October 28, 2010

ቅዱስ ሲኖዶስ በጳጳሳት ምደባ እና ዝውውር ጉዳይ በፓትርያርኩ በቀረበው ሐሳብ ላይ ውሳኔዎችን ሰጠ

  •  በውጭ የሚገኙት ሊቃነ ጳጳሳትን በተመለከተ የቀረበው የዝውውር ሐሳብ፤
  •  ‹‹ቅንነት የጎደለው እና የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የሚያናጋ›› በሚል ሙሉ በሙሉ ውድቅ ተደርጎ ባሉበት እንዲቀጥሉ ተወስኗል፤
  •  ፓትርያርኩ ብፁዕ አቡነ አብርሃምን ‹‹ብጠራቸው አልመጡም›› በማለት ስሞታ አቅርበውባቸዋል፤
  •  ‹‹ስለ ቤተ ክርስቲያን ሰላም ስል የእናንተን የአባቶቼን ሐሳብ እቀበላለሁ›› (ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል)፤                                      
  •  ‹‹ከእርሳቸው ጋራ አብሬ መሥራት አልችልም›› (አቡነ ጳውሎስ)፤
  •  ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሦስት ሊቃነ ጳጳሳት በዕጩነት ይቀርባሉ፤
  •  አቡነ ፋኑኤል የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ማሠልጠኛ ኮሌጅ የበላይ ሐላፊ  ሆነው ተመድበዋል፤
  •  በጋሻው ደሳለኝ፣ ያሬድ አደመ እና ቲፎዞዎቻቸው ከአቡነ ፋኑኤል ውጭ የሚደረገውን አዲስ ምደባ በመቃወም ብጥብጥ ለማስነሣት ቅስቀሳ በማድረግ ላይ  ናቸው፤
(ደጀ ሰላም፤ ኦክቶበር 28/2010፤ ጥቅምት 18/2003 ዓ.ም):- በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው እና የመንበረ ሐዋርያት ወራሽ የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ ግንቦት 10 ቀን 1991 ዓ.ም ባጸደቀው እና በሥራ ላይ በሚገኘው ሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ ሰባት ንዑስ አንቀጽ 13 መሠረት፣ ሊቃነ ጳጳሳትን እና ኤጲስ ቆጶሳትን በየሀገረ ስብከቱ እና በተለያዩ የሥራ ክፍሎች የመመደብ እና በበቂ ምክንያት የማዘዋወር ሙሉ ሥልጣን ተሰጥቷል፤ የሚሰጠው ውሳኔም የመጨረሻ እና በሌሎች ሕጎች እና አሠራሮች ሊሻር፣ ሊለወጥ የማይችል ነው፡፡

ትናንት ከሰዓት በኋላ ቅዱስ ሲኖዶስ በቋሚ ሲኖዶስ ምክክር እንደተደረገበት የተነገረለት የሊቃነ ጳጳሳት ዝውውር እና ምደባ ጉዳይ በፓትርያርኩ ቀርቦ እስከ ማምሻው ድረስ ከፍተኛ ክርክር እንደተደረገበት፣ መቋጫም ሳያገኝ ለዛሬ በይደር መቆየቱ መዘገቡ ይታወሳል፡፡ የዜና ዘገባውን ተከትሎ በተለይ በብፁዕ አቡነ አብርሃም እና በብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የቀረበው የዝውውር እና የምደባ ሐሳብ ኀዘንም ቁጣም ቀስቅሷል፤ መግለጫም ወጥቶበታል፡፡ አቡነ ፋኑኤልን በተመለከተ ከምእመናን ጋራ ወደማይገናኙበት መምሪያ ወይም ድርጅት እንዲዛወሩ በስሜት ጭምር ሐሳባቸውን የገለጹ ብዙዎች ናቸው፡፡

ዛሬ ከሰዓት በፊት ቅዱስ ሲኖዶስ ባደረገው ስብሰባ ከኢትዮጵያ ውጭ በሚገኙት አህጉረ ስብከት በሐላፊነት በሚገኙት ሊቃነ ጳጳሳት ዝውውር ላይ በአቡነ ጳውሎስ የቀረበውን የማዘዋወር ሐሳብ ሙሉ በሙሉ ውድቅ አድርጎታል፡፡ እንደ ሲኖዶሱ ምንጮች ገለጻ ምልአተ ጉባኤው፣ ‹‹ሦስቱም ሊቃነ ጳሳሳት ዝውውር ይሰጠን ብለው ያቀረቡት ጥያቄ እስከሌለ፣ ጥያቄውም የቀረበበት መንገድ ቅንነት የጎደለው በመሆኑ፣ ይህም ለቤተ ክርስያኒቱ አንድነት መልካም ውጤት ስለማይኖረው እነርሱን በተመለከተ የምናየው ጉዳይ የለም›› በማለት ብፁዕ አቡነ አብርሃም በዋሽንግተን ዲ.ሲ እና አካባቢው፣ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ በደቡብ አውሮፓ እና ብፁዕ አቡነ ማቲያስ በካናዳ አህጉረ ስብከት ባሉበት እንዲቀጥሉ ወስኗል፡፡ ይሁንና በግንቦቱ የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ አሁን በጉባኤው ያልተገኙት አባቶች በአካል ባሉበት ውይይት ተደርጎ ይዘዋወሩ ወይም ባሉበት ይጸኑ እንደ ሆነ ቢወሰን ለቤተ ክርስቲያን አንድነት እና ሰላም እየተደረገ ያለውን ጥረት እንደሚያጠናክር በምልአተ ጉባኤው ሙሉ ስምምነት ተደርሶበታል፡፡

በአገር ውስጥ፣ የዝውውር እና ምደባ ጥያቄ ባቀረቡት እንዲሁም አለመግባባት በተከሠተባቸው አህጉረ ስብከት የሽግሽግ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ በዚህም መሠረት እስከ አሁን መረጃው በደረሰን ሰባት አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት ምደባ እና ዝውውር ላይ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ እነርሱም፡-
     1) ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል - የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን የበላይ ሐላፊ፤
ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል
   2) ብፁዕ አቡነ ገብርኤል - የሲዳማ አማሮ ዞኖች እና ቡርጂ ልዩ ወረዳዎች (ሐዋሳ) ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ (የስዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ማሠልጠኛ ኮሌጅ የበላይ ሐላፊነት የተዛወሩ)፤
   3) ብፁዕ አቡነ ገሪማ    -  የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤
   4) ብፁዕ አቡነ ኢሳይያስ  -  መቐለ  ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ (ከድሬዳዋ የተዛወሩ)፤
   5) ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ - የከምባታ ሐዲያ እና ጉራጌ ዞን አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ (ከወላይታ እና ዳውሮ ዞን አህጉረ ስብከት የተዛወሩ)፤
   6) ብፁዕ አቡነ ሚካኤል - የወላይታ እና ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ (ከሰሜን ምዕራብ ትግራይ ሽሬ እንዳሥላሴ የተዛወሩ)፤
   7) አቡነ ፋኑኤል - የስዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ማሠልጠኛ ኮሌጅ የበላይ  ሐላፊ (ከሐዋሳ የተዛወሩ)፤
ብፁዕ አቡነ ሰላማ
   8) ብፁዕ አቡነ ሰላማ - የሰሜን ምዕራብ ትግራይ ሽሬ እንዳሥላሴን ከአክሱም ሀገረ ስብከት ጋራ ደርበው እንዲያስተዳድሩ

ብፁዕ አቡነ ይሥሐቅ (የባሌ ሀገረ ስብከት)፣ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት)፣ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ (ነገሌ ቦረና ሀገረ ስብከት)፣ ብፁዕ አቡነ ሙሴ(ደቡብ ምዕራብ ሸዋ - ወሊሶ ሀገረ ስብከት) ባሉበት እንዲቀጥሉ ተወስኗል፡፡

ወደ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እንዲዛወሩ የቀረቡት ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ‹‹ዝውውሩ በሌላ ሀገረ ስብከት እንዲለወጥላቸው ለምልአተ ጉባኤው ገልጸዋል›› በመባሉ ለከሰዓት በኋላ ምልአተ ጉባኤው ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሚሆኑ ሦስት ሊቃነ ጳጳሳት በዕጩነት እንዲቀርቡለት ጠይቋል፤ ከሊቀ ጳጳሱም ጋራ ሥራ አስኪያጁም በጥቆማ ቀርቦ የሚወሰንበት ይሆናል፡፡

በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል በማጣራቱ ሂደት ችግር እስካልተገኘባቸው ድረስ ወደነበሩበት መመለስ እንዳለባቸው በመግለጽ በፓትርያርኩ የቀረበውን ሐሳብ በብርቱ በመቃወማቸው ከፍተኛ ክርክር መደረጉ ተዘግቧል፡፡ ይሁንና ፓትርያርኩ ‹‹ከእርሳቸው ጋራ መሥራት አልችልም›› በማለት በግትርነት በመጽናታቸው ሌሎች ብፁዓን አባቶች ብፁዕ አቡነ ሳሙኤልን፣ ‹‹በማጣሪያው ሪፖርት መሠረት አዲስ አበባ ቦታዎ ነው፤ ይገባዎታል፤ ነገር ግን ስለ ቤተ ክርስቲያን ሰላም እና አንድነት ሲሉ ይተውት፤ በኮሚሽኑም የሚሠራው የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ነው" በማለት ስላግባቧቸው ብፁዕነታቸው፣ ‹‹ስለ ቤተ ክርስቲያን ሰላም ስል የእናንተን የአባቶቼን ሐሳብ እቀበላለሁ›› በማለታቸው ለረጅም ጊዜ ሲንከባለል የቆየው ችግር ምዕራፍ የተበጀለት መስሏል፡፡

በተያያዘ ዜና በትናንትናው ዕለት የቤተ ክርስቲያኒቱን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተመለከተ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የሚመለከተው የትምህርት እና ማሠልጠኛ መምሪያ የቤተ ክርስቲያኒቱን ትምህርት በተማረ ባለሞያ ሐላፊነት እንዲመራ፣ ለዚህም መምሪያው ዘመናዊዎቹን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ነባሮቹን የአብነት ትምህርት ቤቶች ጉዳዮች የሚከታተሉ ሁለት ዘርፎች እንዲኖሩት፣ ዘርፎቹም እንደየአግባቡ በሠለጠኑ ምሁራን ሐላፊዎች እንዲመሩ፣ ደቀ መዛሙርቱ በሥነ ምግባር የታነጹ እንዲሆኑ፣ በመምህርነት እና በተማሪ ስም ሰርገው ገብተው በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ መንገድ ተጽዕኖ ከሚያደርጉባቸው አጽራረ ቤተ ክርስቲያን እንዲጠበቁ፣ ወደሚመደቡባቸው አህጉረ ስብከት በመሄድ አገልግሎታቸውን እንዲያጠናክሩ ወስኗል፤ ውሳኔውንም ቋሚ ሲኖዶሱ ተከታትሎ ያስፈጽም ዘንድ አሳስቧል፡፡ ይሁንና ይህ የውሳኔው ቃለ ጉባኤ የተጻፈበት ቀለም ሳይደርቅ በተለይም የቤተ ክርስቲያኒቱ ነባር ትምህርቶች በሚሰጡበት በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ማሠልጠኛ ኮሌጅ የበላይ ሐላፊነት የተመደቡት እና በመስኩ ያላቸው ብቃት አጠያያቂ የሆነው የአቡነ ፋኑኤል ሹመት አነጋጋሪ ሆኗል - ኮሌጁን ለማዘጋት ወይስ በኮሌጁ ባላቸው ሐላፊነት ተጠቅመው አጉራ ዘለል ሰባክያንን እንዲያባዙ ለማድረግ በሚል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ትናንት ማምሻውን ያሬድ አደመ በሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ‹‹ተስፋ ኪዳነ ምሕረት›› በሚል ራሱን ከሚጠራው ቡድን ጋራ በመሆን ‹‹አቡነ ፋኑኤል አባታችን፣ የልማት ጀግናችን ናቸው፤ ከአቡነ ፋኑኤል ውጭ ሌላ ጳጳስ ቢመደብ እንዴት ነው የምንቃወመው?›› በሚል ይዞት በነበረው ዱለታ ሳቢያ ሁከት ተከሥቶ እንደ ነበር ምንጮች ለደጀ ሰላም ገልጸዋል፡፡ እነ ያሬድ በተጠቀሰው ጉዳይ ላይ የሚያደርጉትን የዐመፅ ዝግጅት የተቃወሙ ትምህርት በመከታተል ላይ የነበሩ ቀናዒ ምእመናን ቡድኑ ወደሚዶልበት አዳራሽ በቀጥታ በመግባት ግብግብ ገጥመዋል፡፡ በግብግቡ ጩኸት በመሰማቱ ፖሊስ በአካባቢው ይደርሳል፡፡ የፖሊስ ኀይል በአካባቢው መድረሱን የተረዱት እነ ያሬድም ግብግቡን ትተው በቲፎዞዎቻቸው ታጅበው በአዳራሹ ውስጥ ከቆዩ በኋላ ማምሻውን ‹‹በአንጋቾቻቸው›› ታጅበው ወደየቤታቸው መመለሳቸው ታውቋል፡፡ ዛሬ ከሰዓት በኋላ ለደጀ ሰላም የደረሰው ጥቆማ እንደሚያስረዳው ያሬድ አደመ ‹‹የሀገረ ስብከቱ ጸሐፊ እና የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሐላፊ ስለሆኑ አስፈላጊው ትብብር ይደረገላቸው›› በሚል ከአቡነ ፋኑኤል ደብዳቤ አጽፏል፡፡ ግለሰቡ በመጨረሻው ሰዓት በአቡነ ፋኑኤል ፊርማ እና ማኅተም በዚህ መልክ እንዳጻፈው የተገለጸው የሐሰት ደብዳቤ በቤተ ክርስቲያን ስም በማጭበርበር ጥቅም ለማጋበስ ሊጠቀምበት እንደሚችል በውስጥ ዐዋቂዎች ግምት ተወስዷል፡፡

‹‹ለአዘዞ ቅድስት ማርያም ገቢ አሰባስባለሁ›› በሚል በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ላልተፈቀደ የ‹‹ስብከተ ወንጌል ጉባኤ›› ከሄደበት አዘዞ እና ጭልጋ ወረዳዎች በቀናዒ የቤተ ክርስቲያን ወጣቶች መድረሻ እስኪያጣ ድረስ በውርደት የተባረረው በጋሻው ደሳለኝም፣ ‹‹የሐዋሳን ሕዝበ ክርስቲያን አስታርቃለሁ፤ ከእንግዲህ በፍቅር እናገልግል›› በሚል ለዛሬ ዐሥር ሰዓት በሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ዐውደ ምሕረት ላይ በግብረ በላዎቹ ‹‹መዝሙር›› ታጅቦ ለመቆም በቲፎዞዎቹ ቅስቀሳ እያካሄደ እንደ ሆነ ተገልጧል፡፡

ይህ የእነበጋሻው ሙከራ ሲኖዶሱ የአጣሪ ኮሚቴውን ሪፖርት በመመልከት ባሳለፋቸው ውሳኔዎች እና እርሱን ተከትሎ በሚፈጠሩት አዲስ ሁኔታዎች ሳቢያ በአካባቢው መሠረት ላለማጣት የሚደረግ መፍጨርጨር እንደ ሆነ ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡ አጣሪ ኮሚቴው እነ ያሬድ አደመ በዐውደ ምሕረት ላይ እንዳይቆሙ እግድ ካሳለፈበት ካለፈው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ በመድረኩ ላይ የስብከተ ወንጌል አገልግሎቱ በሊቁ መልአከ ምሕረት ጳውሎስ ቀጸላ እና በብሉይ እና ሐዲስ መጻሕፍት ምሁርነታቸው በሚታወቁት መምህር ኄኖክ እየተሰጠ እንደ ሆነ ከሐዋሳ ለደጀ ሰላም የደረሰው ዘገባ ያስረዳል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ በወሳኝ መልኩ እያካሄደ ባለው ስብሰባ በ29ው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ የተለላፉ የጋራ አቋም መግለጫዎችን በማጽናት፣ ከማእከል ተጠይቆ ፈቃድ ተሰጥቶት ካልተላከ ሰባኬ ወንጌል በቀር በጎን በሚደረግ ሽርክና በመንደርተኞች የስብከተ ወንጌል ጉባኤያትን ማካሄድ ፈጽሞ የተከለከለ እንደ ሆነ ጥብቅ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)