November 11, 2010

የሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ ሹመት እያነጋገረ ነው


ሊ/ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ
  • ‹‹በቅዱስ ሲኖዶስ ጥፋተኛ የተባለን ሰው ሹመት መስጠት ብቻ  ሳይሆን በሥራ መመደብ ስሕተት ነው፡፡››   (የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ተቃውሞ) 
  • በአስተዳደር እና አቅም ግንባታ መምሪያ ቦታ አዲስ ሹመት ተሰጥቷል
(ደጀ ሰላም፤ ኖቬምበር 11/2010፤ ኀዳር 2/2003 ዓ.ም) የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን በተመለከተ በቅዱስ ሲኖዶስ የተሠየመው አጣሪ ኮሚቴ ለጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ባቀረበው ሪፖርት እንዲሁም በ29ው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ስብሰባ ላይ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሪፖርት ውስጥ ተካትቶ በቀረበው የቁጥጥር አገልግሎት ሪፖርት ቃለ ዓዋዲውን ተከትሎ ከመሥራት እና መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አኳያ በተገኘባቸው ከፍተኛ ግድፈት የተነሣ ከሥራ አስኪያጅነት ሐላፊነታቸው እንዲወገዱ፣ የፈጸሟቸው በደሎች ሁሉ ተጣርቶ በሕግ እንዲጠየቁ የተወሰነባቸው ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ማዕርግ የልማት ጉዳዮች ዘርፍ ሥራ አስኪያጅ ሆነው መሾማቸው ጥያቄዎችን እያስነሣ ይገኛል፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ ወቅታዊ ችግሮች ዙሪያ በምእመኑ ዘንድ አንድ አቋም እና ግንዛቤ እየተፈጠረ የመጣበትን አትኩሮት ለማስቀየስ የሚደረግ ጥረት አካል ተደርጎም ተወስዷል፡፡

ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን የተመደቡበት ቦታ በሹመት የሚሰጥ እና የልማት ዘርፍ ተግባራትን የሚከታተሉበት በመሆኑ ሰውዬው ከሚታወቁበት ማንነት፣ ውሳኔው የተሰጠበት ጊዜ እና አኳኋን አንጻር የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡበት ይገኛል፡፡ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በአሁኑ ጊዜ በአስተዳደር፣ በመንፈሳዊ ጉዳዮች እና በልማት ዘርፎች ሦስት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጆች ያሉት ሲሆን በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 30 ንኡስ አንቀጽ ዘጠኝ እና አንቀጽ 31 ንኡስ አንቀጽ አንድ እና ሁለት መሠረት የሁሉም ሹመት ቅቡልነት ሊኖረው የሚችለው - ሥልጣነ ክህነት፣ በቂ የትምህርት ደረጃ እና ችሎታ ያላቸው በዕጩነት ለቋሚ ሲኖዶስ ቀርበው ሲመረጡ፣ በምርጫቸውም ቅዱስ ሲኖዶስ ሲስማማበት፣ ይህም በጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ፊርማ በፓትርያርኩ ፈቃድ እንደተሾሙ የሚገልጽ ደብዳቤ እና የሥራ ድርሻቸውም በውስጠ ደንብ ተዘጋጅቶ በቋሚ ሲኖዶስ ጸድቆ ሲሰጣቸው ነው፡፡ የሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሹመት በአጀንዳነት የቀረበው በሐምሌ ወር 2002 ዓ.ም ተሠይሞ እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2003 ዓ.ም በሥራ ላይ የቆየው የቀድሞው ቋሚ ሲኖዶስ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 11 ንኡስ አንቀጽ አንድ እና ሁለት መሠረት ለሦስት ወር የቆየበትን የሥራ ጊዜ አገባድዶ በሌላ ለመተካት በተዘጋጀባቸው የመጨረሻዎቹ ሁለት እና ሦስት የመሸጋገርያ ቀናት ውስጥ ነው፡፡

ብፁዕ አቡነ ቶማስ፣ ብፁዕ አቡነ ዮናስ፣ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ እና ብፁዕ አቡነ ኢሳይያስ በሚገኙበት የቀድሞው ቋሚ ሲኖዶስ አባላት መካከል ብዙዎቹ ተሟልተው በማይገኙበት ዕለት ነው ዕጩዎች በተገለጸው መስፈርት መሠረት በዋና ሥራ አስኪያጁ ሳይዘጋጁ አጀንዳው ተይዞ ሹመቱ እንዲሰጥ የተደረገው፡፡

በተመሳሳይ የሕገ ቤተ ክርስቲያኑ አንቀጽ መሠረት የቋሚ ሲኖዶስ አባላት እንዲሆኑ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ከሚመረጡት አራት ብፁዓን አባቶች ጋራ የቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ እና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ በአባልነት፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በሰብሳቢነት ይገኙበታል፡፡ የሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሹመት አጀንዳ ሆኖ በቀረበበት ስብሰባ የቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፣ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ምልአተ ጉባኤው ጥፋተኛነታቸውን አረጋግጦ ከሐላፊነታቸው ያስወገዳቸው እና በሕግ እንዲጠየቁ የወሰነባቸው ሆነው ሳለ ስንኳንስ በሹመት ቦታ ማስቀመጥ ይቅርና በተዋረድ በሚገኙ ሥራዎች ላይ መመደብ እንደማይገባቸው በብርቱ በመቃወም በድምፅ ተለይተው ነበር፡፡

ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ይህንንሰ አቋም በመያዛቸው በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 25 ንኡስ አንቀጽ አራት፣ ‹‹የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ከቅዱስ ሲኖዶስ የሚሰጠውን ውሳኔ እና ትእዛዝ ሁሉ በተግባር ላይ መዋላቸውን እንደሚከታተል እና እንደሚቆጣጠር›› የሰፈረውን ድንጋጌ ቃል እና መንፈስ ማስከበራቸውን ያጠይቃል፡፡ በዚህ ረገድ ብፁዕነታቸው የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ መክሮ የወሰነባቸውን 18 ቃለ ጉባኤዎች በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መዝገብ ቤት በኩል ለሚመለከታቸው ሁሉ ደርሶ እንዲታወቅ እና እንዲተገበር በወቅቱ በፊርማቸው ማስተላለፋቸውም የሚጠቀስ ነው፡፡ በተለይ የአቡነ ጳውሎስ ሐውልት እና ቢልቦርዶቻቸው እንዲነሣ፣ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን የበላይ ሐላፊ ሊቀ ጳጳስ እንዲሆኑ፣ የቤቶች እና ሕንጻዎች አስተዳደር ድርጅት ቦርድ ተበትኖ እና የሥራ አስኪያጁም ውል በጥር ወር መጨረሻ አብቅቶ በአዲስ ቦርድ እና ሥራ አስኪያጅ እንዲመራ እንዲሁም የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ሥምሪት ማእከላዊ እና መዋቅሩን የጠበቀ እንዲሆን ውሳኔ የተላለፈባቸው ቃለ ጉባኤዎች እስከ አሁን ከመዝገብ ቤቱ ወጪ ሆነው ለዋና ሥራ አስኪያጁ ጽ/ቤት እንዲደርሱ አለመደረጋቸው ታውቋል፡፡

ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ለልማት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅነት ከመታጨታቸው አስቀድሞ ታስበው የነበረው ከጥቅምት አንድ ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ አቶ ደሳለኝ መኮንን በሐላፊነት ይዘውት ለቆዩት የአስተዳደር እና አቅም ግንባታ መምሪያ ነበር፡፡ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ አንቀጽ 30 ንኡስ አንቀጽ 10 መሠረት የመምሪያ እና የልዩ ልዩ ድርጅት ሐላፊዎችን እያጠናና እና እየመረጠ ፓትርያርኩን በማስፈቀድ የሚሾመው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ነው፡፡ በዚህ ድንጋጌ እንዲሁም የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ለዚህ መምሪያ ሐላፊነት መታሰባቸው በፓትርያርኩ ሲቀርብ ዋና ሥራ አስኪያጁ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ በብርቱ ተቃውመዋቸዋል፤ እንዲያውም በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ መሠረት ለሦስት ዓመት ከሚቆዩበት ሐላፊነታቸው እንደሚለቁ ፓትርያርኩን አስጠንቅቀዋቸው ነበር፡፡

የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምንጮች ዘግይተው እንደጠቆሙት አቶ ደሳለኝ መኮንን በፈቃዳቸው በለቀቁት በአስተዳደር እና አቅም ግንባታ መምሪያ ሐላፊነት ቦታ አቶ ነገደ የተባሉ በአዲስ አበባ አስተዳደር የአቅም ግንባታ ቢሮ በአማካሪነት በመሥራት ላይ የሚገኙ ባለሞያ መመደባቸው ታውቋል፡፡ ከዚህ ቀደም በሦስት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ከፍተኛ ቦታዎች በተሰጠው ሹመት በሁለት በኩል ለተሳሉት የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት ቅድሚያ እንዲሰጥ የተሰጠው ትችት ከቁም ነገር እንዳልተጣፈ፣ በተከታይም ሊመጡ በሚችሉት ምደባዎች ይህ ምክር ሰሚ ጆሮ እንደማይኖረው የብዙዎች ስጋት ነው፡፡

በቀጣዩ ጊዜ አዲስ የተሾመ ቋሚ ሲኖዶስ አባላት ማለትም ብፁዓን አበው ጢሞቴዎስ፣ ጎርጎርዮስ፣ ኤጲፋንዮስ እና ገሪማ (አቡነ ማቴዎስን ተክተው) ይህንን ችግሩ ያስተካክሉት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)