November 1, 2010

ብፁዕ አቡነ ገብርኤል የሐዋሳ ሊቀ ጳጳስ እንዲሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰነውን የዝውውር ውሳኔ የሚቃወም አድማ እየተካሄደ ነው

  • አድማውንያስተባበሩት በጋሻው ደሳለኝ እና ምርትነሽ ጥላሁን ናቸው
  • አድማውን በመጠቀም ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ እና በጋሻው ደሳለኝ ሐውልቱ እንዲነሣ ቅዱስ ሲኖዶስ ያስተላለፈው ውሳኔ ተፈጻሚነት እንዳያገኝ የሚጠይቅ የአቤቱታ ፊርማ እያሰባሰቡ ነው
  • የእነ ያሬድ አደመ የዐመፅ ጎራ በተወሰደው አቋም ላይ መከፋፈሉ እየተነገረ ነው
  • መንግሥት የማያባራው የዐመፅ ድራማ እንዲያበቃ ተጠይቋል
 ደጀ ሰላም፤ ኖቬምበር 31/2010፤ ጥቅምት 22/2003 ዓ.ም)‹‹የአጣሪ ኮሚቴው ሪፖርት ሳይሰማ ቅዱስ ሲኖዶስ አቡነ ፋኑኤል ከሲዳማ አማሮ እና ቡርጂ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጵጵስና እንዲነሡ እና ብፁዕ አቡነ ገብርኤል እንዲመደቡ የወሰነውን ዝውውር እንቃወማለን”  በሚል ከሐዋሳ፣ ዲላ እና ይርጋዓለም ከተሞች የተውጣጡ ናቸው የተባሉ ተቃዋሚዎች አዲስ አበባ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ደርሰው ተመልሰዋል፡፡ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ቅ/ፓትርያርኩን ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ባሉበት ያነጋገሩት አቤቱታ አቅራቢዎቹ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል እንዳይነሡብን ቢሉም አንድ ጊዜ ቅ/ሲኖዶሱ መወሰነኑን፣ አሁን ከተመደቡላቸው ሉቀ ጳጳስ ጋር እንዲሠሩ እንደተነገራቸው፤ እነርሱም ቢያንሥ ሥራ አስኪያጁ ይነሡ የሚለው ነገር እንዲቀር ጠይቀዋል ወደ መጡበት ተመልሰዋል ተብሏል።
 
ተቃዋሚዎቹን ከዲላ ከተማ በጋሻው ደሳለኝ፣ ከይርጋለም ከተማ ምርትነሽ ጥላሁን፣ ከሐዋሳ ከተማ ዓለምነህ ሽጉጤ እና ያሬድ አደመ የጎጠኝነት ስሜት በተቀላቀለበት ቅስቀሳ ጭምር በመጠቀም እያንዳንዳቸው 25 ሰው የመጫን አቅም ባላቸው ዘጠኝ አይሲዙ መኪኖች ወደ አዲስ አበባ እንዳመጧቸው ነው የደረሰን ዘገባ የሚያስረዳው፡፡ ያሬድ አደመ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ከሥልጣናቸው በተወገዱት መልአከ ሕይወት ፀሐይ መልአኩ ፊርማ እና በሀገረ ስብከቱ ማኅተም ‹‹የሀገረ ስብከቱ ሕዝብ ግንኙነት ሐላፊ›› እንደሆነና በሚፈጽመው ተግባር ትብብር እንዲደረግለት በቅርቡ ያጻፈው የድጋፍ ደብዳቤ ከበጋሻው ጋራ በመሆን በየገጠሩ ላካሄደው የዐመፅ ቅስቀሳ ሳያግዘው እንዳልቀረ ውስጥ ዐዋቂዎች ለደጀ ሰላም አስረድተዋል፡፡

ብዙዎቹ ተሰላፊዎች በለጋነት የዕድሜ ክልል የሚገኙ እና በጥቅም የተደለሉ ነዳያን እንደ ሆኑ፣ ስለ እንቅስቃሴው በቂ ግንዛቤ የሌላቸው፣ በሰበካ ጉባኤ ይሁን በሰንበት ት/ቤት አባል ያልሆኑ፣ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ መሆናቸው የሚያጠራጥር እንደሆኑ የቅርብ ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡ ‹ተቃዋሚዎቹ› በከፊል ከሐዋሳ ከተማ ውጭ ከገጠር ወረዳዎች የተሰባሰቡ እንደ ሆኑ፣ የአድማው አስተባባሪዎች በሐዋሳ ከተማ ያሰቡትን ያህል የተቃዋሚ ብዛት ማግኘት እንዳልቻሉ እንዲያውም የተፈጠረው ችግር በአጣሪ ኮሚቴው ተጠንቶ ለቅዱስ ሲኖዶስ በቀረበበት እና የተመደቡት ሊቀ ጳጳስም በተግባር ባልታዩበት ሁኔታ ዐመፁ ተገቢ እንዳልሆነ አቋም በያዙ ቡድኖች ሳቢያ ኀይላቸው መከፋፈሉ ተገልጧል፡፡ በሚካሄደው ዐመፅ ዓለምነህ ሽጉጤ የተባለውና ‹‹የሚበቃውን ጥቅም ያህል ከአቡነ ፋኑኤል ማግኘቱን›› ያለሀፍረት የሚናገረው ግለሰብ በዚህ የዐመፅ እንቅስቃሴ ለሚፈጠረው ችግር ደረጀ ዘርጋው፣ ኮ/ል ወልደ መስቀል (የደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ሰበካ ጉባኤ አባል እንዲሆኑ በሕገ ወጥ መንገድ በአቡነ ፋኑኤል የተመረጡ) እና መቶ አለቃ ከሚባሉ ግለሰቦች ጋራ ሐላፊነቱን እንደሚወስድ በይፋ መናገሩ የተገለጠ ሲሆን አቡነ ፋኑኤልም አዲስ አበባ ላይ ሆነው ያደረ ቂም የያዙባቸውን የብፁዕ አቡነ ገብርኤልን ስም ‹‹ጴንጤ እና ፒያኖ ተጫዋች ነው›› በሚል እያጠፉ አድማው እንዲጠናከር፣ የሀገረ ስብከቱ ምእመናን እርሳቸው ‹‹ብቸኛ አባታቸው እና የልማት ጀግናቸው በመሆናቸው›› እንዳይቀሩባቸው በስልክ እየደወሉ እያጨናነቋቸው መሆኑን በሞባይል ስልክ የተናገሩበትን የድምፅ ማስረጃ የያዙ ደጀ ሰላማውያን አስረድተዋል፡፡ በተለይም ዓለምነህ ሽጉጤ አመራር የመስጠት ሚና የሚጫወትበት ‹‹ተስፋ ኪዳነ ምሕረት›› እየተባለ የሚጠራው ቡድን እና ያሬድ አደመ ያደራጃቸው ቴኳንዶዎች በሐዋሳ ፍትሕ እና ልማት ኮሚቴ አባላት እንዲሁም የሚፈጽሙትን ደባ በሚያጋልጡ ሌሎች ምእመናን ላይ የማስፈራራት እና ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ አካላዊ ድብደባ በመፈጸም ላይ እንደ ሆኑ የደረሱን ጥቆማዎች ያስረዳሉ፡፡

የክልሉ መንግሥት አስተዳደር ቅዱስ ሲኖዶስ በተላከው አጣሪ ኮሚቴ አማካይነት ጉዳዩን ተመልክቶ ውሳኔ መስጠቱን፣ እኒህ የዐመፅ ኀይሎች ውሳኔውን የመቀበል ግዴታ እንዳለባቸው ማሳሰቢያ ከመስጠቱም በላይ ተፃባኢ የሆኑትን ኀይሎች ለማደራደር እና ለማስማማት ያደረገው ጥረት ‹‹አልያዘለትም›› ተብሏል፡፡ ይሁንና ምእመኑን በመከፋፈል የክልሉን ጸጥታ በማደፍረስ ላይ የሚገኙትን እነ ያሬድ አደመን እና መሰሎቻቸውን በተግባር ለመቆጣጠር እያሳየ በሚገኘው ዳተኝነት ሳቢያ ጉዳዩ አንዳች የፖሊቲካ ዓላማ አልያም ቤተ ክርስቲያኒቱን በቀጣይ የውስጥ ትርምስ መካከል በማቆየት ገጽታዋን የማበላሸት እና የማዳከም፣ በዚህም ሂደት የሆኑ ግለሰቦችን እና ቡድኖችን ጥቅም የማስጠበቅ ፍላጎት ሳይኖረው እንደማይቀር እየተነገረ ነው - ‹‹በማኅበራት ስም የሚካሄደው ኪራይ ሰብሳቢነቴ ይቅር !!›› ይላል ‹ተቃዋሚዎቹ› በመኪናዎቻቸው ላይ ከለጠፏቸው መፈክሮች አንዱ፡፡

በሌላ በኩል ለአቡነ ጳውሎስ ሐውልት መሠራት እና መተከል ግንባር ቀደም ሚና የተጫወቱት ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ እና በጋሻው ደሳለኝ ቅዱስ ሲኖዶስ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን እንዳይፋለስ ለመጠበቅ፣ ሥርዐተ አበውን ለማስከበር የወሰነው ውሳኔ ተፈጻሚነት እንዳያገኝ የሚቃወም የአድማ አቤቱታ ፊርማ በማሰባሰብ ላይ እንደሚገኙ ተገልጧል፡፡ በአንጻሩ መንግሥት ቀደም ሲል ከብፁዓን አባቶች ጋራ ሲያደርግ በቆየው ውይይት በገባው ቃል መሠረት የቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ ተግባራዊ ፍጻሜ ያገኝ ዘንድ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ፣ በሐዋሳ የአጣሪ ኮሚቴው ሪፖርት መሠረት በቁጥጥር ሥር መዋል ያለባቸውን ሐላፊዎች ይዞ ለፍርድ በማቅረብ በመብት ጥያቄ ስም በማያባራ መልኩ እየቀጠለ የሚገኘው የዐመፅ ድራማ እንዲያበቃ ያደርግ ዘንድ በመጠየቅ ላይ ነው፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)