October 10, 2010

አቡነ ፋኑኤል እና ሥራ አስኪያጁ ከሐላፊነታቸው እንዲነሡ የሚጠይቀው የሐዋሳ ምእመናን አቤቱታ ለፓትርያርኩ ቀረበ(ደጀ ሰላም፤ ኦክቶበር 10/2010፤ መስከረም 30/2003 ዓ.ም):- መስከረም 25 ቀን 2003 ዓ.ም ማለዳ፤ የቤተ ክርስቲያናቸው መደፈር ያቃጠላቸውን፣ የመብታቸው መረገጥ የሚገዳቸውን የሐዋሳ ከተማ ምእመናን እንዲሁም የፍትሕ እና ልማት ኮሚቴ አባላት የያዙት አምስት የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች ማልደው ወደ አዲስ አበባ የጀመሩትን ግስጋሴ እንደ ቀጠሉ ናቸው፡፡ የሀገረ ስብከታቸው ሊቀ ጳጳስ አባ ፋኑኤል ከሥራ አስኪያጁ መልአከ ሕይወት ፀሐይ መልአኩ፣ በቅርቡ ለሀገረ ስብከቱ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ በጸሐፊነት ከተቀጠረው ላእከ ወንጌል ያሬድ አደመ እና በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ተሰግስገው ጥቅማቸውን ከሚከላከሉላቸው ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ ጋራ እየፈጸሙ ለሚገኙት ምእመኑን የሚከፋፍል እና የሚያበጣብጥ ተግባር እልባት እንዲሰጠው ለመጨረሻ ጊዜ ለመጠየቅ አንድ ልብ አንድ ቃል ሆነው የሚጓዙት አቤቱታ አቅራቢዎቹ የእግዚአብሔርን ኀያልነት፣ የሃይማኖታቸውን ቅድስና እና የቅዱሳንን ተራዳኢነት የሚመሰክሩ መዝሙራትን በጋለ መንፈስ ይዘምራሉ፡፡

ቁጥራቸው ወደ 500 ያህል የሚሆኑት ምእመናኑ እና ተወካዮቻቸው 250 ኪ.ሜ ተጉዘው ከቀኑ 5፡00 ግድም መዳረሻቸውን በመንበረ ፓትርያርክ  ጠቅላይ ቤተ ክህነት አድርገው ወደ ግቢው በመዝለቅ በሕንጻዎች መካከል በሰልፍ እየዞሩ መዝሙራቸውን ማሰማት ጀመሩ፡፡ ብዙዎች መብታቸው ተረግጦ በግፍ በተባረሩበት፣ የመታፈን ድባብ በሰፈነበት፣ ለውጭው ማኅበረሰብ በሐሳብ ኋላ ቀርነት እና ቅልጥፍና በሚጎድለው የተቋማዊ መዋቅሩ ትብትብነት መለዮ እስከ መሆን በደረሰው ግቢ ሐዋሳውያኑ የነጻነት መዝሙሮችን ዘመሩበት፤ ‹‹ኀይል የእግዚአብሔር ነው›› የሚለው የዝማሬያቸው ድምፅ መሬት አንቀጥቅጥ ነበርና ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የዋና ሥራ አስኪያጁ ቢሮ ጀምሮ የጳጳሳቱን መኖሪያ ዐጸድ ተሻግሮ እስከ መንበረ ፓትርያርኩ ድረስ ተሰምቷል፡፡

የምእመናኑን በግርማ መምጣት ማንም ሳይነግራቸው በራሳቸው መስማታቸውን የተናገሩት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ  አቡነ ጳውሎስ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ወደ መ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ እንዲገቡ በማድረግ በዚያ ሰዓት በግቢው የሚገኙ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እና የመመሪያ ሐላፊዎች በሙሉ እንዲገኙ ትእዛዝ ይሰጣሉ፡፡ ስምንት ሊቃነ ጳጳሳት እና የልዩ ልዩ መመሪያ ሐላፊዎች በተገኙበት የሐዋሳ ምእመናን በመረጡት ተወካያቸው አስተባባሪነት አቤቱታቸውን ማሰማት ይጀምራሉ፡፡ በእንባ ሲቃ ታጅቦ በቀረበው አቤቱታቸው ምእመናኑ አስቀድመው የወቀሱት ፓትርያርኩን ነበር፡፡ ፓትርያርኩ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ለዘመን መለወጫ በዓል በቃሊቲው የመኖሪያ ቪላቸው ያደረጉላቸውን ግብዣ ተቀብለው በመገኘታቸው እየታሙ መሆናቸውን ያወሱት አቤቱታ አቅራቢዎቹ ባለፈው ዓመት ያቀረቧቸው ችግሮቻቸው እንዳልተፈቱላቸው ይልቁንም ከአስተዳደራዊ ጉዳይ አልፎ ሃይማኖታዊ (ዶግማዊ) መልክ በመያዝ እየከፋ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

‹‹እኛ ከሕግ በታች እንጂ ከሕግ በላይ አይደለንም›› ያሉት ምእመናኑ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ እና ሥራ አስኪያጁ መፍትሔ ከመሻት ይልቅ በግትርነታቸው በመቀጠላቸው ጉዳዩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አሳውቀዋል፡፡ ሊቀ ጳጳሱ ከሰበካ ጉባኤው ቃለ ዐዋዲ ውጭ በራሳቸው የመረጧቸውን በምእመኑ ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸውን የሦስት ግለሰቦች ስም ዝርዝር በፊርማቸው አጽድቀው የሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ሰበካ ጉባኤ አባላት መሆናቸውን በጉባኤ ማሳወቃቸውን አመልክተዋል፡፡ በማን አለብኝነታቸው ቀጥለው ከአስተዳደራዊ ችግሮች ባሻገር ሃይማኖታዊ ዳኅፅ ውስጥ እየገቡ የመጡትን የሀገረ ስብከቱን ሐላፊዎች በሌሎች አህጉረ ስብከት እንደታየው ‹‹እየዠለጡ ማባረር›› እንዳላቃታቸው በብሶት የገለጹት ምእመናኑ፣ ፓትርያርኩ እና የሚመለከታቸው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሐላፊዎች ቀደም ሲል ስምምነት በተደረሰበት መልኩ ስለ ችግሩ የሚያጣራውን ኮሚቴ ወደ ሀገረ ስብከቱ በአስቸኳይ በመላክ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሔ እንዲሰጡ አሳስበዋል፡፡

ስሜትን በሚነካው የምእመናኑ የአቤቱታ አቀራረብ ከምእመናኑ ጋራ ሲያነቡ የታዩት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ (ፎቷቸውን ይመልከቱ) “ልባችን አዝኗል፤ ብዙ ጉድ ተሸክማችሁ ነው የኖራችሁት፤ አሁኑኑ፣ ዛሬውኑ አትበሉን እንጂ በመጪዎቹ ሁለት እና ሦስት ቀናት አጣሪ ጉባኤ ሠይመን ወደ ስፍራው በመላክ ችግሩን እንፈታለን” ብለዋል፡፡ መፍትሔው ዋና ሥራ አስኪያጁ ባሉት መሠረት እንደሚሰጥ የተናገሩት ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ አቡነ ፋኑኤል “ከምእመናኑ ጋራ ይቅር ተባብለናል፤ ታርቀናል” ብለው የነገሯቸውን በመያዝ ችግሩ እልባት ያገኘ መስሏቸው እንደ ነበር ለምእመናን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ አያይዘውም “አቡነ ፊልጶስ እንዳሉት ችግሩን በሁለት እና ሦስት ቀናት እንፈታለን፡፡ እኔ ማንም ሰው እንዲጠፋ አልፈልግም፡፡ በአጣሪ ኮሚቴው ጥናት መሠረት በአጉል ድርጊት የተገኙ የሥራ ሐላፊዎች መነሣት ካለባቸው ይነሣሉ፤ ባለመግባባት ቅራኔ ተፈጥሮ ከሆነም ችግሩ በዕርቀ ሰላም እንዲፈታ እናደርጋለን” ብለዋል፡፡ ምእመናኑ ሊቀ ጳጳሱ እና ሥራ አስኪያጁ ከሐላፊነታቸው እንዲነሡ የሚጠይቀውን የአቤቱታ ፊርማቸውን ለቅዱስ ሲኖዶስ እና ለዋና ሥራ አስኪያጁ ጽ/ቤት በማስገባት ወደ ሐዋሳ ተመልሰዋል፡፡

በምእመናኑ የቀረቡትን አቤቱታዎች ለማጣራት አምስት አባላት ያሉት የልኡካን ቡድን ዓርብ፣ መስከረም 28 ቀን 2003 ዓ.ም ወደ ሐዋሳ እንደሚያመራ ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም እስከ አሁን በደረሰን መረጃ መሠረት አለመንቀሳቀሱ ታውቋል፡፡ አጣሪ ልኡኩ በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የሚመራ ሲሆን ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ (የጠቅላይ ቤተ ክህነት ም/ዋና ሥራ አስኪያጅ)፣ ሊቀ ካህናት ብርሃኑ ገብረ ዐማኑኤል (የትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ)፣ ሊቀ ትጉሃን ሠርጸ አበበን እና በኩረ ትጉሃን ዓለም አታላይን በአባልነት ይዟል፡፡ 

ለስምሪቱ መጓተት ምክንያቱ ለልኡኩ ተግባር አስፈላጊ የሆኑ ደብዳቤዎች አለመሟላት እና ሊቀ ጳጳሱ በምእመኑ ያልተመረጡ የሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ሰበካ ጉባኤ አባላትን በራሳቸው ወስነው፣ አጽድቀው ከፈረሙበት ካለፈው ሳምንት አጋማሽ ጀምሮ በሀገረ ስብከቱ የሌሉ በመሆናቸው ነው፡፡ እንደ ውስጥ ዐዋቂዎች መረጃ አቡነ ፋኑኤል በአሁኑ ወቅት ዓላማው ባልታወቀ ጉዞ በስዊድን ይገኛሉ፡፡ በአቡነ ፋኑኤል (ፎቷቸውን ይመልከቱ) ትእዛዝ የሰበካ ጉባኤ አባል እንዲሆኑ የተመረጡትን ግለሰቦች ዝርዝር ላእከ ወንጌል የሚል ማዕርግ የተለጠፈለት እና የሀገረ ስብከቱ የሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ጸሐፊ ሆኖ እንዲሠራ የተቀጠረው ያሬድ አደመ ይፋ ማድረጉ ተዘግቧል፡፡  


Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)