November 1, 2010

አቡነ ጳውሎስ ‹‹የሐውልት ፍለጋ›› ዑደት ጀምረዋል

  • ትናንት የደብር ቅዱስ ደብረ ጽጌ ማርያም ገዳምን ጎብኝተዋል፤
  • በዚህ ሳምንት ውስጥ ከግብጽ ገዳማት ወደ አንዱ ለማምራት እየተዘጋጁ ነው፤
(ደጀ ሰላም፤ ኖቬምበር 1/2010፤ ጥቅምት 22/2003 ዓ.ም) ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ትናንት ጥቅምት 21 ቀን 2003 ዓ.ም በዋለው እሑድ ሰንበት በሰሜን ምዕራብ ሸዋ - ሰላሌ ሀገረ ስብከት የምትገኘዋን የደብር ቅዱስ ደብረ ጽጌ ማርያም ገዳምን ጎበኙ፡፡ የሥሪቷ ጥንታዊነት እስከ መካከለኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ ወደኋላ በሚቆጠርላት የደብር ቅዱስ ደብረ ጽጌ ማርያም ገዳም አሁን ቆሞ የሚታየው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን የተሠራው በኢትዮጵያዊው ቀዳማዊ ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ዘመን በ1952 ዓ.ም ነው፡፡ በገዳሟ ቤተ መቅደስ ውስጥ ያለውን በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ መልክእ የተቀረጸውን ምስል የጎበኙት ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ምስሉ ፎቶ ግራፍ እንዲነሣ ማዘዛቸውን፣ በቃላቸውም ትእዛዝ መሠረት ምስሉ ፎቶ ግራፍ መነሣቱ ተዘግቧል፡፡ ነዋሪነታቸውን በጀርመን ሀገር ያደረጉ ወገኖች ‹‹ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ስለነበራቸው ፍቅር›› ከዜና ዕረፍታቸው በኋላ እንዳሠሩት የሚነገርለትን ይህንኑ የቁም ምስል የጎበኙት ፓትርያርኩ ከነገ በስቲያ የሐውልት ማፈላለግ ዑደታቸውን በመቀጠል በግብጽ በርሓ ከሚገኙት ገዳማት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሐውልት ይገኛል የሚባልበትን ገዳም እንደሚጎበኙ ተነግሯል፡፡
ባለፈው ዓመት በደብር ቅዱስ ደብረ ጽጌ ማርያም ገዳም ለሚገነባው የአብነት ትምህርት ቤት እና የአረጋውያን መጦርያ እብነ መሠረት እንዲያኖሩ ጥሪ ተደርጎላቸው ያለበቂ ምክንያት ያልሄዱት አቡነ ጳውሎስ፣ ትናንት የእመቤታችን የወር በዓል ከአብነት ት/ቤቱ እና የአረጋውያን መጦርያ ተቋም መጠናቀቅ ጋራ መገጣጠሙን ሰበብ አድርገው ሪባን ቆርጠው ለመመረቅ ተገኝተዋል፡፡ ፓትርያርኩ በገዳሙ ከተገኙ በኋላ ከመቅደሱ በር በስተቀኝ የሚገኘውን የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ሐውልት አብረዋቸው ለተጓዙ ጳጳሳት እያሳዩ ፎቶ ግራፍ እንዲነሣ ማዘዛቸው፣ ቅዱስ ሲኖዶስ በቁማቸው ሳሉ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ጥሰው ሥርዐተ አበውን ተላልፈው ያሠሩት ሐውልታቸው እንዲፈርስ ያስተላለፈውን ውሳኔ እዚህም እዚያም በግለሰቦች ተፈጸሙ እና መሠረታዊ እውነታውን የማይቀይሩ ስሕተቶችን በልማዳዊ ምልከታዎች ላይ ተመሥርቶ እንደ ማስረጃ በማቅረብ እንዳይፈጸም ለሚያደርጉት ጥረት ጉልሕ ማሳያ መሆኑን ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅዱሳት ሥዕላት ቀኖና እና ትውፊት ሥርዓተ አምልኮን ለመፈጸም፣ የሥዕሉ ባለቤት የሆነውን ቅዱስ ትምህርት፣ ገድል እና ተኣምር ለመዘከር እና ከቃል ኪዳኑ በረከት ለማግኘት እንዲሁም ምእመናንን ለማስተማር አገልግሎት ላይ የሚውሉት የቅብ እና የጭረት ሥዕሎች እንጂ እውናዊ መልክእ ያላቸው ቅርጾች አይደሉም፡፡ እኒህም ተፈጻሚ የሚሆኑባቸው የራሳቸው ጊዜ እና ሥርዓት አላቸው፡፡ አቡነ ጳውሎስ በደብር ቅዱስ ደብረ ጽጌ ማርያም ገዳም ትናንት የጀመሩት ዑደት ይህን ቀኖና ቤተ ክርስቲያን በማፋለስ እና ሥርዓተ አበውን በመጣስ በራሳቸው ምሳሌ ያቆሙት ሐውልት እንዲነሣ ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳለፈውን ውሳኔ በተግባር የመገዳደር ውጥን በመሆኑ ብፁዓን አባቶች ሊነቁበት እንደሚገባ ተመልክቷል፡፡
መሠረቱ ሰማያዊ የሆነው ፍጹማዊው ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ለኅሊናቸው ከሚያስረግጥላቸው እውነት ይልቅ ከራሳቸው ልባዌ ጋራ የሚጣጣም እና በዳሰሳዊ (ኢምፔሪሲስታዊ) አስረጅ ላይ የተመሠረተ ሐሰሳ ውስጥ የሚዳክሩት ፓትርያርኩ፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 15 ንኡስ አንቀጽ 1 - 15 በዝርዝር በተደነገገው መሠረት ‹‹ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰነውን በሙሉ ልብ ተቀብሎ ለማስፈጸም›› ካለባቸው ግዴታ ይልቅ የቅዱስ ሲኖዶሱን ተቋማዊ ልዕልና፣ አሠራር እና ውሳኔ ደረጃ በደረጃ በግለሰባዊ ዐምባገነንት በሚተካ ትሮትስካዊ ዘይቤ ራሳቸውን ማሠማራታቸው ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እንደ ወርቅ ጠርቶ በሚታይበት ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን፡፡

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 20 ቀን 2003 ዓ.ም በተጠናቀቀው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የሐውልቱን መሠራት ጨምሮ የሲኖዶሱን ማእከላዊ አሠራር ያልጠበቁ አካሄዶች በተመለከተ በተዘረጉት አጀንዳዎች ላይ በመንፈስ ልዕልና እና በሐሳብ የበላይነት አቋማቸውን ፊት ለፊት እያስረገጡ ከመወያየት ይልቅ በዝምታ/ቸልታ ሲያዘናጉ ቆይተዋል፤ በስብሰባው መዳፊያ ላይ ግን እንዲህ ባለው ወሳኝ አካል የሚካሄዱ ውይይቶች እና የሚተላለፉ ውሳኔዎች የሕዝቡን ቀልብ የሚይዙ በመሆናቸው በስተመጨረሻ የሚሰጡ ጋዜጣዊ መግለጫዎች እና የሚዘጋጁ ጋዜጣዊ ጉባኤዎች ከፍተኛ የሕዝብ ግንኙነት ፋይዳ ይኖራቸዋል፡፡ ይህን ለመረዳት ብፁዓን አባቶች የልምድ ውስንነት እንደነበረባቸው ታይቷል፡፡ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ግን የሳምንት አርምሟቸው የአንደበት እንጂ እንደ በቁት አባቶቻችን የጽማዌ እንዳልነበር መድረኩ ያለውን ዋጋ በስተመጨረሻ በብልጣብልጥነት በመጠቀም አሳይተውናል - ብልጥ ያለአንድ ቀን አይበልጥም እንጂ!! ከብፁዓን አባቶች የነበረባቸውን ተግዳሮት ከአንድ ዓመት በፊት እንደነበረው ‹‹በተውሶ ጡንቻ›› ሳይሆን በብልጣብልጥነት ቀጭን ጎዳና የተወጡት የመሰላቸው አቡነ ጳውሎስ፣ አሁን ደግሞ በዳሰሳዊ ዕውቀት ላይ የተመሠረቱ ሙግቶችን (Empirical evidences) በማቅረብ በራሳቸው አስተሳሰብ የክብራቸው ትእምርት የሆነው ሐውልታቸው እንዳይፈርስ በመትጋት ላይ ናቸው፡፡

በመሠረቱ በልማድ ተይዘው የሚፈጸሙ እና የሚደጋገሙ ነገሮች የሚሰጡትን አጠቃላይ መልክእ በመያዝ ላመኑበት አቋም እንደ አስረጅ የሚያቀርበው ዳሰሳዊ ዕውቀት (Empirical Knowledge) መነሻ ቢሆን እንጂ የመጨረሻ ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም፡፡ ዳሰሳዊ ዕውቀት በባሕርዩ የነገሮችን መሠረተ እውነት /አመክንዮ ከመመርመር ይልቅ የልማዱን ተቀብሎ የማደር ግዴታን የሚጥል፣ ለጭቆና የተመቸ እና በይዘቱም ጥልቀት የሚጎድለው ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ (በመንበሩ ላይ እስካሉ ድረስ በዚህ ማዕረግ ይጠሩ ዘንድ ሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 14 ንኡስ አንቀጽ አንድ ያዝዛል) በጀመሩት የእልህ/የቁልቁለት መንገድ እስከ ግብጽ በረሐ ወርደው የሚያፈላልጉት እውነት ቢገኝ እንኳን ፍጽምና የሚጎድለው እና በተሳሳተ መሠረት ላይ የቆመ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የመጨረሻው ከፍተኛ ሥልጣን ባለቤት የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ ስለሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎች አፈጻጸም ሕገ ቤተ ክርስቲያኑ የሚለውን የተመለከትን እንደሆነ ግን፣ በአንቀጽ 11 ንኡስ አንቀጽ አንድ ቋሚ ሲኖዶሱ፣ በአንቀጽ 15 ፓትርያርኩ፣ በአንቀጽ 20 ኤጲስ ቆጶሳቱ፣ በአንቀጽ 25 የቅዱስ ሲኖዶስ ጸሐፊው እና በአንቀጽ 30 የቤተ ክህነቱ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ የመፈጸም እና የማስፈጸም ግዴታ እንደተጣለባቸው ይደነግጋል፡፡ በመሆኑም ስለ ሐውልቱ መፍረስ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም አንገብጋቢ አጀንዳዎች ላይ ቅዱስ ሲኖዶስ ያስተላለፋቸው ውሳኔዎች ተፈጻሚነት በተጠቀሱት አካላት የቅርብ ክትትል ሊደረግባቸው ይገባል፡፡ በአፈጻጸሙ ሂደት አስቸኳይ እና ድንገተኛ እክሎች ቢያጋጥሙ በየዓመቱ ጥቅምት 12 እና ትንሣኤ በዋለ በሃያ አምስተኛው ቀን/በርክበ ካህናት/ ከሚደረገው ጉባኤ ውጭ ቅዱስ ፓትርያርኩ ወይም የቋሚ ሲኖዶስ አባላት በሚያደርጉት ጥሪ አልያም ከጠቅላላው አባላት ከሦስት ሁለቱ እጅ የሚሆኑ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ምልአተ ጉባኤ እንዲደረግ በጠየቁ ጊዜ ጥሪ ሊደረግ እና ስብሰባው ሊካሄድ ይችላል (አንቀጽ 10 ንኡስ አንቀጽ 1 - 2)፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)