November 4, 2010

ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ ወደ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ቅጽር ግቢ እንዳይገቡ የተጣለባቸው እገዳ እየተከበረ አይደለም

ወ/ሮዋ በሐውልቱ ምረቃ ዕለት ንግግር ሲያደርጉ
  • ወይዘሮዋ ‹‹ሲኖዶሱ በእኛ ገንዘብ ምን አገባው?›› በሚል የምልአተ ጉባኤውን ውሳኔ አፈጻጸም በመቃወም ተግባራዊነቱን የሚያደናቅፍ ቡድን አደራጅተው ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው፤
  • በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ላይ ጠንካራ ትችት የሰነዘሩባቸውን ብፁዓን አባቶች እየደወሉ በመሳደብ እየዛቱባቸው ነው፤
  • ያሬድ አደመ ‹‹በደረቅ ቼክ ማጭበርበር››፣ በጋሻው ደሳለኝ ‹‹በስም ማጥፋት››  ወንጀሎች ተከሰዋል፤
(ደጀ ሰላም፤ ኖቬምበር 4/2010፤ ጥቅምት 25/2003 ዓ.ም)ጥቅምት 25 ቀን 2003 ዓ.ም፤ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የዋና ሥራ አስኪያጁ ጽ/ቤት የአቡነ ጳውሎስን ‹‹ሐውልተ ስምዕ›› በኻያ ቀናት ውስጥ ከቦታው በማንሣት እና በየአብያተ ክርስቲያኑ የተሰቀሉትን የፓትርያርኩን ቢልቦርዶች በመሰብሰብ በመንበረ ፓትርያርኩ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር ውስጥ እንዲያስቀምጥ ያስተላለፈው ውሳኔ አንድ ሳምንት ያህል ሆኖታል፡፡ ለውሳኔው አፈጻጸም የዋና ሥራ አስኪያጁ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ጽ/ቤት በቁርጠኛነት እየተንቀሳቀሰ ስለመሆኑ ጠርጣሪዎች በርካታ ጥያቄዎችን እያነሡ ይገኛሉ፡፡ ጠርጣሪዎቹ ጥያቄ ለማንሣት የተገደዱት ሐውልቱን በማሠራት እና ቢልቦርዶቹን በመስቀል ግንባር ቀደም ሚና ያላቸው ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ በቤተ ክርስቲያኒቱ የመጨረሻው ሥልጣን ባለቤት የሆነውን የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ በመጻረር በተገኙት መድረኮች ሁሉ በራሳቸው እና ሌሎች ኀይሎችን በመጠቀም በሚያደርጉት ፀረ - ሲኖዶሳዊ ቅስቀሳ ነው፡፡

እንደ ውስጥ ዐዋቂ ምንጮች ገለጻ ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ ወደ መንበረ ፓትርያርኩ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ቅጽር ግቢ እንዳይገቡ በቅዱስ ሲኖዶስ የተጣለባቸውን እገዳ በመተላለፍ ከትናንት በስቲያ ምሽት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ሕንጻ ውስጥ ፌሽታ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ እስከ ምሽቱ ሦስት ሰዓት ግድም ‹‹ወደ አባቴ ቤት እንዳልገባ የሚያግደኝ ማነው?›› በማለት ጦር አውርድ ሲሉ የቆዩት ወይዘሮዋ በምልአተ ጉባኤው ስብሰባ ወቅት ጠንካራ ትችት ወደሰነዘሩባቸው አራት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ስልክ በመደወል፣ ‹‹እርስዎ ነዎት እኔን ‹እንዲህ እና እንዲያ› የሚሉኝ፤ ዶክመንታችሁ'ኮ በእጄ ነው፤. . .›› በማለት በአስነዋሪ ንግግር እንደዘለፏቸው እና እንደዛቱባቸው ተነግሯል፡፡ ወይዘሮዋ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ውስጥ በሕግ እና በይፋ የታወቀ ሐላፊነት የሌላቸው ተራ ግለሰብ ከመሆናቸው ጋራ በተያያዘ እርሳቸውን በተመለከተ ቅዱስ ሲኖዶሱ ያስተላለፈውን እገዳ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ባቀረቡት ሐሳብ መሠረት ለመንበረ ፓትርያርኩ የጥበቃ ሐላፊ በመንገር ተፈጻሚ እንዲሆን ነበር ስምምነት የተደረሰበት፡፡ ይሁንና የወይዘሮዋ ለዚያውም በምሽት ሰዓት እዚያ መገኘት ለስምምነቱ መተግበር ብፁዕ ሥራ አስኪያጁ የቅዱስ ሲኖዶሱ ጽ/ቤት እና የቋሚ ሲኖዶሱ ክትትል ምናልባትም የመንግሥት የጸጥታ ኀይሎች እገዛ ሳያስፈልጋቸው የሚቀር አይመስልም፡፡

በሌላ በኩል ‹‹የአቡነ ጳውሎስ ሐውልት ተነሥቶ እና ቢልቦርዳቸው ተሰብስቦ በመንበረ ፓትርያርክ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር እንዲቀመጥ›› የሚል ውሳኔ የሰፈረበት ቃለ ጉባኤ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መዝገብ ቤት በኩል ውሳኔውን ለሚያስፈጽመው የጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ቢሮ እስከ አሁን ባልደረሰበት ሁኔታ ወይዘሮ እጅጋየሁ የሲኖዶሱን ውሳኔ የሚቃወም ግርግር በመፍጠር ተግባራዊነቱን እግዳት (deadlock) ውስጥ የሚያስገባ፣ በሂደትም ‹‹ውሳኔውን የሚደግፉ እንዳሉ ሁሉ የሚቃወሙም አሉ›› የሚል ብዥታን በመንግሥትም ዘንድ ሳይቀር ፈጥሮ አፈጻጸሙን አጣብቂኝ ውስጥ በመክተት የሚያስተጓጉል ቡድን አደራጅተው በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡ ውዥንብሩን በመፍጠር እየተንቀሳቀሱ መሆናቸው የተነገረው ቀሲስ ሳሙኤል እሸቱ፣ መምህር ሰሎሞን በቀለ፣ በጋሻው ደሳለኝ፣ ያሬድ አደመ እና ሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ግለሰቦች በተጨማሪ አንዳንድ የአዲስ አበባ አድባራት እና ገዳማት አስተዳዳሪዎችን ለማነሣሣት ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ተገልጧል፡፡

“ሲኖዶሱ በእኛ ገንዘብ ምን አገባው” በሚል አፍቃሬ ሐውልት ዐመፅ ለመቀስቀስ የሚጥሩት ሴትዮዋ ለአቋማቸው ያግዘኛል ያሉትን ማንኛውንም መድረክ እየተጠቀሙ ነው፡፡ ጥቅምት 23 ቀን 2003 ዓ.ም የሐዋሳ እና ዲላ ከተሞች የፍትሕ እና ልማት ኮሚቴ አባላትን እንዲሁም ማኅበረ ቅዱሳንን “በሥልጣን ጥማት፣ በጥቅም አጋባሽነት እና በፀረ ሰላምነት” በመወንጀል፣ አቡነ ፋኑኤልን እና ሥራ አስኪያጃቸውን “የልማት እና የወንጌል አባት” እያሉ በማመሰጋገን ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ለተቃውሞ የመጡት ኀይሎች ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ እና ብፁዓን አባቶች ጋራ በተወያዩበት መድረክ ላይ ሐውልቱ እንዲነሣ ቅዱስ ሲኖዶስ ያስተላለፈውን ውሳኔ የሚቃወሙ አስተያየት ሰጪዎች እንዲናገሩ አድርገዋል፡፡ ተቃዋሚዎቹ ከመጡባቸው ዘጠኝ ተሽከርካሪዎች መካከል የአምስቱን መኪኖች ወጪ ስፖንሰር ማድረጋቸው የተነገረላቸው ወ/ሮ እጅጋየሁ፣ ያሬድ አደመ እና በጋሻው ደሳለኝ ቅዱስ ሲኖዶስ አቡነ ፋኑኤልን ያዘዋወረው “በአዋሳ አካባቢ ያሉ መናፍቃን እና የጳጳሱ መኖር ጥቅማቸውን ያሳጣባቸው አንዳንድ ባለሀብት ፀረ ቤተ ክርስቲያኖች በፈጠሩት ጫና፣ ግፊት እና ውዥንብር በመወናበድ በመሆኑ እንዲጣራላቸው” በሚል ተቃዋሚዎቹ ሰጡት የተባለውን አስተያየት እንደሚጋሩ ነው የሚታመነው፡፡

ያሬድ አደመ ስለ "ሐውልቱ" ላደረገው "አስተዋጽዖ" ሲሸለም
በተያያዘ ዜና ያሬድ አደመ በሙስና ባጋበሰው ገንዘብ በሐዋሳ ከተማ በከፈተው “የቅዱስ አትናቴዎስ ዐጸደ ሕፃናት” ልጆቻቸውን የሚያስተምሩ ምእመናን “ልጆቻችን ከሌባ ምን ይማራሉ” በሚል እየሰበሰቡ ሲሆን በተመሳሳይ አኳኋን በከፈተው ዳቦ ቤት ለዕቃ ግዥ ለተስማማቸው አካላት ተቀማጭ ገንዘብ በአካውንቱ የሌለበትን ደረቅ ቼክ በመስጠቱ በማጭበርበር ወንጀል ክስ እንደተመሠረተበት ለማወቅ ተችሏል፡፡ የዓላማ ተጋሪው በጋሻው ደሳለኝ ደግሞ በዐውደ ምሕረት ላይ እንዳይቆም በጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ፣ በስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ የበላይ ሐላፊ ደብዳቤዎች በየደረጃው ከታገደ በኋላ ሚያዚያ 19 ቀን 2002 ዓ.ም በድሬዳዋ ሳባ ደብረ ኀይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ‹‹ንጉሥ በዙፋኑ አለ›› በሚል ርእስ ባሰማው ንግግር ‹‹ብዙ ጋዜጦች ቢጽፉበትም፣ ብዙ ቪሲዲ ቢበተንም ዛሬም በመድረኩ ቆመናል፤ አንድ ማኅበር አለ - ማኅበረ ቅዱሳን የሚባል - ደም መጣጭ ማኅበር፤ የወንድሞችን ደም አፍስሶ ደማቸውን ለመጠጣት በጣሳ የሚቀበል፤ ብዙ አባቶችን ያሳደዱ፣ በጋዜጣቸው ያዋረዱ፤ መንግሥት አዲስ ሕግ አውጥቶ በፖሊቲካ ሲይዛቸው ሃይማኖተኞች ነን የሚሉ፣ በሃይማኖት ሲይዛቸው ደግሞ በፖሊቲካ የሚሄዱ. . . ሌቦች፣ ዘራፊዎች. . .” በሚል በአደባባይ በፈጸመው የስም ማጥፋት ወንጀል ፈጽሞ ነበር፡፡
በጋሻው ስለ "ሐውልቱ" ላደረገው "አስተዋጽዖ" ሲሸለም
ግለሰቡ ራሱ ሕገ ወጥ ሆኖ በፈጸመው የከተማውን ሰላም በሚያደፈርስ ተግባሩ ሳቢያ በማኅበረ ቅዱሳን የድሬዳዋ ማእከል ሚያዝያ 20 ቀን 2002 ዓ.ም ክስ ተመሥርቶበት ነበር፡፡ ይሁንና የድሬዳዋ አስተዳደር ካውንስል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በጋሻው ከዚህ በፊት በተሰጠው ጊዜ ቀጠሮ ባለመቅረቡ ነገ ጥቅምት 26 ቀን 2003 ዓ.ም ጠዋት በፖሊስ ታስሮ እንዲቀርብ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ጉዳዩ እንደሚታይ ይጠበቃል፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)