October 26, 2010

የቅ/ሲኖዶስ የዛሬ ከሰዓት ውሎ፦ ቅዱስ ሲኖዶስ በሐውልቱ፣ በፖስተሩ እና በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሹም ሽር ጉዳዮች ፓትርያርኩ ማብራሪያ እንዲሰጡ ብርቱ ተቃውሞ እና ጥያቄ አቀረበ


  • የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት በአንድ ሊቀ ጳጳስ እና በአንድ ሥራ አስኪያጅ ብቻ እንዲመራ ተወሰነ
  • ፓትርያርኩ ለሀ/ስብከቱ የመረጡትን ጳጳስ ለመሾም ያቀረቡት ጥያቄ ውድቅ ተደርጎባቸዋል
  • ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ሲኖዶሱ ወደ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እንዲመልሳቸው ጠይቀዋል
  • ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ የፈጸሟቸውን በደሎች በዝርዝር አጥንቶ በሕግ እንዲጠየቁ የሚያደርግ ኮሚቴ እንዲቋቋም ተወስኗል
  • ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ አቡነ ሳሙኤልን ‹‹በመፈንቅለ ፓትርያርክ›› ለመክሰስ ሞክረዋል
  • ‹‹ለራስ ሐውልት ከማቆም በላይ ምን ውርደት አለ? ዐፄ ኀይለ ሥላሴም ለሞተች ውሻቸው ሐውልት አቁመዋል ይባላል፤ በእርስዎ ዘመን አፍረናል፡፡›› (ብፁዕ አቡነ ኄኖክ)
 (ደጀ ሰላም፤ ኦክቶበር 25/2010፤ ጥቅምት 15/2003 ዓ.ም):- ቅዱስ ሲኖዶስ በዛሬው ከሰዓት በኋላ ቆይታው ቀደም ሲል በተያዙት አራት አጀንዳዎች ላይ ተነጋግሯል፤ በብዙዎቹም ላይ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ በአራተኛ ተራ ቁጥር በተያዘው ‹‹ማእከሉን ባልጠበቀ መንገድ ከቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ውጭ በተሠሩ እና በሚሠሩ ጉዳዮች ላይ ተነጋግሮ መወሰን›› በሚለው ወቅታዊ አጀንዳ ላይ ቅዱስ ሲኖዶሱ በዕሥራ ምእቱ በዓል አከባበር ፓትርያርኩ ‹‹ሰማዕት ዘእንበለ ደም፤ የሚሌኒየሙ አባት›› በሚል ተሠይመው በየአብያተ ክርስቲያኑ ፖስተራቸው ስለ ተሰቀለበት፣ በ18ኛ ዓመት በዓለ ሢመታቸው ዋዜማ በቦሌ ደብረ ሳሌም መጥምቁ ዮሐንስ እና በደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ካቴድራል ደጃፍ (በአንዳንዶች አገላለጽ ናቡከደነፆር የራሱን ምስል ካቆመበት ዱራ ሜዳ ጋራ ተነጻጽሮ ይጠራል) ላይ እንዲቆም ፈቅደው ስለባረኩት የራሳቸው ‹‹ሐውልተ ስምዕ››፣ በቅርቡ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የሒሳብ እና በጀት መምሪያ እንዲሁም የአስተዳደር እና አቅም ግንባታ መምሪያዎች ላይ ስለተደረጉት ሹም ሽሮች፣ ‹‹የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን አስተዳደር አየር ባየር ይመራሉ›› ስለሚባሉት (በአንዳንድ አባቶች አገላለጽ ሴቷ ጳጳስ እስከ መባል የደረሱት) የማፊያ ቡድኖች ጉዳይ ብርቱ ጥያቄ እና ተቃውሞ ለፓትርያርኩ አቅርቧል፡፡

ፖስተሩ
ፖስተሩም ይሁን ሐውልቱ ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን እና ከሥርዓተ አበው ውጭ መሆኑን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ሐውልት ብለው ጣዖት አቁመዋል፤ ሐውልቱ የዘመናችን አርጤምስስ ነው›› ያሉት ብፁዕ አቡነ እንድርያስ፣ ‹‹በመፍራት እና በማፈር ሰው ይሰነካከላል፤ በእግዚአብሔር የሚታመን ግን ደስ ይለዋል፡፡ የሰው ኀጢአቱ በደለኛ ያሰኛዋል፤ በእግዚአብሄር የታመነ ሰው ግን ይድናል፡፡ ብዙ ሰዎች በመኳንንት ፊት ይላላካሉ፤ የሰው ፍርዱ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፤ እውነተኛ ሰው በግፈኛ ሰው ዘንድ የተናቀ ነው፤ ቀና መንገድም በኀጥአን ዘንድ አጸያፊ ነው›› የሚለውን ኀይለ ቃል ከመጽሐፈ ተግሣጽ ምዕራፍ 5 ቁጥር 24 - 27 በመጥቀስ መንበረ ፓትርያርኩ ቤተ ክህነቱ ቤተ ክርስቲያኒቱ የማታውቃቸው እና ያልወከለቻቸው ግለሰቦች የሚፈነጩበት እና ጉዳያቸውን የሚያስፈጽሙበት ተቋም መሆኑን በማስመልከት ሰፊ እና ብዙዎችን ያሳመነ ማብራሪያ መስጠታቸው ተገልጧል፡፡ ሌሎችም ብፁዓን አባቶች የቤተ ክርስቲያኒቷ ቀኖና እየተጣሰ፣ አስተዳደሯ እየተበላሸ ከቀን ወደ ቀን የምትዋረድበት ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን በተባበረ ድምፅ አስረድተዋል፡፡ በ1991 ዓ.ም ተሻሽሎ በጸደቀው ሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ ሰባት ስለ ቅዱስ ሲኖዶስ ሥልጣን እና ተግባር ከተደነገገው በተቃራኒ በቅርቡ ስለተደረጉት ቅዱስ ሲኖዶስ ስለማያውቃቸው ሹም ሽሮችም ጉዳይ  ፓትርያርኩ እና የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ተጠይቀዋል ፡፡

ለጥያቄው ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ሰጥተውታል በተባለው ምላሽ በለውጡ ጥናት ሂደት ምክክሩ ውስጥ የነበሩትን እና በልማት ኮሚሽኑ ውስጥ ያሉትን ኃላፊዎች ስም በመዘርዘር፣ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጋራ እርሳቸውም ተጨምረውበት ሹም ሽሩ እንደተፈጸመ አስረድተዋል፡፡ የብፁዕነታቸው አገላለጽ የአካሄዱን ስሕተተኛነት ያጋለጠ የመሰላቸው ፓትርያርኩም በእጅጉ መቆጣታቸው ተመልክቷል፡፡ ከእኒህም በተጨማሪ ሲኖዶሱ በሌሎች የአሠራር ጥሰቶች ላይ መነጋገሩ የተዘገበ ሲሆን ‹‹ከሲኖዶሱ ፈቃድ ውጭ ይህን ላደረጉበት ማብራሪያ ይስጡ›› በማለት ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ቅዱስነታቸውም ‹‹አባቶቼ፣ አንተ ቤተ ክርስቲያኗን አዋርዳሃታል፤ አቆርቁዛሃታል አላችሁኝ፤ ስለዚህ በጉዳዩ ላይ አስቤበት ለነገ መልስ እሰጣለሁ›› በማለት ወደ ስድስተኛው የአጀንዳ ተራ ቁጥር ሊሻገር የነበረው ጉባኤው የፓትርያርኩን ምላሽ አዳምጦ ለመወሰን ለነገ እንዲያድር ተደርጓል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶሱ ቀደም ሲል በተመለከታቸው ሌሎች አጀንዳዎች በፓትርያርኩ ልዩ ጸሐፊ አማካይነት ‹‹ቃለ ምዕዳን›› በሚል በንባብ የቀረበውን በከፊል ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የሚወነጅል ጽሑፍ ሙሉ በሙሉ ውድቅ አድርጓል፡፡ በጽሑፉ ላይ ቅዱስነታቸው በብፁዕ አቡነ ሳሙኤል በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጭ ተፈጽሞብኛል ያሉትን ‹‹የማሳደም፣ የማሳመፅ እና የመፈንቅለ ፓትርያርክ ሙከራ›› በጊዜ እና በቦታ እየለዩ ዘርዝረዋል፡፡ ከውንጀላው ብዙው ክፍል የተፈጸመው ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል በ2001 ዓ.ም ከግንቦት - ሐምሌ ወር ድረስ በሥራ ላይ በነበረው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ጸሐፊ ሆነው በሚሠሩበት ወቅት ነው፡፡ ‹‹በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሕንፃ ግንባታ ወቅት 15 ሚልዮን ብር በጀት ተፈቅዶ ሳለ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ለአዳራሽ እና ለአሳንሰር ማሠሪያ ተጨማሪ ገንዘብ ወጪ ማድረጋቸው፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሒሳብ አሠራሩን ዘመናዊ(ኮምፒዩተራይዝድ) በማድረጉ›› ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የተለመደ እና የሚረዳ አለመሆኑ ሌሎች በአቡነ ሳሙኤል ላይ የቀረቡ ክሶች ናቸው፡፡ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ለክሱ በሰጡት ምላሽ ለሕንፃ ሥራው ወጪ የተደረገው ተጨማሪ ገንዘብ በወቅቱ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በነበሩት በብፁዕ አቡነ ይሥሐቅ እና በራሳቸው በፓትርያርኩ በቀረበው ጥያቄ መሠረት የተፈቀደ በመሆኑ ሕገ ወጥ ሊባል እንደማይችል፣ ተጠያቂነትም ካለ የሚመለከተው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን የቤቶች እና ሕንፃዎች አስተዳደር መሐንዲስ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ስለ ሒሳብ አሠራሩም ሀገረ ስብከቱ በእርሳቸው አስተዳደር ጀምሮት የነበረውን ዘመናዊ አሠራር ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የቆየ አሠራር ጋራ ለማጣጣም ሲባል ወደ ኋላ እንዲመለስ የጋራ ስምምነት ስለተደረሰበት በወቀሳ መልክ ሊቀርብ እንደማይገባው ነው ብፁዕነታቸው ያስረዱት፡፡

ጉባኤው በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ በመነጋገር ውሳኔ ካሳለፈባቸው ጉዳዮች ውስጥ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅን ከኃላፊነት ማንሣት ይገኝበታል፡፡ በውሳኔው ላይ ሥራ አስኪያጁ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ ለፈጸሙት የምዝበራ ወንጀል በሕግ እንዲጠየቁ፣ ለዚህም ከተሾሙበት እስከ ወረዱበት ጊዜ ድረስ የሠሯቸውን ጥፋቶች በዝርዝር አጥንቶ በሕግ አግባብ ለፍትሕ አካል የሚያቀርብ ኮሚቴ እንዲሠየም ተወስኗል፡፡ ይህ ውሳኔ በሲኖዶሱ ምልአተ ጉባኤ በሚተላለፍበት ወቅት ከሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ጋራ የሥራ ግንኙነት የነበራቸው ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ያሳዩት አርምሞ ተሰብሳቢ ሊቃነ ጳጳሳቱን እንዳስደመማቸው ተገልጧል - አንዳንዶች ግን አርምሞው በቀጣዩ አጀንዳ ላይ ተቀባይነት ለማግኘት የተደረገ ‹‹የሰጥቶ መቀበል መርሕ›› ነበር ይላሉ - እርሱም አልተሳካም እንጂ፡፡

በቀጣዩ አጀንዳ ምልዓተ ጉባኤው የተመለከተው በአጀንዳ ተራ ቁጥር ሦስት ላይ የተጠቀሰውን ‹‹ስለ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ችግር በቅዱስ ሲኖዶስ በተሠየሙት ሊቃነ ጳጳሳት ተጠንቶ የቀረበውን ጥናት›› የተመለከተ አጀንዳ ነበር፡፡ ጥናቱ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለአራት/ለአምስት የመከፋፈልን ጥቅም እና ጉዳት በአማራጭ ዕይታ ያጤነ ነበር፡፡ አሁን ባለው አስተዳደራዊ ሁኔታ ሀገረ ስብከቱን መከፋፈል ‹‹ለተንዛዛ አካሄድ እና ለሌላ ነገር በር ይከፍታል›› ያለው ጥናቱ ሀገረ ስብከቱ ቅዱስ ሲኖዶስ በሚሠይመው አንድ ሊቀ ጳጳስ እና ሊቀ ጳጳሱ አጭቶ በሚያቀርበው እና ቅዱስ ሲኖዶስ በሚያጸድቀው አንድ ሥራ አስኪያጅ እንዲመራ ሐሳብ አቅርቧል፡፡ ፓትርያርኩ ይህን ተከትለው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስን እርሳቸው መርጠው ለመሾም ያቀረቡት ሐሳብ ሥልጣኑ የሲኖዶሱ መሆኑን በጠቀሰው የብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ሌሎች ብፁዓን አባቶች ብርቱ ተቃውሞ ውድቅ ተደርጓል፡፡ ይሁንና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እና ምናልባትም በሐዋሳ እንደሚቀመጡ ተስፋ የተሰጣቸው የሚመስሉ በጥንካሬያቸው የተመሰገኑ አንዳንድ ብፁዓን አባቶች ፓትርያርኩን ከወቀሳ ነጻ ለማድረግ እና በፊታቸው ‹‹ሞገስ ለማግኘት›› በሚሰጧቸው ጥቅምን እና ጎጥን ማእከል ያደረጉ ከንቱ ምስክርነቶች ከፍተኛ ተግሣጽ አግኝቷቸዋል፡፡ ይህም ‹‹አቡነ ጳውሎስ ስለ ቤተ ክርስቲያኒቷ ልዕልና እና ህልውና መጠበቅ በሊቃነ ጳጳሳቱ ዘንድ የተያዘውን የአቋም አንድነት ለማላላት ምን ያህል እየሠሩ እንደሆነ ያሳያል ይላሉ›› ታዛቢዎች፡፡

ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል
ለአንድ ዓመት ያለሥራ መቀመጣቸውን እና በተደረገው ማጣራት ንጹሕ መሆናቸው መረጋገጡን የተናገሩት ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል በበኩላቸው ቅዱስ ሲኖዶስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ወደነበራቸው ኃላፊነት ይመለሱ ዘንድ እንዲፈቅድላቸው ጠይቀዋል፡፡ ለብፁዕነታቸው እና የሐዋሳ ሀገረ ስብከትን አጣሪ ልኡክ ሪፖርት በመጠበቅ ላይ የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶሱ በተራ ቁጥር አራት ላይ፣ ‹‹ሀገረ ስብከት ለሌላቸው እና ዝውውር ለጠየቁ ሊቃነ ጳጳሳት ተነጋግሮ መወሰን›› በሚለው አጀንዳ በነገው ዕለት እንደሚወስን የተገኘው ዘገባ ያስረዳል፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)