November 15, 2010

በዱባይ ሻርጃ ለአንድ ወር የሚዘልቅ የስብከተ ወንጌል ጉባኤ ሊካሄድ ነው

  • በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የሊባኖስ እና አካባቢው አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዲሜጥሮስ አህጉረ ስብከታቸውን እያወኩ በሚገኙት ሕገወጦች  ላይ ርምጃ እንዲወሰድ ቋሚ ሲኖዶሱን በደብዳቤ ጠይቀዋል፡፡ 
  • ከሕገ ወጦቹ አንዱ የሆነው እና በአገር ውስጥ በስም ማጥፋት ወንጀል ክስ የተመሠረተበት በጋሻው ደሳለኝ ነገ ወደ ሥፍራው ይጓዛል፤
  • "የዱባይ ቅዱስ ሚካኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን"  በሚል ጉባኤ ለማካሄድ የተዘጋጁት አካላት ሕገ ወጥ መሆናቸው ተገልጧል፤
(ደጀ ሰላም፤ ኖቬምበር 14/2010፤ ኅዳር 5/2003 ዓ.ም)በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የሊባኖስ እና አካባቢው አህጉረ ስብከት ሥር በሚተዳደረው በዱባይ - ሻርጃ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ለአንድ ወር የሚዘልቅ የስብከተ ወንጌል ጉባኤ ተዘጋጀ፡፡ የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳደር የስብከተ ወንጌል ጉባኤውን ለማስተዋወቅ ‹‹ሕዝቤ ሆይ ወደ ቤትህ ግባ›› በሚለው የነቢዩ ኢሳይያስ መሪ ቃል ባወጣው ፖስተር ላይ እንደተገለጸው፣ ጉባኤው የሚካሄደው በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዲሜጥሮስ ተባርኮ ወደ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የገባው የሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ታቦት ኅዳር 12 ቀን 2003 ዓ.ም ከመንበረ ክብሩ ወጥቶ የሚደረገውን ክብረ በዓል መሠረት አድርጎ ነው፡፡

በዕለቱ ታቦቱ በአበው መነኮሳት እና ካህናት እንዲሁም የሀገራቸውን ሥርዐተ እምነት እና የተቀደሰ ትውፊት በሚያከብሩ የተዋሕዶ ልጆች ታጅቦ ከመንበሩ ክብሩ እንደሚወጣ የተገለጸ ሲሆን በስደት ያሉ ወገኖች ሁሉ እንዲሁም በተለያዩአጋጣሚዎች በአካባቢው የሚኖሩ ኦርቶዶክሳውያን በክብረ በዓሉ ላይ በመገኘት እና በጉባኤው በመሳተፍ ከሊቀ መልአኩ በረከት እንዲሳተፉ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

በአህጉረ ስብከቱ ከተመሠረተች ዐሥራ አምስት ዓመታት ያህል ያስቆጠረችው የዱባይ-ሻርጃ ቅድስት ማርያም እና ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በአህጉረ ስብከቱ ከሚገኙት የአቡዳቢ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም እና ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት እና የአላየን ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ቀደምት የሆነች ነች፡፡ በአህጉረ ስብከቱ በከፊል በቤት ሠራተኝነት እና በሌሎች የቀን ሥራዎች ላይ የተሠማሩ ቀናዒ እና ትጉሃን ምእመናን ይገኙበታል፡፡ ምእመናኑ ከዐበይት በዓላት መካከል የመስቀል ደመራ በዓልን በዱባይ-ሻርጃ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም እና ቅዱስ ሚካኤል፣ ልደተ እግዚእን እና ትንሣኤን በአቡዳቢ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም እና ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ ከተራን/ጥምቀተ ክርስቶስን በአላየን ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል አብያተ ክርስቲያን በመሰብሰብ በአንድነት የማክበር በጎ ልማድ አላቸው፡፡

ከዚህ በፊት በቀደምቷ የዱባይ-ሻርጃ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም እና በሌሎቹም አብያተ ክርስቲያን በርካታ ሰባክያነ ወንጌል እና ዘማርያን በአህጉረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ፈቃድ ከአዲስ አበባ እና ከሌሎቹም ክፍላተ ዓለም እየሄዱ የቀናውን ኦርቶዶክሳዊ ትምህርተ ሃይማኖት እና ሥርዐተ እምነት፣ ምክር እና ተግሣጽ የሚመሰክር አገልግሎት ሰጥተዋል፤ በአገልግሎቱም የማይናቅ ውጤት ተገኝቷል፡፡ ከኅዳር 12 ቀን ጀምሮ ለአንድ ወር በሚዘልቀው የስብከተ ወንጌል ጉባኤ አገልግሎት ለመስጠት ከአዲስ አበባ ጥሪ የተደረገላቸው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የደቡብ አፍሪካ ሀገረ ስብከት ስብከተ ወንጌል ሐላፊ መምህር ዳንኤል ግርማ እና ዘማሪት ለምለም ከበደ ናቸው፡፡

ዘማሪ ቴዎድሮስ ዮሴፍ
ከሁለቱ አገልጋዮች ተልእኮ ቀደም ብሎ ካለፈው ዓመት ነሐሴ ወር መጀመሪያ አንሥቶ እስከያዝነው ዓመት መስከረም ወር ድረስ በመምህር ጳውሎስ መልክአ ሥላሴ እና ዘማሪ ቴዎድሮስ ዮሴፍ ሲሰጥ የቆየው አገልግሎት በምስል ወድምፅ ተቀርጾ የዚህ መጦመሪያ መድረክ ተከታታይ በሆኑ ዱባያውያን ደርሶን እንደተመለከትነው፣ በአሁኑ የስብከተ ወንጌል ጉባኤ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባቸው ነጥቦች የተነሡበት ሁኔታ ይታያል፡፡

ከፊልሙ መረዳት እንደሚቻለው በአንድ የጥያቄ እና መልስ መርሐ ግብር ላይ ምእመናኑ ለመምህር ጳውሎስ ካቀረቡላቸው ጥያቄዎች ብዙዎቹ ክብረ ቅዱሳንን እና ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን የሚከቡ ናቸው፡፡ በወቅቱ መምህሩ ለጥያቄዎቹ መድረኩን የሚመጥን አጥጋቢ ምላሽ ቢሰጡም ጥያቄዎቹ ግን ከይዘታቸው ባሻገር በአቀራረባቸው በአህጉረ ስብከቱ ውስጥ ሥር የሰደደውን ከባድ ፈተና የሚጠቁሙ ጭምር ናቸው፡፡ ምእመናኑ በጥያቄአቸው ውስጥ ቅዱሳንን ማክበር እና በቃል ኪዳናቸው አማላጅነት መማፀን - ‹‹ግብጻውያን የጫኑብን ጣጣ ስለሆነ እንደማያስፈልግ›› መማራቸውን ተናግረዋል፡፡ እንደ ምእመናኑ ጥያቄ፣ አንዲት ሴት በደመ ጽጌዋ ወቅት ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዳትገባ እና ቅዱስ ቁርባንን እንዳትቀበል የምትከለከለው - ‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን ኦሪታውያን ስለሆንን ከዚያ በልማድ ተይዞ ነው እንጂ እንደማያስፈልግ›› ተምረዋል፤ እንዲያውም ልማደ አንስት እየታያቸውም ቢሆን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቆሞ ማስቀደስ እና ሥጋ ወደሙን መቀበል እንደሚችሉ፣ ይህን መቃወም ‹‹አጉል ማክረር›› መሆኑን ያስተማሯቸውን መምህራን በስም ይጠቅሳሉ፡፡ ከዚህ በባሰ መልኩ ‹‹የተለያየ ችግር ያለባቸውን በቤት ውስጥ ለማጥመቅ እና በግል ምክር ለመስጠት›› በሚል የቤተ ክርስቲያኒቱን ትምህርተ ሥጋዌ እና ነገረ ቅዱሳን በማሳከር በድብቅ የሚያስተምሩ ውስጠ ተኩላ ‹ሰባክያን› እንዳሉ፣ ምእመናኑ በቅዱሳን መላእክት፣ በቅዱሳን ጻድቃን፣ በቅዱሳን ሰማዕታት ስም ሲያደርጉ ከቆዩት ዝክር በማሸሽ - ‹‹በኢየሱስ/መድኃኔዓለም ስም›› እንዲዘክሩ መደረጋቸውን የጥያቄው መንፈስ ጨምሮ ያጋልጣል፡፡

ለ‹‹መምህራን ነን›› ተብዬዎቹ እኒህን እና ሌሎችንም የለየላቸው የተሐድሶ መናፍቃን አግባብ የተከተለ የክሕደት እና ጥርጥር እርሾ ለመዝራት በዋናነት ቅልዝ መሬት/fertile ground/ የሆነላቸው፣ በአህጉረ ስብከቱ ሥር ከሚተዳደረው የዱባይ-ሻርጃ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከፍለው በመወሰድ በሰበሰቧቸው ምእመናን ያለአህጉረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ፈቃድ እና ቡራኬ አቋቁምነው የሚሉት የ‹‹ዱባይ ቅዱስ ሚካኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን›› ነው፡፡

በመሠረቱ በ1991 ለሦስተኛ ጊዜ ተሻሽሎ በወጣው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ቃለ ዓዋዲ አንቀጽ 44 እና በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 37 መሠረት አንድ የሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሀገረ ስብከቱ ውስጥ አዲስ ለሚተከሉ አብያተ ክርስቲያን በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት ፈቃድ የመስጠት፣ የመሠረት ድንጋይ የማኖር እና ቅዳሴ ቤቱን የመባረክ ሥልጣን እና ተግባር አለው፡፡ ሊቀ ጳጳሱ በሀገረ ስብከቱ ያሉትን አብያተ ክርስቲያን አስተዳደር በጠቅላላ ሐላፊነት የሚመራ፣ በየጊዜው መንፈሳዊ ምክር፣ መምሪያ እና ቡራኬ በመስጠት የሚያበረታታ የካህናቱ እና የምእመናኑ ሁሉ መንፈሳዊ አባት ነው፡፡ ስለሆነም አንዲት፣ ቅድስት፣ ከሁሉ በላይ እና ሐዋርያዊት የሆነችው ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊነቷ እና ታሪካዊነቷ በሰላም ተጠብቆ እንዲኖር እንዲሁም ምእመናን በባዕድ እምነት አስፋፊዎች እንዳይሰረቁ ብርቱ ጥበቃ ያደርጋል፡፡ በቃል እና በጽሑፍ ፈተና ተጣርተው ለሚቀርቡለት የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች የዲቁና እና የቅስና ማዕርግ ይሰጣል፤ በሞያቸው ብቁ የሆኑትን እና በግብረ ገብነታቸው የታወቁትን እያጠና እና እየመረጠ የገዳማት እና አድባራት አስተዳዳሪ አድርጎ ይሾማል፤ ከሚያገለግሉበት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መሸኛ ደብዳቤ ላልያዙ እና በቂ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ለሌላቸው ክህነት አይሰጥም፡፡ በሀገረ ስብከቱ ስም በባንክ የሚገኘውን ገንዘብ ከሥራ አስኪያጁ ጋራ በጣምራ ፊርማ ያንቀሳቅሳል፡፡

አቡነ ዲሜጥሮስ (ከመካከል)
በባር ዱባይ በሲሞናዊ መንፈስ በሚመሩት ሕገ ወጥ አካላት የሚፈጸመው ተግባር ግን ከዚህ በላይ ለሊቀ ጳጳሱ የተሰጠውን ሥልጣን እና ተግባር የማያከብር፣ የግል እና የቡድን ጥቅምን ከማሳደድ በቀር የቤተ ክርስቲያኒቱ አሐቲነት መጠበቅ፣ የኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ እና ሥርዐት መጽናት እና መስፋፋት የማይገደው ነው፡፡ ሕገ ወጡ የጥቅም እና የኑፋቄ ቡድን በቅዱስ ሚካኤል ስም አቋቋምኩት የሚለው ‹‹ቤተ ክርስቲያን›› በፍትሐ ነገሥት ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ አንድ በሚያዝዘው መሠረት በኤጲስ ቆጶሱ ፈቃድ የተሠራ፣ ቅዳሴ ቤቱም በክፍሉ ኤጲስ ቆጶስ የተባረከ አይደለም፤ ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን›› ተብሎ ሊጠራም አይችልም፡፡ የአንቀጹ ድንጋጌ እንደሚከተለው ይላል - ‹‹ቤተ ክርስቲያን ግን የጸሎት ቤት ናት፤ ማንም ሰው ከኤጲስ ቆጶሱ ፈቃድ ውጭ ቤተ ክርስቲያንን ቢሠራ ለዘላለሙ ቁርባን አይቅረብባት፤ ቁርባን ያቆረበባት ካህን ቢኖር እንኳን ለዘላለም ክህነቱ ይሻር፡፡››

የሕገ ወጥ ቡድኑን ድርጊት በቅርበት ከሚከታተሉ ወገኖች አንዳንዶቹ በ‹‹ዱባይ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን›› ለማስመሰል ከሚታየው ባእድ ነገር በቀር በርግጥም ታቦተ ሚካኤል እንደሌለ በአንድ ወቅት ለአገልግሎት ተጠርተው በስፍራው አጭር ቆይታ ያደረጉቱ የሚሰጡትን ዋቢ በመጥቀስ ቢናገሩም፣ ሌሎች ጥቂቶችም ‹ታቦቱ› ውዝግቡን በጠነሰሱት እና በደፈደፉት ወይዛዝርት ትእዛዝ ተደብቆ እንጂ ብፁዕ አባት ተባርኮ መምጣቱን እንደሚያውቁ ቢጠቅሱም ሊሳት የማይገባው ዐቢይ ጉዳይ ግን ሁሉም ነገር ከሆነው ጀምሮ እንደ ፍትሐ ነገሥቱ ትእዛዝ በክፍሉ ጳጳስ ፈቃድ የተከናወነ አለመሆኑ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ይቅርና ታዛቢዎቹ እንደሚመሰክሩት፣ ቡድኑ በገንዘብ እያማለለ ካመጣቸው ካህናት ብዙዎቹ በጸሎተ ቅዳሴው ወቅት በሥርዐቱ የታዘዘውን ጠንቅቆ በመፈጸም ረገድ የሚያሳዩት ግዴለሽነት በዋናነት የግል ጥቅማቸውን ለማድለብ የሚተጉ መሆናቸውን ከማመልከቱም ባሻገር ወትሮም ያልጣፈባቸውን ኦርቶዶክሳዊ ማንነት የሚያጋልጥ ነው፤ ጉዳዩ ለንግግር የሚመች ባለመሆኑ እዚህ ላይ ለመግለጽ የማይሞከር ነው፡፡

ብፁዕ አቡነ ዲሜጥሮስ
በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የሊባኖስ እና አካባቢው አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ዲሜጥሮስ ተገንጣዩ ቡድን ያለመንበረ ጵጵስናው ፈቃድ ከአዲስ አበባ በየጊዜው ሕገ ወጥ ‹ሰባክያን›ን በሕገ ወጥ መንገድ ማምጣቱን እንዲያቆም፣ ከሻርጃ ሰአሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በቦታ መራቅ በማሳበብ ለይቶ በግለሰብ ቤት ‹‹በጽዋ ማኅበር›› ስም በማሰባሰብ ቆይቶ በባር ዱባይ ወደ አዳራሽ ያስገባቸው ምእመናን ወደ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው እንዲመለሱ፣ ‹‹የቅዱስ ሚካኤልን ቤተ ክርስቲያን ለማሠራት እና አገልጋዮችን ከአዲስ አበባ ለማስመጣት›› በሚል በተለያዩ ጊዜያት የገቢ ማስገኛ መርሐ ግብሮች እየተዘረጉ በግለሰቦች የግል አካውንት እየገባ ያለው የገባሬ ሠናይ ምእመናን ገንዘብ ብዝበዛ እንዲቆም አብዝተው እና መላልሰው ለሰጡት መምሪያ እና ምክር ለመገዛት ፈቃደኛ አልሆነም።

እንዲያውም ሊቀ ጳጳሱን ፊት ለፊት ከመዝለፍም በላይ ከሀገረ ስብከቱ ለማስነሣት አዲስ አበባ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ድረስ በሀገር ውስጥ ጉዳይ አስፈጻሚዎቻቸው ደጅ የጠኑ፣ እርሳቸው ያልፈቀዱትን ‹‹ቤተ ክርስቲያን›› ሕጋዊነት ለማልበስ የጣሩ፣ በንዋያቸው ብዛት ‹‹አገልጋይ ነን›› ባዮችን እያማለሉ እንዳሻቸው መዘወር የለመዱ ወይዛዝርትን እስከማየት ተደርሶ ነበር። በመሆኑም ሊቀ ጳጳሱ ውግዘት አስተላልፈውባቸዋል፡፡ ጉዳዩን ለማጣራት ቅዱስ ሲኖዶስ ብፁዕ አቡነ ገሪማ፣ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ እና መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ዮሐንስ የሚገኙበት ልኡክ ወደ ስፍራው ልኮ ነበር፡፡ ለቅዱስ ሲኖዶስ የቀረበው የአጣሪው ልኡክ ሪፖርት ‹‹የሊቀ ጳጳሱን ትዕግሥት እናደንቃለን›› የሚል ቃለ አንክሮ ማስቀመጡ ብፁዕነታቸው የቱን ያህል ጉዳዩን በጥንቃቄ እንደ ያዙት ያስረዳል፡፡

ይሁንና ትእግሥቱ እርምት ያልሆናቸው ሕገ ወጡ ቡድን አባላት በአውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር ባወጡት መርሐ ግብር ከኖቬምበር 12 - 19 ቀን 2010 ዓ.ም የሚቆይ ‹‹የትምህርተ ወንጌል ጉባኤ›› ማዘጋጀታቸውን ካሰራጩት ፖስተር ለመረዳት ተችሏል፡፡ በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የሊባኖስ እና አካባቢው አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዲሜጥሮስ አህጉረ ስብከታቸውን እያወኩ በሚገኙት ሕገ ወጦች ላይ ርምጃ እንዲወሰድ ቋሚ ሲኖዶሱን በደብዳቤ ጠይቀዋል ተብሏል፡፡

‹‹ነፍሴ ወደ ሕያው አምላክ ተጠማች›› በሚል ርእስ ሕገ ወጦቹ የሚያዘጋጁት ጉባኤ ዋነኛ አስተባባሪ አሁን በስፍራው በክህነት እያገለገለ እንደሆነ የሚነገርለት ቀሲስ ተስፉ እንዳለ ነው፡፡ ቀሲስ ተስፉ በጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ የዱባዩ ‹ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን› ሕጋዊ እንዲሆን በዱባይ ምእመናን ስም ለመጠየቅ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ዘንድ ቀርቦ የነበረ ቢሆንም ጉዳዩ በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በኩል እንዲመጣ በብፁዕነታቸው በኩል ስለተነገረው ፊቱን ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ዙሪያ ወደሚገኙ ግለሰቦች ማዞሩ ተገልጧል፡፡

ነገ ሰኞ ወደ ዱባይ እንደሚበር የተነገረለት በጋሻው ደሳለኝ በማኅበረ ቅዱሳን የድሬዳዋ ማእከል የስም ማጥፋት ወንጀል ክስ ተመሥርቶበት በፖሊስ ታስሮ ከቀረበ በኋላ ለኅዳር 23 ቀን 2003 ዓ.ም ለብይን እንዲቀርብ መቀጠሩ ይታወሳል፡፡ በማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን በተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅነቱ ከተባረረ በኋላ በደቡብ ኢትዮጵያ (አላባ) ቀናኢ ኦርቶዶክሳውያንን በማሳደድ የታወቀው ተረፈ ለማ በያዝነው የትምህርት ዘመን ወደ ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የተቋሙን የቅበላ መስፈርት ሳያሟላ የትብብር ደብዳቤ በጻፉለት አካላት ውትወታ በመግባቱ ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠመው ነው፡፡ በተመሳሳይ አኳኋን የዲግሪው መርሐ ግብር ለመከታተል በሕገ ወጥ መንገድ ባጻፈው የትብብር ደብዳቤ እና ከኮሌጁ የቅበላ መስፈርት ውጭ ወደ ተቋሙ የገባው አሰግድ ሣህለ ጉዳዩ በኮሌጁ የበላይ ሐላፊ ሊቀ ጳጳስ እና በኮሌጁ የአስተዳደር ጉባኤ እየተጤነ ይገኛል፡፡ የዓላማ ተጋሪው የሆነው ቀሲስ አሸናፊ ገብረ ማርያምም በተመሳሳይ አኳኋን ግፊት በፈጠሩለት ወገኖች እገዛ ወደ ኮሌጁ በቀኑ መደበኛ መርሐ ግብር ተመዝግቦ ቢገባም ውሳኔው ተቃውሞ ስለገጠመው በአስተዳደሩ እየተጤነ ይገኛል፡፡

አሰግድ በኮሌጁ ትምህርቱን በዲፕሎማ መርሐ ግብር ይከታተል በነበረበት ወቅት በአዲስ አበባ ደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤት እንዲሁም በኮሌጁ የመማር ማስተማር ሂደት እና በደቀ መዛሙርቱ መካከል ያደርግ የነበረው የኑፋቄ እንቅስቃሴ ተደርሶበት ከሰንበት ት/ቤቱ የተባረረ ሲሆን በኮሌጁ አስተዳደር ደግሞ ዲፕሎማው ተይዞበት እንደቆየ ተዘግቧል፡፡

በ29ው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ስብሰባ ላይ በስብከተ ወንጌል ቀን ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አህጉረ ስብከት ስለሚልኳቸው ደቀ መዛሙርት የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ምክትል አካዳሚክ ዲን ‹‹የአንዳንድ አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት በፊርማቸው እና በማኅተማቸው የሚልኳቸው ደቀ መዛሙርት በእነርሱ ደብዳቤ ‹አራት ዓይና› ተደርገው ቢሞገሱም፣ ከ75 - 80% በመቶ ለቤተ ክርስቲያን ትምህርት ዝግጅት ትኩረት በሚሰጠው የኮሌጁ የመግቢያ ፈተና ማጣራት ሲደረግ ግን በግብረ ዲቁና ሙሉ ያልሆኑ፣ በስመ አብ ብለው ውዳሴ ማርያም መድገም የማይችሉ›› በመሆናቸው ውድቅ እንደሚደረጉ አስረድተው ነበር፡፡ ዲኑ አያይዘው እንደገለጹት ርምጃው ከተወሰደ በኋላ አንዳንድ ሊቃነ ጳጳሳት ስልክ እየደወሉ፣ ‹‹የደቡብን ቤተ ክርስቲያን ለመዝጋት ተነሥተሃል›› እያሉ ሁኔታውን ወዳልታሰበ አደገኛ አቅጣጫ በመውሰድ በሚፈጥሩት ግፊት ኮሌጁ ያለአግባብ ገና በሀሁ ደረጃ ያሉትን እና ውዳሴ ማርያም ያልደገሙትን ከሊቃውንቱ ጋራ ቀላቅሎ ለማስተማር እየተገደደ እንደሆነ አጋልጠዋል፡፡

አሁን ብዙዎችን እያሳሰበ የሚገኘው ቀደም ሲል የተዘረዘሩት ግለሰቦች ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከሀገረ ስብከታቸው ውጭ በሚገኙ ብፁዓን አባቶች ሳይቀር የድጋፍ ደብዳቤ እያጻፉ መግባታቸው ብቻ አይደለም፡፡ ከዚህ በላይ ወደ ተቋማቱ ከገቡ በኋላ የማቴሪያል እና የፋይናንስ ሰቀቀናቸውን በሚያሟሉላቸው አጽራረ ቤተ ክርስቲያን እገዛ ደቀ መዛሙርቱን በገንዘብ እንርዳ በሚል በጥቅም ለመደለል፣ በድለላው ዙሪያም መልካም ስም እና ዝና በማትረፍ ዓላማቸውን የሚጋራ አንጃ/ቡድን በማበራከት ልዩነትን መፍጠር፣ ከተቋሙ የሚሰጣቸውን ዲፕሎማ እና ዲግሪ በመያዝ የቤተ ክርስቲያኒቱን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት መቆጣጠር እና በዐውደ ምሕረቷ ላይ በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ስልት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በማጠናከር ዓላማቸውን ማሳካት መሆኑ ግልጽ እየሆነ መምጣቱ ነው፡፡

በኮሌጁ የሚኖራቸው ቆይታ በመጤን ላይ እንደሆነ ከተገለጸባቸው ከእነዚህ ግለሰቦች ብዙዎቹ በዱባይ የሚገኘውን ሕገ ወጥ ቡድን እንቀስቃሴ ከጅምሩ አንሥቶ በማደራጀት ሚና የነበራቸው ናቸው፡፡ አሁን እናደርገዋለን የሚሉት ‹‹የትምህርተ ወንጌል ጉባኤም›› የሀገር ውስጥ ክስረታቸውን ከመሸፈን የዘለለ ዓላማ ሊኖረው አይችልም፡፡ በመሆኑም በስደት ይሁን በሥራ ጉዳይ በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የሊባኖስ እና አካባቢው አህጉረ ስብከት የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን ሁሉ በዱባይ-ሻርጃ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ኅዳር 12 ቀን 2003 ዓ.ም በሚካሄደው የሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ክብረ በዓል ላይ በመገኘት እና ለአንድ ወር የሚዘልቀውን የስብከተ ወንጌል ጉባኤ በመሳተፍ አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ ቀርቧል፡፡

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)