October 26, 2010

የቅ/ሲኖዶስ የዛሬ ውሎ ዝርዝር ሪፖርታዥ

(ደጀ ሰላም፤ ኦክቶበር 26/2010፤ ጥቅምት 16/2003 ዓ.ም):- ቅዱስ ሲኖዶሱ በዛሬው ውሎው ከቅዱስ ፓትርያርኩ “ሐውልተ ስምዕ” መፍረስና ሌሎች ተጨማሪ ወሳኝ እርማጃዎች በተጨማሪም ከጥቅምት አንድ 2003 ዓ.ም ጀምሮ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የአስተዳደር ጉዳዮች ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ልዑል ሰገድ ግርማ፣ የአስተዳደር እና አቅም ግንባታ መምሪያ ሐላፊ አቶ ደሳለኝ መኮንን እንዲሁም የሒሳብ እና በጀት መምሪያ ሐላፊ ወ/ሮ ጽጌሬዳ ዓለሙ የቅጥር ሁኔታ በሕገ ቤተ ክርስቲያን ለቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠውን የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን መዋቅር እና የአስተዳደር ደረጃ የመወሰን ሥልጣን የሚጋፋ መሆኑን አመልክቷል፡፡ ስለዚህም የሐላፊዎቹ የፈረሙት ኮንትራክት ካለ የኮንትራክት ጊዜያቸው ሲያበቃ እንዲሰናበቱ፣ የፈረሙት ኮንትራክት ከሌለ ግን በአስቸኳይ እንዲሰናበቱ ወስኗል፡፡

በትናንቱ የከሰዓት በኋላ ውሎው ቅዱስ ሲኖዶስ ፓትርያርኩ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን፣ ሥርዓተ አበውን እና የቅዱስ ሲኖዶሱን ማእከላዊ አሠራር በመጣስ ሲፈጽሟቸው ስለ ቆዩት ተግባራት ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠይቋቸው ምላሻቸውን በዛሬው ዕለት ጠዋት እንደሚሰጡ ገልጸው ነበር ስብሰባው ለዛሬ ያደረው፡፡ ዛሬ ጠዋት ፓትርያርኩ ስብሰባው በጸሎት ከተከፈተ በኋላ ምላሽ ይሰጣሉ ተብሎ ቢጠበቅም ርእሰ መንበር ሆነው በተቀመጡበት መስቀል የጨበጠ እጃቸውን በጠረጴዛው ላይ ዘርግተው፣ አንገታቸውን አጽንነው ለረጅም ሰዓት በሊቃነ ጳጳሳቱ እየተለመኑ ቆይተዋል፡፡ ‹‹ኧረ ይበሉ እንጂ ይናገሩ፤ መልስ እንፈልጋለን›› የሚለው የሊቃነ ጳጳሳቱ ተማጥኖ የበዛባቸው ፓትርያርኩም ‹‹አባቶቼ፣ እኔ አልተሳሳትኩም፤ የቀደሙት አባቶች ሐውልት ሲያሠሩ ነው የኖሩት፤ ሐውልት ማሠራት በእኔ አልተጀመረም፤ የተለየ ነገር አላደረግኹም›› በማለት ፍርጥም ብለዋል፡፡ ብፁዓን አባቶችም በተለያዩ አጋጣሚዎች እንደተገለጸው ድርጊቱ በሲኖዶሱ ያልተመከረበት፣ በሥርዓተ አበው የተቀደሰ ትውፊት ያልነበረ እና ሕገ ቤተ ክርስቲያንን የጣሰ ስለ መሆኑ አበክረው ያስረዳሉ፡፡

ሲኖዶሱ ኅቡረ ልብ፣ ኅቡረ ቃል መሆኑን የተረዱት አቡነ ጳውሎስም፣ ‹‹እንግዲያውስ ሐውልት የተሠራ መሆኑን አላውቅም ነበር፤ ያወቅሁት ከቦታው ከደረስኩ በኋላ ሐውልቱ ሲገለጥ ነው›› ሲሉ ከፊተኛው ምላሻቸው ጋራ የሚለያይ ምላሽ ይሰጣሉ፡፡ በወቅቱ ሐውልቱ እንደተሠራ እና በበዓለ ሢመታቸው ዋዜማ እንደሚገለጥ በብዙኀን መገናኛዎች በወጡ ዜናዎች፣ ሐተታዊ ጽሑፎች እና የሕዝቡን ኀዘን የሚገልጡ ቃለ ምልልሶች እንደ ተሠራጨ፣ እርሳቸውም ሐውልቱን እንዳይባርኩ በብፁዓን አባቶች እና በቅርብ ቤተ ዘመዶቻቸው ሳይቀር መለመናቸውን፣ ይሁንና ልመናውን ወደ ጎን በመተው ሐውልቱን ለሚያሠራው ኮሚቴ ድጋፍ እንዲደረግለት ትእዛዝ መስጠታቸውን፣ ሐውልቱ ከቆመ በኋላም በሥፍራው በመገኘት መመረቃቸውን፣ በዐውደ ምሕረቱም የሐውልቱ መገንባት ተገቢ ስለመሆኑ ከቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ እና ከሥርዓተ አበው ውጭ የሆነ ጽሑፍ ሲቀርብ በአኵቴት መቀበላቸውን እንዲያውም ‹‹ክብሩ የሲኖዶሱም ጭምር ስለ መሆኑ›› መናገራቸውን፣ ከዚያም በኋላ ተቃውሞው ሲበረታ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ውስጥ ራሳቸውን የሾሙ ግለሰቦች የሐውልት ሥራውን ተገቢነት በመጥቀስ መሟገታቸ ተዘንግቶ በዚህም ሁሉ ውስጥ ‹‹አላውቅም›› ሊሉ እንደማይችሉ አስታውሰዋቸዋል፡፡ የዘወትር ችግራቸውም ‹‹እኒህን ሁሉ ምክሮች ያለማዳመጥ፣ ቆም ብሎ ያለማየት አስተዳደራዊ ብልሽት›› መሆኑ በተለይ እንደ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ እና ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ባሉት አባቶች ተነግሯቸዋል፡፡

ከዚህ በኋላ ሊቃነ ጳጳሳቱ የመንግሥት አካል በተገኘበት ውሳኔያቸውን እንደሚያሳውቁ ቢያስጠነቅቋቸውም ፓትርያርኩ አርምሞን በመምረጣቸው፣ ሐውልቱ እና ፖስተሩ የቤተ ክርስቲያኒቷን ሥርዓት እና የተቀደሰ ትውፊት የሚያናጋ መሆኑ በሁሉም ብፁዓን አባቶች ቃል እየተገለጸ በሙሉ ስምምነት እንዲፈርስ እና እንዲወገድ ተወስኗል፡፡ ጥቅምን ማእከል ካደረገው የጭከና እና የማበጣበጥ ግብራቸው የተነሣ ‹‹ኤልዛቤል›› የሚል ቅጽል ስም የተሰጣቸው እና ከዕሥራ ምእቱ በዓል አከባበር ዋዜማ ጀምሮ ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ከድመት ጠጉር ልመው በመግባት የፓትርያርኩ ፖስተር እንዲሰቀል፣ ሐውልታቸው እንዲቆም ከፍተኛ ሚና በመጫወት እና ከዚህም መጠኑ ያልታወቀ ጥቅም በማጋበስ የሚታወቁት ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነም ወደ መንበረ ፓትርያርኩ ቅጽር ዝውር እንዳይሉ የማገጃ ውሳኔ ተላልፎባቸዋል፤ ውሳኔውንም ለማስፈጸም የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ሐላፊነቱን መውሰዳቸው ተዘግቧል፡፡ ‹‹ሲኖዶሱ ሳይበተን እኔ ራሴ ውሳኔውን አስፈጽማለሁ፤ በዚህ ተወሰነ መባሉም ለቅዱስ ሲኖዶሱ ክብር ጥሩ አይሆንም›› ብለዋል ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ፡፡ በውሳኔው በመደሰት የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱን እጅ እየሳሙ ቅዱስ ሲኖዶሱ ህልውናውን በእኒህ መሰል ውሳኔዎች ማረጋገጡ እንዳስደሰታቸው የገለጹት ደጀ ሰላማውያን ውሳኔው ተግባራዊ ፍጻሜ ስለማግኘቱ ያላቸውን ጥርጣሬ ከመናገር አልቦዘኑም፡፡ በመሆኑም ሲኖዶሱ ጉባኤው ሳይጠናቀቅ ፍጻሜውን እንዲያሳየን አልያም ራሱን የቻለ አስፈጻሚ አካል እንዲሠይም ጠይቀዋል፡፡ በርግጥም ከዚህ በፊት የተላለፉት የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች ጥርስ የሌላቸው የወረቀት ላይ አንበሶች ሆነው ቢቆዩም፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያን በተደነገገው መሠረት የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት፣ ቋሚ ሲኖዶሱ እና ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የምልዓተ ጉባኤውን ውሳኔ የማስፈጸም ግዴታ እንዳለባቸው በጥቁር እና ነጭ ሰፍሮ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡

በተያያዘ ዜና ቅዱስ ሲኖዶስ በዛሬው የከሰዓት በኋላ ቆይታው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ከቅዱስ ሲኖዶሱ ዕውቅና ውጭ በፓትርያርኩ ብቸኛ ውሳኔ መሾም፣ በመቐለ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ቅዱስ ፍሬምናጦስ ኮሌጅ ብሪጅ ኦቭ ሆፕ እየተባለ በሚታወቀው በአሜሪካ በሚገኝ የፕሮቴስታንት ኮሌጅ ተገኘ በሚባለው የድኅረ ምረቃ ፈንድ ስለሚፈጸመው የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ፣ ከፍተኛ ሙስና እና ምዝበራ ይፈጸምበታል ስለሚባለው የቤቶች እና ሕንፃዎች አስተዳደር ችግሮች በሰፊው በመያየት ሁኔታውን ለውውይት በሚያመች መልኩ አጥንቶ የሚያቀርብ ኮሚቴ በመሠየም የአራተኛ ዕለት ስብሰባውን አጠናቅቋል፡፡
ተፈጸመ በሰላመ እግዚአብሔር፡፡
 አሜን፡፡
(የዜናውን ዝርዝር በቆይታ እንመለስበታለን)፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)