October 27, 2010

በጳጳሳት ዝውውር እና ምደባ ጉዳይ በፓትርያርኩ የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ከፍተኛ ክርክር አስነሣ


(ደጀ ሰላም፤ ኦክቶበር 27/2010፤ ጥቅምት 17/2003 ዓ.ም):- ከተጀመረ አምስተኛ ቀኑን ያስቆጠረው የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ የጳጳሳት ምደባ እና ዝውውርን አስመልክቶ በቋሚ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ውይይት የተደረገበት ነው በተባለው እና በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ለውሳኔ በቀረበው ሐሳብ ላይ ተወያየ፤ ውይይቱ ከፍተኛ ክርክር የተካሄደበት በመሆኑ ሳይቋጭ ለነገ እንዲያድር ተደርጓል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶሱ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በነበረው እና ማምሻውን በተጠናቀቀው የስብሰባው ውሎ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ባቀረቡት የዝውውር እና ምደባ ሐሳብ፡-
  • ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ኮሚሽነር (በብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ተቀባይነት አላገኘም)፤          
  • በካናዳ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ማቲያስ - የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንዲሆኑ፤
  • የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ሐላፊ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ገብርኤል በሲዳማ ጌዲኦ ዞኖች አማሮ እና ቡርጂ ወረዳዎች(ሐዋሳ) ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንዲሆኑ፤            
  • የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ኢሳይያስ ወደ መቐለ ትግራይ ሀገረ ስብከት ተዛውረው በምትካቸው አቡነ ፋኑኤል እንዲተኩ፤ (አቡነ ፋኑኤል ተቃውመውታል)፤
  • በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ሽሬ እንዳሥላሴ ሀገረ ስብከት የነበሩት ብፁዕ አቡነ  ሚካኤል ወደ ባሌ ሀገረ ስብከት እንዲዛወሩ (በብፁዕ አቡነ ይሥሐቅ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል)፤
  • የዲሲና አካባቢው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም፤ ወደ ምስራቅ ጎጃም ደ/ማርቆስ፤ በምትካቸው ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ እንዲተኩ፤
  • የደቡብ አውሮፓው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ወደ ነገሌ ቦረና፣ በምትካቸውም ብፁዕ አቡነ ሙሴ እንዲተኩ፤
  • ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ወደ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ ወሊሶ እንዲዛወሩ፤
  • ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ የከምባታ፣ ሐዲያና ጉራጌን ሀ/ስብከት እንዲያስተዳድሩ፤
በካናዳው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ማቲያስ እንዲሁም በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ሊቀ ጳጳስ ፈንታ እነማን እንደሚተኩ አልታወቀም፡፡ ባለፈው ዓመት በሞተ ዕረፍት በተለዩን የከምባታ ሐዲያ እና ጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ምትክ ሊቀ ጳጳስ እንደሚሾም፣ ሌሎችም ዝውውሮች እና ምደባዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡ አንዳንድ የስብሰባው ምንጮች ለደጀ ሰላም እንደተናገሩት ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል፣ ‹‹ከነበርኩበት ያሥነሳኝ ማኅበረ ቅዱሳን ነው፤ ማኅበረ ቅዱሳን ወደሌለበት መድቡኝ›› በማለት የዘወትር ስጋታቸውን መግለጣቸው ተዘግቧል፡፡ 
ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የአዲስ አበባን ሀገረ ስብከት ጉዳይ ባጣራው ኮሚቴ ሪፖርት ችግር እንደሌለባቸው በመረጋገጡ እና ለአንድ ዓመት ያለሥራ ተቀምጠው በመንገላታታቸው ቅዱስ ሲኖዶስ ወደ ቀደመ ሐላፊነታቸው ይመለሱ ዘንድ እንዲፈቅድላቸው ጠይቀዋል፡፡ በአንጻሩ ከሲኖዶሱ ስብሰባ ቀደም ሲል የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሠራተኞች፣ የገዳማት እና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ጸሐፊዎች እና ካህናት ‹‹ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ወደ ሀገረ ስብከቱ እንዳይመለሱ የሚያሳድም ፊርማ ሲሰበሰብ መቆየቱ›› እና ይኸው ‹‹ጥያቄ›› በፓትርያርኩ ለቅዱስ ሲኖዶሱ በዘገባ መልክ ቀርቦ ውድቅ መደረጉ ይታወሳል፡፡

ስለ ሁኔታው በደጀ ሰላም የተጠየቁ የጉዳዩ ተከታታዮች እንደሚያስረዱት፣ ቅዱስ ሲኖዶስ በትናንትናው ዕለት ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ እና የሲኖዶሱን ማእከላዊ አሠራር በመፃረር ሲፈጸሙ የቆዩትን ተግባራት በመቃወም /በመቀልበስ/ የእርማት ርምጃ ወስዶ ዐቢይ ውሳኔ እንደ ወሰነ ሁሉ፣ በሐምሌ ወር 2001 ዓ.ም በአቡነ ጳውሎስ ውሳኔ ያለአግባብ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስነታቸው የታገዱትን ብፁዕ አቡነ ሳሙኤልን ወደ ሐላፊነታቸው በመመለስ፣ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴውም የተቋቋመለትን ተልእኮ ለማከናወን የሚያስችለውን ሥልጣን መልሶ በማጠናከር ታሪካዊ ውሳኔውን ምሉዕ እንዲያደርገው እና የቅዱስ ሲኖዶሱን ልዕልና እና ክብር ወደ ፍጹማዊነት እንዲያደርሰው ጠይቀዋል፡፡

በ1991 ዓ.ም ተሻሽሎ በጸደቀው ሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት በጳጳሳት ምደባ እና ዝውውር የመጨረሻው ሥልጣን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ነው፡፡ በመሆኑም የመጨረሻውን እና ትክክለኛውን ውሳኔ በነገው ዕለት የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ሲጠናቀቅ የምንመለስበት ይሆናል፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን፡፡ አሜን።
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)