October 14, 2010

አቡነ ፋኑኤል እና ሥራ አስኪያጁ ከሐላፊነታቸው እንዲነሡ የተቀጣጠለው ተቃውሞ በዲላም ተጠናክሮ ቀጥሏል

  •  አጣሪ ኮሚቴው የዲላውንም ችግር አጥንቶ የመፍትሔ ሐሳብ እንዲያቀርብ ታዟል
  • ‹‹ችግሩ ከጥቅምቱ ሲኖዶስ በፊት ካልተፈታ አስከፊ ሁኔታ ሊከተል ይችላል››   (አቤቱታ አቅራቢ ምእመናን) 
  •  አቡነ ፋኑኤል በ‹‹ሥነ ሥርዓት አስከባሪ›› ስም ባደራጇቸው 400 ቴኳንዶዎች ይጠበቃሉ
  • ‹‹ለሰው ይቅርና የምትችሉ ከሆነ ለመድኃኔዓለም እንኳ ብታመለክቱ እኔ አልፈራም!›› (አቡነ ፋኑኤል)
(ደጀ ሰላም፤ ኦክቶበር 14/2010፤ ጥቅምት 4/2003 ዓ.ም):- በሲዳማ ጌዴኦ አማሮና ቡርጂ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ሀገረ ስብከት በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ የሚገኙ የስድስት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ምእመናን፣ ‹‹ቃለ ዐዋዲውን በመጣስ የምእመኑ ውክልና የሌላቸውን ግለሰቦች በሰበካ ጉባኤ አባልነት እያስቀመጡ፣ የልማት ከሚቴዎችን እያፈረሱ፣ በነውረኛ ተግባራቸው የተነሣ ምእመኑ ከየደብሩ የሚያባርራቸውን ማዕርገ ክህነታቸው በውል የማይታወቅ አለቆችን በመመደብ በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ላይ በደል አድርሰዋል፤ የቤተ ክርስቲያንን ሀብት እና ንብረት እየዘረፉ ዕድገቷን እና ልማቷን አቀጭጨዋል፤ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ገዷቸው በየጊዜው አቤቱታ የሚያቀርቡ ምእመናንን በጥቅም እየደለሉ ባደራጇቸው ቡድኖች በማሰደብ እና በማንጓጠጥ አስፈራርተዋል፤ ብስለት የሚጎድላቸውን ሰባክያን በመመደብ ነዋሪው በእምነት ልዩነት እርስ በርሱ እንዲጋጭ የሚያነሣሣ፣ ምእመኑን የሚከፋፍል ቅሰቀሳ አካሂደዋል›› ያሏቸው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፋኑኤል እና ጉዳይ አስፈጻሚያቸው የሆኑት የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሕይወት ፀሐይ መልአኩ በየደረጃው ከሚገኙ ሌሎች ግብር አበሮቻቸው ጋራ የፈጸሟቸው አሳዛኝ እና አሳፋሪ ድርጊቶች ተጣርተው ከሐላፊነታቸው እንዲነሡ፣ በምትካቸውም ምእመኑን ሳይከፋፍሉ አስማምተው በመንፈሳዊ እና ሞያዊ ብቃት የሚመሩ ሐላፊዎች እንዲመደቡ የሚጠይቅ አቤቱታ አቀረቡ፡፡ ቀደም ሲል የሐዋሳ ከተማ ምእመናን በሊቀ ጳጳሱ፣ በሥራ አስኪያጁ እና ሌሎች የግብር አበሮቻቸው ላይ ባቀረቡት ተደጋጋሚ አቤቱታ መነሻነት በሀገረ ስብከቱ እና በሥሩ በሚገኙ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር መካከል የተፈጠረውን ችግር የሚያጣራ ኮሚቴ የሠየመው የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት፣ በዲላ ከተማ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን የተከሠተውም ችግር በኮሚቴው ተጣርቶ ይቀርብለት ዘንድ አዝዟል፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በቁጥር 10/57/2003 በቀን 2/2/2003 ዓ.ም ለአጣሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ ለሆኑት የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በጻፈው እና ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት፣ ለሲዳማ ጌዴኦ አማሮና ቡርጂ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት እንዲሁም ለጌዴኦ ዞን አስተዳደር ጽ/ቤት ግልባጭ ባደረገው ደብዳቤ በተለያዩ ምክንያቶች የማጣራቱ ሥራ ሳይከናወን በመጓተቱ የአቤቱታ አመልካቾች ቁጥር እየጨመረ እንደመጣ ገልጧል፡፡ በሀገረ ስብከቱ እና በሥሩ በሚገኙት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን የተከሠተውን ችግር አንድ በአንድ በመያዝ፣ ገዳዩ የሚመለከታቸውን ሁሉ በማነጋገር ከሚገባው የመፍትሔ ሐሳብ ጋራ በአስቸኳይ እንዲያቀርብ ያዘዘው ደብዳቤው ኮሚቴው በሐዋሳ የፍትሕ እና ልማት ኮሚቴ አባላት የቀረበውን ባለዘጠኝ ገጽ አቤቱታ፣ በዲላ ከተማ ምእመናን የቀረበውን ባለሰባት ገጽ አቤቱታ ‹‹እንደ መነሻ በመጠቀም ጭምር›› የማጣራቱን ሥራ እንዲያከናውን አሳስቧል፡፡

‹‹የቤተ ክርስቲያናችን ዕድገት የእኛም ዕድገት ነው፤ የቤተ ክርስቲያን ልማት የእኛም ልማት ነው፤ ለቤተ ክርስቲያናችን ደኅንነት እና ልማት ሳናሰልስ እንሠራለን፤ ይህን እንድናደርግ ክርስቲያናዊ ሕይወታችን ያስገድደናል›› ያሉት በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ ነዋሪ የሆኑት የስድስት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ምእመናን መስከረም ዘጠኝ ቀን 2003 ዓ.ም ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ባቀረቡት ባለሰባት ገጽ አቤቱታ ‹‹በአሁኑ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን በእውነተኛው ሃይማኖታዊ መንገድ እየተመራች ነው ወይስ የማስመሰል ተግባር እየተፈጸመባት ነው?›› የሚለውን ኀዘናቸውን እንዲመለከቱላቸው ተማፅነዋል፡፡ ሐምሌ 12 ቀን 2002 ዓ.ም ለአቡነ ፋኑኤል 15 ነጥቦችን የያዙ ጥያቄዎችን በጽሑፍ እና በቃል ባመለከቱት መሠረት  ሕዝቡ ተሟልቶ ሊገኝ በማይችልበት ነሐሴ 22 ቀን 2002 ዓ.ም ከሥራ አስኪያጁ ጋራ እንደ መጡ በአቤቱታቸው የጠቀሱት ምእመናኑ፣ ሊቀ ጳጳሱ ከአንድ መንፈሳዊ አባት በማይጠበቅ ወደፊትም በማንም መደገም የማይገባውን የመከፋፈል እና የመለያየት ሥራ መሥራታቸውን ገልጸዋል፡፡ ‹‹አስፈላጊውን የምወስነው እኔ ነኝ›› በሚል ጥቂቶች በተገኙበት ስብሰባውን የመሩት አባ ፋኑኤል፣ ‹‹ተቃዋሚ በዚህ ጎራ ተቀመጥ፤ ካህናትም በተለያዩ ጎራዎች ተቀመጡ፤ ዲያቆናት እና ሰባክያን በዚያ ጎራ ተቀመጡ፤ ሴቶችም እንደዚሁ ተከፋፍላችሁ በተለያየ ጎራ ተቀመጡ፤ የሰንበት ት/ቤት አባላት ለብቻ ሁኑ›› በማለት በካህናት እና በምእመናን እንዲሁም በምእመኑ መካከል ልዩነት የሚፈጥር አካሄድ መከተላቸውን አስረድተዋል፡፡

በስብሰባው ላይ ቀደም ሲል በጽሑፍ ለሊቀ ጳጳሱ የተላኩት ጥያቄዎች በንባብ ተሰምተዋል፡፡ ከጥያቄዎቹ መካከል አቡነ ፋኑኤል በቅድስት ሥላሴ ገዳም እና በዳማ ቅዱስ ጊዮርጊስ አብያተ ክርስቲያን ልማት እና ለአገልጋይ ካህናቱ ኑሮ መሻሻል ታስቦ የተቋቋመውን ሕንጻ አሠሪ ኮሚቴውን በማፍረስ በራሳቸው ያለ ሕዝቡ ውክልና በሰበካ ጉባኤ አባልነት ባስመረጧቸው ግለሰቦች እንዲመራ መመሪያ መስጠታቸው፣ ከቃለ ዐዋዲው በተፃራሪ ምእመኑ ሳይመርጣቸው የተቀመጡት ግለሰቦችም ‹የልማት ኮሚቴው ወደፊት ይቋቋማል› በሚል የልማት ኮሚቴውን አፍርሰው ራሳቸው ገንዘብ ሰብሳቢ፣ ራሳቸው ዕቃ ግዢ፣ ራሳቸው ዕቃ አቅራቢ፣ ራሳቸው ገንዘብ አስገቢ እና አውጪ በመሆን የቤተ ክርስቲያኒቷን ሀብት ለብክነት መዳረጋቸው ይገኝበታል፡፡

በስብሰባው ላይ ሊቀ ጳጳሱ የእርሳቸውን ሐሳብ ለሚደግፉ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ የሰንበት ት/ቤት አባላት፣ ሰባክያን፣ ከምእመናንም ለሁለት ሰዎች ብቻ ዕድል በመስጠት ሕዝቡ ለቤተ ክርስቲያን ጠቃሚ በሆኑ ሐሳቦች ዙሪያ እንዳይወያይ በመከልከል የመናገር እና በነጻነት የመወያየት መብቱን አፍነዋል፡፡ በምትኩ ጉዳይ የሚያስፈጽሙላቸውን የሁለቱን አብያተ መቅደስ አስተዳዳሪ፣ የስብከተ ወንጌል ሐላፊ እና ሌሎች ካህናትን ተራ በተራ በማስነሣት በበጎ አድራጎታቸው የተከበሩትን የ27 ዕድሮች የሕዝብ ሽማግሌዎች እንዲሰደቡ፣ እንዲንጓጠጡ አስደርገዋል፤ ‹‹በመንግሥት ደኅንነት ትያዛላችሁ›› በሚል ዛቻም አስፈራርተዋል፡፡ ለስብከተ ወንጌል ሳይበቁ ዐውደ ምሕረቱን የጠሉትን የመሳደቢያ፣ የጠቀማቸውን የማወደሻ መድረክ ያደረጉ ዋልጌዎች በድምፅ ማጉያ ተጠቅመው የሌሎችን እምነት በማንኳሰስ በሰላም ተከባብሮ በኖረው ሕዝብ መካከል ግጭት ለማስነሣት ሞክረዋል፡፡ ተንኳሽ ቅስቀሳውን ያደረጉት ሰባኪ ነን ባዮች በአሁኑ ወቅት በፍርድ ቤት ክስ ተመሥርቶባቸው ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ ቢሆኑም በአቡነ ፋኑኤል ፊት የተፈጸመው ደንታ ቢስ እና አሳፋሪ ወንጀል ከዚህ በፊት በስፍራው ተፈጽሞ እንደማያውቅ ምእመናኑ በአቤቱታቸው ዘርዝረዋል፤ ‹‹ከሕዝብ አፈንግጠው ወዴት ለመሄድ ያስባሉ?›› በማለትም ጠይቀዋል፡፡ ሥራ አስኪያጁ መልአከ ሕይወት ፀሐይ መልአኩም በሌሎች ወረዳዎች በሥነ ምግባር ብልሹነታቸው ሳቢያ በምእመኑ የጋራ ውሳኔ የተባረሩትን፣ በአንዱ ደብር ዲያቆን በሌላው ደብር ቄስ ነን በማለት የሚያጭበርብሩ አለቆችን በፈጠሩት የጥቅም ትስስር በሁለቱ አብያተ መቅደስ ላይ በአስተዳዳሪነት በመሾም የቤተ ክርስቲያኑን ሀብት ለብክነት በመዳረጋቸው ከፍተኛ በደል እንደፈጸሙባቸው ተገልጧል፡፡ በዚሁ ስብሰባው ላይ ሥራ አስኪያጁ ሊቀ ጳጳሱን በመከተል አቤቱታ አቅራቢዎችን ሲሳደቡ እና ሲያንጓጥጡ ውለዋል፡፡

ቀደም ሲል የሐዋሳ ምእመናን ለመንበረ ፓትርያርኩ ባቀረቡት አቤቱታ፣ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ በመኖርያ ቤት ውድነት በምትታወቀው ሐዋሳ ከአንድም ሁለት የመኖርያ ቤቶችን ሠርተዋል፤ ግልጽነት በጎደለው አኳኋን ልጆቻቸውን በሀገረ ስብከቱ የተለያዩ መዋቅሮች ውስጥ አስቀጥረዋል፤ ያለሰበካ ጉባኤ የሚተዳደረውን የቅዱስ ሩፋኤልን ቤተ ክርስቲያን ምእመናንን፣ ‹‹ስለ ገንዘብ እና ጉልበት አስተዋፅኦ እንጂ ስለ አስተዳደሩ አያገባችኹም›› በማለት የግለሰቦች መጠቀሚያ አድርገውታል፤ በቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ያለሰበካ ጉባኤው ዕውቅና ንብረቱ እንዲሸጥ ወስነዋል፤ ከሰበካ ጉባኤው ዕውቅና ውጭ ቅጥር በመፈጸም ካህናቱን፣ ‹‹የቀጠርኳችኹ እኔ ነኝ፤ ላነሣችኹም ሥልጣን አለኝ›› እያሉ ተጽዕኖ ያደርጋሉ፤ የደብር አስተዳዳሪዎችን በሐሰተኛ መረጃ በመክሰስ ያስፈራራሉ፤ የሥራ ሞራላቸውን ይጎዳሉ፤ ግራ ያጋባሉ፤ በደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም በቃለ ዐዋዲው መሠረት እና በጠቅላላ ጉባኤው የተመረጡትን የሰንበት ት/ቤቱን አመራሮች በመበተን፣ ከዓላማ እና የጥቅም አጋሮቻቸው ጋራ የሰንበት ት/ቤቱን ቁልፍ በመሮ ሰርስሮ በመሥበር እና በሌላ ቁልፍ በመቀየር ቀደም ሲል ከሰንበት ት/ቤቱ የታገዱ ሰዎችን አስገብተው እንዲተኩ አድርገዋል፤ አቤቱታ ያቀረቡ የምእመናን ተወካዮችን ‹‹ፀረ ሰላም፣ የዐመፅ እና የሽብር ኀይሎች ናቸው›› በማለት በአደባባይ ወንጅለዋል፡፡

በአንጻሩ ቀደም ሲል በነበሩት ሊቀ ጳጳስ እና በራሳቸው በሥራ አስኪያጁ ፊርማ ከአገልግሎት የታገደውን፣ የሐዋሳ ቅድስት ሥላሴን ማኅተም እንዲሁም ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ያሉ ግለሰቦችን እና ተቋማትን የሐሰት ማኅተም ተጠቅሞ ገንዘብ በመሰብሰብ ሕገ ወጥ ጉባኤ ለማካሄድ የተንቀሳቀሰውን ራሱን ‹‹ተስፋ ኪዳነ ምሕረት ፀረ - ኤድስ ማኅበር›› እያለ የሚጠራውን አካል ተመስጋኝ የልማት ተቋም አድርጎ በማቅረብ ምእመኑ ከእርሳቸው ጋራ እንዳለ ለማስመሰል እና ያደረሱትን አስተዳደራዊ በደል ለመሸፈን ተንቀሳቅሰዋል፡፡ በመሆኑም ላለፉት አራት ዓመታት በሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ እና በተባባሪዎቻቸው የሚፈጸመው ከፍተኛ የኾነ አስተዳደራዊ በደል እና የቤተ ክርስቲያን ገንዘብ ምዝበራ ሥር መስደዱን እና አስከፊ ደረጃ ላይ መድረሱን በመግለጽ ከሐላፊነታቸው እንዲነሡ የሐዋሳ ምእመናን አቤቱታ አቅርበው እንደ ነበር ይታወሳል፡፡

‹‹ዝምታን የመረጠ አእምሮ መፍትሔን አያመነጭም›› በሚል መርሕ አቤቱታቸውን በእውነተኛ እና በበቂ ማስረጃዎች ላይ አስደግፈው እንዳቀረቡ የገለጹት የዲላ ከተማ ምእመናን፣ ‹‹ሰማይን የማረስ ጳጳስን የመክሰስ የነገር አቁማዳ›› ይዘው እንዳልተነሡ አስገንዝበዋል፡፡ ይልቁንስ ‹‹የአቡነ ፋኑኤል አስተዳደር በቃለ ዐዋዲው ደንብ እና መመሪያ ላይ ሳይሆን በራሳቸው ውድ እና ፈቃድ ላይ ተመሥርቶ የሚመራ ሆኖ ስላገኘነው፣ ከእንግዲህ ከሊቀ ጳጳሱ ጋራ አንድ አድርጎ እና አስማምቶ የሚያሠራን መንገድ አይኖርም፡፡ ስለሆነም ከሊቀ ጳጳሱ ጀምሮ የግብር አበሮቻቸው ሁሉ የፈጸሙት አሳዛኝ ድርጊት በቅዱስነትዎ በኩል በሚሠየመው አጣሪ ልኡክ ተጠንቶ ከሓላፊነታቸው እንዲነሡ፣ በምትካቸው አስታርቀው እና አስማምተው በመንፈሳዊ እና ሞያዊ ብቃት የሚመሩን አባቶች እንዲመደቡልን እንጠይቃለን›› ብለዋል፡፡

ምእመናኑ ይህን መሰሉን አቤቱታ በቆይታ ለበላይ አካል እንደሚያቀርቡባቸው የተረዱት አቡነ ፋኑኤል የእብሪታቸውን ልክ ምናልባትም የእምነታቸውን ጤናማነት በውል በሚያሳይ አኳኋን የሚከተለውን ዐረፍተ ነገር በስብሰባው ላይ መናገራቸው በምእመናኑ አቤቱታ ላይ ተመልክቷል - ‹‹እንኳንስ ለሰው ይቅርና የምትችሉ ከሆነ ለመድኃኔዓለም ብታመለክቱ እኔ አልፈራም፡፡›› ይህን ተከትሎ ምእመናኑ በአቤቱታቸው የመጨረሻ መሥመሮች ላይ ባሰፈሩት ቃል ደግሞ ከሚከተለው ውሳኔ ላይ ደርሰዋል - ‹‹ጳጳሱ ራሳቸውን ከመድኃኔዓለም ጋራ አወዳድረው እኛን አመልካቾችን ማፌዣ እና ማላገጫ አድርገውናል፤ ይህን በማድረጋቸው እኛም ከእርሳቸው አባትነት ርቀናል፡፡››

የሀገረ ስብከቱን ወቅታዊ ሁኔታ በአጠቃላይ የሊቀ ጳጳሱን የቀን ተቀን ብልሽት በተለይ በቅርበት የሚከታተሉ የሐዋሳ እና አንዳንድ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምንጮች አቡነ ፋኑኤልን ከዚህ መሰሉ እብሪት ሊያደርሳቸው የሚችለውን መንሥኤ ይናገራሉ፡፡ እንደምንጮቹ መረጃ ብልሽቱ አቡነ ፋኑኤል በመጪው ጥቅምት በወሳኝ መልኩ እንደሚካሄድ በሚጠበቀው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በሀገረ ስብከቱ እንደማይቀጥሉ ሊወሰን እንደሚችል ዐውቀው/ ተነግሯቸው በቀቢጸ ተስፋ የሚያደርጉት መወራጨት ሊሆን ይችላል፡፡ ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች ደግሞ የአቡነ ፋኑኤል (የቀድሞው አባ መላኩ) ብልሽት የአሁን ሳይሆን የሊቃነ ጳጳሳቱ ልብስ ሰፊ ሳሉ ጀምሯቸው በሀገረ አሜሪካ ሥር የሰደደ መሆኑን ያስታውሳሉ፡፡ ‹‹በሙግት መኖር እንደሆነ የኖርኩበት ነው፤ ሲሻችሁ በቺቺ መጫረስ ትችላላችሁ፤ በቺቺ ተጫረሱና እኔ ከአሸናፊው ጋራ እሆናለሁ›› ማለት የለመደባቸው ማኬቬሊያዊው አቡነ ፋኑኤል ከዜግነታዊ ማንነታቸው አንሥቶ ክስ ያልተለያቸው ናቸው፡፡

በአሜሪካዊ ዜግነታቸው የሚኮፈሱት አቡነ ፋኑኤል በሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ዐውደ ምሕረት ላይ፣ ‹‹ይሞታል ወይ ታዲያ! ስለ ራሴም ዝና እናገራለሁ፤ እኔ አሜሪካ ሄጄ በሊሞዚን መሽሞንሞን እችላለሁ፤ በችግር የምትቆራመደው አንተ ነህ!!›› በማለታቸው የማያፍሩ ናቸው፡፡ ሊቀ ጳጳሱ በየወሩ የቅዱስ ሚካኤል በዓል ዕለት ከአሜሪካው የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ምእመናን  ገንዘብ እንደሚሰበሰብላቸው/ እንደሚዋጣላቸው፣ መዋጮውንም ‹‹በሐዋሳ የካህናት ማሠልጠኛ ውስጥ ለምረዳቸው አሳዳጊ አልባ ሕፃናት አውለዋለሁ›› በሚል እንደሚሰበስቡ ተነግሯል፡፡ ዶላሩን ለማጋበስ የማስመሰያ ቪዲዮ እያቀናበረ የሚረዳቸውም በሥራ አስኪያጁ የድጋፍ ደብዳቤ የሐዋሳ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ሰብሳቢ የሆነው ዓለምነህ ሽጉጤ (እርሳቸው በኲረ ትጉሃን የሚል ማዕርግ የሰጡት የተስፋ ኪዳነ ምሕረት ፀረ ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠርያ ማኅበር አመራር) የተባለ ግለሰብ ነው፡፡

አቡነ ፋኑኤል በሀገረ አሜሪካ ያካበቱትን እና በአንዳንድ ጳጳሳትም ዘንድ ሳይቀር ‹‹በእናት ቤተ ክርስቲያን ሥር ነን›› እያሉ ንብረትነታቸው ግን የሊቃነ ጳጳሳቱ የግላቸው በማድረግ የመቀሸብ ልምድ በሐዋሳ የካህናት ማሠልጠኛ እና በውስጡ በሚገኘው የቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን ላይም እያስፋፉት ይገኛሉ፡፡ ንቁህ እና ትጉህ የሀገረ ስብከቱ አገልጋዮች እና ምእመናን እንደሚያውቁት ጠቅላይ ቤተ ክህነት ለማሠልጠኛው በየዓመቱ 50‚000 ብር በጀት ይመድባል፤ የት እንሚገባ፣ ምን እንደሚሠራበት የሚያውቅ የለም እንጂ፡፡ በቅጽሩ የሚገኘው የቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያንም ሰበካ ጉባኤ ሳይቋቋምበት የሥራ አስኪያጁ መልአከ ሕይወት ፀሐይ መልአኩ እና ሀገረ ስብከቱን አየር ባየር እንደሚመራ የሚነገርለት የያሬድ አደመ መጠቀሚያ እንደሆነ ነው የሚነገረው፡፡ ይህን አስመልክቶ ጥያቄ የሚያቀርቡ ምእመናንም ‹‹ስለ ገንዘብ እና ጉልበት አስተዋፅኦ እንጂ ስለ አስተዳደሩ አያገባችኹም›› የሚል ምላሽ በሥራ አስኪያጁ እንደተሰጣቸው የሐዋሳ ምእመናን ባለፈው ዓመት ባቀረቡት አቤቱታ ላይ ተመልክቷል፡፡

የማፊያው ቡድን በቤተ ክርስቲያን ላይ ስለሚፈጥረው ችግር የተቆርቋሪ ምእመናን አቤቱታ ሲቀርብላቸው ‹‹ሲፈልግ ለምን እሳት አይለቅባትም›› ከማለት አንደበታቸውን ያልመለሱት አቡነ ፋኑኤል ለምእመኑ የሚያሳዩት ንቀት ምናልባትም በታሪክ የሚታወሱበት ሌላው ብልሽታቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ሥራቸውን ትተው፣ ቤታቸውን ዘግተው ስለ ቤተ ክርስቲያን ችግር የሚንከራተቱ የሐዋሳ ምእመናን ተወካዮች እግራቸው ሥር ወድቀው በልቅሶ ቢለምኗቸው፣ ‹‹ዘወር በል፤ በልቅሶ የሚሆን ነገር የለም፤ የአዋሳን ምእመን እንዲህ የሚያደርገው'ኮ ወንጌል overdose ሆኖበት ነው›› በማለት የግብረ በላዎቻቸውን ድምፅ የሚያሰማ ኀይለ ቃል ተጠቅመዋል፡፡ ይህም ሳይበቃቸው የሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ምእመናን የሰበካ ጉባኤው ምርጫ በቃለ ዐዋዲው መሠረት እንዲካሄድ ያቀረቡትን ተቃውሞ ችላ ብለው በራሳቸው የመረጧቸውን እምነት የማይጣልባቸው ግለሰቦች ካስቀመጡ በኋላ፣ ‹‹የሕዝቡን ጫጫታ እንደ ሳውንድ ትራክ ተጠቅመን ሥራችንን ሠርተናል›› በማለት መሣለቃቸው ተሰምቷል፡፡

ከዚህ በመለስ በመንበረ ጵጵስናው ለመናገር የሚያሳፍር አጸያፊ ተግባር እየተፈጸመ መሆኑ በሐዋሳ ምእመናን ፊት ያለ የዕለት ተዕለት እውነታ ነው፡፡ መንበረ ጵጵስናውን ከሚያረክሱት ዋናው ደግሞ ‹አቡነ› የሚል የፌዝ ቅጽል በሕዝቡ የተሰጠው ያሬድ አደመ ነው፡፡ ከዲላ ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ እስከ ዱባይ ድረስ የቤተ ክርስቲያንን አሐቲነት በማናጋት የሚታወቀው ያሬድ አደመ በሀገረ ስብከቱ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ጸሐፊ ሆኖ ከተቀጠረ በኋላ ቀድሞም አየር ባየር የሚመራውን የአቡነ ፋኑኤልን ብልሹ አመራር በውክልና እስከ መረከብ (እርሳቸው በሕዝብ ገንዘብ ወዳሠሩት የአዲሳ'ባ ቪላቸው ሲሄዱ) መድረሱ እየተገለጸ ነው፡፡ ከተግባሮቹ ዋነኛውም የቴኳንዶ ሥልጠና የወሰዱ፣ ከሀገር ውስጥ እና ከባሕር ማዶ በዝርፊያ ከሚገኘው የቤተ ክርስቲያን ሀብት ጥቅም የሚቋደሱ 400 የከተማውን ወጣቶች ባለ አረንጓዴ ቢጫ እና ቀይ ቀለም ዩኒፎርሞችን በማልበስ ‹‹ሥነ ሥርዐት አስከባሪ›› የሚል ባጅ ተለጥፎላቸው በውስጥ እና በዐውደ ምሕረት አገልግሎት ወቅት ጠረጴዛን እንደ ማገጃ /physical barrier/ በመጠቀም ጭምር አቡነ ፋኑኤልን እንዲጠብቁ፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን አቤቱታ የሚያቀርቡ ምእመናንን እንዲያሳድዱ ነው፡፡ አቡነ ፋኑኤል ስለ እነዚህ የግል ‹አንጋቾቻቸው› ባለፈው ዓመት እነያሬድ አደመ በደነፉበት ያልተሳካው የመስቀል አደባባይ ስብሰባ ወቅት ፍንጭ ሰጥተው እንደነበር የከተማው ምእመናን ያስታውሳሉ፡፡ በወቅቱ አቡነ ፋኑኤል በአደባባዩ እንዲህ ብለው ነበር - ‹‹መንግሥት የራሱን ወታደር አሠማርቶ እነዚህን ሰዎች (የሐዋሳ የፍትሕ እና ልማት ኮሚቴ አባላት) የማይቆጣጠር ከሆነ እኔ የራሴን ሚልሻ እመለምላለሁ፡፡›› በአንዳንዶች አስተያየት አቡነ ፋኑኤል እና የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ቀኝ እጃቸው ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ አቤቱታ የሚያቀርቡ ምእመናንን ‹‹በመንግሥት ደኅንነት ትያዛላችሁ›› እያሉ የሚያስፈራሩት እኒህን ‹‹ቅልጥም ሰባሪ›› ቴኳንዶዎቻቸውን ተጠቅመው ካልሆነ በቀር መንግሥት የሐዋሳ ፍትሕ እና ልማት ኮሚቴ አባላት የሰላም ኀይሎች መሆናቸውን በውል ይገነዘባል ተብሎ ይታመናል፤ መገንዘብ ብቻ ሳይሆን ሊቃና የማይችል ሁለንተናዊ ብልሽት ውስጥ የተዘፈቁትን ‹የጎበዝ አለቆች› ወደ ተካረረ ቅራኔ ውስጥ እየገባ የመጣው ስድስት ወራትን ያስቆጠረው የምእመኑ ኀዘን እና ልቅሶ ከስትራቴጂ አንጻር የአጥቂነት አሰላለፍ ይዞ የማያዳግም ምቱን ሳያሳርፍባቸው በፊት ‹‹በቃ ማለት በቃ ነው›› ሊላቸው ይገባል፡፡ ምእመናኑንም ችግሩ በያዝነው ወር አጋማሽ ላይ ከሚካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በፊት ካልተፈታ ቀደም ሲል ወደ መንበረ ፓትርያርኩ ከተመመው ምእመን በላይ የሆነ ሕዝባዊ ንቅናቄ እንደሚፈጥሩ፣ አቡነ ፋኑኤል እና ሌሎች ግብረ አበሮቻቸው በሀገር ውስጥ እና በውጭ የፈጸሟቸውን ቅሌቶች የሚያሳዩ በእጃቸው የሚገኙ ማስረጃዎችን ይፋ እንደሚያደርጉ ነው ያስታወቁት፡፡

የሀገረ ስብከቱን ችግሮች እንዲያጣራ በብፁዕ ወቅዱስአቡነ ጳውሎስ ፊርማ የተሠየመው አጣሪ ኮሚቴም ለኅሊናው እና ለቤተ ክርስቲያኒቱ ክብር ሲል በሐቅ እንዲሠራ ለደጀ ሰላም አስተያየታቸውን የሰጡ ምእመናን ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡ እንደ ምእመናኑ አስተያየት አቡነ ፋኑኤል ከወዲሁ፣ ‹‹የአጣሪ ኮሚቴው አባላት ጓደኞቼ ናቸው፤ እኔ ከእነርሱ ጋራ ቀደም ብዬ ጨርሻለሁ፤ ዝም ብለው ነው የሚደክሙት. . .›› በማለት በተለይ የሀገረ ስብከቱ እና ከፍተኛ ምዝበራ የተፈጸመባቸው አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን የሒሳብ ሪፖርቶች እንዳይመረመሩ የሚያደርጉትን መከላከል እና አስተያየትን የማዛባት አሉባልታ ኮሚቴው ተረድቶ በዲላ ይሁን በሐዋሳ እስከ አጥቢያ ድረስ ወርዶ ማጣራት እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ያለው ምእመንም በጸሎት እንዲያስባቸው ተማፅነዋል፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)