October 5, 2010

ዘሪሁን ሙላቱ የመከላከያ ማስረጃዎቹን አቀረበ፤ ብይኑ ለፊታችን ዓርብ ተቀጠረ


(ደጀ ሰላም፤ ኦክቶበር 5/2010፤ መስከረም 25/2003 ዓ.ም):-‹‹የሐውልቱ ሥር ቁማርተኞች›› በሚለው ጽሑፍ በእነ ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ፣ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጩ እና በጋሻው ደሳለኝ የስም ማጥፋት ወንጀል ክስ ቀርቦበት በቃሊቲ ወኅኒ ቤት የሚገኘው ሊቀ ትጉሃን ዘሪሁን ሙላቱ ክሱን የሚከላከልለትን የሰው፣ የሰነድ እና የድምፅ ማስረጃዎች ለፌዴራሉ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት አቀረበ፡፡ ፍርድ ቤቱ የቀረቡለትን ማስረጃዎች እና የምስክርነት ቃል መርምሮ ብይን ለመስጠት ለዐርብ፣ መስከረም 28 ቀን 2003 ዓ.ም ጠዋት ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ 

ትናንት መስከረም 24 ቀን 2003 ዓ.ም ጠዋት ሦስት ሰዓት በተሠየመው እና እስከ ስድስት ሰዓት በዘለቀው የፍርድ ቤቱ ውሎ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ጋራ የተገኙት ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ ተከሳሹ በድምፅ ሊያቀርብ የተዘጋጀውን ማስረጃ የሳል እና ልቅሶ ጉርምርምታ ድምፅ በማሰማት ችሎቱን ለመረበሽ በመሞከራቸው በዳኛው ተግሣጽ እና ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡
ለሊቀ ትጉሃን ዘሪሁን በምስክርነት የቀረቡት ዲያቆን ዓባይነህ አሰፋ የተባሉ የመልቲሚዲያ ፕሮዳክሽን ባለሞያ እና የተከሳሹ የቅርብ ባልንጀራ ናቸው። የተከሳሹ ንብረት ለነበረው አስተርእዮ ጋዜጣም በሪፖርተርነት እና ስርጭትም ሠርተዋል፡፡ የምስክሩ ቃል በዋናነት ከሳሾቹ ክስ የመሠረቱት በቂም በቀል ተነሣስተው እንደሆነ የሚያስረዳ ነው፡፡ ለከሳሾቹ ምስክር ሆነው የቀረቡት ዲያቆን ዳንኤል ገብረ ሥላሴ እኅታቸው የተከሳሹ የቀድሞ ፍቅረኛ እንደነበረች፣ በመካከላቸው በተፈጠረ አለመግባባት የምስክሩ እኅት ከተከሳሹ ጋራ የነበራቸውን ግንኙነት አቋርጠው ከሌላ ሰው ጋራ ትዳር መሥርተው ወደ ውጭ እንደሄዱ፣ ይሁንና ለተከሳሹ ከነበራቸው ከፍተኛ ወዳጅነት የተነሣ በውጭ አገር የመሠረቱት ትዳር እንዳልተቃናላቸው በዚህም የተነሣ ምስክሩ ተከሳሹ ‹‹የእኅቴን ሕይወት አበላሽቷል›› በሚል ተከሳሹን ለመበቀል እንደሚፈልግ ነግረዋቸው እንደ ነበር አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም ምስክሩ ‹‹የሐውልቱ ሥር ቁማርተኞች›› በሚለው መጽሐፍ ጀርባ ላይ የወጣውን የወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ የጋብቻ ምስክር ወረቀት ከኅትመቱ አስቀድሞ በዲያቆን ዳንኤል ገብረ ሥላሴ እጅ ላይ አይተውት እንደ ነበር፣ ከየት እንዳገኙት ሲጠይቁም አንዲት የወ/ሮ እጅጋየሁ ዘመድ እና ለራሳቸው ለምስክሩ የቅርብ ጓደኛ የሆኑ ሴት እንደሰጧቸው ዲያቆን ዳንኤል በገዛ አንደበታቸው እንደነገሯቸው፣ ከዚህም የተነሣ ምናልባትም ‹‹የሐውልቱ ሥር ቁማርተኞች›› መጽሐፍን ራሳቸው ጽፈውታል ብለው እንደሚጠረጥሩ መስክረዋል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በጋሻው ደሳለኝ ከሳሽም ምስክርም ሆኖ በመቅረቡ ጉዳይ ላይ በሰጡት ምስክርነት በጋሻው ደሳለኝ ባለፈው ዓመት የካቲት 16 ቀን 2002 ዓ.ም ቦሌ ዓለም ሕንፃ ላይ በሚገኝ ካፌ ውስጥ አግኝቷቸው፣ ‹‹ዘሪሁንን የምበቀልበት ቀን ዛሬ ነው፤ አብረን ሥራ እንሥራ›› በማለት ሊያግቧቧቸው እንደሞከሩ ተናግረዋል፡፡

ዐቃቤ ሕግ ለምስክሩ ባቀረበው መስቀለኛ ጥያቄ ምስክሩ የእያንዳንዱን ድርጊት ቀን እና ሰዓት እንደምን አስታውሰው ሊናገሩ እንደቻሉ ጠይቋቸው ነበር፤ ምስክሩም ሞያቸው የመልቲሚዲያ ፕሮዳክሽን ሥራ በመሆኑ ማንኛውንም ተግባራቸውን በየዕለቱ ርግጡ (ልኩ) በታወቀ ሰዓት የመምራት ልምድ በማዳበራቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በመቀጠል ተከሳሹ ሦስት የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቧል፡፡ የፓትርያርኩን ሐውልት ሐሳብ ከማመንጨት ጀምሮ ሐውልቱን የተመለከቱ እና በሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ ስም በግል ጋዜጦች ሲወጡ የቆዩትን ጽሑፎች ማዘጋጀታቸውን አምነው፣ ‹‹ዐይን አይቶ ልብ ይፈርዳል፤ እኔ የሐውልት ኮሚቴ አባል በመሆን ከፓትርያርኩ ምስክር ወረቀት ተሸልሜያለሁ፤ እንደምን እኔ የሐውልቱ ሥር ቁማርተኞች ብዬ የሐውልቱን ምስል አውጥቼ የሐውልቱን መተከል በመቃወም እጠረጠራለሁ?›› በማለት ጠይቋል፡፡ ደጀ ሰላም ከዚህ ቀደም ሊቀ ትጉሃን ዘሪሁን ሙላቱ የቤተ ክህነቱ የማፊያ ቡድን ‹ስውሩ ጸሐፊ› (Ghost Writer) እንደ ሆነ በተጨባጭ ማስረጃ አጋልጣ እንደ ነበር ይታወሳል፡፡

ተከሳሹ ለችሎቱ በመከላከያነት ያቀረበው ሌላው የሰነድ ማስረጃ በ1997 ዓ.ም በጋሻው ደሳለኝ የምርጫ - 97ን መነሣሣት ተከትሎ የተከሠተውን የፖለቲካ ትኩሳት በመጠቀም ትርፍ ለማግበስበስ፣ አንድም በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የአንደኛ ዓመት ተማሪ ሆኖ ሳለ በአካዳሚያዊ ድክመቱ የተነሣ በአስተዳደሩ በመባረሩ ትኩረት ለማስቀየር ላሳተመው ከመናፍቃን የተቃረመ ‹‹የመስቀሉ ሥር ቁማርተኞች›› ጽሑፍ ‹‹የስድብ አፍ›› በሚል ርእስ ምላሽ ያዘጋጀበትን ጽሑፍ ነው፡፡ ምላሹ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የገንዘብ ድጋፍ እና በፓትርያርኩ ፈቃድ መዘጋጀቱን ያስታወሰው ዘሪሁን ሙላቱ፣ በጋሻው ደሳለኝ በእርሱ ላይ ከሳሽም ምስክርም ሆኖ የቀረበው ለዚህ ምላሹ የበቀል አጸፋ ለመስጠት መሆኑን አስረድቷል፡፡

በመጨረሻ ተከሳሹ በወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ ላይ ባቀረበው የድምፅ ማስረጃ በ1996 ዓ.ም የአስተርእዮ ጋዜጣ ባለቤት እና ዋና አዘጋጅ በነበረበት ወቅት ከድምፃዊ መሐሙድ አሕመድ (በጥምቀተ ክርስትና ስሙ ሀብተ ወልድ) ጋራ ያደረገውን ቃለ ምልልስ ለችሎቱ አሰምቷል፡፡ በወቅቱ ለቃለ ምልልሱ ምክንያት የነበረው ድምፃዊው ከወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ ጋራ በፍቺ በመለያየታቸው ሳቢያ ወይዘሮዋ ‹‹መሐሙድ መልሶ ሰለመ›› በማለት አሉባልታ አናፍሰውበት ነበር፡፡ በወቅቱ ‹ዜናዌ ጥበብ› በሚል ማዕርግ ይጠራ የነበረው ተከሳሹ፣ ድምፃዊው በእንባ እየታጠበ ወ/ሮ እጅጋየሁ በትዳሩ ላይ የሠሩበትን ደባ በማስረዳት እርሳቸው እንደሚያስወሩበት ‹‹መልሶ እንዳልሰለመ›› ያስተባበለበትን ቃለ ምልልስ ለፍርድ ቤቱ አሰምቷል፤ ቃለ ምልልሱ ታትሞ የወጣበት አስተርእዮ ጋዜጣም ከድምፅ ማስረጃው ጋራ ተያይዞ ለችሎቱ ቀርቧል፡፡ ወ/ሮ እጅጋየሁ እርሱን ያሳሰሩት እና ክስም የመሠረቱበት ለዚህ ተግባሩ የበቀል ምላሽ ለመስጠት በማሰብ ነው ብሎ እንደሚያምንም አስረድቷል፡፡ የድምፅ ማስረጃው በፍርድ ቤቱ ሊደመጥ በነበረበት ሰዓት በችሎቱ የተገኙት ወይዘሮዋ ተደጋጋሚ ሳል እና የልቅሶ ድምፅ ማሰማታቸው ሆነ ተብሎ የችሎቱን ጸጥታ ለማደፍረስ የሚደረግ በመሆኑ ዳኛው ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋቸዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የድምፅ ማስረጃው በጽሑፍ ተገልብጦ እንዲቀርብለት ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡ ዳኛው መስከረም 14 እና 21 ቀናት በችሎቱ ቢገኝም ከራሱ በቀረበ ጥያቄ ጉዳዩ ሳይታይለት የቆየው ተከሳሽ ዘሪሁን ሙላቱ ያሰማቸውን የሰው፣ የሰነድ እና የድምፅ የመከላከያ ማስረጃዎችን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለፊታችን ዓርብ፣ መስከረም 28 ቀን 2003 ዓ.ም ጠዋት ቀጠሮ ሰጥተው ችሎት መልስ ሆኗል፡፡

5 comments:

ዘ ቢለንጊዮርጊስ said...

ሰላም ደጀ ሰላሞች ዘሪሁን ሙላቱን በተመለከተ ትንሽ ቢቀጣ ጥሩ ነው ምክንያቱም እንደአጠቃላይ ቤተክርስቲያንን ሲያምስ ስለኖረ አሁንም ገንዘብ ባያጣላቸው ኑሮ ቤተክርስቲያንን ከማመስ የማይመለስ ስለሆነ መቀጣቱ አይከፋም።ምአልባት ህግ ነጻ ቢያወጣው እንኳን በቀጣይ የበደላትን ቤተክርስቲያን ሌሎች እውነተኛ ምስጢሮችን በማውጣት ይክ ሳታል ብየአምናለሁ። እግዚአብሄር ባለህበት ማስተዋሉን ይስጥህ

Unknown said...

selam yetkebrachu yedjeslam azgajoch zrun ezaw biqo lbtkristyantwa addisu andgnaw mieraf enditgenr yadergatal neger gen ejigayo betgba degm 10 gnaw meraf betkrstian tigbalch

Anonymous said...

አንተ ዘ ቢለንጊዮርጊስ የምትባል አስተያየት ሰጭ ምን እያልክ ነው ያለከው?ግለሰቡ እነወይዘሮ እጅጋየሁን ማጋለጡ ተገቢነት የለውም ካልክ በዚሁ ላይ መተቸት ትችላለህ። ነገር ግን ዘሪሁን ነፃ ከወጣ እውነተኞችን ምስጢር በማጋለት ሲበድላት የነበረችውን ቤተክርስቲያን ነገ ይከሳታል ብለሃል።
ቤተ ክርስቲያን የምትከሰስባቸው ምን እውነት ምስጢሮች አሉ? ቤተክርስቲያናችን ሌሎች ይበድሉአት ካልሆነ በስተቀር በማንም ላይ ሊያስከስሳት የሚችል ወንጀል ፈጽማ ከቶውንም አታውቅም። በአሁኑ ሰዓት እየደረሰባት ያለው በደል ግን አላሳሰበህም። አንተ ከቤተክርስቲያን ይልቅ ለግለሰቦች ስም መጥፋት
የምትጨነቅ ትመስላለህ።

FNOTE LOZA said...

ሰላም ደጀ ሰላሞች!!! በእውነት የእነዚህ ሰዎች መጋለጥ ለቤተክርስቲያን መልካም ነው። እንዚህ ተኩላዎች ከቤተክርስቲያናችን እንዲወገዱ እግዚአብሔር ይርዳን። አሜን!!!

Anonymous said...

Dear Anonymous read properly it is "ይክ ሳታል" not "ይከሳታል"

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)