October 31, 2010

ርእሰ አንቀጽ፦ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ “በቃ” ሊባሉ ይገባል፤

  • "ተዘልፎ ልቡን ያደነደነ ድንገት ይሰበራል፤ ፈውስም የለውም" (ምሳሌ 29፡1)
 (ደጀ ሰላም፤ ኦክቶበር 30/2010፤ ጥቅምት 20/2003 ዓ.ም):- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በታሪክዋ ገጥሟት የማያውቅ ችግር ላይ ለመሆኗ ነጋሪ የማያሻው የአደባባይ ምስጢር ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ በእርግጥ በረዥም ዘመን ታሪክዋ የተለያዩ ፈተናዎች ተፈራርቀውባታል ከውጭና ከውስጥ ጠላቶች፤ ዳሩ ግን በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዘመነ ፕትርክና የገጠማት ግን ከቶ ሆኖ የማያውቅ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በራሷ ልጆች መመራት ከጀመረችበት ካለፉት 50 ዓመታት ጀምሮ አቡነ ጳውሎስን ጨምሮ 5 ፓትርያርኮችን አስተናግዳለች። በአረፍተ ዘመን በተገቱት በሦስቱ ፓትርያርኮችና በሕይወት ባሉት 4ኛ ፓትርያርክ ዘመን ቤተ ክርስቲያኒቱ አሁን እንዳለው ያለ ውሳጣዊ ችግር አልገጠማትም፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ራሳቸው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ናቸው። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በሁለት ወገን የተሳለ ሰይፍ የተሰኘ ቅኔ ተዘርፎላቸው በመንበሩ ላይ ከተሰየሙ ማግስት ጀምሮ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ የተደረጉትንና እየተደረጉ ያሉትን በደሎች በወፍ በረር እንቃኛቸው፡-
  1. ምእመናንን የማሰላቸት ተግባር
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በአዲስ አበባ ምእመናን አፍ ውስጥ መጀመሪያ የገቡት የንግስ ክብረ በዓል ሥርዓትን ያለመጠን በማራዘማቸው ነው ባለው የቤተ ክርስቲያኒቱ ባሕልና ልምድ መሠረት አንድ የንግስ በዓል ቅዳሴውን አካቶ ቅዳሴው ተሰዓት ከሆነ ቢዛ ዘጠኝ ሰዓት ተኩል ላይ ሰርኦተ ሕዝብ ይሆናል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ግን በረዥም ፖለቲካ ቀመስ ትምሀርት ሕዝቡን ለሁለት ለሦስት ሰዓት ያህል ያግቱታልአብዛኛው ዲስኩራቸው ምእመኑን የሚዘልፍ ያለውን መንግስት የሚያወድስ በመሆኑም ምእመኑ ጥሏቸው እንዳይሄድ ታቦቱን አቁመዋል አንጀቱ እያረረና ዳግመኛ እርሳቸው በሚገኙበት የንግስ በዓል ላይ ላለመገኘት ለራሱ እየማለ የግዱን በረከት አገኝበታለሁ ብሎ ሄዶ ጨጓራ በሽታ ሸምቶባት ይመለሳል፡፡

በዚህ ምክንያት የተነሳ ብዙ ምእመናን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ይገኛሉ ብሎ የሚጠረጥረው ንግስ ላይ አይገኝም፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የሚገኙበት የንግስ በዓል ቅዳሴው ጠዋት ከሆነ ሰርኦተ ሕዝብ የሚሆነው ፈጠነ ከተባለ ዘጠኝ ነው፡፡ ከሰዓት ከሆነ አስራ አንድና አስራ ሁለት ነው፡፡ ይህ ሆን ተብሎ ምእመኑን ከቤተ ክርስቲያን እንዲርቅ የማድረግ ተልእኮ እንደሆነ ተቆርቋሪዎች ብዙ ጊዜ የሚናገሩት ነው፡፡

2. የቤተ ክርስቲያኒቱ አመራር በወሮበሎች እንዲያዝ ማድረግ
በቤተ ክርስቲያኒቱ የአብነት ትምህርት ቤቶችና ቤተ ክርስቲያኒቱ ባሏት መንፈሳዊ ተቋማት ደክመው ቤተ ክርስቲያኒቱን በፈሪሃ እግዚአብሔር እያገለገሉ ያሉ ብዙ ማዕምራነ ቤተ ክርስቲያን እያሉ እርሳቸው ግን ቤተ ክርስቲያኒቱን ፈጽሞ የማያውቁ እንደውም ሲዘርፉ፤ የሰው አጥር ሲዘሉ የኖሩ ወሮበሎችን በመብራት እየፈለጉ በተለይ በአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት ላይ ምንኩስናን በስም ካልሆነ በግብር የማያውቁትን ስመ ምንኩስናን ለሹመትና ለዝርፊያ የተጠቀሙትን ሰዎች ሰግስገው እነሆ ምእመኑን ከጋጣው እያስወጡት የቤተ ክርስቲያኒቱን የገንዘብ ቤት ባዶውን በማስቀረት ላይ ይገኛሉ፡፡

በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አማካይነት የአዲስ አበባን ገዳማትና አድባራት የተቆጣጠሩት በአብዛኛው የአራት ኪሎ ሊስትሮዎች ባወጡላቸው ስም ልጠቀምና የፍንዳታ መነኮሳት ናቸው፡፡ እነዚህ ሳይገባቸው ለሹመትና ለዝርፊያ የምንኩስናን አስኬማና ቀሚስ የደፉና ያጠለቁ ወሮበሎች ምንኩስናን በዓላማ የተቀበሉትን የእውነተኞቹን መነኮሳትን ስም ለማጥፋትና በምእመኑ ዘንድ ያላቸውን አባታዊ ስሜት ለማሳነስ እየጣሩ ነው። ይህም መነኮሳትን በምእመናን ዘንድ ተቀባይነት እንዲያጡ እየተደረገ ያለ ሴራ አካል ነው፡፡ ምንኩስና ወንጌል ያመጣቻት ሕግ ናት “ምንኩስናሰ ጥበበ ሕግ መሢሐዊት ይእቲ” እንዲል ፍትሕ መንፈሳዊ፡፡ መነኮሳትም ምድራውያን መላእክት ሰማያውያን ሰዎች ናቸው፡፡ በግብራቸው ሰማያውያን፣ በተፈጥሯቸው ምድራውያን መባላቸውን ልብ ይሏል፡፡

እነዚህ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዘመነ ፕትርክና እንደ አሸን የፈሉት መነኮሳት ግን እንኳን መላእክትን በግብር ሊመስሉ ከሰውነት ተርታም የወጡ ናቸው፡፡ መነኮሳት በሥራቸው ሁሉ ሐዋርያትን ያከሉ የመሰሉ ናቸው። ከዚህ ዓለም ገንዘብ በመለየት ሹመት ሽልማትን በመተው ክርስቶስን በፍጹም ልባቸው በፍጹም ነፍሳቸው የተከተሉ መሆን አለባቸው፡፡ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዘመነ ፕትርክና የፈሉት “መነኮሳት” ግን ልብሰ ምንኩስናውን መድመቂያ አስኬማውን ማጭበርበሪያ ከማድረጋቸው ውጪ በጠራራ ፀሐይ በማናለብኝነት መነኮሳት ሊገቡበት ቀርቶ ስለ እርሱ ሊሰሙ የማይገባቸው ቦታ በመገኘት፤ እውነተኛ አባት መስለዋቸው ለንስሐ የሚቀርቡዋቸውን እህቶች በዝሙት በመፈታተን፤ የቤተ ክርስቲያን ሙዳይ ምጽዋትን በመዘቅዘቅና ብዙ አሳፋሪ ድርጊት የተሰማሩ ናቸው። ስለ እነርሱ በየጊዜው እየተሰማ ከዚህ ጉድ ይገላግሉናል በማለት ምእመናን ወደ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አቤት ሲሉ የሚሰጣቸው መልስ “ጆሮን ጭው የሚያደርግ”፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ፍጹም የሚያርቅ ነው፡፡

በአንድ ወቅት በአንድ ደብር ላይ ተመድቦ የነበረ በእንጦንስ ቆብ የሚነግድ ወንበዴ የደብሩን ካዝና በማራቆቱ ዋልጌነቱ ገደብ ያለፈ በመሆኑ የአጥቢያው ምእመናን ወደ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አቤት ሊሉ ይሄዳሉ። ለዚህ ተግባር ሾመው ሸልመው የላኩት ዋናው አዝማች እርሳቸው መሆናቸውን ያላወቁት ምእመናን (አባት አግኝተው) ለአቤቱታ ነበር ወደእርሳቸው የሄዱት ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የሰሙት ግን ያልጠበቁትና ኅሊናን የሚያስት ነበር“ገንዘባችንን በላ ብላችሁ ነው እዚህ ድረስ የመጣችሁት? ገና እናንተን የሚበላ ይሾምላችኋል” የሚል ነበር መልሳቸው፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ሐሰት አልተናገሩም። በአዲስ አበባ አድባራት ላይ ሰው በላ የሆኑ በምንኩስና ልብስ የደመቁ አውሬዎችን ማሰማራታቸው አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ያደባባይ ምስጢር ነው፡፡ እነዚህ የቀበሮ ባሕታውያን የምእመኑን ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ሕይወቱን ሁሉ እየሰረቁ ለተኩላ አሳልፈው እየሰጡት ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ፊት አውራሪው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ መሆናቸው የተረጋገጠ ነው፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ወሮበላ “መነኮሳትን” ብቻ አይደለም በዚህች ቤተ ክርስቲያን ላይ ያዘመቱባት ቀኝና ግራቸውን የማያውቁ  ውርጋጦችንም ጭምር ነው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ይህቺን ቤተ ክርስቲያን ለማጥፋት ጦር ሰብቆ ከመጣው ጋር ሁሉ አብሮ ለመስራት ፈቃደኛ ናቸው። ለቤተ ክርስቲያኒቱ የሚያስብ ሁሉ የእርሳቸው ጠላት ነው እርሳቸውን ቢቃወም እንኳን ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማጥፋት ጦር ሰብቆ ዘገር ነቅንቆ የመጣ ከሆነ የዓላማ አጋራቸው ነውና ከእርሱ ጋር እጅና ጎንት ሆነው ይሰራሉ። ለዚህም እርሳቸውን ሰድቦ መጽሐፍ ጽፎ ከነበረው ግራና ቀኙን ከማያውቀው እንጭጭ ጋር የፈጠሩት ሕብረት አንዱ ማስረጃ ነው፡፡
  • ቤተ ክርስቲያኒቱን ሊቃውንት አልባ የማድረግ ዘመቻ፤
የቤተ ክርስቲያኒቱ ጠበቆች የሆኑት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እየተገፉ ከቤተ ክህነቱ አስተዳደር በአፍኣ እንዲሆኑ ማድረግ የጀመሩት በመንበራቸው ላይ ጥቂት ዓመታትን እንኳን ሳያስቆጥሩ ነው። ይህ የሚያሳየው የቤተ ክርስቲያኒቱን ቀኖናና ሥርዓት ለማጥፋት ዓልመው የመጡ ናቸውና ከሊቃውንቱ ተቃውሞ እንዳይገጥማቸው በማሰብ ነው፡፡ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ብርሃን የሆኑ ብዙ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን አስመርረው አስወጥተዋል፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ “የቆብ ዘረኝነት”ን አንግሰው በሕግ (በትዳር) ያሉ ሊቃውንትን ነቅለው በምትካቸው ለመሾም ብለው የምንኩስና ቆብ ያጠለቁ ምንደኞች መነኮሳትን ተክለዋል። በዚህም ለዘመናት የኖረውን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ባሕልን አጥፍተው ካቶሊካዊ ሥርዓትን የመተካት ዕቅዳቸውን ጀምረውታል።

በረዥሙ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ሕጋውያን በቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ውስጥ ትልቅ ሥፍራ እንደ ነበራቸው የቤተ ክርስቲያኒቱን ጉዞ የሚያውቅ ሁሉ የሚገነዘበው ሀቅ ነው፡፡ አሁን ግን መጻሕፍትን የሚያራቅቁ፣ አስተዳደርን ጠንቅቀው የሚያውቁ መንፈሳዊነታቸው የተመሰከረላቸው፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚወዱና ሌት ተቀን ለቤተ ክርስቲያኒቱ የሚያስቡ ሕግ ገብተው ያሉ ሊቃውንት እየተሽቀነጠሩ እየተጣሉ ትንታግ በሆኑት በእነዚህ አበው ሊቃውንት ምትክ ለሹመት ለሽልማት ብሎ የምንኩስና ቆብ ደፍቶ በመጣ በማንኛውም ተርታ ሰው እየተተኩ ነው፡፡ ይህ ቤተ ክርስቲያኒቱ አሁን ላለችበት ውድቀት ታላቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡  

  •  የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነት ማናጋት፤
ከሀገር ውጭ ያለችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አሁን ላለችበት መለያየት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ። በመንበሩ ላይ ከተሰየሙበት ጊዜ አንስቶ ለይስሙላና ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ከዋለ  የለበጣ የእርቅ ጥረት ያለፈ ያደረጉት መሠረታዊ የእርቅ አጀንዳ የለም። እንዲያውም ልዩነቱን ወደባሰ ደረጃ አድርሰውታል። በውጭ ያሉት አባቶች እልህ ተጋብተው ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ጥሰው ጳጳሳትን እንዲሾሙ አስተዋጽኦ አድርገዋል። በገለልተኝነት ያሉትም ባሉበት እንዲጸኑ እያበረታቱ ይገኛሉ። ይህን የሚያደርጉት የሥልጣን ዘመናቸውን ለማራዘምና ቤተ ክርስቲያኒቱን የማጥፋት ተልዕኳቸውን ለማሳካት ነው፡፡

  • የቅዱስ ሲኖዶስን ሉዓላዊነት መጋፋት፤
ቤተ ክርስቲያን ዘኢትዮጵያ ሐዋርያዊት እንደመሆንዋ የምትመራው በሕገ ሐዋርያት ነው። ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ በሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ ትተዳደራለች። የቅድስት ቤተ ክርስቲያን የመጨረሻ ወሳኝ አካል ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡ አምስተኛው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ጰውሎስ ግን ልክ እንደ አምባገነን ምድራዊ መሪ የሲኖዶሱን ሥልጣን በአምባገነንነት ነጥቀው ያሻቸውን ሲሾሙ ያሻቸውን ሲያባርሩ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን ያለ ሕጓና ሥርዓትዋ ሲዘውሯት ኖረዋል። በምድራውያን አምባገነን መሪዎች የማይደረገውን እስከማድረግ ደርሰዋል። በቁማቸው ሐውልት እስከማቆም፡፡ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ላይ መሳለቅ የሲኖዶስን ውሳኔ አሽቀንጥረው ራሳቸው ካደራጁት የማፍያ ቡድን ጋር የራሳቸውን ኔት ወርክ ዘርግተው የቅዱስ ሲኖዶስን ህልውና እስከመዘንጋት ደርሰዋል፡፡ ምእመኑም በቀቢጸ ተስፋ ውስጥ ሆኖ “ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ አለ ወይስ የለም?” እስከማለት ደርሷል፡፡ 

ሰሞኑን የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የወሰዱት ቁርጠኝነት ምእመኑን ከቀቢጸ ተስፋ ያወጣ ሲሆን በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በኩል የሚታየው አልሞት ባይ ተጋዳይነት የውስጥ ሥውር አጀንዳቸውን ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነው፡፡

አሁን የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አምባገነናዊና ኢ-ኦርቶዶክሳዊ አመራርና አሠራር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተነቅሎ የሚጣልበት ወቅት መሆን አለበት። ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በወሰኑት ውሳኔ መሠረት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የማይስማሙ ከሆነ ከዚህ በላይ መታገስ ሕዝበ ክርስቲያኑን ከቤተ ክርስቲያን ማራቅ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱንም ለተኩላዎች አሳልፎ መስጠት ነው። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ  ቅዱስ ሲኖዶስ ከወሰነው ውሳኔ እንደለመዱት አፈንግጠው በራሳቸው መንገድ ያደራጁትን የማፍያ ቡድን ይዘው የሚጓዙ ከሆነ ሊወገዙና ከቤተ ክርስቲያኒቱ መንበር ሊወገዱ ይገባል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ይህን ካላደረገ ጥርስ የሌለው አንበሳ ሆኖ ለመቀጠል ይገደዳል ማለት ነው፡፡ በበኩላችን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ “ረግረጉና እቋሪው ውኃ ግን ጨው እንደሆነ ይኖራል እንጂ አይፈወስም” እንደተባለው (ሕዝ.47፤11) ከእንግዲህ ወዲህ የማይፈወሱ ድዊውይ ናቸውና ቅዱስ ሲኖዶስ ከመንበሩ ሊያስወግዳቸው ይገባል፡፡

ቸር ወሬ ያሰማን፤ አሜን
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)