October 13, 2010

መንግሥትን “አበጀህ፣ ጎበዝ” እንበለው ወይስ ገና ነው?

(ደጀ ሰላም፤ ኦክቶበር 12/2010፤ ጥቅምት 2/2003 ዓ.ም):- በዋነኝነት በመንግሥት ሐሳብ አመንጪነት እና አስተግባሪነት ተካሂዷል በተባለ የቤተ ክህነት አዲስ ሹመት እና ማስተካከያ በቤተ ክህነቱ ውስጥ ያለው ሕገወጥነት እና ብልሹነት ሊስተካል የሚችልበት አግባብ እንዲፈለግ አዳዲስ ሰዎች ወደ አስተዳደሩ ብቅብቅ ብለዋል። በሪፖርታዣችን እንደጠቀስነውም ተሹዋሚዎቹ ሙያዊ ብቃት ያላቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገመታል። በሌላ በኩል ደግም በብዙ አስተያየት ሰጪዎች አስተያየት ሹመት እና ማስተካከያው በ1966ቱ አብዮት የቤተ ክርስቲያን እና መንግሥት ግንኙነት መልኩን ከለወጠ በኋላ ደርግ ቤተ ክህነቱን በድርጅታዊ አሠራር በመቆጣጠር ፓትርያርክ እስከ ማስመረጥ የደረሰበትን እና እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ ‹‹ጥቁር ራስ›› ሥራ አስኪያጅ ይሾም የነበረበትን ዘመን አስታውሷቸዋል፡፡ ደርግ ‹‹በእግዚአብሔር ፈቃድ፣ በሕዝቡ ኀዘን፣ በሰራዊቱ ብርታት እና በተማሪው ጩኸት መጥቷል›› ባለው አብዮት ስም ፓትርያርክ አቡነ ቴዎፍሎስን አስሮ በግፍ ከመግደል ጀምሮ በኢኮኖሚ ይሁን በሞራል ከፍተኛውን ጉዳት ያደረሰው በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ነበር፡፡

በርግጥ ከ1966ቱ አብዮትም በፊት ቤተ ክርስቲያን እና መንግሥት ስማዊ በሆነው የ‹‹ሲሶ ለቀዳሽ›› የመሬት ፖሊሲ ተዘምደው ቤተ ክርስቲያን በንጉሡ እና በመንግሥት ሞግዚትነት ሥር ቅብዐ መንግሥት እየፈጸመች ቅቡልነትን እና ሕጋዊነትን ስታሰጥ ኖራለች፡፡ ቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ የመንግሥት እና ቤተ ክርስቲያንን ግንኙነት የመጨረሻው ጫፍ ላይ በማድረስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅና ያላት የመንግሥት ቤተ ክርስቲያን (Established Church) እንድትሆን አድርገዋታል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የመንግሥት ጥገኛ በመሆኗ በየዓመቱ ከመንግሥት የ1.9 ሚልዮን ብር በጀት ይመደብላት እንደነበርና የጳጳሳት ደመ ወዝ ሳይቀር ከመንግሥት ግምጃ ቤት እየወጣ ይከፈል ነበር፡፡ ኦይቪንድ ኤዲ የተባሉ ጸሐፊ ‹‹Revolution and Religion in Ethiopia›› በሚለው መጽሐፋቸው እንደሚገልጹት፣ የቤተ ክርስቲያኒቷ መሪዎች በመንግሥት እና ቤተ ክርስቲያን ‹ፍጹማዊ ጋብቻ› እንደሚያምኑበት ቢጽፉም፣ ቤተ ክርስቲያን በንጽጽር ካልተመዘነ በቀር የሚባለውን ያህል ተጠቃሚ እንዳልነበረች እንዲያውም ንጉሠ ነገሥቱ ‹‹ለዘመናዊነት›› በሰጡት ትኩረት በተለይም በዳር አገር ለፕሮቴስታንት አብያተ እምነት መስፋፋት በር በመክፈታቸው የሚተቿቸው ጸሐፊዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡

ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት በ1987 ዓ.ም ባጸደቀው ሕገ መንግሥት የሃይማኖት ነጻነትን ብቻ ሳይሆን መንግሥት እና ሃይማኖት የተለያዩ መሆናቸውን ደንግጓል፤ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ፣ ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ ዐውጇል፡፡ ድንጋጌው ሰፊ ትርጉም የሚሰጥ በመሆኑ በተግባር ምን ማለት እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ግልጽ እና ተመሳሳይ ግንዛቤ የለም፡፡ እንዲህም ስለሆነ ኢሕአዴግ የሃይማኖት ተቋማትን በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አመራር መቆጣጠር እንዳለበት አልዘነጋም፡፡ ይህም ‹‹በደርግ ይሁንታ ተመርጠዋል፤ ደርግንም ይደግፋሉ›› የሚባሉትን ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስን ከሥልጣን በማውረድ፣ ‹‹የኢሕአዴግን ከፍተኛ አመራሮች ልጆቻችን›/ልጄ›› በማለት የሚታሙትን እንደ ምርጫ - 97 በመሳሰሉት ወርቃማ አጋጣሚዎች የቁርጥ ቀን ወዳጅነታቸውን ያረጋገጡትን ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስን በማሾሙ ጉልሕ ሆኖ ይታያል፤ በአናቱም ለቤተ ክርስቲያኒቷ ደርግ የወረሰባት ሕንጻዎቿ እና ንብረቶቿ እየተመለሱላት ቢሆንም ኢሕአዴግ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሪነት መሠረት ይዞ የቆየውን የጥንታዊቷን ኢትዮጵያን ማንነት በመናድ ‹‹አዲሲቷን ኢትዮጵያን›› በአዲስ ርእዮተ ዓለም ለመገንባት ከጅምሩ ዐውጆ ተነሣ፡፡

ይህን አቋሙን መነሻ በማድረግ እንደ አቶ ተፈራ ዋልዋ (picture) ባሉት ቱባ የሥርዐቱ ሹማምንት የቤተ ክርስቲያኒቱ ነዋሪ ሚና በሚያንኳስስ አኳኋን ‹‹በታሪክ በርካታ ስሕተት የፈጸመች ነፍጠኛ፣ ዐፄያዊ እና ደርጋዊ›› በማለት ተፈረጀች፡፡ የአዲሱ ርእዮተ ዓለም እና አገራዊ አወቃቀር ሌላው ገጽታ በሆነው ‹‹የብሔር ብሔረሰቦች በነጻነት መደራጀት፣ ለቋንቋቸው እና ባህላቸው ልዩ ትኩረት መሰጠት›› ሳቢያ ቤተ ክርስቲያኒቱ አሐቲነቷ ተዘንግቶ፣ ምእመኖቿ ተከፋፍለው በሀገር ውስጥ እና በተለይም በባሕር ማዶ የጎሳ እና የፖሊቲካ ቡድኖች እዚህም እዚያም ባለዐምባ ራስ ሆነው ለጥቅማቸው የሚነዳደፉባት የፍልሚያ ጎራ ሆነች፡፡ ‹‹በእናት ቤተ ክርስቲያን ሥር ነን›› እያሉ፣ የፓትርያሪኩን ስም እየጠሩ ከአብያተ ክርስቲያኑ የሚያገኙትን ገቢ በግል አካውንታቸው እያስገቡ በሁለት ቢላዎ የሚበሉ ወንበዴ እና መናፍቅ ‹ቆሞሳት›፣ መኪና በሞዴል አማርጦ ከመግዛት፣ G+1  እና G+2 ሕንጻዎችን ከመሥራት በቀር ሕልም በሌላቸው ሃይማኖታቸው በተከለሰ፣ ምግባራቸው ባጸጸ ጳጳሳት ተሞላች፡፡

ፕሮፌሰር መድኀኔ ታደሰ ‹‹መርሕ ያልተበጀለት የነጻነት ንቅናቄ›› (unregulated freedom of religious activism) ብለው በሚጠሩት የሃይማኖት እና መንግሥት ግንኙነት የሚመራበት ከምዕራባዊ ተጽዕኖ የተላቀቀ፣ ቁጥጥር የሚደረግበት አገር በቀል ሞዴል እና ዝርዝር ስትራተጂ ባለመኖሩ ቤተ ክርስቲያኒቷ ከውስጥ ሀብቷን እና መንጋዋን የሚቦረቡሩትን በማጋለጥ፣ ከውጭ አፋቸውን ለሚያላቅቁባት አጽራረ ቤተ ክርስቲያን መልስ በመስጠት በአጠቃላይ በመከላከል አገልግሎት ተጠመደች፡፡ ኢሕአዴግ በፖሊሲ ደረጃ ሁሉንም እምነቶች በእኩልነት እንደሚመለከት በዓለም አቀፍ ሪፖርቶች ሳይቀር የተመሰከረለት ቢሆንም በአፈጻጸም/አተገባበር ረገድ ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን የሚያስተናግድበት መንገድ ግን ችግር እንዳለበት ብዙዎች ይስማማሉ - አስፈጻሚ ሹማምንት ሁሉንም እኩል አያገለግሉም [የባሌ ሀገረ ስብከት በጊኒር ወረዳ ሰዌና ኪዳነ ምሕረት ሕዝበ ክርስቲያን ላይ ስለደረሰው ችግር ለባሌ ዞን አስተዳደር ጽ/ቤት በ13/1/03 በጻፈው ደብዳቤ የክርስቲያኖችን ማዕተብ እየበጠሱ የሚደበድቡ፣ ካህናቱን እናጠፋለን እያሉ የሚዝቱ ዋልጌ ሙስሊሞችን ለማረጋጋት የሞከሩ ክርስቲያን ፖሊሶች ጥቃት ደርሶባቸዋል፤ የአስተዳደር አካላቱም እየሰሙ እንዳልሰሙ ሆነዋል] ፓርቲው የሃይማኖት መሪዎችን ይጫናል፤ ፖሊሲዎች እና ሕጎች ሲዘጋጁ የሃይማኖት ተቋማቱ ድምፅ አይደመጥም፤ ባለሥልጣናቱ ፀረ ሃይማኖት የሆነ ንግግር ያደርጋሉ፤ ከቱሪዝም ሀብታቸው ተገቢውን ጥቅም እያገኙ አይደሉም፤. . . ፡፡

በአንዳንድ ባለሞያዎች ዕይታ ከምርጫ - 97 ንዝረት በኋላ ኢሕአዴግ የሃይማኖት ተቋማትን የሚይዝበት መንገድ ተቀይሯል፡፡ እስከ ምርጫ - 97 ድረስ የሃይማኖት ተቋማቱን አመራር በመያዝ ተወስኖ የነበረው ኢሕአዴግ ከዚያ በኋላ እስከ ታችኛው መዋቅራቸው ድረስ ዘልቆ መመልከት እና መያዝ እንዳለበት ያመነበት ይመስላል፡፡

ኢትዮጵያ በርካታ እምነቶች የሚገኙባት አገር ብትሆንም የሃይማኖት ጉዳዮችን በወጉ የሚከታተል መንግሥታዊ አካል አልነበራትም፡፡ ሃይማኖት ነክ ግጭቶች መነሣት ከጀመሩ በኋላ ግን በተለያዩ እምነት መሪዎች መካከል እና በእምነቶቹ ተቋማት ውስጥ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋራ ተከታታይ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት የሚታወቀው በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የሃይማኖቶች እና እምነቶች ዳይሬክቶሬትም ነገሩን በቅጡ መከታተል የጀመረው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመሆኑ ገና ብዙ ተግባራትን (ይህኛው ስጋት ነው፤ ያኛው ለዘብተኛ ነው ከሚለው ፍረጃው ተላቆ) ማከናወን ይጠበቅበታል፡፡

የቤተ ክርስቲያንን እና መንግሥትን ግንኙነት የሚያጠኑ ምሁራን እንደሚናገሩት ኢሕአዴግ የሃይማኖት ነጻነትን በሕገ መንግሥት ደረጃ በማረጋገጥ ሰፊ ሥራ ቢያከናውንም በአደባባይ እንደሚለፈፈው ሃይማኖት እና መንግሥት ተለያይተው የሚታዩ አይደሉም፡፡ እንዲያውም ‹‹የኢሕአዴግን/መንግሥትን እጅ ቤተ መቅደስ ውስጥ ማየት ይቻላል›› የሚሉ አሉ፡፡ የመስኩ ምሁራን እንደሚሉት እምነቶች የተከታዮቻቸውን ንፅረተ ዓለም፣ ግለሰባዊ እና ቡድናዊ ፖሊቲካዊ አመለካከቶች እና አቋሞች በመቅረጽ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው፡፡ ተቋማቱ የሚደግፉት ዕሴት እና ለተከታዮቻቸው የሚሰጡት ማኅበራዊ አገልግሎት በመንግሥት ፖሊሲዎች እንዲንጸባረቁ ከሚኖራቸው ፍላጎት በመነሣት ከፖሊቲካ ፈጽሞ ነጻ ሆነው መቆም አይቻላቸውም፡፡ በአንጻሩ መንግሥት እና አስተዳደሩ የዜጎቹን አመለካከት መቅረጽ፣ በፖሊሲዎቹ እና በዕቅድ አፈጻጸሞቹ ድጋፋቸውን ማግኘት. . .ወዘተ ይፈልጋል፡፡ በሃይማኖት ነጻነት ሽፋን አገራዊ ሕጎች እንዳይጣሱ የመቆጣጠር ሐላፊነትም አለበት፡፡ ስለዚህም በአንድ ይሁን በሌላ መንገድ መንግሥት እንደ አካል፣ መሪዎቹም እንደ ግለሰብ ከሃይማኖት ተጽዕኖ ነጻ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ የሌሎች አገሮች ተሞክሮ እንደሚያሳየው የመንግሥት እና የሃይማኖት በተግባር መለያየት በዐዋጅ እና በአንድ ጊዜ ሳይሆን ደረጃ በደረጃ በመጠን እና በጉዳይ እየቀነሰ በመሄድ የሚፈጸም ነው፡፡ እስከዚያው ድረስ ለመንግሥት፣ ለቤተ ክርስቲያን እና ለሕዝቡ ታላቅ ጠቀሜታ የሚኖረው በአሁኑ ወቅት ምእመኑ በመንፈሳዊ አባቶቹ እና በራሱ ላይ እምነት እንዲያጣ እያደረገው ያለው የሞራል ድቀት ተወግዶ በማንነቱ የሚተማመን፣ የመንፈስ ልዕልና ያለው ሆኖ እንዲጠናከር መሥራት ላይ ነው፡፡

ሰሞኑን መንግሥት ከቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ጋራ ለመምከር በዘረጋቸው -ወጋዊ መድረኮች ለአምስት ዓመቱ የዕድገት እና መዋቅራዊ ለውጥ ዕቅድ ተፈጻሚነት የቤተ ክርስቲያኒቱን ሚና አስፈላጊነት ያጠይቃል፡፡ በሰነዱ ውስጥ በማኅበራዊ ልማት መስክ፣ በፍትሕ እና በመልካም አስተዳደር መስፈን፣ በእምነቶች መካከል መከባበርን በማጎልበት በቱሪዝም መጠናከር እና መስፋፋት፣ በሥነ ሕዝብ ልማት ቤተ ክርስቲያን ተጨባጭ አስተዋፅኦ ልታበረክት እንደምትችል ይታመናል፡፡ ይሁንና ከዚህ ሁሉ በፊት በቤተ ክህነቱ ላዕላይ እና ታህታይ መዋቅሮች ተገቢ የአስተሳሰብ እና የአሠራር ለውጥ በአፋጣኝ ሊመጣ ግድ ነው፡፡

በዋናነት ከመንግሥት በተደረገው ግፊት ተመልምለው በዛሬው ዕለት ከቀትር በኋላ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሠራተኞች ጋራ ትውውቅ የሚያደርጉት ባለሞያዎች ለእውነተኛ ለውጥ ሊሠሩ ከሆነ እሾህ እና ጋሬጣ በበዛበት ሰበካ መቆማቸውን እና በአንገብጋቢ ጊዜ መምጣታቸውን ይረዳሉ ተብሎ ይታመናል፡፡ ወቅቱ በፍርድ ቤት ከሚታዩት ጉዳዮች መካከል ከመሬት ይዞታ ክርክር ቀጥሎ ቤተ ክርስቲያንን የተመለከቱ የከሳሽ እና ተከሳሽ መዝገቦች ከመብዛታቸው የተነሣ መንግሥት ለቤተ ክህነቱ ብቻ ራሱን የቻለ ችሎት ለመክፈት የተገደደበት ነው፡፡ ጊዜው በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሌላው ቀርቶ ዓመታዊ ዕቅድ እና በጀት ማዘጋጀት የሚባል ነገር የማይታወቅበት ነው፡፡ እንዲህ ለሚሉት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሠራተኞች፣ ‹‹ለነገ አትበሉ፤ ለነገ ክፋቱ ይበቃዋልና›› የሚለው ‹ገበሬ አስደንግጥ› ጥቅስ የሚጠቀስበት ተቋም ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ ለገቢ እና ወጪ ሒሳቦች የበጀት ርእስ የሌለበት፣ ይህ ነው የሚባል ተግባር የሌለው የአንድ መምሪያ ሐላፊ ብቻ ለተቋሙ ሥራ በተሰጠው የቢሮ ስልክ እስከ 18‚000 ብር የሚከፈልበት፣ ስልኩም ለዘመድ አዝማዶቹ እንደ ቴሌ ሴንተር የሚያገለግልበት ሁኔታ ይታያል፡፡

በቀጥተኛ የፓትርያሪኩ ትእዛዝ የሚንቀሳቀሱ ሐላፊዎች ባሉባቸው በተለይ በትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት በአየር ባየር የኅትመት ውጤቶች ሽያጭ፣ በቊልቢ ንዋያተ ቅድሳት ማደራጃ በጥሬ ብር እና በስእለት የሚገቡ መባዎች(ባለፈው ዓመት ሐምሌ ክብረ በዓል በዐይነት የተሰጠው ስእለት ሳይቆጠር በጥሬ ገንዘብ 24 ሚልዮን ብር ገቢ አስገኝቷል) እና በኪራይ ቤቶች አስተዳደር መምሪያ በኪራይ የሚገኙ ገቢዎች ለቁጥጥር በሚያስቸግር አኳኋን በተከፈቱ በርካታ የባንክ አካውንቶች ያለጠያቂ እየተመዘበሩ ይገኛሉ፡፡ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቅራቢነት እና በፓትርያሪኩ ይሁንታ ጉቦ እየሰጡ የሚሾሙ ከፍተኛ ገቢ ያላቸው አድባራት እና ገዳማት አስተዳዳሪዎች በየጊዜው ለመንበረ ፓትርያሪኩ እጅ መንሻ ያቀርባሉ፤ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የሚወስዷቸውን ሞዴላሞዴሎች(ሞዴል 30 - የገንዘብ ገቢ፣ ሞዴል 64 - የገቢ ማጠቃለያ፣ ሞዴል 6 - የገንዘብ ወጪ፣ ሞዴል 19 - የተገዛ ንብረት ማስገቢያ፣ ሞዴል 20 - የንብረት ግዥ መጠየቂያ፣ ሞዴል 22 - የተገዛ ንብረት ማውጫ) በፎርጅድ አስመስሎ በመሥራት ከፍተኛ ገቢዎችን በሐሰተኛው ሰነድ እየተቀበሉ ለአጥቢያው ጭፍጫፊውን ገቢ በሕጋዊ ሰነድ የሚያሳዩበት ድፍረት እንግዳ አይደለም - ሙዳየ ምጽዋትን በመገልበጥ፣ የቃለ ጉባኤ ሰነድን በማጥፋት የሚዘረፈውማ ምኑ ይነገራል!!

የአስተዳደር እና አቅም ግንባታ መምሪያውም ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ 18 መምሪያዎች ምን ያህሎቹ ከቤተ ዘመድ ሹመኞች እና ሌላው ቀርቶ በመጠኑ የሚቀራረብ ሞያዊ ልምድ ያላቸው ሐላፊዎች ትርጉም ባለው ደረጃ እንደሌሉበት ሊያስተውለው ይገባል፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት ተጀምሮ የነበረውን በየመምሪያው ረጅም ዓመት ካስቆጠሩት ሠራተኞች ጎን ለጎን ተተኪ የሰው ኀይል በመቅጠር በሂደት አግባብነት ባላቸው ባለሞያዎች ተቋሙን የማጠናከር ጅምር በትኩረት ሊያየው ያስፈልጋል፡፡

ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)