October 25, 2010

ሰበር ዜና፦ አባ ሰረቀ ብርሃን ደጀ ሰላምን እና ማ/ቅዱሳንን ሊከሱ ነው

(ደጀ ሰላም፤ ኦክቶበር 24/2010፤ ጥቅምት 14/2003 ዓ.ም):- የሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ዋና ኃላፊ ቆሞስ አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል “ደጀ ሰላም የተሰኘው ‘ድህረ ገጽ’ (ድረ ገጽ ለማለት መሆኑ ነው) … በማንነቴና በሃይማኖቴ ላይ ከባድ የግድያ ወንጀል” ስለፈፀመ “የሀገሪቱን ሕገ መንግሥት በመጠቀም ወደ ፍርድ ለማቅረብ ቅድመ ዝግጅቱ እየተጠናቀቀ” መሆኑን ሰሞኑን በጻፉት ደብዳቤ ገልጸዋል።
በጥቅምት 11/2003 ዓ.ም “ለቅዱስ ሲኖዶስ፣ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ፣ ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ለሚመለከታቸው የቤተክርስቲያን ሊቃውንት” የተጻፈውና በግልባጭ በደፈናው “የዚህ ኮፒ ለሚመለከተው ሁሉ ይድረስ” የተባለለት ይህ ደብዳቤ ማ/ቅዱሳን እንዴት ሲያሳድዳቸው እንደኖረ በአራት ነጥቦች ከዘረዘሩ በኋላ በ5ኛነት “ደጀ ሰላም በተባለው በአባላቱ የሚመራው ድህረ ገጽ የስም ማጥፋት ዘመቻ” እያደረገባቸው መሆኑን ጠቅሰዋል። ስም ማጥፋቱ ምን እንደሆነ ዘግየት ብለው ሲያብራሩም ከሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ ጋር የተጻጻፉት እና በጡመራ መድረኩ ላይ የወጣው ፀረ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የምሥጢር ግንኙነታቸው (CLICK HERE TO READ) መሆኑን አብራርተዋል።

አባ ሰረቀ ስለ ደጀ ሰላም ማንነት ሲገልፁም “ፓትርያርኩን ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን ከቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን ከመንግሥት፣ መንግስትም ከቤተ ክርስቲያን ለማጋጨት፣ ያልተደረገውን ተደረገ፣ ያልተባለውን ተባለ እያለ ራሱን በቤተ ክርስቲያኒቱ ታዛ ሥር ደብቆ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት እስከ ዋሽንግተን ዲሲ ሀገረ ስብከት መረቡን ዘርግቶ እየተንቀሳቀሰ” የሚገኘው “ደጀ ሰላም የተሰኘው ድህረ ገጽ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ያሳደረው ጫናና የፈጸመው በደል ቀላል አይደለም” ብለዋል።

ደጀ ሰላም “በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ያሳደረው ጫናና በደል ቀላል” አለመሆኑን ለማጠየቅ “በአውራምባ ታይምስ ላይ ከወጣ በኋላ አስተማሪነቱ ታምኖበት በጡመራ መድረካችን ላይ በድጋሚ ያወጣነውን፣ ነገር ግን በባሮክ ዘሣልሳይ ሺሕ የተዘጋጀውን “ቤተ ክህነቱ ያጣው የቤተ ክህነቱ ሰው” (Click HERE to Read) የሚለውን ጽሑፍ አባሪ አድርገው አቅርበዋል። ጽሑፉ የሚያስከስስ ከሆነ “አውራምባ ታይምስን”ም አብረው ይከሱት እንደሆነ ገና አልታወቀም።

አባ ሰረቀ በዚህ ወቅት ደብዳቤውን ለቅዱስ ፓትርያርኩ እና ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እንዲሁም በግልባጭ በደፈናው “የዚህ ኮፒ ለሚመለከተው ሁሉ ይድረስ” በማለት ያቀረቡት ቅዳሜ የተጀመረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ ላይ እንዲታይላቸው በመፈለግ፤ ለዚህም አስቀድመው የተወሰኑ ሊቃነ ጳጳሳትን በማናገር እና በማሳመን መሆኑን ምንጮቻችን ገለጸዋል። ከቅዱስ ፓትርያርኩ በተጨማሪ በገልባጭ ያሳወቋቸው እነማን መሆናቸው ባይዘረዘርም በከዚህ በፊት የደብዳቤ አጻጻፋቸው ምሳሌነት የሚኬድ ከሆነ ለመንግሥት የጸጥታ እና የደኅንነት አካላት ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል። “ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሠረት” እከሳለሁ ማለታቸውም ይህንኑ ሊጠቁም የገባ ሳይሆን እንደማይቀር ተገምቷል። ቆሞስ አባ ሰረቀ በዚህ የጥቅምት ወር 2003 ዓ.ም ማዕረገ ጵጵስና እንዲፈቀድላቸው “በአጭር ዝርዝር” ውስጥ (short list) ከገቡት በተለይም ብዙ ነቀፋ ካለባቸው እና ይህ ማዕረግ አይገባቸው ተብለው ከሚከሰሱት መካከል መሆናቸው ይታወቃል። ደጀ ሰላምም የኚህን እና ተመሳሳይ ግብር ያላቸው የሌሎች ጥቂት መነኮሳትን ወደ ጵጵስና መምጣት ለመቃወም ዝግጅት እያደረገች ነበር። አሁንም በዚሁ ትገፋበታለች። በደጀ ሰላም ሰበብ የክስ መዝገብ የተዘጋጀለት ማ/ቅዱሳን ስለጉዳዩ የሚያወጣው መግለጫ ካለ ወደፊት የሚታይ ይሆናል። ማኅበሩ ከዓመት አስቀድሞ “ደጀ ሰላም የእኔ አይደለችም” ሲል መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።

++++++++++++++++++
 ከዚህ በፊት ስለ አባ ሰረቀ ምን ተዘግቧል?

September 28, 2009


የሰሞኑ የዜና ርዕስ የሆኑት አባ ሰረቀ ማን ናቸው? በአሜሪካ ምን ምን ሲሰሩ ኖሩ?

(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 27/2009)፦
ሰሞኑን በማኀበረ ቅዱሳንና በጠቅላይ ቤተ ክህነት አንድ መምሪያ መካከል የተፈጠረው ውጥረት ፈንድቶ መውጣቱንና መንግሥትን ማሳተፉን ከሰማን ወዲህ ስማቸውን በጉልህ መስማት ከጀመርናቸው ሰዎች መካከል አንደኛውና ግንባር ቀደሙ ሰሜን አሜሪካ የነበሩትና በደንብ የምናውቃቸው “አባ ሰረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል” ናቸው። ስለዚህ ይህ ጽሑፍ ስለኚሁ ሰው የአሜሪካ ቆይታ እውነተኛ እማኝነት ይሰጣል። ቤተ ክርስቲያናችንን የሚመሯትና ነገ ጳጳስ ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁት እኚህ ሰው ምን ዓይነት ሰው እንደሆኑ ያብራራል።

አባ ሰረቀ የዛሬ 15 ዓመት አካባቢ ወደ አሜሪካ ሲመጡ ለመጀመሪያ ጊዜ የሄዱት ወደ ሎስ አንጀለስ ካሊፎርኒያ ነበር። በዚያም አባ ኃ/ሥላሴ ከተባሉ አባት ጋር የጻድቁን የአቡነ አረጋዊን ቤተ ክርስቲያን ማገልገል ጀምረው ነበር። ይሁን እንጂ አባ ሰረቀ ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ የሄዱበት አካባቢ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትን ሰላም በማወክና በመበጥበጥ የታወቁ እንደመሆናቸው አቡነ አረጋዊንም ወዲያውኑ መበጥበጥ ጀመሩ። የአቡነ አረጋዊ ቤተ ክርስቲያንን ቦርድ በመቅረብ “መቀደስና ማገልገል የምፈልገው በትግርኛ ቋንቋ ብቻ ነው” ማለት ጀመሩ። በዚህም የዘወትር አገልግሎት የሚሰጥባቸውን ግዕዝንና አማርኛን ዜሮ አደረጓቸው። ቦርዱን በመጠምዘዝና በማሳመን በትግርኛ ብቻ እንዲቀደስ ለማድረግም ችለው ነበር።

በዚህ መልክ ከ6-8 ወራት ከቆዩ በኋላ በቦርዱ አባላት መካከል እንደገና ጥርጥር፣ አለመግባባትና ልዩነት በመፍጠር ለመክፈል ሞከሩ። ወደ ትግርኛ የቀየሩት ቅዳሴ አላዋጣ ሲላቸው ወይም “ስልታዊ ለውጥ” ማድረግ ሲፈልጉ እንደገና “ወደ አማርኛና ግዕዝ” መመለስ ፈለጉ። በዚህ ጊዜ ቦርዱ እምቢ አለ። “ለምን መጀመሪያ ወደ ትግርኛ ወሰዱን ለምን ይመልሱናል? እኛ የእርስዎ መጫወቻ አይደለንም። ደግሞ የቤተ ክርስቲያናችን አባላት ለምደውታል” ብለው እምቢ አሉ።

አባ ሰረቀ ይህ አልሳካላቸው ሲል ዲሲ አካባቢ ከሚገኘው የመድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ተጋጭተው የወጡ የትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎችን በማስተባበር “ቤተ ክርስቲያን ለመክፈት” ተስማሙ። ይህ ከመድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን የወጣው ቡድን ያን ጊዜ የአሜሪካ ሀ/ስብከት አሁን የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ የሆኑትን ብፁዕ አቡነ ማትያስን በማነጋገር “በትግርኛ ብቻ አገልግሎት የሚሰጥበት ቤተ ክርስቲያን ለመክፈት” ሞክረው ሳይሳካላቸው የቀሩ እንደነበሩ ጉዳዩን የሚያውቁ ሰዎች ይናገራሉ። እናም በሎስ አንጀለስ አቡረ አረጋዊ ያልተሳካላቸው አባ ሰረቀ ቨርጂኒያ ሌላ የአቡነ አረጋዊ ቤተ ክርስቲያን “ከፈቱ”። የሎስ አንጀለስ ምዕመናንን ያሳሳቱት ሳይበቃ የቨርጂኒያዎችንም አጭበርብረው በዘረኛ መንፈሳቸው የዋኃኑን አጠመዷቸው። ትናንትና አባ ሰረቀ “የከፈቱት አቡነ አረጋዊ ቤተ ክርስቲያን” ዛሬ ደግሞ አባ ኃ/ሚካኤልን የመሰሉ መናፍቅ መነኩሴ አቅፎ ይዟል። (አስተዳዳሪው ቀሲስ ተከስተ የተባሉ ወጣት ቄስ ናቸው)። አባ ኃ/ሚካኤል ከአባ ሰረቀ ሚሽን ተቀብለው ወደ አሜሪካ የመጡ መሆናቸው በስፋት ይነገራል፤ ይታወቃልም።

አባ ሰረቀ ወደ ቨርጂኒያ እንደመጡ የሀገረ ስብከቱን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማትያስን በመቃወም ማስተማር ጀመሩ። ብፁዕ አቡነ ማትያስን ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው ጵጵስናንና ፕትርክናን በመቃወም “ጳጳስም፣ ፓትርያርክም አያስፈልግም” እያሉ ዐውደ ምሕረቱን ከያዙ ጀምሮ በትግርኛ ብቻ በመቀደስና ማስተማር ክፍፍልን መዝራት ጀመሩ። “ጳጳስ አያስፈልግም አዲስ ቤተ ክርስቲያን ለመክፈት ከሆነ እኔ ራሴ ‘መባረክ’ና መክፈት እችላለሁ” ማለት ጀመሩ። በዚህ የተጀመረው ልዩነት ሰፍቶ አቡነ አረጋዊን ራሱን ለሁለት ለመከፈል አበቁት።

ከዚያም የቤተ ክርስቲያኑን ስምና ንብረት በመውሰድ ጥለው ወደ አሌክሳንደሪያ (ቨርጂኒያ) ሄዱ። በዚያው ስም አቡነ አረጋዊ ብለው በመሰየም “አዲስ ቤተ ክርስቲያን ከፈቱ”። በአባ ሰረቀ ጎትጓችነት ተታለው ከመድኃኔዓለም ወጥተው የነበሩትም ምእመናን ልዩነታቸው በማቻቻል ከቀደመው ቤተ ክርስቲያናቸው ጋር ታረቁ። ይሁን እንጂ አባ ሰረቀ ንብረታቸውን በሙሉ ዘርፈው እንደወጡ እንዲቀሩ አልፈቀዱላቸውም። የሕግ ዕውቀት ያላቸው ሰው በማነጋገርና ርዳታ በማግኘት አባ ሰረቀን ሕግ ፊት አቆሟቸው። አባ ሰረቀም የወሰዱትን ሀብትና ስም በሙሉ በግድ ለመመለስ ተገደዱ። በሕግ ፊት የተዋረዱት አባ ሰረቀም አቡነ አረጋዊን አስረክበው ሲያበቁ በቅ/ጊዮርጊስ ስም “አዲስ ቤተ ክርስቲያን በቨርጂኒያ ከፈቱ”። ይህ ቤተ ክርስቲያን ዛሬም በቨርጂኒያ እንደሚገኝ ይታወቃል።

አባ ሰረቀ በዚህ መልክ ቤተ ክርስቲያንን ሲከፋፍሉና ሲያዋርዱ ቆይተው ጊዜ እየተቀየረ ሲሄድ “ጳጳስ የመሆን ሌላ ጾር ሲነሣባቸው” በፊት “አያስፈልግም” ሲሉት የነበረውን “ጵጵስና፣ ፕትርክና እና ቅዱስ ሲኖዶስ” ሸውደው “እጅ ሰጥተው” የአቡነ ጳውሎስ ጋሻ ጃግሬ ሆነው ወደ ኢትዮጵያ ገቡ። አባ ሰረቀ የዲሲና አካባቢው ማህበረ ካህናት ጉባዔ አባል በነበሩባቸው ዘመናት ሁሉ እያጥላሉ ሲሳደቡ የነበሩትን ፓትርያርክ “ካለ እርስዎ ሰው የለም፣ ቅዱስ የለም” ብለው ጫማ ስመው የመምሪያ ኃላፊነት ሽልማት ተሰጣቸው። ይሁን እንጂ ሲጓጉለት የነበረው ጵጰስና ሳይሳካላቸው ቀረ። የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የሆኑ ብፁዓን አባቶች “እንዲህ ዓይነቱን ወንበዴ፣ ቤተ ክርስቲያንን ሲያሰቃይ የኖረ ሰው እንዴት ጵጵስና እንሾመዋለን” በማለታቸው ሳይሳካ ቆይቶ ነበር። ውስጥ አዋቂዎች እንደሚናገሩት ከሆነ በመጪው ጥቅምት በሚደረገው የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ ጵጵስና እንዲሾሙ ይቀርባሉ ከሚባሉት አባቶች መካከል አንደኛው እኚሁ ዘረኛ መነኩሴ አባ ሰረቀ ብርሃን እንደሚሆኑ ታውቋል።

አይ ዘመን፤ የሚገርመው እኚህኑ አባ ሰረቀን ዛሬ እሑድ በተላለፈው የሀገር ፍቅር ሬዲዮ ላይ ድምጻቸውን ሰማነው። ያውም የቤተ ክርስቲያን “ጠበቃና ተቆርቋሪ” ሆነው። አይ ቤተ ክርስቲያን!!! መከራሽ አያልቅ!!!
ቸር ወሬ ያሰማን
(http://www.addisadmass.com/news/news_item.asp?NewsID=1462)
++++++++++++

November 3, 2009


ቤተ ክህነት “ደጀ ሰላም”ን ወነጀለ

(ደጀ ሰላም፤ ኖቬምበር 3/2009)፦
“ደጀ ሰላም” የጡመራ መድረክን የጠቀሰ የክስ ዶኩመንት ሰሞኑን ከቤተ ክህነት ይፋ ሆነ። በሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ እና በማህበረ ቅዱሳን መካከል በተነሣው ውዝግብ ደጀ ሰላምን በማስረጃነት የጠቀሱት የመምሪያው ሃላፊዎች መሆናቸውን ዶኩመንቱ (PDF) ገልጿል። ደጀ ሰላም ጁላይ 9/2009 ያወጣችውን የሚከተለውን ዜና በማስረጃነት በመጥቀስ በቅዱስ ፓትርያርኩና በመንግሥት ባለሥልጣናት ፊት የከሰሰሱት የቤተ ክህነት ባለሥልጣናት ደጀ ሰላምን “የማህበረ ቅዱሳን” መሆኗን ጠቅሰዋል።
ደጀ ሰላም በወቅቱ ያወጣችው ዜና ከዚህ በታች ተያይዞ ቀርቧል።

(ደጀ ሰላም፤ ጁላይ 9/2009)
• “ከዚህ በሁዋላ ከፓትርያርኩ ጋር አብረን አንሠራም” ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ፤ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ
• “ሀገረ ስብከቴን ተረከቡኝ” ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል፣
• ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ፣ ያልተጠበቁ የፓትርያርኩ ደጋፊ፣
• ፓትርያርኩ “ተቃዋሚዎቻቸውን ይበቀላሉ” ይባላል፣
• አቡነ ሳሙኤልን ስላገቱት ሰዎች ፌዴራል ፖሊስም አያውቅም፣

ቅዱስ ሲኖዶሱ ያረቀቀውን ቃለ ጉባዔ ሳያጸድቅ፣ የጀመረውን አጀንዳ ሰይቋጭ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን ሜዳ ላይ ጥሎ ወደ ቤቱ ገብቷል። ከስምምነት ላይ የተደረሰበት ውሳኔ በፊርማ እንዳይጸድቅ ብፁዓን አበው እስጢፋኖስ፣ ኤጲፋንዮስና ጎርጎርዮስ የሞት ሽረት ትግል አድርገው፣ አባቶችን በጥብጠው ውሳኔው እንዲከሽፍ አድርገዋል። በተለይም በምዕራብ ኢትዮጵያ በጀመሩት መልካም አገልግሎት በሕዝቡ እየተመሰገኑ የነበሩት ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ይህንን ገዳይ አቋም እንዴት ሊይዙ እንደበቁ እንቆቅልሽ ሆኗል። ገሚሱ በገንዘብ ተገዝተው ነው ሲል ሌላው ደግሞ ውስጠ ዘ በሆነ ማስፈራሪያ ሊሆን ይችላል እያለ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ወደ አሸናፊነቱ እየመጡ ያሉት ፓትርያርኩ የበቀል በትራቸውን እንደሚመዙ እየተጠበቀ ነው። የመጀመሪያ ተጠቂዎች የሚሆኑት በአዲስ አበባ የሚገኙ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ሲሆኑ ባለፈው ሳምንት በብፁዕ አቡነ ሳሙኤል መሪነት ስብሰባ ካደረጉ በሁዋላ የፓትርያርኩን ድርጊት የሚቃወም መግለጫ ማውጣታቸው ይታወሳል። ከዚህም ባሻገር ይህንን ሁሉ ሕዝብ ያስተባብርብኛል ያሉት ማህበረ ቅዱሳንም ላይ ጥርሳቸውን ነክሰዋል ተብሏል።
የቤተ ክህነቱ ድራማ ዛሬ ሲተወን ጠዋት በማለዳው ስብሰባ እንዳይገቡ የታገቱት ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ለምን እንደታገቱ ፌዴራል ፖሊስ ራሱ አያውቅም። የደህንነት ክፍሉ ደግሞ ለደህንነታቸው ብዬ ነው ብሏል። ድራማው ሊቀ ጳጳሱን ከስብሰባው በማስቀረት ውሳኔውን ማክሸፍ ከሆነ በርግጥም ዘዴው ሰርቷል ማለት ይቻላል።መንግሥት በበኩሉ ጉዳዩን እያጠናው እንደሆነ ውስጥ አዋቂዎች ገልጸዋል።

በተያያዘ ዜና ፓትርያርኩ የተነሣባቸውን ተቃውሞ ለመስበርና አባቶችን አንገት ለማስደፋት የሚሆን ገንዘብ ራሳቸው በግላቸው ከሚያዙበት ከቁልቢ ገብርኤል ካዝና ወጪ መደረጉ ታውቋል። የብሩ መጠን ለጊዜው ባይታወቅም ገንዘቡ ለአንዳንድ የፖሊስ ሃላፊዎች፣ ደህንነቶችና ጉልበት ላላቸው ሰዎች መበተኑ ሲታወቅ መንግሥት በውስጡ ሌላ መንግሥት ያለበት አስመስሎታል። እስከ ዛሬም በመንግሥት ስም ቤተ ክርስቲያኒቱን እግርተወርች አስረው ሲበሏት፣ ሲግጧትና ሲያዋርዷት የነበሩ ሰዎች የፓትርያርኩ ዘመዶችና ወዳጆች ብቻ ሳይሆኑ በመንግሥት ሥልጣን ላይ የተንፈራጠጡ ሰዎችም መሆናቸው እየተገለጸ መጥቷል። መንግሥት ጉዳዩን አጣርቶ ሕገ ወጦቹ እጃቸውን ከቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እንዲያነሱ ያደርጋል ተብሎ ይገመታል።

ነገሩ በዚህ ከቀጠለ ቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ አላት ለማለት እንደማያስደፍር አንድ ሊቀ ጳጳስ ተናግረዋል። ከዋሺንግተን ዲሲ ተጠርተው የተሾሙት የሲዳሞ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስና የሥራ አስፈጻሚው አባል ብፁዕ አቡነ ፋኑኤልም በበኩላቸው “ሀ/ስብከቴን ተረከቡኝ” ማለታቸው ተሰምቷል። በርግጥም ሊቀ ጳጳሱ እንዲህ ካደረጉ ጳጳሳት የሥራ መልቀቂያ የሚያስገቡበት፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ሳይሆን በፓትርያርክና በሴት ወይዘሮዎች ብቻ የሚመራ ቤተ ክህነት ይፈጠራል ማለት ነው።
አንድ አስተያየት ሰጪ እንደተናገሩት የፊታችን ሰኞ ስብሰባ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ስብሰባው የተጠራው በቅዱስ ፓትርያርኩ ከመሆኑ አንጻር ምንም ተለየ ነገር አይጠበቅም። ቅዱስነታቸው የፊታችን እሑድ በዓለ ሲመታቸውን እንደሚያከብሩ ይታወቃል።
ለማንኛውም ደጀ ሰላም በበኩሏ “ተስፋ አንቁረጥ፣ እግዚአብሔር ሥራው ድንቅ ነውና” ትላለች።
ቸር ወሬ ያሰማን፣

አሜን
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)