November 13, 2010

በሐዋሳ ለብፁዕ አቡነ ገብርኤል ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው

  • ከ20 በላይ መኪኖች እና ሰባት ሞተረኞች ጥቁር ውኃ ላይ ተሰልፈው  ተቀብለዋቸዋል፤ ፓትርያርኩ አልተገኙም፡፡
  • ብፁዕነታቸው፣ ‹‹ውበት የሚኖረው በአንድነት ውስጥ በመሆኑ በኅብረት   አንድ ሆነን መገኘት ያስፈልገናል፤›› በማለት መክረዋል፡፡ 
  • ጥቂት ቲፎዞዎች ጥቁር ጨርቅ ሲያውለበልቡ ታይተዋል
  • እነ ያሬድ አደመ የተለቀቁት፣ ‹‹ዐቃቤ ሕግ የምርመራ ሂደቱን ከጊዜ ቀጠሮው  በፊት ማጠናቀቁን ሪፖርት በማቅረቡ የዋስ መብት ተጠብቆላቸው ነው›› ተብሏል፡፡
(ደጀ ሰላም፤ ኖቬምበር 13/2010፤ ኀዳር 4/2003 ዓ.ም)በጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የሲዳማ፣ አማሮ እና ቡርጂ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው የተመደቡት ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ዛሬ ረፋድ ላይ ሐዋሳ ከተማ ሲገቡ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡ ሊቀ ጳጳሱን ለመቀበል ከሀገረ ስብከቱ፣ ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን እና ከምእመናን ተውጣጥቶ የተቋቋመው 40 አባላት እና ልዩ ልዩ ዘርፎች ባሉት የአቀባበል ኮሚቴ፣ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ከብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፣ ብፁዕ አቡነ ያሬድ እና ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ጋራ በሐዋሳ ከተማ መግቢያ - ጥቁር ውኃ አምስት ሰዓት ግድም ሲደርሱ በበጎ ፈቃድ በተሰለፉ ከኻያ በላይ መኪኖች እና ሰባት ሞተር ሳይክሎች በማጀብ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡ በሁለት የትራፊክ ፖሊስ ሞተረኞች እየተመሩ በማእከለ-ሐዋሳ ወደሚገኘው ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የደረሱት ብፁዕነታቸው የመልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን ‹‹ንቁም በበህላዌነ›› የጽናት ዐዋጅ በሚያገናዝቡ የአራት ሊቃውንት ቅኔዎች፣ የካህናቱ ሃሌታ እና የምእመናኑ የማያቋርጥ እልልታ ተከበው ውለዋል፡፡

የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ በሆኑት ሊቀ ኅሩያን ዓለም እሸቱ በተመራው በዚሁ የአቀባበል መርሐ ግብር ስለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ምስጋና ያቀረቡት ብፁዕ አቡነ ገብርኤል በአጭሩ በሰጡት ቃለ ምዕዳን፣ ‹‹አንድ እጅ አያጨበጭብም፤ አነዋወራችን ውበት ሊኖረው የሚችለው ያለልዩነት በኅብረት መሥራት ስንችል በመሆኑ አንድነትን ማጥበቅ እና ሰላምን መሻት ይገባናል›› በማለት መምከራቸው ተዘግቧል፡፡ የመርሐ ግብሩ መሪ ሊቀ ኅሩያን ዓለም እሸቱ ለመርሐ ግብሩ ሰላማዊነት ከፍተኛ እገዛ ላደረጉት የክልል መንግሥት አስተዳደር አካላት፣ ለፌዴራል እና የክልል ፖሊስ እንዲሁም የአቀባበሉን መርሐ ግብር ላዘጋጁት የከተማው ምእመናን ምስጋናቸውን በማቅረብ ትብብሩ ወደፊትም እንደሚቀጥል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡ በዕለቱም 300 ጥሪ የተደረገላቸው ሰዎች የተገኙበት የምሳ ግብዣ በመንበረ ጵጵስናው ተደርጓል።

በብፁዕነታቸው መምጣት ኑፋቄን የማስፋፋት፣ ጥቅማቸውን የማስጠበቅ እና ቤተ ክርስቲያኒቱን በቀጣይ የትርምስ አዙሪት ውስጥ በማሰንበት የማዳከም ዓላማቸው የከሰመባቸው አካላት ያሰለፏቸው ጥቂት ቲፎዞዎች በአቀባበሉ መርሐ ግብር ላይ ጥቁር ጨርቅ በማውለብለብ ስሜታቸውን ለመግለጽ መሞከራቸው ተገልጧል፡፡ ጥቁር ጨርቅ ሲያውለበልቡ እና በግልጽ ያላወጡትን የጽሑፍ መፈክር የያዙት በቁጥር ከ40 የማይበልጡት ቲፎዞዎች በከፊል በዕድሜያቸው አነስተኛ እና በሰንበት ት/ቤት ያልታቀፉ እንደ ሆኑ ታዛቢዎች ተናግረዋል፡፡ ታዛቢ ደጀ ሰላማውያን እንዳስረዱት፣ በአቀባበሉ ሂደት ቲፎዞዎቹ በጸጥታ ኀይሎች እገዛ ከብዙኀኑ ምእመን ጋራ እንዳይቀላቀሉ እና ለብቻቸው ተነጥለው እንዲታዩ በመደረጉ በቆይታ አፍረው ለመበታተን ተገደዋል፡፡

በሌላ በኩል ባለፈው ሳምንት እሑድ በገዳሙ ሕጋዊ የሰንበት ት/ቤት አባላት ላይ ጉዳት በማድረስ ሁከት በመፍጠራቸው በቁጥጥር ሥር ውለው በተጎጂ ቤተሰቦች ክስ የተመሠረተባቸው እነያሬድ አደመ፣ ዓለምነህ ሽጉጤ እና ሌሎች 11 ተባባሪዎቻቸው ትናንት ማምሻውን ከእስር የተለቀቁት፣ ‹‹ዐቃቤ ሕግ ፍርድ ቤቱ በረቡዕ ዕለት ውሎው ከሰጠው ቀነ ቀጠሮ በፊት ምርመራውን መጨረሱን በቢሮ ጉዳዩን ለያዙት ዳኛ በማቅረቡ የተከሳሾቹ የዋስ መብት ተጠብቆላቸው ነው፤›› ተብሏል፡፡ የክሱ ሂደት ግን ኅዳር አንድ ቀን 2003 ዓ.ም ፍርድ ቤቱ በሰጠው ቀጠሮ መሠረት እንደሚቀጥል ተገልጧል፡፡ በትናንትናው ዕለት ማምሻውን በገዳሙ ሰንበት ት/ቤት አዳራሽ የተከሳሾቹን መለቀቅ ለሌሎች በማሳወቅ ‹‹ሲዘምሩ ነበር›› የተባሉት ተከሳሾቹ ራሳቸው ሳይሆኑ ቲፎዞዎቻቸው እንደ ነበሩ ከአካባቢው ምንጮች ለመረዳት ተችሏል፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)