November 10, 2010

በሐዋሳ ቅ/ገብርኤል ውስጥ ብጥብጥ የፈጠሩ ፍርድ ቤት ቀረቡ

  • ያሬድ አደመ እና ዓለምነህ ሽጉጤ አሉበት፤
(ደጀ ሰላም፤ ኖቬምበር 10/2010፤ ኀዳር 1/2003 ዓ.ም)እሑድ ጥቅምት 28 ቀን 2003 ዓ.ም በሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም በተፈጠረው ዐምባጓሮ በሕጋዊ የገዳሙ ሰንበት ት/ቤት አባላት ላይ ከፍተኛ የድብደባ ጉዳት ያደረሱት ያሬድ አደመ እና ዓለምነህ ሽጉጤን ጨምሮ 11 ያህል ሰዎች በትናንትናው ዕለት ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡ በተጎጂ ቤተሰቦች በተመሠረተው ክስ ፖሊስ ሀገረ ስብከቱን በማወክ እና የክልሉን ሰላም በማደፍረስ ሁከት በፈጠሩት ግለሰቦች ላይ ተጨማሪ መረጃ ለማሰባሰብ እና ቀሪ ሁከተኞችን ለማደን የጠየቀው ዘጠኝ ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ጥያቄ የፍርድ ቤቱን ይሁንታ አግኝቷል፡፡ ከሁከቱ በኋላ እሑድ ዕለት ረፋድ ላይ ወደ አዲስ አበባ ለመሔድ ሲዘጋጅ የተያዘውን ያሬድ አደመን፤ አባቶችን፣ የሐዋሳ የፍትሕ እና ልማት ኮሚቴ አባላትን እና ማኅበረ ቅዱሳንን በስም እየለየ የሚያክፋፋ የቅስቀሳ ወረቀት ሲበትን በማግስቱ ሰኞ የተያዘውን ዓለምነህ ሽጉጤን ለማስመለቀቅ ጓደኞቻቸው በየአቅጣጫው የሚያደርጉትን ጥረት ቀጥለውበታል፡፡

በትናንትናው ዕለት በሐዋሳ ከተማ ‹‹ተስፋ ኪዳነ ምሕረት›› እየተባለ በሚጠራው አካል ሥር የተደራጁ እና በሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ከዚህ በፊት ተሹመው የነበሩ አስተዳዳሪ ጥያቄውን ለጸጥታ ኀይሉ ያቀረቡ ቢሆንም ጉዳዩ በሕግ አግባብ ብቻ እንደሚፈታ፣ በምርመራው ሂደት እንዳስፈላጊነቱ እነርሱም ተጠያቂ ሊሆኑ የሚችሉበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ተነግሯቸዋል፡፡ በአዲስ አበባ በበጋሻው ደሳለኝ እና ዘማሪ ዲያቆን ትዝታው ሳሙኤል የተመሩ ቁጥራቸው 25 ያህል ይሆናሉ የተባሉ ግለሰቦች በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ጋራ መወያየታቸው ተዘግቧል፡፡ ጥያቄ አቅራቢዎቹ ከሐዋሳ እንደመጡ ተነግሯቸው ሳለ በጋሻውን እና ዲያቆን ትዝታውን በማየታቸው መገረማቸውን ያልሸሸጉት አቡነ ጳውሎስ፣ ‹‹ተደብድበናል፤ ታስረናል፤ ተገርፈናል፤. . .ወንድሞቻችን ታስረዋል፤ ይፈቱልን›› በሚል ለቀረበላቸው አቤቱታ ጉዳዩ መንግሥት የሚከታተለው እና በሕግ የተያዘ መሆኑን አስረድተዋቸዋል ተብሏል፡፡

አቡነ ገብርኤል
‹‹እነርሱ ካልተፈቱ አቡነ ገብርኤልን ለመቀበል እንቸገራለን›› በማለት አቤቱታቸውን ለማጠናከር የሞከሩት እነበጋሻው፣ ‹‹እናንተ ባትቀበሏቸው ሌሎች የሚቀበሉ አሉ›› የሚል ምላሽ ከፓትርያርኩ እንደተሰጣቸው ተነግሯል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በቅርቡ በተካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ከሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ማሠልጠኛ ኮሌጅ ወደ ሲዳማ፣ አማሮ እና ቡርጂ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ሀገረ ስብት ከተዛወሩት ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ጋራ በመጪው ቅዳሜ ወደ ሐዋሳ እንደሚያመሩ ታውቋል፡፡ ከሕግ የበላይነት ይልቅ በወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ እገዛ ፓትርያኩን መማፀን የመረጡት እነበጋሻውንም በውትወታቸው ብዛት፣ ‹‹ችግሩ እዚያው በሕግ ይፈታል፤ ዋስ ሁን ከተባልሁም ዋስ ሆኜ አስፈታለሁ እንጂ ሌላ ምንም ላደርግ አልችልም፤›› የሚል ቃል ከአቡነ ጳውሎስ ቢሰጣቸውም ‹‹ፍጡነ ረድኤት›› ሆኖ ባላገኙትና በአንዳንዶች ግምት ‹‹ጨዋታው ፈረሰ ዳቦው ተቆረሰ›› ዐይነት ቃና በሚያሰማው ተስፋ ተበሳጭተው መውጣታቸው ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡ እሑድ በሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም በዐመፀኞቹ እየተመቱ ሲወድቁ የነበሩትን ሕጋዊ የሰንበት ት/ቤት አባላት ሁኔታ እና የጸጥታ አስከባሪ ፖሊሶችን ሳይቀር ያስለቀሰውን የሁከተኞቹ ጭካኔ (በያዙት ብትር እየፈነከቱ ‹የሚዘምሩ› ነበሩ) የተመለከቱ የዐይን እማኞች የእነበጋሻውን ‹‹የታሰርን እና ተደበደብን›› አቤቱታ ‹‹የሰብአዊነት ስሜት የማይታይበት ታላቅ ፌዝ/ስላቅ›› ብለውታል፡፡

በሌላ በኩል በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጥሪ የተደረገላቸው አዲሱ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኅሩያን ዓለም እሸቱ፣ አቡነ ፋኑኤል ከቃለ ዓዋዲው በተፃራሪ የመረጧቸው የሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ሰበካ ጉባኤ አባላት እና የገዳሙ አስተዳዳሪ ችግሩ ዘላቂ እልባት በሚያገኝበት እና አዲሱ የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ከክልሉ መንግሥት ጋራ ተባብሮ መሥራት በሚችልበት ሁኔታ ላይ ትላንት መወያየታቸው ተሰምቷል፡፡ በውይይቱ ላይ ስለ ተፈጠረው ችግር ወገንተኛ ማብራሪያ ለመስጠት የሞከሩትን የሰበካ ጉባኤ አባላቱን እና የገዳሙን አስተዳዳሪ የገሠጹት የፖሊስ ኮሚሽነሩ፣ ስለ ውዝግቡ እና በቅርቡ ቅዱስ ሲኖዶስ ስለ ወሰናቸው ውሳኔዎች ዝርዝር መረጃው የሚታወቅ በመሆኑ ሁሉም ወገኖች የክልሉን ጸጥታ ለማስከበር የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አሳስበዋቸዋል፡፡ በተለይ በቅርቡ የሐዋሳ ከተማን 50 ዓመት እና የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የባህል ፌስቲቫል በደመቀ ሁኔታ ለማክበር የከተማውን ገጽታ ከሚያበላሹ ተግባራት ሁሉም ወገኖች እንዲጠነቀቁ መክረዋል፡፡ በተበተነው ወረቀት የተወነጀሉት ባለሀብቶች እና ማኅበረ ቅዱሳን በክልሉ ለሥራ አጦች የሥራ ዕድል በመስጠት፣ ማኅበራዊ እና ልማታዊ አገልግሎት በመስጠት አስተዋፅኦ የሚያደርጉ መሆኑን እንደመሰከሩላቸው ተዘግቧል፡፡ በውይይቱ አካሄድ እንደተከፉ የተነገረላቸው ሕገ ወጦቹ የሰበካ ጉባኤ አባላት ከውይይቱ እንደተመለሱ አስቸኳይ ስብሰባ ተቀምጠው ሁሉም ከሐላፊነታቸው ለመልቀቅ እንደተስማሙ መወሰናቸው ተሰምቷል፡፡

በአንጻሩ የሐዋሳ የፍትሕ እና ልማት ኮሚቴ አባላት እና የሀገር ሽማግሌዎች በመጪው ቅዳሜ ወደ ሀገረ ስብከቱ የሚመጡትን ብፁዕ አቡነ ገብርኤልን በደመቀ ሁኔታ ለመቀበል የተጠናከረ ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆናቸው ተገልጧል፡፡ በቅርቡ በተካሄደው 29ው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ስብሰባ ላይ ስብከተ ወንጌልን አስመልክቶ በተካሄደው ውይይት ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ሰጥተውት በነበረው ጠንካራ ሒስ በአሁኑ ጊዜ በስፋት የሚታየው የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ ‹‹ትምህርት አይሉት ኪነት ግራ የሚያጋባ፣ ከስሙ እና ኀይሉ ጋራ የማይገናኝ እና አደገኛ አካሄድ የያዘ ነው፤ ከሰባክያነ ወንጌሉ አለባበስ ጀምሮ አዘማመሩ እስክስታው ኦርቶዶክሳዊነት አይታይበትም፤ ወጣቱ በቤተ ክርስቲያን መሰብሰቡ መልካም ቢሆንም በስብከተ ወንጌሉ የሃይማኖት ትምህርት የለበትም፤ ትምህርት እና ስብከት ይለያያል፤ ትምህርቱ ተቀብሯል፤ በርግጥ አገልግሎቱ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ሆኗል፤ ገቢው በቤተ ክርስቲያን ስም የተደራጀ ነገር ግን የቤተ ክርስቲያን ያልሆነ ነው፤›› በማለት ተችተዋል፡፡ የሠርክ ክፍለ ጊዜ ስብከተ ወንጌል ለመጀመሪያ ጊዜ በ1978 ዓ.ም በአዲስ አበባ ማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ከተጀመረበት ጊዜ አኳያ ሲታይ ዕድገት ማሳየቱን ዕድገቱ ግን የተጣመመ/በመጥፎ መሆኑን ያስረገጡት ብፁዕነታቸው፣ ዛሬ ድረስ ኦርቶዶካሳዊ ይዘቱን እና ያሬዳዊ ለዛውን አጥቶ፣ የሰዎች ጸጥታ እና ፕራይቬሲ እስኪታወክ ድረስ እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት በሞንታርቦ እየተጯጯኸ የሚሰጠው ስብከት ሥርዐት መያዝ እንደሚገባው አሳስበው ነበር፡፡ ብፁዕነታቸው ይህን ማሳሰቢያቸውን እና ሌሎችንም ልምዶቻቸውን በአዲሱ ሀገረ ስብከታቸው እውን በማድረግ በአርኣያነት እንደሚያስጠሩት ተስፋ እናደርጋለን፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)