌው ታምሩን እና አራት ዐይናውን መልአከ ገነት ገብረ ሥላሴ ዐወቀን ዘክረዋቸዋል፡፡

ታዋቂው አቶ ዓለማየሁ ፋንታም፦
“ካህን ሞተ ብለው አይነግሩም ዐዋጅ፣
እንዲያው በየደብሩ መልአክ ነበር እንጅ”፣
“ከእንግዲህ መቃብር ጠንክረህ ተማር፣
ድጓ ተሸክሞ መጣልህ መምር›”፤
‹‹ሃሌ ሉያ ዝንቱሰ ብእሲ፣
እንዴት ካህን ይሙት ካህን ይቀበር፣
ጸናጽሉ የወርቅ መቋሚያው የብር”
. . . በሚሉ ስንኞች ባሰሙት ዘለሰኛ ታዳሚው በዶ/ር ሥርግው የተዘረዘሩትን ብፁዓን አባቶች እና ሊቃውንት በጥልቅ ስሜት እንዲያስባቸው የትዝታ ክንፍ እና ሠረገላ ሁነው አምሽተዋል፡፡

በመታሰቢያ መርሐ ግብሩ ላይ በመገኘት ቃለ ምዕዳን የሰጡት ብፁዕ አቡነ ገሪማ የመጋቤ ብሉይ አሟሟት “ታሪካዊ” እንደ ሆነ፣ ብዙ ቅርስ ትተውልን የሄዱ በመሆኑ እንዳሉ እንጂ እንደ ሞቱ አድርገን ልናስብ እንደማይገባ መክረዋል፡፡ መጋቤ ብሉይ ሰይፈ በድንገት ከማረፋቸው በፊት ለአባቶች ዕርቀ ሰላም ተልእኮ ከሄዱበት አሜሪካ - ዋሽንግተን ዲ.ሲ ወደ ሀገር ቤት ከብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ እና ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ጋራ የ17 ሰዓታት የመልስ ጉዞ ማድረጋቸውን የተናገሩት ብፁዕነታቸው የመጨረሻዎቹን አብሮነታቸውን እና ዜና ሞታቸውን እንዲህ አስታውሰውታል፦
       “. . .በአውሮፕላኑ ውስጥ እኔ እና ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ አንድጋ፣ መጋቤ ብሉይ ሰይፈ እና ንቡረ እድ አንድጋ ተቀምጠን ነበር የምንመጣው፡፡ ልኡካኑ በጋራ የምንመለከተው አንድ[መጽሐፍ] ስለነበር እርሱን ከአንዳችን ወደ ሌላችን        እያቀባበሉ ውይይታችንን የሚያንሸራሽሩልን መጋቤ ብሉይ ነበሩ፡፡ ጠዋት ቦሌ ስንደርስ ሻንጣችንን ይዘውልን የወረዱት መጋቤ ብሉይ ነበሩ፡፡ ወዲያው ከረጅም ጉዞ ስለገባን ቶሎ ዕረፍት ለማድረግ እኔ እና ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ በአንድ መኪና፣ መጋቤ ብሉይ ሰይፈ እና ንቡረ እድ ኤልያስ በሌላ መኪና ተከታትለን ወደየቤታችን አመራን፡፡ በየቤታችን ደርሰን ለማረፍ ስንል በሩ ተንኳኳ እና “ወንድማችን ታመዋል” ተባልን፡፡ ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስን ጠርቼ ሄድን...ካሉበት ሆስፒታል ስንደርስ ‹ከመኪና ሲወርዱ ዐረፉ› አሉን፡፡ ፊታቸውን ስናየው ነፍስ የተለየው ሥጋ አይመስልም፡፡ አሟሟታቸው       ሕመም፣ ጣዕር፣ ጋዕር የሌለው ታሪካዊ ነው፡፡. . .”

የዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የሆኑት መጋቤ ምስጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ ግን ከብፁዕነታቸው ለየት ባለ መልኩ በሰጧቸው ፍርንዱስ ቅኔዎች (ግእዝ አማርኛ ቅልቅል) መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሕይወታቸው - በመታዘዝ፣ ፍቅር እና ትሕትና፤ ሞታቸውምመታዘዝ፣ ፍቅር እና ትሕትና የተፈጸመ እንደሆነ፣ የሞታቸው ምክንያት እንደማይታወቅ እና “የቆለፉባቸው”ም እንዳልተገኙ፣ ሐዘኑ የሰዎች ብቻ ሳይሆን የሚገልጣቸው ያጡት መጻሕፍት ጭምር እንደሆነ፣ “የውጭ አልጋ የቤት ቀጋ” የሆነችው ቤተ ክህነት የውጩን ሞያ (ባለ ኤቢሲዲዎቹን) በማክበር እንደ ድመት የራስዋን ልጆች (ባለ አቡጊዳዎችን) እንደምትበላ፣ ይሁንና “ክርስቲያን እና ዶሮ ክብሩ ከሞቱ በኋላ ነውና” በመጋቤ ብሉይ ዕረፍት ሊቁ ለሚታወቁበት ግእዝ ቋንቋ እና ቅኔ እንግዳ የሆነው፣ እርሱ የማያውቀን እኛም የማናውቀው ዩኒቨርሲቲ ቤተ ክህነቱን ቀድሞ ቤተ ክህነቱ ሊሠራው ይገባ የነበረውን መዘክር በማዘጋጀት ነቀፋ/ተግሣጽ እንደሆነበት አመልክተዋል። የቤተ ክህነቱ ተግባር “መድገም/ደገማ” ብቻ እንደሆነባቸውም አልሸሸጉም፡፡

‹‹ቅኔን ለሰይፈ ሲያሳርሙት፣ ከሰይፈ ጋራ ሲነግሩት ደስ ይላል፡፡ እኛ እርሱን እየጠየቅን በምንሰጠው ቅኔ ነበር በአደባባይ ሊቅነታችንን የምናሳየው፤ ሰው መስለን የምንታየው፡፡ ከሰይፈ ወዲህ ቅኔው ጠፍቶብናል - ማንን እንጠይቅ፣ ከማን ጋራ እንስጥ? በእግዚአብሔር ሥልጣን አንገባም እንጂ ሞትም ቀሎብናል፤ መንገዳችን ወደ ሰይፈ ነውና›› በማለት የተሰማቸውን ከፍተኛ ብሶት እና ሐዘን በእንባ ገልጸዋል፡፡ በንግግራቸው መግቢያ ላይ “በመጀመሪያ መናገር አቀበት ነው፤ በመጨረሻ መናገር ቁልቁለት ነው” ያሉት የመጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ዮሐንስ የረጅም ጊዜ ባልንጀራ መጋቤ ምስጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ በመታሰቢያ ምሽቱ ላይ የታዳሚውን ቀልብ የሳቡትን የሚከተሉትን ቅኔዎች አበርክተዋል፡፡

ጉባኤ ቃና
ሕይወቱ ወሞቱ ለሰይፈ እሙንቱ
ትሕትና ወፍቅር ወተአዝዞ ሠለስቱ

መወድስ - 1
መጻሕፍተ ብሉይ ኪዳን ወቅኔያቲሁ፤
ለሰይፈ ሥላሴ መዋቲ ጸሎተክሙ አዕርጉ፤
ወኢትብይክዎ ሎቱ ወመሪረ ሐዘን ኅድጉ፤
ዳዕሙ ተዝካሮ ግበሩ በሕጉ፤
እስመ ተአዘዘ ለዘኖመ፤
ተዝካሮ ይግበሩ አዝማደ ሥጋሁ ወዘውጉ፡፡

ለዓለም
“የሰይፈ አሟሟቱ አልታወቀም፤ ‹የቆለፉበት›ም አልታወቁም”

ያርኅውዎሂ ለቤተ ቅኔ ዘአጸውዎ በደርጉ፤
ዉሉደ እንድርያስ ወጳውሊ ኅቡረ አንገለጉ፤
ሰይፈ ሥላሴ ሊቅነ ለቤተ ቅኔ መንሰጉ፤
እስመ ጠፍኣ ወኀጥእነ ምክንያተ ዘንጼጉ (ግብተ እስመ ጠፍኣ ወጠፍኡ ዘነሰጉ)

መወድስ - 2
‹‹ቅኔያት እና ዩኒቨርስቲው ተገናኙ››
ግብረ ቤተ ክህነት ኮነ ግብረ ዩኒቨርሲቲ፤
እስመ ዩኒቨርሲቲ ሰበከ ትንሣኤ ሙታን በዐውዳ፤
እንዘ ቤተ ክህነት ይእቲ ለውሉደ ቤታ ቤርሙዳ፤
ወሚመ ከመ አርዌ ቤት ትበልእ ውሉዳ፤
ወቅኔያቲነ ይሰግዳ፤
ለዩኒቨርሲቲ ውእቱ እስመ ለቅኔያት እንግዳ፡፡

ለዓለም
‹‹ቤተ ክህነት የውስጥ ቀጋ የውጭ አልጋ››
ለቤትሂ አሜከላሁ ወአራተ አፍኣ ለባዕዳ፤
ቤተ ክህነት ለውሉዳ ዘኮነት ቤተ ፍዳ፤
እም ጥበብ ርእሳ ታከብር ጥበባተ ባዕድ ጸኣዳ፤
አምጣነ አክበረት ኤቢሲዲ ወአስሐቀረት አቡጊዳ፡፡

በንግግሩ፣ በቅኔው እና በፊልሙ በዩኒቨርስቲው የተደረገውን የመጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ዮሐንስ መታሰቢያ የፎክሎር ሥልጡኑ ጋዜጠኛ ኄኖክ ያሬድ እንደሚከተለው በባሕረ ሐሳብ ቀመር ዘክሮታል፡-
     
     በ7503 ዓመተ ዓለም
      በ2011 ዓመተ ምሕረት(በፀሐይ እና በጨረቃ ድምር አቆጣጠር)
      በ2003 ዓመተ ሥጋዌ
      በ1727 ዓመተ ሰማዕታት
      በ55 ዓመተ ድሜጥሮስ
     በ283 ቀመረ ቢዘን
    በ131 ቀመረ ጒንዳጒንዲ
    ሌሊቱ አራት ጨረቃ ስምንት
    አበቅቴ ፀሐይ አራት አበቅቴ ወር 26
    ትንሣኤ ሚያዝያ 16 በሚውልበት
    በዘመነ ሉቃስ ወንጌላዊ የመጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ዮሐንስ መታሰቢያ በአዲስ  አበባ ዩኒቨርስቲ ተደረገ፡፡

ትናንት ከቀኑ 11፡ 40 እስከ ምሸት 2፡00 ድረስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ጥናት እና ምርምር ተቋም አዳራሽ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ገሪማ እና ዲሜጥሮስ፣ የዩኒቨርስቲው ምሁራን እና ተማሪዎች፣ የመጋቤ ብሉይ ቤተሰቦች እና ወዳጆች በተገኙበት የተከናወነውን የመታሰቢያ መርሐ ግብር ከኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ጋራ በመተባበር ያዘጋጁት የኢትዮጵያ ጥናት እና ምርምር ተቋም፣ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናት እና ምርምር ማእከል፣ የሥነ ልሳን እና ፊሎሎጂ ትምህርት ማእከል ናቸው፡፡

12 comments:

Anonymous said...

በጣም ደስ የሚል ነገር ነው

Anonymous said...

menkir ! Etsub ! Etsub ! Grum...

Anonymous said...

Thank you Very much DS and Thank you Megabi Mestir Wolderufaiel for your touching geez poems.

ሰይፈ ሚካኤል said...

ይሄንን በጣም ወደድኩት...

‹‹ቤተ ክህነት የውስጥ ቀጋ የውጭ አልጋ››
ለቤትሂ አሜከላሁ ወአራተ አፍኣ ለባዕዳ፤
ቤተ ክህነት ለውሉዳ ዘኮነት ቤተ ፍዳ፤
እም ጥበብ ርእሳ ታከብር ጥበባተ ባዕድ ጸኣዳ፤
አምጣነ አክበረት ኤቢሲዲ ወአስሐቀረት አቡጊዳ፡፡

ማህበረ፡ክርስቲያን said...

ከንቱ፡ውዳሴ፡የሚባል፡ነገር፡ሰምተን፡የምናቅ፡ከሆነ፡ቢበቃን፡ጥሩ፡ነው፡፡

Anonymous said...

Qinewocu beqenenetachew yibel yemibalu nachew. Bezu yatsatsaf sihitetoch selalu gin tsehafiw biyaremachew.

Bogale Dagne

Anonymous said...

መጋቤ ብሉይ ሰይፈ የተከበሩ ዐይናማ ምሁር ናቸውና መታሰባቸው አግባብ አለው። ነገር ግን "አኮኑ አፅባዕት እምነ አፅባዕት የዐቢ" እንደተባለ የሊቅነት ደረጃቸውም ኾነ ሕዝብን በዑቀታቸው ያገለገሉት አገልግሎት መጠን እንደርሳቸው በዚሁ ዘመን ካለፉት ከነአለቃ አያሌው እና አቡነ መርሐ-ክርስቶስ "ሕቀ ዘየሐፅፅ" መኾኑን ራሳቸውም የሚክዱት አይመስለኝም።

እናሳ ዩኒቨርሲቲው በነአለቃ ስም ምን አድርጎ ኖሯል አኹን "ፋውንዴሽን" ምናምን የሚለው? የምርጫ ሚዛኑ ላገር ያበረከቱት አስተዋፅኦ ብቻ ሳይኾን ፖለቲካዊ ወይም ወዳጅነት ቢጤ ያለበት ይመስላል።

Anonymous said...

ይህ ዝክር ለብጹዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስና መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ በጣም ያንሳቸዋል። በሞታቸው እጅግ... ባዝንም ኡፍ እግዚአብሔር ይመስገን እንኳን የሁለታቸው ቴዎሎጂን ሳልሸምት ወደ አከበርኸው መኖርያ አልወሰድካቸው!!!

የመቀለ ቴዎሎጂያን

Anonymous said...

ይህ ቀረህ ለማይባለው አራት አይናማ ሊቅ ለመጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ አይቻለንም እንጅ ከዚህም በላይ ቢደረግላቸው ባልከፋ ነበር።ነገር ግን አዲስ አበባ ዩኒበርሲቲ እኒህን መተኪያ የሌላቸው ሊቅ ስለዘከረ ሰይጣናዊ ቅናት ያደረባችሁ ሰወች የምትጽፉትን ሳነብ በጣም ገርሞናል።እግዚአብሔር ይህን ክፉ የቅናት መንፈስ ያርቅላችሁ።
ለአዲስ አበባ ዩኒበርሲቲ ፥ለመጋቤ ምሥጢር ወልደ ሩፋኤል ፥ ለዶክተር ሥርግው ገላው እና ለዚህ የተቀደሰ ተግባር አስተዋጽኦ ያደረጋችሁትን ሁሉ እግዚአብሔር ሁል ጊዜ በመልካም ነገር ያስባችሁ።

ደጀ ሰላም አንቺንም እግዚአብሔር ይባርክሽ።
አንቺ ባትኖሪ ኑሮ ይህን የመሰለ መልካም ዜና ማን ያበስረን ነበር ።
M.T.A.B.

ዘ ሐመረ ኖህ said...

ለተወህዶ እምነታችንና ለሥርዓተ ቤተከርስትያን መከበር ብዙ መስዋእትነት ከፍለው ካለፉት ሊቃውንት መካከል እንደነ አለቃ አያሌው እና አቡነ መርሐ ክርስቶስ ወዘተ ያሉትን እንደ መጋቤ ሰይፈ ሥላሴ መዘከር ያስፈልጋል ሊቃውንቱን ለመዘከር አድልዎ አይኑር አድልዎ ለቋሚም ለሟችም ጉዳት እንጂ ጥቅም የለውም እንኳን ላረፉትንና ይቅርና ለቆሙትም አደልዎ መፈጸም ሃጥያት ነው ይህንን ማለት ደግሞ እንደ M.T.A.B.ሰይጣናዊ ቅናት አይደለም ማንም ሰው ለሚሰራው ስራም ሆነ ለሚሰጠው አስተያየት በመድርም ይሁን በሰማይ ዋጋውን ከአግዚአብሔር ያገኛል አግባብ ባለው መልኩ ቋሚንም ሟችንም ማመስገን መልካም ቢሆንም ውዳሴ ከንቱ ግን ዋጋ የሚያሳጣ ከመሆኑም በላይ ኃጥያት ነው በየተገኘው አጋጣሚ ከምንናቆር ይልቅ ቢያንስ ያረፉት ሊቃውንት ያስተማሩንን ተግባራዊ ብናደርገው ግን ለነሱም ለኛም ትልቅ ጥቅም አለው ባይ ነኝ ቸር ይግጠመን

tad said...

I remeber some brothers and sisters were telling us Seife and Abune Merha were among the leading members of tehadisos in EOC. I am happy the time came to broaden our mind.
Seife and Abune Merha both are irreplaceable theologians.
Fathers, R.I.P.
Tad

Anonymous said...

Don't you know Abune Merha Kirstos?
Sorry, in my long-time, his grace was the only theoretical and practical philosopher, father of the curch, all-rounded man of Christ. I really tasted him. It was after him, the Synod came to be broken into two and then multiple pieces.

Ahhhhhhhhhhhhhhhhhhhhhhhhhhhhhh!!!

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)