November 8, 2010

ሐውልቱ እንዲፈርስ ከተወሰነ 10 ቀን አለፈው፤ የብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ‹‹የመታሰቢያ ሐውልት›› ተመረቀ

  •  "ከ30 ምእመናን 26ቱ ሐውልቱ እንዲወገድ የተላለፈውን ውሳኔ እና ሐውልት ማቆም በቀኖና ቤተ ክርስቲያን እንደሚከለከል ያውቃሉ፡፡›› (ካፒታል ጋዜጣ ያሰባሰበው የሕዝብ አስተያየት)
  •   ፓትርያርኩ የሲኖዶሱ ምልአተ ጉባኤ ከወሰነባቸው ቃለ ጉባኤዎች አራቱን እስከ አሁን ለጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ አልመሩም፤
(ደጀ ሰላም፤ ኖቬምበር 8/2010፤ ጥቅምት 29/ 2003 ዓ.ም) - ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን እና ከሥርዐተ አበው በተፃራሪ እንዲሁም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውሳኔ ሳይደገፍ የተተከለው የአቡነ ጳውሎስ ሐውልተ ስምዕ እንዲነሣ እና በየአብያተ ክርስቲያኑ የተሰቀሉት ቢልቦርዶች እንዲሰበሰቡ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የሰጠው ትእዛዝ ከዐሥር ቀናት በላይ አስቆጥሯል፡፡

በዚህ ቀን በብሔራዊው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጣቢያ የዕለተ ሰንበት ቀትር ዜና ላይ በምዕራባዊ ፖላንድ በምትገኘው የስዊቦድዚን ከተማ አጠቃላይ ርዝመቱ 36 ሜትር፣ ክብደቱ 440 ቶን የሆነው ከዓለም ረጅሙ ‹‹የመድኃኔዓለም ክርስቶስ ሐውልት›› ግንባታ መጠናቀቅን የሚመለከት ዘገባ ተላልፏል፡፡ በኢኮኖሚ ዕድገቷ የቆረቆዘችውን ከተማ ቁልቁል ‹በግርማ› የሚመለከተው ይኸው ሐውልት የሮማ ካቶሊክ እምነት ተከታይ ከሆነው የከተማው ሕዝብ የተዋጣው ከአንድ ሚልዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ለአምስት ዓመታት ከፈሰሰበት በኋላ ነው ግንባታው መፈጸሙ የተነገረው፡፡ የብራዚል እና የመዲናዋ ሪዮ ዲ ጄኔሮ ከተማ መለዮ በመሆን ለ80 ዓመታት ከዓለም ግዙፉ ‹‹የመድኃኔዓለም ክርስቶስ ሐውልት›› (Statue of Christ the Redeemer) ሆኖ የቆየውን ሐውልት በሦስት ሜትር እንደሚበልጥ የተነገረለት የፖላንዷ ስዊቦድዚን ከተማ ሐውልት መቆም በሀገሪቱ ካቶሊካውያን መካከል ልዩነት መፍጠሩ ተገልጧል፡፡

ዘጋርድያን እንደ ዘገበው የግንባታውን ፕሮጀክት የመሩት የአጥቢያው ካህን እና ሌሎች ጥቂቶች ሐውልቱ በቆመበት አኳኋን መሠራቱ፣ ‹‹ለከተማዋ ዓለም አቀፍ ዝና ያስገኝላታል፤ ተሳላሚ ምእመናንን እና ቱሪስቶችን በመሳብ ለከተማዋ ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና ያስገኝላታል፤›› ብለዋል፡፡ የአካባቢው ሚዲያዎች እና ቀላል ቁጥር የሌላቸው ካቶሊካውያን ግን ፕሮጀክቱን የመሩት ካህን በልብ ሕመም መሠቃየታቸውን እንዲሁም በግንባታው ሂደት በሰው ላይ የደረሰውን አደጋ ዋቤ በማድረግ ሐውልቱ ከክርስትና አስተምህሮ ጋራ ምንም ግንኙነት የሌለው ‹ጉድ› (monster of a statue) እና ከተማይቱን የሀገር መሣቂያ ስለሚያደርጋት ካቶሊካውያን ሁሉ ንቀው አጸይፈው እንዲተዉት መክረዋል፤ ገንዘቡ አሳዳጊ አልባ ለሆኑ ሕፃናት መርጃ እና ለአረጋውያን የመጦሪያ ማእከል ግንባታ ቢውል ይመርጡ እንደ ነበር ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

ሐውልትን የመሳሰሉ ቅርጻ ቅርጾችን የሥርዐተ እምነት መፈጸሚያ እና መገለጫ ማድረግ እንግዳ ባልሆኑት ካቶሊካውያን መካከል እንዲህ ያለልዩነት መፈጠሩ አስገራሚ መስሎ ሊታይ ይችላል፡፡ ቁም ነገሩ ግን ፖላንድ የዐሥርተ ዓመታት ኮሚኒስታዊ አገዛዝ ያላከሰመው ከጠቅላላ ነዋሪዋ 96 ከመቶው ሕዝብ የሮም ካቶሊክ እምነት ተከታይ የሆነባት ሀገር ናት፤ ግዙፉ የክርስቶስ ሐውልት በየጊዜው እየታደሰ በክብካቤ የሚያዝባት ብራዚልም ከጠቅላላው ነዋሪዋ 74 ከመቶዎቹ የሮም ካቶሊክ እምነት ተከታዮች ናቸው፡፡ ካቶሊክ - ሐውልት - ካቶሊክ፡፡

ወደ ሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ስንመለስ በአብነታዊ ተግባር ሩጫቸውን ጨርሰው፣ ተጋድሏቸውን ፈጽመው ብሔራዊ ተምሳሌት ለሆኑ ሰማዕታት እና የሕዝብ ባለውለታዎች ከሚቆምላቸው የመታሰቢያ ሐውልት በመለስ፣ እንደ ወርቅ በእሳት ተፈትኖ ደገኛነቱ ከተረጋገጠው ክርስቲያናዊ ምግባራቸው የተነሣ የጽድቅ እና የሰማዕትነት አክሊል ለሚቀዳጁ ቅዱሳን ሐውልት ማቆም ከኦርቶዶክሳዊ ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥርዐተ እምነት እና የተቀደሰ ትውፊት አንጻር የተፈቀደ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ - በቁመናም ሳሉ ይሁን ከሞት በኋላ ሐውልት ማቆም የተፈቀደ አለመሆኑን በሚያዝዘው ቀኖና ቤተ ክርስቲያን እና ሥርዐተ አበው ለሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ - ተጠሪ እንደመሆናቸው አብዝቶ እና ተመላልሶ እየተሰጠ ያለውን ይህን ትምህርት፣ ምክር እና ተግሣጽ በአባታዊ ሐላፊነታቸው ማጽናት ሲገባቸው በየሥርቻው በግለሰቦች ፈቃድ ላይ ተመሥርቶ የሚፈጸሙ ልማዶችን አጠናክሮ በአርኣያነት በማሳየት ትክክለኛውን አቋም ለማስተባበል በሂደትም ለማሳፈር እየተጉ ይገኛሉ፡፡

ፓትርያርኩ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ የወጠኑትን የሐውልት ፍለጋ ዑደት በማጠናከር ቅዳሜ ዕለት በከምባታ ሐዲያ እና ጉራጌ ዞን ሀገረ ስብከት ቡኢ ወረዳ አኖሁዳድ ቀራንዮ መድኃኔዓለም ገዳም በመገኘት ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ የፈጸሙትን ገናና ልማታዊ እና ሃይማኖታዊ ተግባር ‹‹ትውልድ እንዲያስበው በማሰብ የቆመ ነው›› የተባለውን ‹‹የመታሰቢያ ሐውልት›› ታቦት አቁመው ጸሎተ ወንጌል አድርሰው ባርከዋል፤ መርቀዋል፡፡ ሐውልቱ ከገዳሙ ቅጽር ምዕራባዊ ማዕዝን ፊቱን ወደ ምሥራቅ መልሶ የቆመ በዐይን ግምት ከሁለት ሜትር ያላነሰ ቁመት ያለው ሲሆን ብፁዕነታቸው በቀኝ እጃቸው መስቀላቸውን በግራ እጃቸው ብትረ ሙሴያቸውን ጨብጠው እንደ ቆሙ ያሳያል፡፡ በእግረ ሐውልቱ በሚታየው ሰሌዳ ላይ ብፁዕነታቸው በ1952 ዓ.ም በሞህር ኢየሱስ ገዳም አካባቢ ተወልደው በ2002 ዓ.ም እንዳረፉ፣ ቀብራቸውም በተወለዱበት እና ብዙ በደከሙበት በሞህር ኢየሱስ ገዳም መፈጸሙን ይገልጻል፡፡ በማስከተልም ሐውልቱ ብፁዕነታቸው በመሠረቱት እና በደከሙበት በዚሁ አኖሁዳድ ቀራንዮ መድኃኔዓለም ገዳም ቢትወደድ ባሕሩ አብርሃም የተባሉ ምእመን ‹‹ትውልድ የብፁዕነታቸውን ገናና ልማታዊ እና ሃይማኖታዊ ተግባር ያስበው ዘንድ›› እንዳቆሙላቸው ያትታል፡፡

በሥነ ሥርዐቱ ላይ ባለፈው ዓመት በሞተ ዕረፍት የተለዩን ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ የአካባቢውን ሕዝብ በማስተባበር ገዳሙን ከመመሥረታቸውም በላይ በትውልድ ቋንቋቸው የሚያስተምሩ ወጣት ሰባክያነ ወንጌል የሚሠለጥኑበትን አዳሪ ት/ቤት ጠንካራ ተቋም ያደረጉ ሐዋርያዊ አባት እና የልማት አርበኛ እንደነበሩ የሚገልጡ ሪፖርቶች ቀርበዋል፤ ፓትርያርኩም ይህንኑ በመመስከር ‹‹እንዲህ ለነበሩት ብፁዕ አባት የተደረገው መታሰቢያ የሚገባ መሆኑን›› መስክረዋል፤ በቅርቡ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የሆኑትን ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስንም አስተዋውቀዋል፡፡ በአዳሪ ትምህርት ቤቱ ለአንድ ወር ያህል ከ260 ሰዓታት በላይ ሥልጠና የተከታተሉ እና በጉራጊኛ ቋንቋ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት የሚሰጡ 36 ተተኪ መምህራን በአቡነ ጳውሎስ ተመርቀዋል፡፡ በመርሐ ግብሩ መንዛዛት የተነሣ ታቦቱን ያከበሩት ካህናት መቀያየራቸው የተዘገበ ሲሆን ከምእመናኑም ጥቂት የማይባሉት አቋርጠው ወደየቤታቸው መሄዳቸው ተመልክቷል፡፡ ከምእመናኑ አንዳንዶቹ የአቡነ ጳውሎስ ሐውልት እንዲነሣ እና ቢልቦርዳቸው እንዲሰበሰብ በቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠው ውሳኔ ግብራዊ ፍጻሜ በሚጠበቅበት በአሁኑ ወቅት፣ ፓትርያርኩ ለዚያውም በገዳሙ ቅጽር ውስጥ የተሠራውን የብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ‹‹የመታሰቢያ ሐውልት›› መባረካቸው እና መመረቃቸው የራሳቸውን ሐውልት እንዳይነሣ ለማድረግ የጀመሩትን የልማዱን ስሕተት የማጠናከር ጥረት አካል አድርገው ተመልክተውታል፡፡ በጣዕመ ስብከታቸው የሚታወቁት ብፁዕ አባት መታሰቢያ ከሐውልት ሥራ ጋራ መያያዙም ለዚሁ ተመሳስሎ ይረዳቸዋል ይላሉ፡፡

በ2001 ዓ.ም በተካሄደው የግንቦቱ ርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ እና በዚያው ዓመት ሐምሌ ወር ቀጥሎ በነበረው ስብሰባ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑን ለማስከበር ፓትርያርኩን በመቃወም ያደረጉትን ተጋድሎ የሚያስታውሱ ወገኖች ደግሞ ‹‹የመታሰቢያ ሐውልቱ›› ከብፁዕነታቸው ዕረፍት በኋላ የተሠራ መሆኑን በመጥቀስ አቡነ ጳውሎስ በቁማቸው ሳሉ ሐውልት መትከላቸው ‹‹ሊያሳፍራቸው ይገባል›› ማለታቸው አልቀረም፤ በቀብራቸው ቀንም አቡነ ጳውሎስ ከመንገድ መመለሳቸው ፈጥሮባቸው የነበረውን ቅሬታ በማስታወስ ዛሬ ምእመኑ እስኪሰላች ድረስ በተንዛዛው መርሐ ግብር ትዕግሥት ማድረጋቸው፣ ሣቅ - ሣቅ ማለታቸው ያስገርማቸዋል፡፡ ከመርሕ አኳያ ሲታይ ግን የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል በቅርቡ ለዶቼ ቬሌ ሬዲዮ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፣ በቁመተ ሥጋም ይሁን ከሞት በኋላ በቤተ ክርስቲያን ሐውልት ማቆም ኦርቶዶክሳዊ አይደለም፡፡ የቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ይህን መግለጫ በመስጠታቸው፣ ‹‹የእኛ መግለጫ ሰጪ ሌላስ መግለጫ የለህም!›› በሚል በአቡነ ጳውሎስ እንደተብጠለጠሉ የመንበረ ፓትርያርኩ ምንጮች ያስረዳሉ፡፡

በቤት ክዳን ቆርቆሮ አምራችነታቸው የሚታወቁት ‹‹የመታሰቢያ ሐውልቱ›› አሠሪ እና ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩን ለማስተናገድ ሽር ጉድ ሲሉ የነበሩት እልፍኝ ባሕሩ አብርሃም ገንዘባቸውን የቤተ ክርስቲያኒቱ ማኅበራዊ አገልግሎት በሚጠናከርበት ክሊኒክ ወይም ዐጸደ ሕጻናት አልያም ስብከተ ወንጌሉ በሚስፋፋበት የአዳሪ ት/ቤቱ ላይ ቢያውሉት ብፁዕነታቸውን ይበልጥ ያስመሰግኑ እንደ ነበር ታዛቢዎች አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡ ይሁንና ጠንካራ ኦርቶዶክሳዊ ማንነት በተገነባበት፣ ዣንጥላ ዘቅዝቆ መለመን ነውር በሆነበት እና ከፍተኛ የሥራ ባህል በሚታይበት አካባቢ የተገኙ ክርስቲያን ሆነው ሳለ ባለሀብቱ በሐውልት ሥራ እንቶ ፈንቶ ውስጥ መጠመዳቸው ጥርጣሬ ያሳደረባቸው ብዙዎች ‹‹ቢትወደድ›› በሚለውና እንደ ዋዛ በአቡነ ጳውሎስ እንደተሰጣቸው በሚነገረው ስመ ማዕርጋቸው ላይ ያተኩራሉ፡፡ 
ማዕርጉ በቤተ መንግሥት በሕግ ከመሳፍንቱ በላይ ሆኖ እንደ ወደደ፣ እንደ ፈቀደ ለሚያደርገው የንጉሠ ነገሥቱ ባለሙሉ ሥልጣን አማካሪ እና ጉዳይ ፈጻሚ የሚሰጥ ነበር፡፡ ‹ቢትወደድ› ባሕሩ አብርሃምስ በቤተ ክርስቲያኒቱ ቅጽር ውስጥ ምን ያደርጉ ዘንድ ሥልጣን ተሰጥቷቸው ይሆን? ያም ሆነ ይህ ባዕለ ጸጋው ክፉውን ምክር ወግድ ብለው እንደ ትጉህ አገልጋይ በሀብታቸው ደግ ደጉን በመሥራት መክሊታቸውን ያበዙ ዘንድ መድኃኔዓለም ክርስቶስ የቀናውን ያመለክታቸው ዘንድ እንመኝላቸዋለን፡፡

ወዲህ ግን ከድጡ ወደ ማጡ ሆኖ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ለዐሥር ቀናት ያህል ባደረገው ስብሰባ ውሳኔ እና መምሪያ መስጠቱ ከተመዘገበባቸው ቃለ ጉባኤዎች በአራቱ ላይ ፊርማቸውን በልዩነትም ቢሆን አለማስፈራቸው ታውቋል፡፡ እኒህም፣ ምልአተ ጉባኤው በቤቶች እና ሕንፃዎች አስተዳደር ልማት ድርጅት አሠራር ዙሪያ በመወያየት የነበረውን ቦርድ እና ሥራ አስኪያጅ በማሰናበት በአዲስ የቦርድ አባላት እና ሥራ አስኪያጅ እንዲተካ የወሰነበት፣ በስብከተ ወንጌል ዙሪያ አገልግሎቱ ሕገ ወጥ ሰባክያንን ለመከታተል ያመች ዘንድ መዋቅሩን ተከትሎ በማእከል እንዲሠራ መፍትሔ የሰጠበት፣ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን የበላይ ሐላፊ ሊቀ ጳጳስ እንዲሆኑ እንዲሁም የኮሚሽነሩን ሪፖርት በማዳመጥ ሕገ ወጥ የሆኑ እና ለሙስና የሚያጋልጡ አሠራሮች እንዲስተካከሉ ያዘዘበት በመጨረሻም የፓትርያርኩ ሐውልት ተነሥቶ እና ቢልቦርዳቸው ተሰብስቦ በመንበረ ፓትርያርኩ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር/ግምጃ ቤት/ እንዲቀመጥ የወሰነበት ናቸው፡፡

ውሳኔው ቢያንስ በመግለጫ መልክ ከተላለፈ ከአንድ ሳምንት በላይ ቢሆነውም ፓትርያርኩ በሕገ ቤተ ክርስቲያን እንደተደነገገው የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔን ለማስፈጸም ባለባቸው ግዴታ መሠረት ለአፈጻጸሙ በቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ቀርቦላቸው ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ መምራት ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ፣ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ በአባልነት የሚገኙበት ቋሚ ሲኖዶስ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 12 ንኡስ አንቀጽ 1፣ ‹‹በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እየተወሰኑ የሚተላለፉ መምሪያዎችን እና ልዩ ልዩ ጉዳዮችን ተግባራዊ መሆናቸውን በየዕለቱ የመከታተል›› ሐላፊነት ስላለበት ለጉዳዩ ምዕራፍ እንደሚያበጅለት ይጠበቃል፤ መንግሥትም ቀደም ሲል ፓትርያርኩን ጨምሮ ከብፁዓን አባቶች ጋራ በተደጋጋሚ ባደረገው ውይይት ሲኖዶሱ በአንድነት መክሮ የሚወስነው ውሳኔ ለአገር ሰላም መጠበቅ እና ለልማቱ ቀጣይነት ካለው ከፍተኛ ሚና አንጻር እንደሚተባበር በገባው ቃል መሠረት ይዞታል የሚባለውን ቁርጠኝነት ከዳር እንደሚያደርሰው ተስፋ ተጥሏል፡፡

ፓትርያርኩ በተድበሰበሰ አኳኋንም ቢሆን በቅዱስ ሲኖዶሱ የስብሰባ መጨረሻ ቀን ባነበቡት መግለጫ የመጨረሻው አንቀጽ ላይ የሚከተለው ቃል ሰፍሯል፤ ‹‹ማእከሉን ባልጠበቀ መንገድ የተሠሩት ተግባራት ሁሉ ምልዓተ ጉባኤውን የሚያወያዩ ሆነው በመገኘታቸው ቅዱስ ሲኖዶስ ያለውን ሁኔታ መርምሯል፤ እንደመረመረውም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውሳኔ ያልተደገፈው ተግባር ሁሉ ከሕዝበ ክርስቲያኑ ፍላጎት ጋራ ተጣጥሞ የማይራመድ ካለና ያለበቂ ጥናት የተሠራው ሥራ እየተጠና እንደ አስፈላጊነቱ እርማት ይደረግ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ የአፈጻጸም መምሪያ ሰጥቷል፡፡›› ሳምንታዊው የእንግሊዝኛ ጋዜጣ ካፒታል በዛሬው ጥቅምት 28 ቀን 2003 ዓ.ም እትሙ በተለይም ቅዱስ ሲኖዶሱ ሐውልቱ እንዲወገድ የሰጠው ጊዜ ገደብ ስድስት ቀናት ብቻ እንደቀሩት ያመለከተው ጋዜጣው የአቡነ ጳውሎስን ሐውልት መነሣት አስመልክቶ ስለተላለፈው ውሳኔ ሕዝቡ ምን ያህል መረጃ እንዳለው የሚያሳይ ኢ-መደበኛ የሆነ የምእመናን አስተያየት ማሰባሰቡን ዘግቧል፡፡ በተሰበሰበው አስተያየት ከተጠየቁት 30 ሰዎች ውስጥ 26ቱ በጉዳዩ ላይ የቅርብ ክትትል እንዳላቸው፣ ሐውልት የአገር ባለውለታ ለሆኑ እና ታላላቅ ተግባር ለፈጸሙ ታዋቂ መሪዎች፣ ግለሰቦች እና አርበኞች እንጂ ለቤተ ክርስቲያን አባት ማቆም (የመቃብር ሐውልት ሳይቀር) የተከለከለ መሆኑን በቤተ ክርስቲያን ትምህርት መሠረት እንደሚገነዘቡ መግለጻቸውን አትቷል፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)