October 24, 2010

አጣሪ ኮሚቴው በሐዋሳ

(ደጀ ሰላም፤ ኦክቶበር 24/2010፤ ጥቅምት 14/2003 ዓ.ም):- የሐዋሳውን ችግር ለመፍታት ቃል በተገባው መሠረት አጣሪ ኮሚቴው ሐዋሳ ከተማ ከገባ በኋላ ምእመናኑን ማነጋገሩን ትናንት ቅዳሜ ጀምሯል። የሊቀ ጳጳሱ ደጋፊዎች እና አቤቱታ አቅራቢዎች የየበኩላቸውን አቤቱታ ለአጣሪው ለማሰማት ሲሞክሩ መጯጯሆች ይሰሙ ነበር። ሁለቱም ቡድን በቅርብ ርቀት የየበኩሉን ደጋፊ አደራጅቶ የበለጠ ለመሰማትም ለመታየትም ሞክሯል። ሁለቱም አካላት ባሉበት በሐዋሳው በቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ላይ መታየት ሲጀምር ቅዱስ ፓትርያርኩ በአጣሪ ኮሚቴ አባላቱ በኩል ለአዋሳ ምዕመናን የጻፉት ደብዳቤ ተነብቧል።

በቀን 12/02/03፣ በቁጥር 10/51/2003 የተጻፈውና በግልባጭ ለክልሉ የፍትሕ እና አስተዳደር አካላት፣ ለወረዳ ቤተ ክህነቶች እና ለተለያዩ አድባራት የተላከው ይኸው ደብዳቤ የማጣራቱ ሒደት የሚታይባቸው አካላት አጣሪው ኮሚቴ ሥራውን እስኪፈጽም ድረስ ከማንኛውም የዐውደ ምሕረት አገልግሎት እንዲታገዱ ያሳስባል/ ያዛል። ደብዳቤ የማጣራቱ ሒደት የሚታይባቸው አካላት ያላቸው ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ፣ መልአከ ሕይወት ፀሐይ መላኩ ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም ላዕከ ወንጌል ያሬድ አደመ እና መጋቤ ምሥጢር ፍስሐ ናቸው።

ደብዳቤው ከተነበበ በኋላ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ምእመናን ችግራቸውን በእንባ አጅበው አሰምተዋል። ለአቤቱታው መልስ የሰጡት ንቡረ ዕድ ኤልያስ አብርሃ (የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመንፈሳውያን ጉዳዮች ዘርፍ ም/ዋና ሥራ አስኪያጅ) “የእናንተ ጉዳይ የኢትዮጵያ አጀንዳ ሆኗል፤ በዓለም ሁሉ ተሠራጭቷል። የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በሙሉ ያውቁታል፤ ሰምተውታል። እኛም የመጣነው ችግራቸሁ ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ እንዲፈታ ነው” ብለዋል። ቀጥሎም ከሁለቱም ወገን ያለውን ነጥብ ሊያቀርቡ የሚችሉ 25/25 ሰዎች እንዲመረጡና እንዲቀርቡ መመሪያ ሰጥተዋል።  በወቅቱ ከሀ/ስብከቱ በተጻፈ ደብዳቤ ከየገጠሩ የመጡ ካህናት የሚያሰሙት ነገር አለ በሚል ክስ ከሚቀርብባቸው ሰዎች ወገን የተነሣ ቢሆንም ለሌላ ጊዜ እንዲቀርቡ ተወስኖ ጉዳዩ ለቅዳሜ ከሰዓት ተዘዋወረ።

ከምሳ በኋላ ማጣራቱና አቤቱታ መስማቱ በሐዋሳው የቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል አዳራሽ እስከ ማታ ድረስ ቀጥሏል። ምእመናኑ በቅደ ሁኔታነት ያቀረቡት የእነ ያሬድ አደመ ከየዐውደ ምሕረቱ መገለል ተቀባይነት አግኝቶ በፓትርያርኩ ደብዳቤ መገለፁ ውጥረቱን ያረገበ ሲሆን ሕዝቡን ለማረጋጋት ደግሞ ለረዥም ጊዜ በደብሩ እና በሀ/ስብከቱ ሲያገለግሉ የኖሩት ሊቁ መልአከ ምሕረት ጳውሎስ ቀጸላ በማስተማር ላይ ናቸው ተብሏል። አጣሪ ኮሚቴው ሥራውን ዛሬ እሑድም ካካሄደ በኋላ ወደ ውሳኔ ኢሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)